የእለት ዜና

በ600 ሚሊዮን ዶላር የሲሚንቶ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

ለሚ ግሪን ቢውልዲንግ ማቴሪያልስ የተሰኘ በኢትዮጵያ እና እንግሊዛዊ ባለሀብቶች ሽርክና የሚመራ የሲሚንቶ ፋብሪካ በሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ አካባቢ እንደሚገነባ ተገለጸ። የሲሚንቶ ፋብሪካው ቦታ ተጠንቶ ፈቃድ ወሰዶ ግንባታ የመጀመር ሂደት ላይ ነው። ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ የሚደረግበት ፕሮጀክት መሆኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከፍተኛ የኮሚኒኬሽን አማካሪ የሆኑት ሄኖክ ሰለሞን ገልጸዋል።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባወጣው የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ላይ 2 ነጥብ 05 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የወጪ ኢንቨስትመንት በዘጠኝ ወራት ውስጥ መሳብ እንደተቻለ ተገልጿል። ለሚ ግሪን ቢውልዲንግ ማቴሪያልስ የሲሚንቶ ፋብሪካ ፕሮጀክት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከተገኙ የውጭ ኢንቨስትመንቶች አንዱ መሆኑም በሪፖርቱ ታውቋል።

በአገራችን 60 በመቶ በላይ የሚሆነው የሥራ ዕድል የሚፈጠረው በኮንስትራክሽ ዘርፍ በመሆኑ የሲሚንቶ ምርት ለሥራ ዕድልና ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ነው ተብሏል። ዛሬ በአለማችን እንደ ቻይና ባሉ አገራት አንድ ሰው በዓመት ከ1000 ኪሎ ግራም በላይ ሲሚንቶ በነፍስ ወከፍ እንደሚጠቀም መረጃዎች ያሳያሉ።

የዓለም አማካኝ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ፍጆታ 521 ኪሎ ግራም ሲሆን፣ የእኛ አገር 70 ኪሎ ግራም አለመድረሱን፣ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መላኩ አለበል የናሽናል ሲሚንቶ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ የግንባታ የመሰረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት ተናግረዋል።
በአገራችን የተገነቡ አጠቃላይ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በዓመት እስከ 14 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ ያመርታሉ ተብሎ ቢጠብቅም፣ 9 ሚሊዮን ቶን መድረስ አልቻሉም። አገራችን ለሲሚንቶ ምርት ካላት ምቹነት አኳያ ኤክስፖርት ልናደርገው የምንችለውን ያህል የሀገር ውስጥ ገበያውን ማርካት አልቻልንም። ስለሆነም የህዝባችንን አኗኗር ለማሻሻልና በዓለም ደረጃ ያለንበትን ሁኔታ ለመቀየር ገና ብዙ ተጨማሪ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች ያስፈልጉናል ሲሉ አማካሪው ተናግረዋል።

በኢንቨስትመንት ኮሚሽን የዘጠኝ ወር ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው፣ የኢንቨስትመንት ፍላጎት አሳይተው ከተለዩ የውጭ ባለሀብቶች ውስጥ ለ132 ባለሀብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተስጥቷል። የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ወደ ኢንደስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ ከመደገፍ አንፃር 12 ፕሮጀክቶች ወደ ኢንደስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ ተደርጓል። በዚህም 58 ሺሕ 631 ዜጎች፣ ማለትም 43 ሺሕ 206 ሴቶች እና 15 ሺሕ 425 ወንዶች የሥራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸው ተገልጿል።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት በዘጠኝ ወራት ውስጥ 70 በመቶ ክንውን ማድረስ እንደተቻለ እና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የዘርፍ ድልድል አምስት በመቶ በግብርና 58 በመቶ በማኑፋክቸሪንግ 37 በመቶ በአገልግሎት ዘርፍ ኢንቨስት ማድረግ እንደጀመሩም በሪፖርቱ ተካቷል።

በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በጃማ ቤልት የሲሚንቶ እጥረትን ለመፍታት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የሲሚንቶ ኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸው የሚታወስ ነው ።
በቅርቡም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንሳሮ ወረዳ በ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ለሚገነባው የሲሚንቶ ፋብሪካ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸው ይታወሳል። ፋብሪካው በኢትዮጵያው ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ እና በቻይና ዌስት ኢንተርናሽናል ድርጅት በሽርክና እንደሚገነባ ተገልጿል።

የ18 ወራት ጊዜ በተያዘለት የመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ ሶስት ፋብሪካዎች ወደስራ የሚገቡ ሲሆን፣ በቀን 10 ሺሕ ቶን ሲሚንቶ፤ በዓመት 30 ሚሊዮን ካሬ ሜትር ጂፕሰም ቦርድ እና በቀን 600 ቶን መስታወት የሚያመርቱ መሆናቸውን የመሰረት ድንጋዩ በተቀመጠበት እለት መገለጹ ይታወሳል።


ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!