የምርጫ ቅስቀሳ ተደራሽነት

Views: 196

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ አብዛኛዎቹን የቅድመ ምርጫ ሂደቶችን በማጠናቀቅ ላይ ትገኛለች። በአገራዊ ምርጫው በቅድመ ምርጫ ሂደት ውስጥ ከሚካተቱት መካከል በምርጫው ለመሳተፍ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ ያገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት የምርጫ ቅስቀሳ አንዱ ነው።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ መራጩ ሕዝብ ስለ ምርጫ ግንዛቤ እንዲኖረውና በምርጫው ተሳታፊ ከሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የትኛው የተሻለ እና የሕዝቡን ችግር የሚፈታ ሀሳብ አንግቧል የሚለውን ለመለየት የሚያስችል ስልት ነው። ታዲያ በዚህ ሂደት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች እያደረጉት ያለውን የምርጫ ቅስቀሳ ተደራሽነት እና የምርጫ ቅስቀሳው አመርቂነት ሲመዘን፣ ድሃና ሀብታም የታየበትና በቂ የሚባል የምርጫ ቅስቀሳ እየተደረገ እንዳልሆነ የሚያነሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር አልጠፉም።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የምርጫ ቅስቀሳ የካቲት 8/2013 በይፋ መጀመሩ የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው በዚሁ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ የሚችሉት ከየካቲት 8/2013 አስከ ግንቦት 23/2013 መሆኑ የሚታወቅ ነው። በዚህ ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ የተፈቀደላቸው የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ 16 ቀናት ብቻ ይቀሩታል።

ይሁን እንጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ እስካሁንም ድረስ የምርጫ ዋዜማ ድባብ እንዳልፈጠረ እና የተቀዛቀዘ እንደሆነ በሕዝቡ ዘንድም የሚሰማ ቅሬታ መሆኑ አልቀረም። በምርጫ ቅስቀሳ ሂደቱ እስካሁን ከታየው አንጻር በጣት የሚቆጠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጎልተው የሚታዩበትና አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች በምርጫው የማይሳተፉ እስከሚመስል ድረስ የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜያቸውን በአግባቡ እየተጠቀሙ እንዳልሆነ በአደባባይ የሚታይ እውነታ ነው።

በምርጫ ቅስቀሳው ጎልተው ከሚታዩት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በመዲናችን አዲስ አበባም ይሁን በክልል ከተሞች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ላይ የገዥው ፓርቲ ብልጽግና፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን)፣ እናት ፓርቲ፣ ባልደርስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ(ባልደራስ) እና ሌሎችም በተወሰነ የቅስቀሳ ግለት ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ።

የምርጫ 2013 ቅስቀሳ፣ ኢትዮጵያ የምርጫ ዋዜማ ላይ መሆኗን አጉልቶ የሚያሳይ አለመሆኑን ከሚገልጹትና የምርጫ ቅስቀሳው የሚገባውን ያክል ተደራሽ አልሆነም ከሚሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ(ኢሕአፓ) አንዱ ነው። የኢሕአፓ ሊቀመንበር ቆንጂት ብርሃን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ የምርጫ ቅስቀሳው ድሃና ሀብታም በግልጽ የታየበት ነው ይላሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት ገዥው ፓርቲ ብልጽግና ሀብቱን ተጠቅሞ የምርጫ ቅስቀሳው ወደፓርቲው ሚዛን እንዲደፋ ማድረጉን በማንሳት ነው።

ቆንጂት እንደሚሉት የምርጫ ቅስቀሳ እየተካሄደ ነው ለማለት የሚያስደፍር ነገር አለመኖሩን፣ ቅሰቀሳው ሚዛናዊነት የጎደለውና አንዳንድ ፓርቲዎች የሚወዳደሩ እስከማይመስል ድረስ ቅስቀሳ አለማድረጋቸውን በማንሳት፣ የምርጫ ቅስቀሳውን ተደራሽነት ይኮንኑታል።
የምርጫ ቅስቀሳ ግቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመራጩ ሕዝብ ይዘው የቀረቡትን አማራጭ ሀሳብ የሚሸጡበት፣ ምርጫ መድረሱንና የምርጫን አስፈላጊነት ሕዝቡን እንዲገነዘብና ለመምረጥ እንዲዘጋጅ የሚጠይቁበት የገበያ መድረክ ቢሆንም፣ አሁን ላይ የሚታየው የምርጫ ቅስቀሳ እነዚህን ግቦች መምታት የሚያስችል እንዳልሆነም ነው ቆንጂት የሚጠቅሱት።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ምክትል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ መሳይ ግርማ በበኩላቸው፣ የምርጫ ቅስቀሳው ዓላማ ሕዝቡ ስለ ምርጫ ግንዛቤ እንዲኖረውና ከቀረበለት ሀሳብ የተሻለውን የሚመርጥበትን እድል ማመቻችት ነው ይላሉ። በዚሁ መሰረት ኢዜማ የምርጫ ቅስቀሳ ከተጀመረበት የካቲት 8/2013 ጀምሮ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች እስከ ወረዳ ድረስ ቅስቀሳ እያደረገ መሆኑን የሚገልጹት መሳይ፣ የፓርቲያቸው የምርጫ ቅስቀሳ ተደራሽነት ጥሩ የሚባል ቢሆንም በአንዳንድ አከባቢዎች ፈታና እንደገጠማቸው ይገልጻሉ።

ኢዜማ ባለ አራት ምዕራፍ የምርጫ ቅስቀሳ ስልት መጠቀሙን የገለጹት መሳይ፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ ምርጫ እንዳለ ለሕዝብ ማስገንዘብ፣ ኹለተኛው ምዕራፍ የመራጮች ምዝገባን ማበረታታት፣ ሶስተኛው ምዕራፍ እጩዎችን ማስተዋወቅ ሲሆን፣ አራተኛው ምዕራፍ ሕዝብ ኢዜማን እንዲመርጥ ማስተዋወቅ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በዚህ የምርጫ ስልት የምርጫ ቅስቀሳ ዓላማን ለማሳካት ኢዜማ በቁርጠኝነት እንደሰራ ጠቁመዋል። በዚህም የምርጫ ቅስቀሳ ግብን በስልትና በምዕራፍ በመከፋፈል ኢዜማ ከሌሎቹ ፓርቲዎች የተሻለና ስኬታማ የሆነ የምርጫ ቅስቀሳ ስልት መጠቀሙን መሳይ ገልጸዋል።

የኢሕአፓዋ ቆንጂት በበኩላቸው፣ ፓርቲያቸው የተከተለው የምርጫ ቅስቀሳ ስልት በአደባባይ መስመሮች ላይ ባነሮችን በመስቀልና የተወሰነ የመስመር ላይ ቅስቀሳ መሆኑን ይገልጻሉ። ይሁን አንጅ ፓርቲያቸው ምርጫ ቅስቀሳ እያደረገ ነው ለማለት የሚያስደፍር የምርጫ ቅስቀሳ እንቅስቃሴ አለማድረጉን ይገልጻሉ። ኢሕአፓ የተከተለው የምርጫ ቅስቀሳ ስልት በአዲስ አበባና በክልሎች እስከ ወረዳ ድረስ ቢሆንም፣ የተደራሽነት መጠኑ የተለያየ እንደሆነ ገልጸዋል። በዚህም የፓርቲው የምርጫ ቅስቀሳ ተደራሽነት ውስን እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል።

የኢዜማው መሳይ በበኩላቸው፣ የፓርቲያቸው የምርጫ ቅስቀሳ ተደራሽነት በአዲስ አበባ፣ በአማራ ክልል እና በደቡብ ክልል የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል። በአንጻሩ በኦሮሚያ ክልልና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የምርጫ ቅስቀሳውን ተደራሽ ለማድረግ አለመቻሉን ነው የገለጹት።

ኢዜማ ምርጫ በሚካሄድባቸው በሁሉም ክልሎች ዕጩ ማቅረቡን የጠቆሙት መሳይ፣ እጩዎች በተለይ ኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አፈና እየተደረገባቸው በመሆኑ ቅስቀሳውን ለማካሄድ ተቸግረዋል ብለዋል። በዚህም የምርጫ ቅስቀሳ ተደራሽነት ላይ ትልቅ እንቅፋት ሆኗል ብለዋል። በተጨማሪም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ኢዜማ ንቁ ተሳትፎ የሚደርግበት ክልል ቢሆንም፣ የክልሉ መንግሥት የኢዜማን ቅስቀሳ እያስተጓጎለና ተደራሽነቱን እያቀጨጨው ነው ተብሏል።

በሌላ በኩል፣ የምርጫ ቅስቀሳ አንዱ ስልት የሆነው የፓርቲዎች ባነርን በአደባባይ መስቀል ቢሆንም፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ባነር መቀደድና ከተሰቀሉበት መውረድ ሌላኛው ችግር መሆኑን በርካታ ፓርቲዎች ሲያነሱት የነበረ ጉዳይ ነው።
የምርጫ ቅስቀሳው ተደራሽነት ለምን ውሱንነት ታየበት?

የምርጫ ቅስቀሳው ተደራሽነት ከቦታ ቦታ የተለያየ ቢሆንም የምርጫ ቅስቀሳ ሂደቱን በሚመለከት ለአዲስ ማለዳ ያካፈሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ተደራሽነት ላይ ከፍተት እንዳለ አምነዋል። በምርጫ ቅስቀሳ ተደራሽነት በአዲስ አበባ ብልጽግና፣ አዜማና ባልደራስ የተሻለ እንቅስቃሴ ሲደርጉ ይታያሉ። በአንጻሩ በተወሰነ መጠን አዲስ አበባ ላይ የምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርጉ ሌሎች ፓርቲዎች ቢኖሩም እምብዛም አይደሉም።

ታዲያ የምርጫው ቅስቀሳ መቀዛቀዝና ተደራሽነቱ ለምን ውሱን ሆነ ከተባለ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል የሚነሱ በርካታ ምክንያቶ አሉ። የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ ተደራሽነትና መቀዛቀዝ ምክንያት ሆነዋል ብለው ከሚያነሷቸው ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል፣ እዚህም እዚያም የሚታዩ የጸጥታ ችግሮች፣ በመንግሥት በኩል የሚደረግ አፈና እና የአቅም ውሱንነት ቀዳሚዎቹ ናቸው።

ኢዜማ የምርጫ ቅስቀሳውን በሚገባ ተደራሽ ማድረግ ባልቻለባቸው አካባቢዎች፣ የምርጫ ቅስቀሳው ተደራሽነትን ካስተጓጎሉ ምክንያች መካከል በተለይ በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሆነ የመንግሥት ጫና ሲሆን፣ እጩዎቻችን ቅስቀሳ እንዳያደርጉ ክልከላ ይደረግባቸዋል ብሏል። እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ባለው የጸጥታ ችግር የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ አልቻልኩም ይላል።

ከጽጥታ ጋር በተያያዘ የምርጫ ሂደቶች መስተጓጎል እየገጠማቸው መሆኑን ምርጫ ቦርድ መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ መንግሥት በጸጥታ ምክንያት አካባቢያቸውን ለቀው የተፈናቀሉ ዜጎችን ከምርጫ በፊት ወደ አካባቢያቸው እመልሳለሁ ቢልም መመለስ አለመቻሉ፣ ተፈናቃዮች ስለ ምርጫው ግንዛቤ እንዲኖራቸውና የፓርቲዎችን ሀሳብ ሰምተው የተሻላቸውን የሚመርጡበት እድል እስካሁን አለመኖሩ የምርጫ ቅስቀሳ ተደራሽነቱንና የምርጫ ሂደት አሳታፊነቱን ጥያቄ ውስጥ የሚከት መሆኑን መሳይ ይገልጻሉ።

የኢሕአፓዋ ቆንጂት በበኩላቸው፣ የምርጫ ቅስቀሳው ተደራሽነቱ እንዲቀዛቀዝ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ የአቅም ውሱንነት መሆኑን አንስተዋል። ፓርቲዎች በገጠማቸው የፋይናንስ አቅም ውሱንነት ከገዥው ፓርቲ እኩል የምርጫ ቅስቀሳ ማካሄድ አለመቻላቸውን ነው የሚገልጹት። በዚህም የምርጫ ቅስቀሳ ሂደቱ ሚዛናዊነት የጎደለውና በሕዝበ ዘንድ ሌሎች ፓርቲዎች የት አሉ? የሚል ጥያቄን ያጫረ ነው ብለውታል።

ሊጠናቀቅ 16 ቀናት የቀሩት የምርጫ ቅስቀሳ በቀሪዎቹ ጊዜያት የሚጠበቅበትን ግብ እንዲመታ በአስቸኳይ የታዩትን ችግሮች በመቅረፍ የቅስቀሳውን ተደራሽነት ማረጋግጥ እንደሚገባ ፓርቲዎቹ ጠቁመዋል።
የኢዜማው መሳይ፣ የምርጫ ቅስቀሳ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የምርጫ ሂደቱን ነፃ ማድረግና በመንግሥት በኩል የሚታዩትን አፈናዎች ማስቀረት ይገባል ብለዋል። የምርጫ ቅስቀሳ ሲጠናከር የምርጫው ድባብ እንደሚደራ የገለጹት መሳይ፣ ፓርቲዎችም ሆኑ መንግሥት በምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ስነ ምግባር መመራት ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

የኢሕአፓዋ ቆንጂት በበኩላቸው የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜው እየተገባደደ መሆኑን በመገንዘብ ፓርቲዎች፣ ባላቸው የገንዘብ መጠንና ጊዜ ድምጻቸውን በአግባቡ ለሕዝብ ማድረስ አለባቸው ብለዋል። ፓርቲዎች በተመደበላቸው የክርክርና ነጻ የቅስቀሳ ስዓት ሚዲያዎች ጋር ቀርበው ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በአብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል በሚዲያ የተመደበላቸውን ነጻ የአየር ሰዓት የመጠቀም ውሱንነት መኖሩን የጠቆሙት ቆንጅት፣ ያለውን ቀሪ ጊዜ በአግባቡ በመጠቀም የምርጫውን አሳታፊነትና ፍትሐዊነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com