የአሜሪካን ውግዘት

Views: 225

አሜሪካ ኢትዮጵያን የተመለከተ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን ከሠሞኑ በባለስልጣናቶቿ በኩል አውጥታለች። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ህወሓት ላይ ወታደራዊ እርምጃ መወሰዱን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስትንና የአማራ ክልል ታጣቂዎችን፣ እንዲሁም የኤርትራ መንግስትን ለመኮነን ጊዜ አልፈጀባትም። ከምርጫው ጋር በተገናኘም አውሮፓ ህብረት ታዛቢዎችን እልካለሁ አልክም እያለ እሰጥ አገባ ውስጥ ሠንብቷል። ምዕራባውያኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን የነበሩበት ጊዜ ከግድቡ ጋር በተገናኘ ተቀዛቅዞ ህወሓት መሸነፍ ስትጀምር በተቃራኒ መሰለፋቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያን ሉአላዊነት አሜሪካ መዳፈር ከጀመረች ብትቆይም አሁን በግልጽ ማዘዝና ማስጠንቀቅ መጀመሯ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል። በያዝነው ሳምንት መነጋገሪያ ከሆኑ አጀንዳዎች ቀዳሚ የነበረው ይኸው “የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት” የተባለው ርዕስ ነው። ስለእኛ ህግና መመሪያ ታወጣለች እያሉ ስራዋን የሚተቿት ብዙ ቢሆኑም፣ ማንንም ከመጤፍ ሳትቆጥር ጉልበተኝነቷን ማሳየት ቀጥላለች። ከትግራይ የኤርትራ ጦር ጨርሶ እንዲወጣ፣ ከወልቃይትና ራያ እያስተዳደሩት ያሉት የአማራ ክልል ታጣቂዎችና አስተዳደሮች እንዲወጡ የሚያዝ አይነት ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ በማውጣቷ ከመንግስት ደጋፊዎችም ሆነ ተቃዋሚዎችና ግለሰቦች ተቃውሞ ገጥሟታል። ከህወሓት ደጋፊዎች ሌላ በግልፅ የደገፏት ባይኖሩም ለመኮነን ያልደፈሩም ብዙ ናቸው።

አሜሪካንን ለማውገዝ ኮሚቴ ተቋቁሞ ተግባሯን የሚያወግዝና እጇን እንድትሰበስብ የሚጠይቅ ትዕይንተ ህዝብ ተካሂዷል። ይህ የውግዘት መርሀግብር ሲታቀድ አንዳንዶች የሰነዘሩት አስተያየት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። የኢሳት ስራ አስኪያጅ አንዳርጋቸው ፅጌ “የአሜሪካንን ባንዲራ እስከማቃጠል የሚደርስ የተቃውሞ እርምጃ እንወሰወዳለን” ማለታቸው ለቀናት መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል። እንደሳቸው ሌሎችም የአሜሪካንን ተግባር በመተቸት በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ መግባት የለባትም እያሉ ተግባሯን ሲነቅፉና ሌላውን ሲቀሰቅሱ ነበር። በአንፃሩ አንዳንዶች ደግሞ፣ አሁን ምን የተለየ ነገር መጥቶ ነው ይህን ያህል ተቃውሞ እናሰማ የሚባለው ብለው አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። አሜሪካ ከእኛ በተቃራኒ የቆመችበትን ምክንያት አጥንቶ ወደ እኛ ወገን እንድትመጣ ማድረግ እንጂ መኮነኑና ባንዲራዋን ማቃጠሉ ለማንም አይበጅም ይላሉ። ባንዲራን ማቃጠል ወንጀል ከመሆኑ ባሻገር በእኛም የተከለከለውንና እኛ ላይ እንዲደረግ የማንፈልገውን እነሱ ላይ ማደረጉ ተገቢ አይደለም ያሉም ተሰምተዋል። “አሜሪካ ልኳን ትወቅ” እያሉ፣ ሌላው ሀገር ላይ እንደለመደችው በእኛ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ መግባት እንደሌለባት ለማሳወቅ በሚገባትና ጠንከር ባለ መንገድ ማሳወቅ አለብን ብለው ሀሳባቸውን የገለፁም አሉ። ተቃውሞን ማሰማት አስፈላጊ ቢሆንም በፅንፈኞች የተለመደውን አይነት ባንዲራን ከማቃጠል አይነት ተግባራት ተቆጥበን ተቃወሟችንን በጨዋ ደንብ ማሰማት ነው ያለብን እያሉ የተሟገቱም ነበሩ። የአሜሪካ አብዛኛው ሕዝብ ከጎናችን ሆኖ መንግስታቸው የሚያደርገውን ተገቢ ያልሆነ ተግባር አውቀው ሀሳቡን እንዲያስቀይሩት መጣር እንጂ፣ ሁሉም እንዲታዘበንና እንዲርቀን ከሚያደርግ አካሄድ መራቅ አለብን ብለው ሀሳባቸውን የሰነዘሩም ታይተዋል። ምርቷን ከመጠቀም መቆጠብ፤ መገበያያ ዶላሯን ግድ ካልሆነ አለመጠቀምና የሌላን እንደአማራጭ እንጠቀም እያሉ ተመሳሳይ ቅስቀሳዎችን በማድረግ፣ እንዲሁም ሌሎች ያኮረፉባትን አፍሪካውያንንና እስያውያንን ከጎን ለማሰለፍ እንስራ በማለት ፍላጎታችንን በሰላማዊ መንገድ ማሳካት እንችላለን የሚሉም ሀሳባቸውን በማህበራዊ ሚዲያ አቅርበዋል።

ውግዘቱን በተመለከተ ታምሩ ሁሊሶ ስለተቃውሞው አስተያየቱን ሲሰጥ፣ “የትግራይ ጥላቻ እንጂ በሀገር ፍቅር መቃጠል አይመስልም” ብሏል። ግርማ ካሳ በበኩላቸው፣ “የእኛ ጠላት የዘር ፖለቲካው እንጂ አሜሪካ አይደለችም” የሚል ይዘት ያለው ሰፋ ያለ ጽሁፍ አቅርበዋል። በአንፃሩ ይታገሱ አምባዬ የተባሉ ጣልቃ የሚገቡ የውጭ ሀገራትን የሚያወግዝ ንቅናቄ በመላው ሀገሪቱና በአለም አቀፍ ደረጃ የካሄድ በሚል ሲቀሰቅሱ ነበር። “ብሄራዊ ክብር በሕብር” በሚል መሪ ቃል ተቃውሞው የተሰማ ቢሆንም፣ አሜሪካንን ወዲውኑ ሊያስቆምና ይቅርታ ሊያስጠይቅ አልቻለም። ከግድቡ ጋር በተገናኘ ለእስራኤል ስትል ከግብፅ ጋር መቆራኘቷን የተመለከቱ እንደሚሉት፣ የግብፅ ህዝብ ለፍልስጤማውያን ያለውን ቀናዒ አመለካከት በመጠቀም የሀገሪቱን መንግስት በመጠምዘዝ ኃያላኑ አማራጭ ሲያጡ እኛን ወደመለማመጡ ይመጣሉ ይላሉ። ያም ሆነ ይህ፣ እኛ በምንወደውና ቦታ በምንሰጠው መንገድ ሳይሆን አሜሪካ በምትወደው በገንዘቧና በጥቅሟ ካልመጣንባት ከክፉ ተግባሯ የማትመለስ መሆኗን ብዙዎች ያምናሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com