የቀድሞው ሜቴክ የህዳሴው ግድብ ደን ምንጣሮ ላይ የተሳተፉ 38 ማኅበራትን ባለእዳ አድርጓል ተባለ

Views: 192

በቀድሞው የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በ2006 የታላቁ ሕዳሴ ግደብ ደን ምንጣሮ ሥራ ለሰሩ 160 ጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት መክፈል ያለበትን ገንዘብ ሳይከፍል፣ በተጭበረበረ ሰነድ 38 ማኅበራትን ባለ ዕዳ እንድሆኑ አድርጓል ሲሉ ማኅበራቱ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ሜቴክ በ2006 ከ160 ማኅበራት ጋር ውል ገብቶ ያስመነጠረውን 56 ሺሕ ሄክታር ደን ክፍያ በኹለት ዙር የከፈለ ሲሆን፣ ደን ምንጣሮው ካጠናቀቁ በኋላ ሦስተኛ ዙር ክፍያ እንዳልተከፈላቸው ማኅበራቱ ተናግረዋል።
ሜቴክ በወቅቱ ለ160 ማኅበራት መክፍል የሚገባውን 340 ሚሊዮን ብር እንዳልከፈለ የማኅበራቱ ተወካይ እሱባለው ተካልኝ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ማኅበራቱ 340 ሚሊዮን ብር ሊከፈላቸው ሲገባ፣ ሜቴክ የገባውን ውል ብቻውን በማፍረስ 38 ማኅበራትን የ31 ሚሊዮን ብር ባለ እዳ አድርጓል ሲሉ ነው እሱባለው ጉዳዩን ያስረድት።
ማኅበራቱ የሰሩበት ክፍያ የተከለከሉበት ምክንያት ምንጣሮው የተካሄደበት ቦታ መጠን ልኬት ሲሆን፣ በሰሩት ሥራ በኹለት ዙር ከተከፈላቸው በኋላ የመጨረሻው ከፍያ በሚከፈልበት ጊዜ በኮንትራት ሰጪውና በኮንትራት ተቀባዮቹ መካከል ውዝግብ ያስነሳው የዚሁ የመለኪያ ዘዴው ጉዳይ ነበር።

የመለኪያ ዘዴው ውዝግብም ሜቴክ “በጂፒኤስ ይለካል” ሲል ማህበራቱ ደግሞ፣ “ቦታው ወጣ ገባ የበዛበት ስለሆነ፣ በሜትር ይለካልን” የሚል ሀሳብ ማቅረባቸው ነበር።
ኹለቱ መለኪያዎች ልዩነት ይኖራቸው እንደሆን ለማረጋገጥ ሲባልም፣ ለናሙና የተወሰደ ቦታ በሜትርና በጂፒኤስ ተለካ፣ በሜትር ተለክቶ 12 ሄክታር የሆነው ቦታ፣ በጂፒኤስ ሲለካ ከ6 ሄክታር በታች እንደሆነ እሱባለው አስታወሰዋል።
በዚህም ትክክለኛው መለኪያ ሜትር መሆኑ በኹለቱም ወገኖች ስለታመነበት፣ ሜትር ገመድ እየተጣለ ይለካ ጀመር፣ በዚህም ልኬት ሜቴክ በሦስት የተለያዩ ምዕራፎች ለማኅበራቱ ክፍያ የፈጸመበት ማስረጃ በማኅበራቱ እጅ ይገኛል።
ይሁን እንጅ ማኅበራቱ 340 ሚሊዮን ብር ሊከፈለን ሲገባ ጂፒኤስ ከግማሽ በላይ ልኬቱን እንደሚቀንስ ተረጋግጦ በሜትር እንዲለካ ስምምነት ላይ ተደርሶ፣ በዚሁ መሠረት ሲከፈላቸው ቆይቶ “ልኬቱ ተጭበርብሯል” በሚል ሰበብ ሜቴክ ሥራውን የሰሩ ማኅበራትን ሳያሳትፍ በጂፒኤስ ለክቶ አዲስ የልኬት ውጤትና የሂሳብ መጠን እንዳቀረበ እሱባለው ቅሬታቸውን ገልፀዋል።

አዲስ በቀረበው ልኬትና የሂሳብ መጠን 160 ማኅበራት የሚከፈላቸው 340 ሚሊዮን ብር ቀርቶ 38 ማኅበራት 31 ሚሊዮን ብር ተመላሽ እንድናደርግ ተጠይቀናል ብለዋል እሱባለው። ሜቴክ ለ160 ማኅበራት ሦስተኛ ዙር ክፍያ 340 ሚሊዮን ብር ለመክፈል ለማኅበራቱ የክፍያ ሰርተፍኬት ተስጥቶ እንደነበር እሱባለው ጠቁመዋል።

ማኅበራቱ በ2007 ፍርድ ቤት ክስ አቅርበው ፍርድ ቤቱ መለኪያውን በተመለከተ፣ በተከሳሽ(ሜቴክ) ጠቋሚነት፣ ለኢትዮጲያ ካርታ ሥራዎች ድርጅት፣ “ከጂፒኤስና ከሜትር የትኛው የተሻለ ይህንን መሬት ይለካል?” ብሎ እንዳቀረበ እሱባለው ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ካርታ ሥራዎች ድርጅት፣ “እንደዚህ ዓይነት ወጣ ገባ የበዛበትን ቦታ ለመለካት ሜትር እንደሚመረጥ፣ ጂፒኤስ ግን፣ የእንደዚህ ዓይነቱን ቦታ የቆዳ ስፋት በትክክል እንደማይሰጥ የፃፈው ደብዳቤ ቀርቦ በወቅቱ የተሰየሙት ዳኛ “ፍርድ ቤቱ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል” ማለታቸውን አሱባለው የፍርድ ሂደቱን አስታውሰዋል።

ጉዳዩ በማኅበራቱና በአባላቱ ህልውና ላይ ብዙ ምስቅልቅል ሁኔታዎችን አስከትሏል፤ ንብረታቸውን አስይዘው ለሥራ ማስኬጃ የተበደሩትን መክፈል አቅቷቸው ንብረታቸው ተይዟል፤ ለሠራተኞቻቸው የሚከፍሉት አጥተው ክስ የተመሠረተባቸው፣ ድርጅቶቻቸው የተዘጉ፣ የታሠሩ፣ አገር ለቀው የጠፉ፣ ቤተሰቦቻቸው የተበተኑ እንዳሉ እሱባለው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

አዲስ ማለዳ የቀድሞው ሜቴክ የአሁኑ ኢትዮ -ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሞላልኝ ከሳቴብርሃን አነጋግራ፣ ደርጅቱ በብዙ የሙስና ሥራዎች ተዘፍቆ የቆየ መሆኑን በማስታወስ ጉዳዩ የቀድሞ ደርጅቱ አመራሮች መሆኑን ጠቁመዋል።
ድርጅቱ በቀድሞው አመራሮቹ ምክንያት በሙስና ከአገሪቱ ተቋማት ቀዳሚ እንደነበር የጠቆሙት ሞላልኝ አሁን ላይ ድርጅቱ በልውጥ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 130 ሚያዚያ 23 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com