ኪዊንስ ሱፐር ማርኬት ቅርንጫፎቹን ወደ 30 ሊያሳድግ ነው

Views: 291

ንብረትነቱ የሼህ መሐመድ አሊ አላሙዲን የሆነው ኪዊንስ ሱፐር ማርኬት በአዲስ አበባ አሁን ያሉትን ሰባት ቅርንጫፎች ጨምሮ በቀጣይ ኹለት ዓመታት ቅርንጫፎቹን ወደ 30 ሊያሳድግ ማቀዱን የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀማል አህመድ ገለጹ።

ሱፐር ማርኬቱ ዋጋን ማረጋጋትን ታሳቢ ያደረገ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን በወር 400 ሺሕ የሚደርሱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሰባቱ የኪዊንስ ሱፐር ማርኬት ቅርንጫፎች ግብይት እንደሚያደርጉ እና ይህንን ቁጥር በቀጣይ ኹለት ዓመት ውስጥ አራት ሚሊዮን ለማድረስ መታቀዱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከአዲስ ማለዳ እህት መጽሄት Ethiopian Business Review ጋር ባደረጉት ቆይታ አስታውቀዋል።

በቅርቡ ሰባተኛ ቅርንጫፉን ጊዮን ሆቴል አካባቢ ንብረትነቱ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በሆነው ናኒ ሕንጻ ላይ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ በተገኙበት አስመርቆ ወደ ሥራ ማስግባቱ የሚታወስ ነው።
ሱፐር ማርኬቱ በቀን 20 ሺሕ ያክል የእህት ድርጅታቸው የኤልፎራ ምርት የሆነ እንቁላል በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ የቆየ ሲሆን፣ አሁን በቀን 80 ሺሕ እንቁላል ለማቅረብ እንዳቀደም ጀማል ገልጸዋል። እንቁላል በአሁኑ ወቅት አስከ ስምንት ብር በመሸጥ ላይ ሲሆን በኪዊንስ ሱፐር ማርኬት ከአራት ብር እስከ አራት ብር ከሃምሳ ሳንቲም እንደሚገዙ ተገልጋዮች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የገበያ ማዕከሉ ከሚድሮክ እህት ኩባንያዎችና እርሻዎች የአቅርቦት ሰንሰለት በመፍጠር ነው በምግብ ፍጆታዎች ላይ ቅናሽ በማድረግ በመሸጥ ላይ የሚገኘው። ድርጅቱ የስርጭትና የዋጋ ማሻሻያውን ያደረገው እንደ አዲስ የአመራር ሽግሽግና ሪፎርም ማካሄድ ከጀመረ ወዲህ መሆኑ የሚታወስ ነው።

ኩዊንስ በሲኤምሲ፣ በፓስተር፣ በሾላ፣ በጦር ኃይሎች፣ በሳር ቤት፣ መካኒሳ እና በጊዮን ቅርንጫፎቹ በቅናሽ ዋጋ የሚያቀርባቸው የአግሮ ኢንዱስትሪ ምርቶች፣ እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ውጤቶችን ነው። በዚህም መሰረት ተቋሙ የትርፍ ጣሪያውን እስከ 6 በመቶ ድረስ ዝቅ በማድረግ ከኤልፎራ የሚረከበውንና በገበያ ላይ በነጠላ ስምንት ብር የሚሸጠውን አንድ እንቁላል በአራት ብር ብቻ በመሸጥ ላይ ይገኛል።

የዋጋ ቅናሹ የሚድሮክ እርሻ ውጤት የሆኑትን የፍራፍሬ ምርቶችንም ሚያካትት ሲሆን ብርቱካን፣ መንደሪን፣ እንጆሪ፣ ሎሚ እና ሙዝ በከተማው ካሉ የንግድ ቦታዎች ሁሉ እጅግ በቀነሰ ዋጋ ኩዊንስ የገበያ ማዕከል በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ አሁን ባለው የከተማው ገበያ አንድ ኪሎ ብርቱካን እስከ 100 ብር ድረስ ይሸጣል፡፡ ኩዊንስ ባደረገው የገበያ ድጎማ ኪሎ ብርቱካን በ60 ብር በመሸጥ ላይ እንደሚገኝ ደነረበኞቹን በማነጋገር ለማወቅ ችለናል፡፡ የምግብ ዘይትም በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ላይ ይገኛል የገበያ ማዕከሉ አስታውቋል፡፡
ሱፐር ማርኬቱ ዲጂታል የባንክ አገልግሎቶችን ለመተግበር እየተንቀሳቀሱ ካሉት ባንኮች መካከል አንዱ ከሆነው ዳሸን ባንክ ጋር በመሆን ከዚህ ቀደም ከተገበራቸው የካርድ አገልግሎቶች የተለየ ያለውን የግብይት የስጦታ ካርድ ባለፈው አመት ጥቅምት ወር ላይ ለአገልግሎት ማብቃቱ ይታወሳል።

ይህ የግብይት ካርድ ጦር ኃይሎች አካባቢ በሚገኘው ኪዊንስ ሱፐር ማርኬት ቅጥር ግቢ ውስጥ ይፋ በተደረገበት ወቅት ንግግር ያደረጉት የዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንት አስፋው ዓለሙ እንደገለጹት፣ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት አማራጭ የሌለውና መጪው ጊዜ ከዚሁ ቴክኖሎጂ ጋር በመተሳሰሩ በመንግሥት ደረጃ የተቀረፀውም ስትራቴጂ ይኼው በመሆኑ ባንካቸው በዚህ ቴክኖሎጂ ላይ የበለጠ መሥራቱን እንደሚገፋበት አስታውቀዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 130 ሚያዚያ 23 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com