ዜጎች በሰላም ወጥተው የመግባት መብታቸው ይጠበቅ!

Views: 31

በኢትዮጵያ እያደር እየተበላሸ የመጣው የሰላም ሁኔታ አሁንም መሻሻል ሳይታይበት እየተባባሰ ቀጥሏል። አንድ ኢትዮጵያዊ ባዶ እጁን ከሀገሪቷ ጫፍ እስካ ጫፍ በሰላም መንቀሳቀስ የሚችልበት ጊዜ ተረስቶ፣ አሁን እሠፈሩ ውሎ ለመግባት ስጋት እየሆነ መጥቷል። በግብርናና በከብት እርባታ ላይ የተሰማሩ በቅርብ የፀጥታ ሀይል የሌላቸው አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ስጋት ደግሞ ለመገመትም አስቸጋሪ ነው። የከተማው ዝርፊያ ከመባባሱ ይበልጥ የሚያሳስበው እየተለመደ መጥቶ ወንጀለኛውን ሳይሆን የጠፋን ዕቃ ለማስመለስ ርብርብ የመደረጉ ጉዳይ ነው። ይህ አይነት ስጋት ሳይቀረፍ ለወንጀለኛ የማሪያም መንገድ በመሠጠቱ ተቦዳድነው ጦር መሣሪያ አንግበው አውራ ጎዳናን እየዘጉ የፈለጉትን እንዲያደርጉ በር መክፈቱን አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ከሠሞኑ እጅግ እየተበራከተ የመጣው ይህ የውንብድና ተግባር ሰው ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ገቢውን እንዳያገኝ፣ በከተማ የተቀመጠም ምርት አግኝቶ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዳይገዛ ያደርገዋል። ሠሞኑን ከአዲስ አበባ ባህርዳር የሚያገናኘው መንገድ ላይ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ወንበዴዎች በአንቡላንስ መኪኖችን አስቁመው የመኪኖቹን አሽከርካሪዎች መግደላቸው ተነግሯል። ይህ አይነት ድርጊት የመጀመሪያ ባይሆንም፣ የፈጠረው ስጋትና አለመተማመን ሹፌሮች በባህር ዳር ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ አስገድዷቸዋል። ይህ አይነት ፈር የጣሰ ወንጀል በዚህ ቅርብ ርቀት ላይ ሲፈፀም የፀጥታ ሀይል መቆጣጠር ባይችልም ወንጀሉ ከተፈፀመ በኋላ ተከታትዬ ያዝኩኝ የሚል ለእረጅም ዘመናት የለመድነው ሪፖርትን ሳያሰማን እየቀረ ነው። ከተማ ሙሉ በሙሉ እስኪወድም በርካቶች የሚሞቱበት ጥቃት እየተፈፀመ ባለበት በዚህ ወቅት መንገድ ተዘጋ ማለቱ ትንሽ ነገር ቢመስልም መዘዙ የከፋ እንደሚሆን አዲስ ማለዳ ለማስገንዘብ ትወዳለች።

ዜጎች ሀገራቸውን ብለው መንግሥትን አምነው ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ሳይችሉ ሲቀሩ የሀገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚስተጓጎል ለማንም ግልጽ ነው። ምርጫው መድረሱን ተከትሎ ሰው ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ በሚል እኩይ አላማ ይህን መሰል ተግባር በመፈፀም ህብረተሰቡ ስጋት እንዲሰማው የሚያደርጉ አላማቸው እንዳይሳካላቸው መደረግ አለበት። ከዋና መንገድ 20 ኪሎ ሜትር ድረስ ታጣቂ እንዳይንቀሳቀስ የተባለባቸው የሰሜን ሸዋና የወሎ ግዛቶች አይነት ትዕዛዝ እንዲህ አይነት አስነዋሪ ተግባር በሚፈፀምባቸው ሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ቢታወጅ የተሻለ እንደሚሆን የሚታመን ነው። ይህ አይነቱ ተግባር ወደ ግድቡ በሚያመሩ ተሸከርካሪ ሹፌሮች ላይ ቤኒሻንጉል ውስጥ የሚፈፀም እንደሆነም እየተደጋገመ ይሰማል። “የውጭ ጠላቶቻችን ከውስጦቹ ጋር እያበሩ እረፍት ለመንሳት ነው” እያሉ ደጋግመው የህዝብን ሀዘኔታ ለማግኘትና ከወቀሳ ለመዳን የሚደረጉ ትንታኔዎች ሁሌም ውጤት ላያመጡ ይችላሉ። በተቃራኒው ህዝብ በመንግስት ላይ ተስፋ ቆርጦ ምንም ቢባል አለማመንን ያስከትላል። ይህ በራሱ ቀጥተኛ ችግር ላያመጣ ቢችልም፣ ነገሮችን በራሱ እስከ መወሰን ሊያደርሰው ይችላል። vigilante justice የሚባለውና በህግ ተቀባይነት የሌለው በቀልን የመሰለ እርምጃ ህዝቡ አማራጭ አድርጎ ከመውሰዱ በፊት፣ የህዝብ ድህንነት ጉዳይ በመሆኑ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ወቅቱ የበአል እንደመሆኑ ምርት ከቦታ ቦታ በተለመደው ስርአት ካልተንቀሳቀሰ ህዝብ ላይ ምሬት ማስከተሉ አይቀርም። ሠሞኑን በሰሜን ሸዋ የተፈጠረውን ጥቃት ተከትሎ መንገዶች በመዘጋታቸው፣ እንዲሁም ከጎጃም የሚመጡ አውቶቡሶች ኦሮሚያ ክልል ሊገቡ ሲሉ ተፈጠረ የተባለው የማስቆም የመመለስና የማጉላላት እርምጃ በህዝብ ስነልቦና ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ ቀላል አይደለም። ወቅቱ ይበልጥ የሰው እንቅስቃሴ የሚበዛበት እንደመሆኑ በንግድ እቃዎችና ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ አስከትሏል። 300 ብር ገደማ ይሸጥ የነበረ ቅቤ 500 ብር እስኪገባ ድረስ ይህ አይነት ክስተት ትልቅ አስተዋጽኦ ስለሚያደርግ መንግሥት ቢያስብበት መልካም ነው።

ህጋዊ ሆኖ የሚንቀሳቀስ ሰው በፈለገበት እንዲኖርም ሆነ እንዲነግድ፣ ሰርቶ ግብር የሚከፍለው መንግስት የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች። ይህን የዜጎች መብት መጠበቅ ያልቻለው መንግሥት በኋላ ህዝቡ፣ “አልገብርም፣ ለጎበዝ አለቃዬ ነው የማስገባው” ቢለው ጉልበት ለመጠቀም ወደ ኋላ አይልም። ይህ ከመሆኑ በፊት ሲጠቃ የሚከላከልበትን ጉልበት ህዝቡ እንዳይጠቃ ጋሻ ሊሆንለት ይገባል። ይህን ኃላፊነቱን መወጣት ካልቻለ አሳውቆ፣ ህዝብ ዕጣ ፈንታውን በጊዜ እንዲወስን ማስቻል አለበት። ዘራፊና ወንበዴ ሸማቂም ከመንግስት በላይ ተደራጅቶ መንቀሳቀስ በሚችልበት ሀገር ስለምርጫም ሆነ ስለሌላ ዲሞክራሲያዎ መብት ማውራት ቅንጦት ይሆናል። መጀመሪያ ሰው ሁሉ መኖር እንዲችል ከተደረገ በኋላ ነው ሌሎች ከሰብአዊ መብቱ ቀጥለው የሚመጡ መብቶች የሚከበሩት። ይህ አሁን እየተለመደ የመጣው የህዝብ ሰቆቃና እሮሮ በኋላ ከገነፈለ ከእሳቱ ማውረድ አይቻልም።

በሌላ በኩል፣ ተደመሰሰ የተባለ ሸማቂ ሀይል የክልል ወሰንን እየጣሰ ሠላማዊ ነዋሪን እየገደለ የህዝብ ሀብትና ንብረትን እያወደመ መሆኑ ይታወቃል። የትህነግ መሪዎች፣ “የትም ቢሆን ወሰን አልፈን ጥቃት እንስነዝራለን” እያሉ በይፋ እየተናገሩ በመንግስት ወገን ጦርነቱን አሸንፈናል እያሉ ወታደሮችም ሆነ የህዝቡ ታጣቂ እንዲዘናጋ መደረግ እንደሌለበት አዲስ ማለዳ ታምናለች። አጥፊዎች ሙሉ በሙሉ የእውነት ተደምስሰው፣ ማንም ኢትዮጵያዊ ሳይታጠቅ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እስካልቻለ ድረስ ሁላችንም በተጠንቀቅ እንድንቆምና ጦርነት ላይ እንደሆንን እንዲሰማን ማድረግ ያስፈልጋል። “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” እንደሚባለው፣ መንግስት እኛ ነን ማን ይነካናል ብሎ የመንግስት መሰረት የሆነው ህዝብ እንዲነካ ዕድል መስጠት ነፋስ የነፈሰ ጊዜ ተያይዞ መውደቅን ያስከተላል። ይህ የሀገርን ውድቀት የሚያስከትል አቅመ ቢስነት በህዝቡ ልቦና ሠርጾ ወደ ተስፋ መቁረጥ ከማምራቱ ወዲህ፣ መንግስት የሚጠበቅበትን ግዴታውን እንዲወጣ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች። “የናቁት….” እንደሚባለው መንግስት በቃላት ብቻ የሚያጣጥላቸው አካላት ፊት ለፊት ገጥመው እንዳይዋርዱት፣ የሚያስከብረውን መንገድ በጊዜ መምረጥ ጥሩ ነው። “ጊዜ የሠጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራልም” እንደሚባለው ለህዝብ ጠላቶች ጊዜ መስጠት የራስን ሞት ማፋጠን እንዳይሆን አዲስ ማለዳ ለመጠቆም ትወዳለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 130 ሚያዚያ 23 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com