የበረኸኛው የአቶ ጌታቸው ረዳ እንጉርጉሮዎች! ክፍል 1

Views: 110

በተለያየ ጊዜ ከሩቅ እንዲሁም ቅርብ ከተባሉ ጎረቤቶች የወረራ ሙከራ የተደረገባት ኢትዮጵያ ሁሉንም በአሸናፊነት ተወጥታቸዋለች። በአብዛኛው ታድያ እነዚህ ወረራዎችና የወረራ ሙከራዎች የሚደረጉት ኢትዮጵያ በውስጥ አለመረጋጋት በምትታመስበት፣ በረሃብ፣ በግጭት፣ በፖለቲካ አለመስማማት መካከል በምትሆንበት ጊዜ መሆኑንም ታሪክ ያስረዳናል። ግዛቸው አበበ አሁንም በውጪ ያሉና ኢትዮጵያ ወድቃ ለማየት አልፎም ለመቀራመት የሚመኟት ጎረቤት አገራት ሳይቀሩ በውስጧ ስላለው አለመረጋጋትና ችግር ይህንን ያውቃሉ፣ እናም እንደ አገር ይህን ልብ ማለት ያሻል ሲሉ ሐሳባቸውን እንደሚከተለው አስፍረዋል።

ክፍል 1
የነገሮች አመጣጥንምና ሆነ አካሄድ አቅጣጫና ፍጥነት ለመገመት የሚያስቸግር፣ መጭው ጊዜ ምን እንደሚያመጣ በእርግጠኝነት ለመናገር የሚያዳግት ነውና “የጌታው ረዳ እንጉርጉሮወች” የሚለው አርእስት “የጌታቸው ረዳ ዛቻወች” ወይም “የጌታቸው ረዳ ትንቢቶች” ወይም “የጌታቸው ረዳ ሟርቶች” ሊባል ይገባው ይሆናል። እንዲህ ሲባል ደግሞ ከሕወሐት ወቅታዊ ሁኔታ ይልቅ የብልጽግና ቡድን ደካማነትና ዝርክርክነት ነገሮች ወደየት ሊያመሩ እንደሚችሉ በእርግጠኛነት መናገር አለመቻሉን ለማመልከት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን እነ አቶ ጌታቸው ረዳ የጥቅምቱ “ሕግ-የማስከበር” የተባለ ጦርነት ጊዜ እየወሰደ በመጣ ቁጥር ነገሮችን እንደ ጨዋታ እየተመለከቷቸውና ቀስ በቀስ ብልጽግናዎችን ቀድሞ በኢሕአዴግ ዘመን ሲያደርጉት እንደነበረው እንደ አሻንጉሊቶቻቸው አድርግው ሊጫወቱባቸውና በደካማነታቸው እየተጠቀሙ ሊያንሰራሩ እንደሚችሉ ብቻ ሳይሆን ትግራይን ሙሉ በሙሉ መልሰው እንደሚቆጣጠሩ እርግጠኛነት እየተሰማቸው መሆኑን የሚሳብቁ ሁኔታወች እየታዩ መሆኑ ነው። አዎ! አቶ ጌታቸው ረዳ በውጭ ለሚኖሩ ትግራይን መልሶ መገንቢያው ጊዜ ቅርብ ስለሆነ በሃሳባቸው፣ በሃብታቸውና በችሎታቸው ለመተባበር ቅድም ዝግጅት ያደርጉ ዘንድ ጥሪ ሲያቀርቡ ተሰምተዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ እንደ መስቀል ወፍ እየከራረሙ ብቅ ሲሉ ከሚሰጧቸው መግለጫወች በተደጋጋሚ የተደመጡ ጥቂት ነጥቦች አሉ። በተደጋጋሚ የሚያነሷቸው ነጥቦች የብልጽግና ሰዎች አይረቤነትና አሻንጉሊትነትን ጠቅሰው ብልጽግናወች አገሪቱን ወደ ገደል እየወሰዷት መሆኑን፣ በሕዝቡ ምሬት የትግራይ መገንጠል አይቀሬነትንና የሕወሓት ወደ ገዥነቱ መመለሱ በቅርብ የሚሳካ መሆኑን እና ጸረ-አማራ ዛቻወች ናቸው።

የብልጽግና ሰወች አይረቤነትና አሻንጉሊትነትን…!
አቶ ጌታቸው ረዳ የብልጽግና አውራዎችና የአገሪቱ ጦር መሪዎች መቀለጃዎችና ማሾፊያዎች መሆናቸውን፣ የጦር መሪወች የሚባሉት የሚጠሩበት ማዕረግ የማይገባቸው መሆኑን፣ በከፍተኛ ስልጣን ላይ የተቀመጡት የብልጽግና ምሁራንም በተጭበረበረ መንገድ ባለ ማስተርና ባለ ፒ.ኤች.ዲ. መባላቸውን ወዘተ. ተናግረዋል። አቶ ጌታቸው ይህን ሲሉ የህወሓት/ኢሕአዴግን ስርዓትን ጉድ እየመዠረጡትና እያጋለጡት መሆኑ እንዴት ውል ሊልላቸው እንዳልቻለ ግልጽ አይደለም። አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የያዙት የጦርም ሆነ የትምህርት ማዕረግ አይገባቸውም የሚሏቸው ሰወች ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር መጠን አሁን የያዙትን የጦር ይሁን የትምህርት ማዕረግ ያገኙት ህወሓት ገዥ በነበረበትና እሳቸውም ጭምር ፈላጭ ቆራጭ ባለስልጣን በነበሩበት ጊዜ ነው። የጦሩንም ሆነ የትምህርቱን ማዕረግ በማራከስ ዋናው ተጠያቂ እንደ ድርጅት ህወሓት መሆኑን፣ እንደ ግለሰብም እሳቸውን ጨምሮ ዛሬ የሚሳደዱት የህወሓት አውራዎች በሙሉ መሆናቸውን ማመን አለባቸው። ከዚህ ሌላ ህወሓት ለዘበኝነት የሚመጥኑ ባይሆኑም ታማኞቼን ለከፍተኛ ሹመት አበቃለሁ እያለና አቶ ጌታቸው ረዳ እንደገለጹት ማዕረጎችን እንደ ተራ ነገር አድርጎ እንደ ከረሜላ እያደለ ከከረመ አሁን ፓርቲው የዘራውን እያጨደ ነው ማለት ነው። እዚህ ላይ ህወሓት ይህን የመሰለ የተላላኪወች ምልመላ ያካሄደው የስልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ብሎ ሲሆን፣ እግረ መንገዱን ደግሞ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ምንም የማይጨነቅ መሆኑን ለማሳየት ነው። እነዚህ ሰወች አገሪቱንም ሆነ የኢትዮጵያን ሕዝብ እጅግ ከባድ ዋጋ እያስከፈሉ መቆየታቸው የሚረሳ አይደለም። አሁን ደግሞ በተለየ መልኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ በብዙ መንገዶች ከባድ ዋጋ እየከፈለ ሲሆን አገሪቱም ስጋት ላይ ወድቃለች። የጥቅምቱን ግብግብ ተከትሎ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ በዘርፈ ብዙ መከራወች አበሳውን እያየ ነው።

አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አቶ ስዩም መስፍን፣ አቶ ስብሃት ነጋና ሌሎች የህወሓት አውራዎች ስለ ጠቅላይ ሚ/ሩ ሰብዕና፣ ስለ ትምህርታቸው፣ በስልጣን ጥም ያበዱ ስለመሆናው ብዙ ነገሮችን እየተናገሩ ነው። ለመሆኑ ዐብይ አሕመድ የሚባሉት ሰው ያንን ያህል አጠያያቂ ባህሪና አደገኛ አካሄድ ያላቸው ሰው ከሆኑ ህወሓት ለምንድን ሰውዬው ከክልል እስከ ፌደራል ስልጣን እየተቆናጠጡ እንዲኖሩ የፈቀደው? ጨዋታው ሆነ ችግሩ በሕዝብና በአገር ላይ እንጅ በህወሓት ላይ አይደለም ተብሎ ነው?

በገንዘብ ወይም በሌላ ጥቅማ-ጥቅም ደልሎ ‘አባትህን ግደልልኝ’ ብሎ ካስገደለ በኋላ ከዚህ ሰው ጋር ተሻርኮ መኖሩን የቀጠለ ሰው ሞኝ ነው። ለተራ ጥቅም ብሎ አባቱን የገደለ ሰው ጥቅም የሚያገኝበት ከሆነ ለእሱም እንደማይመለስ መገመት ነበረበት። እነ አቶ ጌታው ረዳ የዘነጉትና የተሞኙት እዚህ ላይ ነው። ለኦሮሞዎች ያልራራ የኦሕዴድ ሹመኛና ኣባል ለህወሓት ሰዎችም ሆነ ለተጋሩ ይራራልን? ለአማራወች ያላዘነ የብአዴን ሹመኛና ኣባል ለህወሓት ሰዎችም ሆነ ለተጋሩ ይራራልን? በደቡብ ክልል ለሚኖሩ ሕዝቦች ህልውናና ደህንነት ያልተጨነቀ የደኢሕዴግ ሹመኛና ኣባል ለህወሓት ሰዎችም ሆነ ለተጋሩ የሚጨነቅ ልብ ይኖረዋልን? የኢሕአዴግ አጋር ድርጅቶች ተብለው ለየሕዝባቸው መርዝ ሆነው የኖሩት ቡድኖች ሹመኞችና አባላትስ ለህወሓትም ሆነ ለተጋሩ ማር እንዲሆኑ ይጠበቃልን?

የትግራይ መገንጠልና የህወሓት ወደ ገዥነቱ መመለስ አይቀሬነትን…
አቶ ጌታቸው ረዳ ትግራይ ሚዲያ ሃውስ ላይ በድምጽም ሆነ በምስል ብቅ ባሉ ቁጥር ራሳቸውን ለችግሮች እንደማይንበረከኩና አገሩን እንደማይከዳ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ቆጥረው የትግራይን ሕዝብ ግን በደረሰበት በደል ተማርሮ ኢትዮጵያዊነቱን እርግፍ አድርጎ የሚተው አድርገው ያቀርቡታል። ሌሎች በትግራይ ሚዲያ ሃውስ ላይ ብቅ የማለት ዕድል ያገኙ የህወሓት ሰዎች ብዙዎቹ አሁን ትግራይ ውስጥ ሽምቅ ውጊያ መጀመሩንና ዓላማው የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን፣ መዳረሻው ትግራይ የምትባል አገርን ዕውን ማድረግ መሆኑን ሳያንገራግሩ በመናገር ላይ ናቸው።

ህወሓት ገና ከምስረታው በነደፈው ማኒፌስቶ ላይ፣ ትግራይን አገር የማድረግ ግብ ይዞ መነሳቱን ይናገራልና እነ አቶ ጌታቸው ረዳ በግልጽ ሊነግሩን የሚገባው በግንቦት 1983 ዓ.ም. ደርግን ሲያሸንፉ እንደ ኤርትራ ተገንጥለው መሄዱን ለምን እንዳልተገበሩት እንጅ፣ ስለ ህወሓትም ሆነ ስለ እያንዳንዱ የፓርቲው አመራርና አባል ኢትዮጵያዊ መሆንና አለመሆን አይደለም። ደግሞስ በ1987 ዓም ድራማዊ በሆነ አካሄድ በሕዝብ ውይይትና ውሳኔ ጸደቀ የተባለው ሕገ-መንግስት ‘የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል’ የሚል አንቀጽ የተካተተው ለማን ተብሎ ነው? በዚህ አንቀጽ ጊዜውን ጠብቆ እንዲጠቀምበት የተፈለገው ማን ነው? ለህወሓት ተብሎ አይደለምን? ለኦነግ፣ ኦብነግና ሌሎች መገንጠልን ሲያቀነቅኑ ለነበሩ ቡድኖች ሊተገበር ያልቻለው ለምንድን ነው?

አቶ ጌታቸው ረዳ እሳቸውና ጓዶቻቸው በረሀ ውስጥ እንዳልሆኑና በሕዝብ ታቅፈው በገጠሩ ሕብረተሰብ መካከል እየኖሩ መሆኑን ተናግረዋል። በሌላ አባባል የተነጠቅነው ከተሞችን፣ የተወገድነውም ከከተማ ስልጣን እንጅ ከጠቅላላው ስልጣን አይደለም እያሉ ነው። በእርግጥ አቶ ጌታቸው ረዳ በድጋሚ ዱር ቤቴ ያለው የህወሓት ቃል አቀባይና አማካሪ ተብለው ቢጠሩም፣ ትልቁ ስራቸው የፓርቲው ትልቅነት እንደተጠበቀ መሆኑን የሚያሳይ ፕሮፓጋንዳ በመስራት፣ በህወሓት በኩል የደረሱ ኪሳራወችን በሚመለከት ሃቆችን በመሸፋፈን፣ የድል ወሬወችን በመፈብረክና ትንንሾቹን የፓርቲውን ስኬቶች አግዝፎ በማቅረብ ለአባላትና ለደጋፊወቹ ብርታትን መፍጠር መሆኑን ማንኛውም ነገሮችን ማመዛዘን የሚችል ሰው መረዳት አያቅተውም። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የትግራይ ሕዝብ በህወሓት ላይ ጀርባውን እንዳያዞር ማግባባትና አልሆን ካለም በማስፈራራት ጠላት እንዳይሆን ወይም ከጠላት ጋር እንዳብር ማድረግ ነው። አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች ብልጽግናን ካመንን እንድናለን ከማለት ይልቅ ህወሓትን ከተቃወምነው ያጠፋናል ብለው የሚያምኑ ይመስላሉ።

ሚዲያዎች ላይ ብቅ የሚሉ የህወሓት ባለስልጣናት ፓርቲው የትግራይን ሕዝብ፣ ከተሞችንና ክምር ሃብቱን ጥሎ የሸሸው ስለተሸነፈ መሆኑን ማመን አይፈልጉም። ህወሓት በኃይለኛ ባላንጣው ተረትቶ ሚስቱን፣ ልጆቹን፣ ቤቱን፣ ሃብትና ንብረቱን አስረክቦ ወይም ጥሎ እንደሸሸ አባወራ ሊቆጠር የሚገባው መሆኑን መካድ አይቻልም፤ አይገባምም። ጥቅምት ላይ ጦርነቱ እንደተጀመረ አቶ ጌታቸው ረዳ መቐለ ላይ ሆነው ማንኛውንም በኢትዮጵያና በኤርትራ የሚገኝ አየር ማረፊያና ከተማ እየተቆጣጠሩ በሚሳይል ጥቃት እንደሚያሽመደምዱት እንጅ ወደ በረሀ ወይም ወደ ገጠር ወርደው እንደሚሽሎከለኩ እንዳልነገሩን ሊረሳ አይገባውም። የክልሉና የፓርቲው መሪ የነበሩት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) አስፈላጊ ከሆነ በብልጽግናወች አናት ላይ መዓት እንደሚያፈሱባቸው እንጅ ብልጽግናወች አባራሪ ህወሓት ተባራሪ እንደሚሆኑ አላሳወቁንም። ሰሜን ዕዝ ከተሸመደመደ ጭራሽ ጦርነት አይመጣብኝም ወይም ጠንካራ ጠላት አይኖርብኝም የሚለው ስሌቱ ስላልሰራ ህወሓት ያላሳበው ዱብ ዕዳ ገጥሞታል። የትግራይን ሕዝብ ጥሎ ራሱን ለማዳን ወደየመደበቂያው በጥድፊያ ሸሽቷል። ትግራይ ውስጥ በሚካሄደው ጦርነት የሚሞተው የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰራዊት ብቻ እንደሆነ፣ ትግራይ ሰላማዊ ሰዎች ብቻ እንጅ እንድም ተዋጊ እንዳልሞተባት ሊነግሩን የሚሞክሩ የፓርቲው ደጋፊና ተቀላቢ የሆኑ መገናኛ ብዙኀን ይህን ሃቅ መርሳትም መካድም የለባቸውም። የፓርቲው ውድቀት ያልተዋጠላቸው ሰዎች ራሳቸውን በእነ አቶ ስብሃት ነጋና በእነ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ፣ በእነ አቶ አስመላሽና በእነ አቶ ስዩም መስፍን ቦታ አሰቀምጠው ነገሩን መገምገም ይገባቸዋል።

እዚህ ላይ ሁለት ሀቆችን ማስቀመጥ ተገቢ ነው። አንዱ ህወሓት በደረሰበት ከፍተኛ ምት ከስልጣኑ የተባረረና የከተማ መዋቅሩ ብትንትኑ የወጣ ቢሆንም፣ እዚህና እዚያ የተበጣጠሰ አደረጃጀቱን እየጠጋገነ፣ ትንንሽ ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ስራወችን እያከናወነና ህልውናውን እንዳያጣ የሚያደርጉትን ሌሎች ትንንሽ ጥረቶችን እያደረገ ተለቅ ውዳለ ውጤት የመምጣት ዕድሉ ዜሮ ነው ማለት አይቻልም። ከዚህ በተጨማሪ እንክትክቱ ወጥቶ ከጥቅም ውጭ ሆነ የተባለን ማንኛውን የሸክላ ዕቃ ባለ ሙያወች ፈጭተው፣ አቡክተው፣ አዲሰ ቅርጽ ሰጥተውት፣ በእሳት ውበትና ጥንካሬ ፈጥረውለት መልሰው ጠቃሚ የሸክላ እቃ እንደሚደርጉት ሁሉ ህወሓትም ከዚህ እንክትክቱ ከወጣበት ደረጃ ተነስቶ ሙሉ በሙሉ ሊያንሰራራ ይችላል ብሎ መከራከር ይቻላል። አንድን ቡድን ለዚህ ዓይነቱ አፈር ልሶ የመነሳት ዕድል የሚያበቃው የራሱ ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን የባላንጣው ወይም የባላንጣወቹ ደካማነትና ዝርክርክነትም ጭምር ነው።

በዚህም ሆነ በዚያ፣ የአቶ ጌታቸው ረዳ የፈጠራም ሆነ በትንንሽ የእውነት ቅንጭብጫቢወችን ተመርኩዘው እንዲገዝፉ የተደረጉ ወሬወች በቁጥር ሁለት ኢሕአዴግ ወይም በብልጽግና ቡድን ደካማነትና ጥበብ የለሽነት ውጤታማ ፕሮፓጋንዳወች እየሆኑ መምጣታቸውን መካድ አይቻልም። ህወሓት ደጋፊዎቹ የሆኑት ተጋሩ በጣረሞት ላይ ያለ ቡድን አድርገው እንዳያዩት ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ የማይደግፉትን ተጋሩም መቅጣትና መኮርኮም እንደሚችል አውቀው በፍርሃት ውስጥ እንዲኖሩ ማድረጉ ተሳክቶለታል። በትግራይ ከተሞች ውስጥ በሚበተኑና በየቦታው በሚለጠፉ ወረቀቶች እንዲሁም ከአሜሪካ ምድር በሚሰራጨው ትግራይ ሚዲያ ሃውስ (TMH) አማካይነት ስሞች በመጥቀስ (በመጥራት) ግለሰቦችን ማስጠንቅ፣ የግድያ ዛቻዎችን በመሰንዘር፣ እርምጃ የተወሰደባቸውን (ገደልኳቸው የሚላቸውን) እና ታፍነው ወደ በረሀ ተወሰዱ የሚላቸውን ለዚህ ካበቃቸው ድርጊታቸው ጋር ይፋ በማድረግ፣ ህወሓትን የማይደግፉ የትግራይ ተወላጆች በሽብር ውስጥ እንዲኖሩ እያደረገ ነው። ፓርቲው የግድያ እርምጃ እንደወሰደባቸው ወይም አፍኖ ወደ በረሀ እንደወሰዳቸው ይፋ ካደረጋቸው መካከል ህወሓትን ጁንታ ብለው የጠሩ፣ ጁንታው እብቅቶለታን ተመልሶ ስልጣን አይዝም ብለው የተናገሩ፣ የህወሓት ታጣቂ የሆነ ቤተሰብ አለህ/አለሽ ብለው ዕርዳታ የከለከሉ፣ ለዕርዳታ የቀረበ እህልን ሰርቀው የሸጡ ወዘተ. እንደሚገኙበት በትግራይ ሚዲያ ሃውስ በኩል ስለሚነገር ትግራይን በመቆጣጠር ላይ እንደሆነ የሚያሳይ ስሜት እየተፈጠረ ነው ማለት ይቻላል።

የህወሓት ማስጠንቀቂያዎች ባንዳዎች ለሚላቸው፣ “ብልጽግና ወይም ዐብይ አሕመድ አያድናችሁም” የሚል ዛቻን ያካተተ ስለሆነ ብልጽግና ስልጣን የሠጣቸው ግለሰቦችም ጭምር የብልጽግና ደጋፊ አለመሆናቸውንና ስልጣን የያዙት የትግራይን ሕዝብ ለመርዳት ብለው መሆኑን አጋጣሚውን ባገኙ ቁጥር ከመናገር አልቦዘኑም። እነዚህ ሹማምንት ሕዝብ የመረጠው ህወሓት ወደ ስልጣን ይመለስ ከሚለው ሃሳብ በስተቀር ፓርቲው ከግንቦት 1983 ዓም ጀምሮ ለክልላዊ ጥቅሙ ሲል ያደረገው ነገር ሁሉ ወደ ነበረበት ቦታ እንዲመለስ ደጋግመው ሲጠይቁ ይሰማሉ። ከነዚህ ሹማምን አንዳንዶቹ ወልቃይት ብቻ ሳይሆኑ ጎንደር የትግራይ ነው፤ ራያ ብቻ ሳይሆን ቆቦ-ወልድያም የትግራይ ነው፤ ብለው ሙግት እስከ መግጠም መድረሳቸው ብዙዎችን ያስገረመ ጉዳይ ነው። እነዚህ ሁኔታዎች ትግራይ ውስጥ እና በተጋሩ ላይ ፓርቲው በውድም በግድም ከባድ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን፣ በማሳመንም በማስፈራራትም ብዙዎችን ማንበርከክ መቀጠሉን ያሳያሉ። ትግራይ ሚዲያ ሃውስ በተደጋጋሚ ስማቸውን እያነሳ በሕዝብ ላይ፣ በአብያተ-ክርስቲያናትና በገዳማት ላይ የሚደርሱ በደሎችን በዝምታ እየተመለከቱ ነው ብሎ ሲተቻቸው ከነበሩት የትግራይ ተወላጆች መካከል ፓትርያርኩ ይገኙበታል። ፓትርያርኩ በቅርቡ የለቀቁት የቪዲዮ መልዕክት ‹‹ታፍኜ ነው እንጅ ዝም አላልኩም›› የሚል መሆኑና ያወገዟቸው ነገሮች በሙሉ በዚያ ሚዲያ ላይ በቀረቡበት መንገድ የተቃኙ መሆናቸው የህወሓት ተጽዕኖ የት ድረስ እየደረሰ መሆኑን በሚገባ ያሳያል። ዞሮ ዞሮ ግን የእምነት መሪወች ለሕባቸው አዛኝና ተቆርቋሪ መሆናቸው፣ ለተጠቂዎችና ለምስኪኖች ድምጽ መሆናቸው ሊለመድ፣ ሊቀጥልና ሊበረታታ የሚገባው ነው።

ለፓትርያርኩ ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ፣ እሳቸው በመንበሩ ላይ በነበሩባቸው ዓመታት በህወሓት ስርዓት በመላ አትዮጵያ ግፍ ሲፈጸም ለምን ድምጸቸውን አላሰሙም? የሚል ቢሆንም ስርዓቱ አልፏልና፣ ኢሕአዴጎች አሸባሪወች ነበርንም ብለዋልና እንተወው። ነገር ግን ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በኦሮምያና በደቡብ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ በርካታ ከተሞች እንዲሁም በድሬዳዋና በሐረር ከተሞች ጥምቀትና መስቀልን ማክበር እጅግ አደገኛ ሲሆን፣ መጥረቢያና ቆንጨራ የያዙ ግለሰቦች ታቦቶች ወደ መቅደሳቸው እንዳይመለሱ ሲገለገሉ፣ በዚህ ቦታ ቤተ-ክርስቲያን ሊኖር አይገባውም እያሉ ለማፍረስ ሲውተረተሩ፣ ለምን ይህን ያህል አልተሰማቸውም ብሎ መጠየቅ ግን ተገቢ ነው።

የብልጽግና ቡድን ትግራይ ውስጥ ግፎች ሲፈጸሙ እንደ ዋዛ አይቶ ማለፉም ሆነ ተፈጸሙ የሚባሉ ግፎችን አጣርቶ እውነት ሆነው ሲገኙ ግፈኞችን ለፍርድ ማቅረብ ሲገባው፣ ያላየና ያልሰማ መስሎ ጀሮ ዳባ ልበስ ማለቱ የኋላ ኋላ ዋጋ ሊያስከፍለው እንደሚችል ሊዘነጋው አይገባም። ትግራይ ውስጥ ‹‹ማሕበረ-ዴጎ›› በሚባለው ቦታ የተፈጸመውን ግፍ ማጣራቱ ቀላል ቢሆንም ብልጽግናዎች ዝምታን መርጠዋል። ይህ ቪዲዮ በመላው ዓለም ሊባል በሚቻል ደረጃ መሰራጨቱ ግልጽ ነው። ቢቢሲን የመሳሰሉ ሚዲያወች የሳተላይት ካርታዎችን በማመሳከር ቦታው ትግራይ ውስጥ መሆኑን፣ ቦታውም እንደተባለው ማሕበረ-ዴጎ የተባለው ስፍራ መሆኑን የሚናገር ሐተታ በመስራት፣ ምስሉ በሌላ አገር የተፈጸምን ድርጊት ትግራይ ውስጥ የተፈጸመ ለማስመሰል በቪዲዮ ኢዲቲንግ የተሰራ አለመሆኑን አሳውቀዋል። ግፉን ሲፈጽሙ ነበሩ የተባሉ ሰዎች ራሳቸው አስከፊዎቹን ድርጊቶችቻውን እየቀረጹ፣ ፊልም የሚሰሩ ይመስል በምስሉ የነሱ ገጽታም እንዲካተት እያደረጉ፣ ነውረኛና ሰይጣናዊ አነጋገሮቻቸውም ከምስሉ ጋር ሆነ ብለው እንዲቀረጽ እያደረጉ በግልጽ ይታያል፤ ይሰማል። ይህን የቀረጹትን ምስል ደግሞ ሆነ ብለው አሰራጭተውታል።

የነዚህ ሰወች ዓላማ ግፍን መፈጸም ነው ወይስ ግፉን በመጠቀም ፕሮፓጋንዳ መስራት? እነዚህ ሰዎች በግል ተነሳሽነት ግፍ የፈጸሙ ናቸው ወይስ ይህን ግፍ ፈጽሙ ብሎ የላካቸው አካል ነበረ? ከዚህ በፊት በዘመነ ህወሓት/ኢሕአዴግ በኦጋዴን ምድር ተመሳሳይ ቪዲዮ ከተመሳሳይ ሰይጣናዊ አነጋገር ጋር ተቀርጾ ኢሳትን ጨምሮ በተለያዩ ሚዲያወች ላይ ቀርቦ ነበረ። እነዚህን መሰል ቪዲዮዎች ግፍን ከመፈጸም በተጨማሪ ልዩ ዓላማ ያላቸው ናቸውና በአስቸኳይ ማጣራቱ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ከዚህ በተጨማሪ የመደፈር፣ የመዘረፍና የመሳሰሉት ግፎች ተፈጽመውብናል የሚሉ የትግራይ ተወላጆችን እያነጋገረ የጉዳዩን ሀቀኝነት እንዲሁም አጥፊዎችን የሚያጣራና ፍትሕ የሚያሰፍን ገለልኛ አካል መቋቋሙ ይዋል ይደር ሊባል የማይገባው መሆኑ ሊዘነጋ አይገባውም። በሰዎች ስቃይ የሚደሰቱትም ሆነ ሰቆቃ እያስፈጸሙ የፖለቲካ ቁማር የሚጫወቱ ሁሉ የስራቸውን ሊያገኙ ይገባል።

እነ አቶ ጌታው ረዳ ራሳቸው ወደ በረሀ እየሸሹ የትግራይ ወጣቶች በዱላ፣ በድንጋይ፣ በመጥረቢያ፣ በቢላዋና በሌላም ማጥቂያ መሳሪያ እንዲፋለሙ ጥሪ አድርገዋል ወይም ትዕዛዝ ሰጥተዋል። ይህን መሰሉ ራስን ለማዳን እየሸሹ ሌሎችን ጭዳ ከማድረግ ያለፈ ውጤት ለሌለው ቅስቀሳ ህወሓት ተጠያቂ አይሆንምን? በአክሱም ከተማ ወጣቶች የተፈጸመው የኤርትራን ጦር የማጥቃት ዘመቻ የዚህ የእነ አቶ ጌታው ረዳ ትዕዛዝ ፍጻሜ ይመስላል። ወጣቶቹ በግልጽ እነደተናገሩት አንዳንዶቹ በየቤታቸው ያገኙትን ዱላና ሌላም ነገር ይዘው ወደ ሻዕቢያዎች ካምፕ ሲሄዱ፣ ሌሎቹ የመሳሪያ መጋዘን ሰብረው መሳሪያ ይዘው፣ መተኮሰ እንኳ ሳይለማመዱ፣ የኤርትራ ጦር ወደሰፈረበት ቦታ መሮጣቸውን ተናግረዋል። ይህን የጥቃት ሙከራ ተከትሎ አክሱም ውስጥ በኤርትራ ወታደሮች ግድያዎች መካሄዳቸው ይፋ ሆኗል።

ግዛቸው አበበ በኢሜይል አድራሻቸው
gizachewabe@gmail.com ላይ ይገኛሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com