ዘሚ የኑስ

Views: 103

ዘሚ የኑስ የኒያ ፋውንዴሽንና የጆይ ኦቲዝም ማዕከል መስራች ነበሩ። “በኮሮና እንዳልሞት ጸልዩልኝ” በማለት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረው እንደነበር የሚታወስ ነው። ይህን ቢሉም የብዙ ኦቲዝም ተጠቂ ህፃናት እናትን ተነጥቀናል።
ዘሚ የዛሬ ዓመት ጥቅምት 2012 ከአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ጋር አድርጋው ከነበረው ቃለ መጠይቅ የቀነጨብኩት ነው። የዘሚን ሃሳብና ማንነት በትንሹ ታገኙበታላችሁ።

“ዘሚ የተወለደችው አዲስ አበባ ነው። እንደ አብዛኛው የአዲስ አበባ ህጻን ከመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ካሉ ሠርቶ አዳሪዎች የተወለደች ግን በጥሩ ያደገች፣ እናትና አባቷ ለአንድ ልጅ የሚገባውን ሁሉ እየሰጡ ያሳደጓት፣ ካቴድራል ትምህርት ቤት የተማረች፣ ደስተኛ እና ራሷን የሆነች ልጅ ናት።” በማለት ነበር ራሷን የገለጸችው።

“ራሷን የሆነች ልጅ ስል ከልጅነት ጀምሮ ማንንም አልከተልም። አዳዲስ ፈጠራዎች ራሴ እፈጥራለሁ፣ መልበስ የምፈልገውን በራሴ ዲዛይን እለብሳለሁ። በዚህ አባቴ በጣም ነው ይደግፈኝ የነበረው፤ ራስሽን ሁኚ ይለኝ ነበር። እናቴ ግን በዚህ ትንሽ አትስማማም። በጣም ጠንካራ እናት ነበረችኝ። ለምሳሌ ልብስሽ አጠረ ብላ ትጥላለች። ግን ጥሩ ነው ያደኩት፤ ልጅነቴንም ተጠቅሜአለሁ። በዝናብ መደብደቡ፣ ጭቃ እና ጎርፍ ላይ መጫወት፣ ተልኬ ስወጣ ጠፍቼ ጓደኞች ጋር መሔድ፣ ያላሳለፍኩትና የማላውቅበት ከእኩዮቼ ጋር መጣላትና መደባደብን ነው።” በማለትም ልጅነቷን እና እድገቷን አስታውሳ ነበር።

“በኒያ ፋውንዴሽን የምንሠራው ኦቲዝም ላይ ብቻ አይደለም። ከኦቲዝም በፊት ወጣቶች ላይ ብዙ ሠርተናል። በተለይም የተቸገሩ ወጣቶች ላይ፣ ሴተኛ አዳሪ ሆነው የሚተዳደሩ ሴቶች ላይ፣ ችግር ላይ ያሉ ወንዶች፣ ምክር፣ ሥራ… ብቻ ሰው የሚፈልጉ ወጣቶች ላይ ብዙ ሠርተናል። ከዛ ነው ወደ ኦቲዝም የገባነው።” በማለትም የበጎ አድራጎት ሥራ ጅማሮዋን ገልጻ ነበር።

ለሳምንታት ያህል በህክምና ሲረዱ ቆይተው ማክሰኞ ግንቦት 3 ቀን 2013 በጳውሎስ ሆስፒታል ማረፋቸውን በተለያዩ ማኅበራዊ ገጾች፣ የመንግስት እና የግል መገናኛ ብዙኀን ደረ ገጾች ላይ ተገልጿል። ዘሚ የኑስ ሚያዝያ 4 ቀን 2013 የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ሲያደርጉ የኮሮና ቫይረስ ስለተገኘባቸው እና ከቀናት በኋላም ለመተንፈስ ተቸግረው ኦክስጅን በማስፈለጉ ሚሊኒየም ሆስፒታል ገብተው ሲታከሙ ነበር። ወደ መጨረሻም ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተዛውረው በጽኑ ህክምና ማዕከል ውስጥ ሲረዱ መቆየታቸውን ተገልጿል።
በጆይ ኦቲዝም ማዕከል የስንብት ሥነ ስርዓት የተከናወነላቸው ሲሆን፣ ግንቦት 3 ቀን 2013 የቀብራቸው ሥነ ስርዓት ተፈጽሟል። ወይዘሮ ዘሚ የኑስ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ነበሩ።


ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com