የአማራ ወጣቶች ማህበር የአማራ ባለአደራ መንግሥት እንዲቋቋም ጠየቀ

Views: 369

በፌደራል ደረጃ በ11 ኮሚቴዎች የተዋቀረው የአማራ ወጣቶች ማህበር፣ የአማራ ባለአደራ መንግሥት እንዲቋቋም ሚያዝያ 16/2013 ለህብረተሰቡ መጠየቁን የማህበሩ ስራ አስፈጻሚ አዲሱ መስፍን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የዜጎች መፈናቀል፣ የንጹሃን ሞት፣ የቤት ንብረቶች መውደም እና የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል እየታየ ማንም የደረሰ የመንግሥት አካላ ባለመኖሩ አገሪቱ መንግሥት አልባ አገር መሆኗን ካረጋገጠ በኋላ ባለአደራ መንግስትን ለማቋቋም መነሳሳቱን አዲሱ ገልጸዋል።

ሕዝብ ችግር ላይ በወደቀበት ሰዓት የባለአደራ መንግስት ወይም ደግሞ በባህላዊ አጠራሩ የጎበዝ አለቃ በማቋቋም በየአካባቢው የሚገኙ ተደማጭነት እና ተዓማኒነት ያላቸውን ወጣቶች በማደራጀት ማኀበረሰቡን እንዲጠብቅ ለማድረግ ታቅዷል።
ሁሉንም የአማራ ክልል ሕዝቦች አሳታፊ ለማድረግ የታሰበው የባለአደራ መንግስት መተዳደሪያ ደንቦችን በማውጣት የሕብረተሰቡን ለማደራጀት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አዲሱ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
በፌደራል ደረጃ በሲቪክ ማህበራት ኤጀንሲ ታህሳስ 2012 እውቅና ተሰጥቶት በስራ ላይ የሚገኘው የአማራ ወጣቶች ማህበር በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራ ሲሳተፍ መቆየቱ ይታወቃል።

ማህበሩ ከዚህ በፊት የጣና ሀይቅ የእንቦጭ አረም ለማስወገድ፣ በተለያዩ ክልሎች የተፈጠረውን የአንበጣ ወረርሽኝ ለማስወገድ እና በመተከል የተፈናቀሉት ወገኖችን ለመደገፍ እስከ 2 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በማሰባሰብ ችግሮችን ሲፈታ የቆየ መሆኑን አዲሱ ተናግረዋል።

ማህበሩ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባልም ደጋፊም ሳይሆን መንግስት እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ህብረተሰቡ ላይ የሚፈጥሩትን አሉታዊ ጫናዎች በመከታተል የሚሞግት ነው።
የዚህ ማህበር አባል የሆነው በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው ለድምፅ አልባ ኢትዮጵያውያን ድምጽ የሆነ ግብረሃይል የተቋቋመ ሲሆን በተለያዩ ክልሎች በአማራው ላይ የሚፈጸመውን ግድያ በመቃወም የአሜሪካን መንግስት እና ህዝብ ድጋፍ ለመጠየቅ በሚቀጥለው ሳምንት ሚያዚያ 28/2013 ሰልፍ ለማካሄድ ጥሪ አቅርቧል።

በተጨማሪም የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ ከእስር እንዲፈቱ የሚጠይቅ እንዲሁም አጠቃላይ ብሄራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚሰራ በኢትዮጵያ ባለሙያዎች የሚመራ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም የግብረሃይሉ ሰብሳቢ ሽመልስ ገሰሰ ጠይቀዋል።

በተያያዘ መረጃ የእነስክንድር ችሎት የፊታችን ሚያዝያ 26/2013 በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በፕላዝማ የሚቀርቡ ሲሆን በዚህ ችሎት ፍርድ ቤቱ ምስክሮች በግልፅ ችሎት ይሰሙ ወይስ በስውር የሚለውን ለይቶ ይፈርዳል።
በመቀጠል ሚያዝያ 28/2013 በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በአካል እንደሚቀርቡ የተያዘው ቀጠሮ ያመላክታል።

የባለአደራ መንግስት እንዳይቋቋም ለመርገጥና የአማራ ሕዝብ የጀመረውን ሕዝባዊ እምቢተኝነት ለመጥለፍ ፣ መንግሥት ነኝ በሚል ስም የሚመጣ የትኛውም ኃይል ለሚከሰቱ ጭግሮች ሙሉ ኃላፊነት የሚወስድ መሆኑን ማህበሩ ያስታወቀ ሲሆን ፣ በዚህ አጋጣሚ የአማራ ሕዝብ በግልጽ መንግሥት አልባ መሆኑን ተረድቶ፣ ከተደቀነበት ጨርሶ የመጥፋት አደጋ ሊታደገው የሚችል የአማራ ባለአደራ መንግሥት እንዲያቋቁም ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አማራን የአገርና መንግሥት ባለቤት ሳያደርግ አይመለስም በሚል ዘመቻ የባለአደራ መንግስትን ለማቋቋም እንደታሰበ አዲሱ ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ገልፀዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 130 ሚያዚያ 23 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com