የኃይማኖት መሪን ግለሰቦች የገመገሙበት ታሪክ

Views: 214

በፖለቲካው ዓለም የበታቾች የበላያቸውን የመገምገም ልምድ የመኖሩን ያህል፣ አንድ የኃይማኖት መሪን ምዕመናን ወደላይ መገምገም አይቻላቸውም። ገምግሞ ማውረዱ ይቅርና አንዴ ከተሾሙ በኋላ በፍላጎት መስማት እንጂ መውቀስ ለተራው ሕዝብ አይፈቀድም። በፈጣሪ ምሳሌነት ተቀብተው ስለሚቀመጡ እነሱን መንካት ሁላችንን የፈጠረንን ገምግሞ ከፈጣሪነት አምላካዊ ዙፋኑ ለማንሳት እንደመሞከር ይታያል።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ፣ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከሰሞኑ የትግራይን ጉዳይ የበለጠ ትኩረት ሰጥተው የተናገሩበት የቆየ ንግግራቸው ይፋ መውጣቱን ተከትሎ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆነዋል። ከዚህ ቀደም የምዕመናን መገደልና መፈናቀል፣ እንዲሁም የአብያተ ክርስቲያናት መውደምን ተከትሎ ድርጊቱ በእሳቸው ዘመን መፈጸሙ አሳዝኗቸው በአደባባይ ማልቀሳቸው አይዘነጋም። ይህን የመሳሰለ ተግባራቸውን በቅርበት የሚከታተሉ ለሁሉም እኩል፣ በተለይ ለተጎዱ ማሰብና መናገር ኃላፊነታቸው እንደሆነም ይናገራሉ። በተቃራኒው ደግሞ ትውልዳቸው ከትግራይ መሆኑንና በህወሓት ዘመን መሾማቸውን የሚያነሱ፣ እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸውን በቅርብ በመከታተል አቃቂር ይፈልጉባቸዋል።

ቅዱስ ፓትርያርኩ በንግግራቸው ላይ ስማቸውን ያልጠቀሷቸው አካላት እንደሚቆጣጠሯቸውና ሲናገሩም እየገመገሙ በተደጋጋሚ ሀሳባቸውን እንደሚያስቀሩባቸው ተናግረዋል። ይህን በመሰለው አጠቃላይ ንግግራቸው የመንግስት ባለስልጣናትና ደጋፊዎቻቸው ወገንተኛ ሆኑ ብለው ወዲያውኑ ሲዘልፏቸው፣ ሌሎች ደግሞ ያላቸውን ጥላቻ እሳቸውን በይፋ በመዘርጠጥ አሳይተዋል። ድርጊቱ የእስልምና ኃይማኖት መሪ የሆኑት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር ኢድሪስ ላይ ተደረገውን አይነት ዘለፋና ትችት ቢመስልም ሳይበርድ ለቀናት ቀጥሏል።

በተቃራኒው የእምነቱ ተከታይ የሆኑ ምዕመናን፣ መምህራንና ካህናት “ሰድባችሁ ለሰዳቢ አትስጡ” በሚል ነቃፊዎቹን ተችተዋል። በየቀኑ በተካሄዱ የቃላት ውጊያዎች አሸናፊው ሳይለይ ተሳታፊዎቹ ጨምረው ጦርነቱ ቀጥሏል። መምህር ዘመድኩንን የመሳሰሉ ተደማጭነት ያላቸው መምህራን ከውጭ አገራት ሽንጣቸውን ገትረው የእሳቸው መሰደብ ኃይማኖቱን እንደሚያሰድብ ለማስረዳት ሞክረዋል። እሳቸውንም በቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ላይ በመጋበዝ ምንም ቢመጣባቸው እንደተወራባቸው አገራቸውን ጥለው የትም እንደማይሄዱ እንዲያሳውቁ እድል ሰጥቷቸዋል። ታደለ ጥበቡን የመሳሰሉ ተቆርቋሪ አክቲቪስቶችም ለቀናት ወጥረው ተከራክረው ሀሳባቸውን ለማስረጽ ጥረዋል። ብዙ ምዕመናን ቢያንስ በአባትነታቸው መከበር ይገባቸዋል እያለ ፎቷቸውን በመለጠፍ ጭምር ጎራውን እየለየም ሆነ ጥይት እያቀበለ መተጋተጉን ተቀላቅሏል። በአንፃሩ ስማቸውን ለማጉደፍ የወያኔን ስራ ሳይተቹ ኖረዋል እያሉ ለሚናገሩም የሌሎች አሁን ባለስልጣናትን ታሪክ እያነሱ ምላሽ የሰጡም ነበሩ።

ከንግግራቸው ጋር በተገናኘ ጥቂት የኃይማኖቱ መምህራን ሲዘልፏቸውም ታይቷል። ከእነሱ በይበልጥ መነጋገሪያ የነበረው የእምነቱ ተከታይ ባልሆኑና የመንግስት ባለስልጣናት በሆኑ የቀረበ አዋራጅ ንግግር ነው። አቶ ታዬ ደንደአን ከመሳሰሉ ሹመኞች ይልቅ በመንግስት ደጋፊነታቸው የሚታወቁ ሰዎችና አቶ ታዬ ቦጋለን የመሳሰሉ ግለሰቦች የሰነዘሩት ስድብ ማለት የሚቻል ነቀፌታን ተከትሎ የተሰሙት ንዴት አዘል ምላሾች ይጠቀሳሉ። “የህወሓት ደጋፊ ናቸው፤ የእነሱን ፕሮፖጋንዳ ነው ያስተላለፉት።” እያሉ የማይወዷቸው ቢዘልፏቸውም፣ ሌሎች ደጋፊዎቻቸውም ሆኑ የእምነቱ ተቆርቋሪዎች “እኔ የሁላችሁም አባት ነኝ፣ የትም አልሄድም” ብለው መናገራቸውን እያወሱ የሕዝቡን ልብ ለመግዛት ሞክረዋል።

የቃላት ሽኩቻው መግለጫ በማውጣትም የታጀበ ነበር። በመጀመሪያ የቅዱስ ፓትርያርኩ ንግግር ቤተክርስቲያንን አይወክልም የሚል ይዘት ያለው መግለጫ ወጥቶ በተለያዩ ሚዲያዎች በፍጥነት እንዲሰራጭ ተደርጓል። መግለጫውን የሰጡት አቡን የመንግስትና የአንድ ሌላ ፓርቲ ደጋፊ ናቸው ተብለው ሲተቹ ውለዋል። “እሳቸውን ማን ወክሏቸው ነው የፓትርያርኩ ንግግር አይወክልም የሚሉት” በሚል የቤተክርስቲያኒቱን የዘመናት ስርዓት የጣሰ አካሄድ ነው ተብለው ተተችተዋል። ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳውያን ወጣቶችና ጎልማሶች ማኀበራት ሕብረት የአቋም መግለጫ አውጥቷል። የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም ይቅርታ በጠየቀበት መግለጫው ብዙ አስተያየተና ትችት ተሰንዝሮበታል። ማኀበረ ቅዱሳንም፣ “ቤተክርስቲያን ስደት ላይ ነች” በማለት የተከፈተባት ዘመቻ ላይ የሚያተኩር መግለጫ አውጥቷል። በአርባምንጭ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጎን ነን በሚል መፈክር የድጋፍ ሰልፍም ተወጥቶ ነበር።


ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com