ኢትዮጵያን ለመቀራመት ያሰፈሰፉ ጎረቤቶች!

Views: 266

በተለያየ ጊዜ ከሩቅ እንዲሁም ቅርብ ከተባሉ ጎረቤቶች የወረራ ሙከራ የተደረገባት ኢትዮጵያ ሁሉንም በአሸናፊነት ተወጥታቸዋለች። በአብዛኛው ታድያ እነዚህ ወረራዎችና የወረራ ሙከራዎች የሚደረጉት ኢትዮጵያ በውስጥ አለመረጋጋት በምትታመስበት፣ በረሃብ፣ በግጭት፣ በፖለቲካ አለመስማማት መካከል በምትሆንበት ጊዜ መሆኑንም ታሪክ ያስረዳናል። ግዛቸው አበበ አሁንም በውጪ ያሉና ኢትዮጵያ ወድቃ ለማየት አልፎም ለመቀራመት የሚመኟት ጎረቤት አገራት ሳይቀሩ በውስጧ ስላለው አለመረጋጋትና ችግር ይህንን ያውቃሉ፣ እናም እንደ አገር ይህን ልብ ማለት ያሻል ሲሉ ሐሳባቸውን እንደሚከተለው አስፍረዋል።

ከጅቡቲ ተነስቶ ሱዳንን አቋርጦ እስከ አሜሪካ በጎን በኩል፣ በታች በኩል ደግሞ ከኬንያ ተነስቶ ግብጽን አቋርጦ እስከ አውሮፓ ያሉ ፖለቲከኞች ስለ ኢትዮጵያችን አሳምረው የሚያውቋቸው ኹለት ሃቆች አሉ።

ሃቅ ቁጥር አንድ
ከሕወሐት/ኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመን ጀምሮ በተለይም የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት የተባለው የሕወሐት ሰነድ የኢትዮጵያን ዕጣ ፋንታ የሚወስን ሰነድ ሆኖ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ፣ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን በገዥዎቿ የተነፈገች አገር ሆናለች። ጠላትም ሆነ ወዳጅ፣ ማንም የውጭ ኃይል አሳምሮ እንደሚያውቀው ኢትዮጵያ ‹ሉዓላዊ› አገር ባትሆንም በውስጧ ያቀፈቻቸው ክልሎች ሙሉ ሉዓላዊነት ያላቸው፣ ኢትዮጵያዊ ሆነው ለመኖርም ሆነ ከኢትዮጵያ ተገንጥለው በመሄድ ኢትዮጵያን እየሸራረፉ ቀስ በቀስ ለማፍረስ ሙሉ መብት ያላቸው ናቸው።

ሕገ-መንግሥቱ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ የመሄድ መብት አላቸው የሚለው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው ስለሚል የአገሪቱ ሉዐላዊነት መነፈግ ምን ያህል የከፋ መሆኑን ያሳያል። ጋምቤላ ውስጥ የኤርትራን ምድር የሚያክል የእርሻ መሬት የያዘ ሰው ልገንጠል የሚል ጥያቄ አቀረበ የሚል ቀልድ የተሰማው አገሪቱን ማፈራረስ ምን ያህል ተራና ቀላል ነገር እንደሆነ ለማሳየት ነው።

ጎረቤቶቻችንም ሆኑ የሩቅ መንግሥታት ኢትዮጵያችን ውስጥ ያለው ራስን በራስ ማስተዳደር እስከ መገንጠል በሚል መርህ አገርን ማፈራረስ የሚፈቅድ መንግሥት ብቻ አይደለም። ይልቁንም ኢትዮጵያ ቅኝ ገዥአችን ናት፣ ኢትዮጵያ መፈራረስ የሚገባት አገር ናት ወዘተ የሚል አጀንዳ ያነገቡ፣ ሕጋዊ የፖለቲካ ቡድን ሆነውም ሆነ ነፍጥ አንግበን እየታገልን ነን የሚሉ በርካታ ቡድኖች የሚተራመሱባት አገር መሆኗን በሚገባ ያውቃሉ።

በተቃራኒው ጅቡቲ ቅንጣት ግዛቷ ተነጥሎ እንዲሄድባት የሚፈቅድ ሕገ-መንግሥትም ሆነ መንግሥት የላትም። ኹለቱ ሱዳኖች፣ ኤርትራ፣ ኬንያም ሆነች ችግር ውስጥ ያሉት የጎረቤት ሶማሊያ መንግሥታትም ከጅቡቲ የተለየ አቋም የላቸውም። በመኻከላቸው የምትገኘው ኢትዮጵያ ግን ዘለዓለማዊ አገራዊ የሉዓላዊነት ክብር የተነፈገች፣ እያነሰችና እየፈረሰች ትሄድ ዘንድ የተፈረደባት አገር ናት።

ጎረቤቶቻችን ይህን የትርምስና የመዝረክረክ ጊዜ በልዩ ትኩረት የሚያዩት ይመስላሉ። እንዲያውም ጥንብ አንሳ አሞራዎች በጣረሞት ላይ ባለ እንስሳ ዙሪያ በጉጉት እያንዣበቡና እያኮበኮቡ ሊቀራመቱት እንደሚቋምጡ፣ ከጎረቤቶቻችን አንዳንዶቹ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ሕልውና ማክተሚያ እንደደረሰና የየድርሻቸውን ለመውሰድ በታላቅ መቋመጥ አቆብቁበው መጠባበቅ የጀመሩ ይመስላሉ። ኧረ እንዲያውም እንደ ጅብ ኢትዮጵያን በቁሟ ‹የቦጨቀ› ጎረቤትም አለ።

ሱዳን መሬቴ ነው የምትለውን ቦታ በወታደራዊ ኃይል ተቆጣጥራ የለምን? ይህ የመሬት ምንተፋና ሃይ ባይ ማጣት የልብ ልብ እንዲሰማት ያደረጋት ሱዳን ቤኒሻንጉል የሚባለው ምድር በሙሉ የኔው ነው የሚል አነጋገር ቡልቅ እያለባት ነው ይባላል። በእርግጥ ሰፋ ያለ መሬት የወረረው የሱዳን መንግሥት ገና በእጄ ያላገባሁት ቀሪ መሬት አለኝ ብሎ በይፋ መንዛቱ የአደባባይ ምስጢር ነው። የሱዳን መንግሥት ይህን ዛቻውን ተከትሎ በአማራ ክልል በኩል የጀመረውን የመሬት ወረራ ቀስ በቀስ እያሰፋና የኢትዮጵያዊ ገበሬዎችን የእርሻ ካምፖች እያወደመ፣ ከብትና ንብረት እየዘረፈ በተደጋጋሚ ማን አለብኝነቱን ዐሳይቷል።

የጀርመኑ ዶቸቨለ በዕለተ እሁድ ሚያዝያ 24/2013 የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ ገብቶ፣ ከሱዳን ድንበር ወደ 70 ኪሎሜትሮች የሚርቀውን የምዕራብ ጎንደር ዞን አካል የሆነውን መንዶካ የተባለውን ቦታ ማጥቃቱንና የኢትዮጵያዊ ገበሬዎች የእርሻ ጣቢያዎችን ማውደሙን አሳውቋል።

በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ስለሚኖሩ ገበሬዎች የሚያውቅ ሰው ይህ ከወረኀ ጥቅምት 2013 ጀምሮ በሰፊውና በተከታታይ የሚካሄድ ጥቃት የሚያደርሰው ውድመት ምን ያህል ግዙፍ እንደሆነ በሚገባ ይረዳዋል። ከንጉሥ ኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ፣ በደርግ ዘመን ተቋርጦ፣ በዘመነ ሕወሐት/ኢሕአዴግ እንደገና በቀጠለው አሠራር መሰረት በእነዚህ አካባቢዎች በእርሻ ሥራ የሚሰማሩ ገበሬዎች በታላላቅ ኢንቨስተርነት የሚመደቡ፣ እጅግ በጣም ሰፊ የእርሻ መሬቶችን የሚስተዳድሩ፣ ሰሊጥ እና/ወይም ጥጥ በሺዎች ካልሆነም በመቶዎች በሚቆጠር ኩንታል የሚያመርቱ፣ የእርሻ ሥራዎቻቸውን የሚያካሂዱባቸው በርካታ ትራክተሮችና የእርሻ መሣሪያዎች ያሏቸው፣ በመቶዎች ወይም በሺዎች የሚቆጠሩ የቀንድ ከብቶችን እንዲሁም ሌሎች የቤት እንስሳትን የሚያረቡ ባለጸጋዎች ናቸው።

የእነዚህ ገበሬዎች ምርቶች በአብዛኛው ለውጭ ገበያ ቀርቦ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ሲሆን፣ የተወሰነው ለአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ቀርቦ ከውጭ ሊገባ የሚችልን ምርት በማስቀረት የውጭ ምንዛሪን ለመቆጠብ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ስለዚህ የእርሻ ካምፕ ተቃጠለ ወይም ተዘረፈ፣ የተከመረ ወይም በመጋዘን የተሰበሰበ ወይም ያልታጨደ ምርት በሱዳን ጦር ተዘረፈ ወይም ወደመ ሲባል በገበሬዎቹም ሆነ በአገሪቱ ላይ የሚደርሰው ኪሳራ ግዙፍ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባዋል።

በዕለተ ፋሲካ እሁድ ሚያዝያ 24/2013 ከንጋቱ አስራ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ ረፋዱ አራት ሰዓት በተሰነዘረው ጥቃት የሱዳን ጦር በከባድ መሣሪያዎች የታገዘ ድብደባ መፈጸሙን የአካባቢውን ነዋሪዎች ጠቅሶ ዶቸቨለ ዘግቧል። ከዛ በተጨማሪ የመተማ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ፋንታሁን ኪሮስን በስልክ በማነጋገር ጥቃቱ ተፈጸመ መባሉ ትክክለኛ መሆኑን አስምሮበታል። ፋንታሁን ኪሮስ መከላከያና ጸረ-ሽምቅ ሚሊሻዎች ወደ ቦታው በመላካቸው አካባቢውን ለማረጋጋት መቻሉን አሳውቀዋል።

የሱዳን መንግሥት ኢትዮጵያን ለመቀራመት ወይም ከኢትዮጵያ መሬት ለመመንተፍ ምቹው ጊዜ አሁን ነው ብሎ ቆርጦ የተነሳ ይመስላል። የሱዳን መንግሥት የአባይ ግድብ ያረፈበት የቤኒሻንጉል ምድር የሱዳን ግዛት የነበረ መሆኑን ከመናገር አልፎ ይህን የቀድሞ ግዛቱን ለማስመለስ እየዛተ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ቢሮው የወጣው መግለጫ ያሳያል። ሱዳን ግዛት ማስፋትን፤ ከብቶችን መታ መታ እና ገፋ ገፋ እያደረገች ጋጣን የማስፋት ያህል ቀልሎ እየታያት ነው ማለት ይቻላል። በሬዎችና ላሞች ምን ያውቃሉ!

‹ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል› ይባል የለ? በቅርቡ ከዓረብ አገራት አንዷ የሱዳንንና የኢትዮጵያን የድንበር ውዝግብ ልሸምግል ብላ የጀመረችውን ጉዞ እናንተ የምትጣሉበትን ለሙን የአልፋሽጋን ምድር እኔ ላልማው ብላ እርፍ ብላለች የሚል ጭምጭምታ ተሰምቷል። ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የላትም የሚል ሕገ-መንግሥት ታቅፈው ኢትዮጵያን እንወዳለን የሚሉት ብልጽግናዎች ያላፈሩ፣ ይህች ዓረባዊት አገር ተንጠራርቼ በአፍሪካ ምድር ግዛት ይኑረኝ ብትል ምን ይገርማል?

የሱዳንን ወረራ ተከትሎ ወደ ጅቡቲም የተሰማ ጉድ አለ። የሰነፍ ጎረቤት ከብቶችን ገፍቶ የራስን ጋጣ ማስፋት ምን ችግር አለው ያለችው ጅቡቲ፣ የአዋሽ ተፋሰስ ልማት ብላ ያዘጋጀችው ካርታ ሰፋ ያለ የኢትዮጵያ አፋሮችን ምድር ወደ ጅቡቲ የደባለቀ መሆኑ ታይቷል። የጅቡቲው ፕሬዘዳንትም በአንዱ ንግግራቸው ይህን የሚያረጋግጥ አነጋገር ካሰሙ በኋላ ጫጫታ ሲከተል አነጋገሬ ተዛብቶ ተተርጉሟል ብለው ጉዳዩን ለማድበስበስ መሞከራቸው ተሰምቷል።

የጅቡቲው መሪ ይህን ማድበስበሻ ያስተጋቡ እንጂ በቢሮአቸው ውስጥ በፍሬም ተከሽኖ የሚታይ ካርታ ጅቡቲ ወደ ምዕራብ ሰፍታና ገዝፋ ያሳያል ከሚል መግለጫ ጋር በሰፊው ሲሰራጭ ከርሟል። ጅቡቲ የሱዳን ፍላጎት ተለጥጦ እስከ ድንበሯ ጥግ ከመድረሱ በፊት የራሴ ነው የምትለውን ድርሻ እያሳወቀች ይሆን? ሌሎች ያልደፈሩትን አገርን በመገነጣጠል ለማፍረስ የሚረዳ ሕገ-መንግሥት ያጸደቅን የዓለማችን ብቸኛ መንግሥት ነን ብለው የሚኩራሩት ሕወሐት/ኢሕአዴጎች በብልጽግና ሥም የሚጨፍሩባት አገር ናትና፣ በጅቡቲና በሱዳን መንግሥታት ድርጊት ብዙም መገረም አይገባንም።

በቅርቡ በአፋርና በሱማሌ ክልሎች መካከል ግጭት ተከስቶ የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ይታወቃል። በዚህኛውም ሆነ በሌሎች በዚያ አካባቢ የሚከሰቱ ግጭቶችና ግድያዎች የጅቡቲ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት መኖሩ በተደጋጋሚ ይነገራል። የጅቡቲ ኃይሎች የጦር ተሽከርካሪዎች የታዩባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውም ይነገራል። ይህን መሰሉ ጣልቃ ገብነት ሃቅነት ያለው ከሆነ የጅቡቲ ድብቅ ዕቅድ ምን መሆኑን ማጥናት ተገቢ ይሆናል።

ማንም እንደሚያውቀው ጎረቤት ሶማሊያና ኤርትራ በኢትዮጵያ የተያዘባቸውና ሊያስመልሱት የሚፈልጉት ምድር እንዳለ አቋም ይዘው ጦርነት በመክፈት መሬት ለመቀማት የሞከሩ አገራት ናቸው። እናም ኢትዮጵያን የመቀራመቱ ጉዳይ በሱዳንና በጅቡቲ የተገደበ አይደለም። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የኤርትራ ጦር በኢትዮጵያ ምድር እየተዋጋ ነው የሚል ወሬ መሰማቱን ተከትሎ ከሰጡት መግለጫ በመነሳት ኤርትራ የኔ ነው የምትለውን ምድር የያዘች ይመስላል።

ሃቅ ቁጥር ኹለት
የዛሬ ወዳጅ የነገ ጠላት፣ የዛሬ ጠላት የነገ ወዳጅ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም፣ ነገራችንን ማንኛውም ወዳጅም ሆነ ጠላት እያልን እንቀጥል። ማንኛውም ጠላት ወይም ወዳጅ አሳምሮ እንደሚያውቀው በግንቦት 1983 በሰፈነው የሕወሐት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን ኢትዮጵያ ለዘበኝነት የማይመጥኑ ነገር ግን ለሕወሐት ያልተገደበ ታማኝነትና ታዛዥነት ያላቸው ራስ ወዳዶች የሚሾሙባትና የሚሸለሙባት አገር ሆናለች። እነዚህ ግለሰቦች ሕወሐት በጠፈጠፋቸው ዘውጌአዊ የፖለቲካ ድርጀቶች ውስጥ አንድን ሕዝብ እንወክላለን ብለው ቢሰባሰቡም፣ ለሕወሐት ያላቸውን ታማኝነት ከሚያሳዩባቸው ዋና ዋና መንገዶች አንዱ እንወክለዋለን የሚሉት ሕዝብ በሕወሐት ተረግጦ እንዲገዛ ማድረግና አሻፈረኝ ካለም ስቃዩንና መከራውን በማብዛት አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር ማድረግ ነው።

በጠቅላላው ሕወሐት የጠፈጠፋቸው የኢሕአዴግ አባል እና አጋር የሚባሉት ድርጅቶች ሕዝብንም ሆነ አገርን ለመጉዳት የተዘጋጁ ግለሰቦችን ያቀፉ መሆኑ ግልጽ ነው። እንግዲህ እነዚህ ድርጅቶች የቀድሞ ሰዎቻቸውን እንደያዙ ራሳቸውን ብልጽግና ብለው አደራጅተው በአገራት ታሪክ ታይቶ ተሰማቶ አያውቅም ለማለት በሚያስደፍር ዝርክርክነት አገሪቱን እንደ ሰካራም እየተንገዳገደችና አቅጣጫው በውል ባልለየለት አካሄድ እያፍገመገሟት መሆኑን ጎረቤቶቻችንም ሆነ የሩቅ መንግሥታት በግልጽ እያዩ ባሉበት ጊዜ ላይ እንገኛለን።
ከአዲሰ አበባ በቅርብ ርቀት ካሉ ጎዳናዎችና ቦታዎች ጀምሮ እስከ ጫፍ ድንበር ድረስ ማንም ሰው፣ በተለይም ከክልሉ ውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ዘና ብሎ ከቦታ ቦታ መጓዝና ሠርቶ መኖር በእጅጉ ርቆታል። ሥም ያላቸውም ሆኑ ሥም የሌላቸው ቡድኖች በየቦታው ውጊያ ይከፍታሉ፣ መከላከያ ወይም ልዩ ኃይል ወደ ቦታው እስኪደርስ ግድያዎችን፣ ዝርፊያዎችንና የማውደም ተግባራትን ይፈጽማሉ። ወደ ቦታው ብቅ ብሎ የነበረው መከላከያ ወይም ልዩ ኃይል ከቦታው ሲወጣ ደግሞ ይኸው ድርጊት እንደገና ይፈጸማል።

ትግራይ ለተጋሩ እንደ ሶርያ ሆናባቸዋለች። ኦሮምያ፣ ቤኒሻንጉልና ደቡብ ክልል ዋና ዒላማ ተደርጎ ለረዥም ጊዜ መከራን ላስተናገደው ለአማራው ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የክልሉ ነዋሪዎች አይደሉም ለሚባሉ ሕዝቦች ሁሉ እንደ ሶርያ ሆነውባቸዋል። እነዚህን የመሳሰሉ ፍጻሜዎች ብዙዎች ኢትዮጵያ እየፈራረሰች ያለች አገር እንደሆነች አድርገው እንዲያስቡ እያደረጋቸው ነው።

ለችግሮች መፍትሔ ከመጠቆም ይልቅ በኢትዮጵያ ላይ አፋቸውን ሞልተው ክፉ ክፉውን በማሟረት ላይ ወይም እጅግ የከፋ ሰቆቃን በመተንበይ ላይ ሰፊ ሥራ የሚሠሩ የተለያዩ በውጭ የሚኖሩ ስደተኞች አሉ። እነዚህ ግለሰቦች ቀድሞ የኢሕአዴግ አባላት የነበሩና ለሕዝብና ለአገር ብለው ሳይሆን ጥቅማቸው ስለተነካ ወይም ይገባናል የሚሉትን ጥቅማ-ጥቅምና ሥልጣን ስላላገኙ ወይም በሌላ ሰበብ አኩራፊ ሆነው ሕወሐት/ኢሕአዴግንና አገሪቱን ጥለው ወደ ውጭ የተሰደዱት ናቸው።

ታምራት ላይኔ፣ በኢትዮ-360 ሚድያ ውስጥ የሚሠሩ ኹለት ግለሰቦችና ሌሎች የሐይማኖት ሰዎች ነን የሚሉ ግለሰቦች፤ በተናጠልና እየተጠራሩ በሚሠሯቸው ፕሮግራሞች ኢትዮጵያ ከሶርያ በብዙ እጥፍ የበለጠ ውድመትን፣ የሩዋንዳውን ፍጅት የሚያስንቅ መራር እልቂትን በቅርቡ እንደምታስተናግድ አፋቸውን ሞልተው ደጋግመው በመናገር ላይ ናቸው። ግለሰቦቹ እነሱ አሜሪካዊ ስለሆኑ ከችግሩ የራቁ ዕድለኞች መሆናቸውንና ይህን ማስጠንቀቂያ የሚሰነዝሩት በአገር ቤት ለሚኖረው ሕዝብ ብለው መሆኑን በኩራት ይናገራሉ።
እነዚህ ስደተኛ ግለሰቦች የኢሕአዴግ ስርዓትን አረመኔነት፣ ለማንም ለምንም የማያስቡና የማይጨነቁ ግለሰቦች የታጨቁበት ድርጅት መሆኑን፣ በአገርም ሆነ በሕዝብ ላይ የመጣው ኪሳራ ቢመጣ ብዙም ግድ የማይሰጣቸው ግለሰቦች የተሰባሰቡበት ድርጅት መሆኑን እነሱን ጨምሮ የሌሎች የቀድሞ ጓዶቻቸውን ተሞክሮ መሠረት አድርገው እየተናገሩ መሆኑ እርግጥ ነው። እነዚህ የቀድሞ የሕወሐት/ኢሕአዴግ አጫፋሪዎች የሕወሐት/ኢሕአዴግ ስርዓት ላለፉት በርካታ ዓመታት ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሆ ብሎ ተነስቶ እየተጨራረሰ ሲዳከም ስርዓቱን የራሱን ዕድሜ ለማራዘም የወጠነው ሴራ ብዙም ያልተሳካው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ሕዝብ እነሱ እንደ መጥፎ አብነት አድርገው እንደሚጠቅሷቸው የሌሎች አገራት ሕዝቦች በመንጋ ተነስቶ በሌላው ወገኑ ላይ ለመዝመት የሚፈቅድ እምነት፣ ባህልና አስተሳሰብ የሌለው ሕዝብ በመሆኑ መሆኑን ረስተውታል።

እነሱ በርካሽ ራስ ወዳድነትና በጠባብ አስተሳሰብ ተነሳስተው የሕወሐት ሎሌዎችና የሕዝብ ጠላቶች እንደሆኑት ሁሉ አሁንም በየብሔረሰቡ ውስጥ በጣም ጥቂት የሚባሉ ግለሰቦች ተሰባስበው የጭካኔ ተግባራትን እየፈጸሙ መሆኑን፣ እነዚህ ጥቂት የሚባሉ ግለሰቦች በየቦታው ግድያዎችንና ውድመቶች የሚያደርሱት ደግሞ የቀድሞ ከኢሕአዴጋዊ ጓዶቻቸው አገርንና ሕዝብን ለመምራት የሚያስችል ዕውቀትና ብስለት ሰለሌላቸው፣ ሌሎቹ ጓዶቻቸው ደግሞ ከጥቂቶቹ ክፉዎች ጋር ተባባሪ በመሆን ጸረ-ሕዝብነታቸውንና ጸረ-ኢትዮጵያዊነታቸውን ስለሚያራምዱ መሆኑን ለአፍታም ሊረሱት አይገባም።

ያም ሆነ ይህ ማናቸውም የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያችን በሕልውናዋና በሕዝቦቿ ደኅንነት ላይ ቁማር እየተጫወቱ ራሳቸውን የሚያበለጽጉና የሚያደልቡ ግለሰቦች ከቀበሌና ከመንድር ሥልጣኖች ጀምሮ እስከ ፌዴራል ሥልጣኖች መኮልኮላቸውን ያውቃሉ። ጠላትም ሆኑ ወዳጆች የውጭ ኃይሎች ሕወሐት/ኢሕአዴግ የሚባለው ቡድን ለኢትዮጵያ ምን ማለት መሆኑን አሳምረው ያውቃሉ።

ጠለቅ ብለውም ኦሕዴድ ለኦሮሞ ሕዝብ ምን ማለት መሆኑን፣ ብአዴን ለአማራ ሕዝብ ምን ማለት መሆኑን፣ ደኢሕዴን ደቡብ በተባለው ክልል ውስጥ ለተጠረነፉት ሕዝቦች ምን ማለት መሆኑን እንዲሁም ሌሎች የኢሕአዴግ አጋር የሚባሉ ድርጅቶች ለየሕዝቦቻቸው ምን ማለት መሆናቸውን አሳምረው ያውቃሉ። የወዳጆቻችንና የጠላቶቻችን እውቀት በዚህ የተገደበ አይደለም። ከአባዱላ ገመዳ እስከ ዐቢይ አሕመድ ያሉት ኦሕዴዶች ለኦሮሞ ሕዝብ ምንና ምን መሆናቸውን፣ ከበረከት ስምዖን እስከ አገኘሁ ተሻገር ያሉት ኢሕዴን/ብአዴኖች ለአማራው ሕዝብ ምንና ምን መሆናቸውን ያውቃሉ።

ጠላቶቻችንና ወዳጆቻችን ደቡብ ክልልን፣ አፋርን፣ ሶማሌን፣ ጋምቤላን፣ ቤኒሻንጉልን፣ ሐረሪን፣ ድሬዳዋን፣ አዲስ አበባን ከታችኛው እስከ ላይኛው ወንበር ተቀምጠው የሚገዙት ፖለቲከኞች ለየሕዝቦቻቸው ምንና ምን መሆናቸውን በሚገባ ይውቃሉ። የውጭ ኃይሎች የቀድሞዎቹ ኢሕአዴጋውን የአሁኖቹ ብልጽግናዎች ምን ዓይነት ሥነ ልቦናና ሥነ አዕምሮ ያላቸው ግለሰቦች መሆናቸውን በሚገባ ያውቃሉ። ለሕወሐት ለመታዘዝና ለመላላክ ሲሉ ሁሉም በየሕዝቦቻቸው ላይ ለጌታቸው አሰፋ ታዛዥ ሆነው ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ ሲሆንም ራሳቸው ጌታቸው አሰፋን ሆነውና ጌታቸው አሰፋን ተክተው በሕዝባቸው ላይ ግፍና በደል፣ ሰቆቃንና ስቃይን እያዘነቡ የኖሩ መሆኑንም በሚገባ ያውቃሉ።

በመጨረሻም የፖለቲከኞችንና የካድሬዎችን ወሬ እየሰሙ በማሸርገድ ሥራ ላይ ለተጠመዱ ምሁራን ዐይኖቻችሁን ግለጹ ማለት ተገቢ ነው። ምሁራኑ ለዘበኝነት የማይመጥኑ አድርባዮች የሚለውን መመዘኛ በማሟላትና ለሹመትና ለሽልማት ራሳቸውን በማዘጋጀት ያሉ ይመስላሉ። ከቤተ-መንግሥት የሚፈበረከውንና ከየካድሬው የሚወሸከተውን መናኛ ወሬ ሁሉ እንደ ትልቅ ቁም ነገር አድርገው በማስተጋባት ላይ ናቸው። እነዚህ ምሁራን ከየዩንቨርሲቲው ብቅ እያሉ ከሚነግሩን ነገሮች እንዱ ከውጭም ሆነ ከውስጥ ለሚከሰቱት ችግሮች ሁሉ መፍትሔው ምርጫውን ማካሄድ ነው እያሉ ነው።

አሁን ያለው የኢትዮጵያ አገዛዝ ሕጋዊና በሕዝብ የተመረጠ ስላልሆነ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን መረበሼን አላቆምም ያለችው ሱዳን ትሁን ጅብቲ፣ ሕወሐት ይሁን ኦነግ ሸኔ፣ የቅማንት ኮሚቴ ይሁን የጉምዝ ነጻ አውጭ ወይም ሌሎቹ መሆናቸውን በሚመለከት ማስረጃ ባያቀርቡልንም ምሁራኑ ምርጫውን እንደ አስማተኛ ወይም ተአምረኛ ሰላም ማስፈኛና የኢኮኖሚአችንን የቁልቁለት ጉዞ ማቆሚያ መሣሪያ አድርገው እየነገሩን ነው።

የአንዳንዶቹ ምሁራን የገደምዳሜ አካሄድ የሐይማኖትና የዘር ማንነታቸውን ተንተርሶ የሚሰነዘር ጭፍንና የግብዝነት ፕሮፓጋንዳ ከመሆን አልፎ አሁን አገሪቱ ዝርክርኳ በወጣበት መንገድ የሚመራት ቡድን ቢመረጥ ሰላምና ብልጽግና ይትረፈረፋል ሊሉን እየሞከሩ ነው። እነዚህ ምሁራን ቀደም ብለው የኢትዮጵን የባሕር ኃይል ስለመመሥረት፣ የኢትዮጵያን የሳይበርና የሕዋ ሠራዊት ወይም ስፔስ ጦር ስለመገንባት በፖለቲከኞች ሲወራ ስለ ተገቢነቱ መግለጫ ሲሰጡንና ስለ አዋጭነቱ ሲያጨበጭቡልን የነበሩ ናቸው።

እነሆ ዛሬ ሕዋ ውስጥ መንጎራደዱ፣ በቀይ ባሕርና በውቅኖሶች ላይ መንፈላሰሱ ቀርቶ ከአዲስ አበባ ጎጃም መሄድና ከአዲስ አበባ ደሴ መድረስ ሕይወትን የሚጠይቅ ፈታኝ ነገር እየሆነ ነው። እነሆ ዛሬ ከክልላቸው ውጭ ለሚኖሩ ዜጎች ኑሮ በሰቀቀን የተሞላ እየሆነባቸው ነው። ታዲያ የእነዚህ ምሁራን የምርጫ ቅስቀሳ ከዚህ የተለየ ውጤት ያመጣ ይሆን?

እነዚህ ምሁራን በሕወሐት/ኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ኦነግና ግንቦት ሰባትን የመሳሰሉ ቡድኖች በኢትዮጵያው ምክር ቤት አሸባሪ ተብለው ተፈርጀው በአሜሪካና በአውሮፓ፣ በግብጽና በሌሎች አገራት እንዳሻቸው እየተሞላቀቁ መኖራቸውን ቢያውቁትም፤ የብልጽግና ምክር ቤት ሕወሐትና ኦነግ-ሸኔን አሸባሪ ብሎ ቢፈርጃቸው መግቢያና መውጫ እንደሚያጡ፣ እንደሚሽመደመዱና እንደሚጠፉ እየነገሩን ነው። ነገሩ የሚገርም ነው። እነዚህ ምሁራን እኮ የአውሮፓንና የአሜሪካን፣ የግብጽንና የሱዳንን መንግሥታትን ብልጽግና እንደሚመራቸው ሊነግሩን እየሞከሩ ነው። ‹የተማረ ይግደለኝ!› የሚለው ተረታችን ትንቢት ሆኖ እየተፈጸመ ይሆን?


ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com