ኮቪድ 19ን የተጋፈጡ የኢትዮጵያ ፈርጦች

Views: 84

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጀምሮ የበርካታ አንጋፋዎች ሕይወት በዚሁ ቫይረስ ምክንያት አልፏል። በኮቪድ ሳቢያ ብዙዎች በየቤታቸው እናት፣ አባት ወይ እህት ወንድም፤ አጎት አልያም አክስት እንዲሁም ወዳጅ ዘመድ ያሉትን ጎረቤትንም ሲነጥቅ እንደ ግል በየቤቱ ሀዘን የተቀመጠው ብዙ ነው።

ይኸው ቫይረስ ወዲህ ደግሞ እንደ አገር የሕዝብ የሆኑ፣ ብዙዎችን የሚያገለግሉ በኢትዮጵያ በሥነ ጥበብ፣ በሕክምና በምርምር፣ በማስተማር በበጎ አድራጎት እና በሌሎች የተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተመሰገኑና ወደፊትም ብዙ የሚጠበቅባቸውን ለሞት ሰጥቷል። ኢትዮጵያም በዚህ ወረርሽኝ ሳቢያ በርካታ አንቱ የተባሉ ሰዎችን አጥታለች።

ከቅርብ ብንጀምር እንኳን ባሳለፍነው ሳምንት እለተ ሰኞ ግንቦት 2 ቀን የኒያ ፈውንዴሽን እና የጆይ የኦቲዝም ማዕከል መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ ዘሚ የኑስን እናስታውሳለን። ዘሚ የኑስ ለራሴ ብቻ ሳይሉ ስለብዙ ኦቲስቲክ ልጆችና እና ኦቲዝም ያለባቸውን ልጆች ለሚያሳድጉ ቤተሰቦች እረፍት ለመስጠትና ለማበረታታት ይተጉ የነበሩ እናት ናቸው። ኢትዮጵያም በቫይረሱ ምክንያት የአገር ባለውለታ የሆኑትን ዘሚ የኑስን አጥታለች።

መስፍን ጌታቸው ሌላው በኮቪድ ምክንያት በሞት የተለየን የጥበብ ፈርጥ ነበር። ደራሲ፣ ዳይሬክተር፣ ተዋናይ ሆኖ በሙያው ያገለግል የነበረው መስፍን ‹የቀን ቅኝት› እና ‹መንታ መንገድ› በተሰኙ ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ ድርሰቶቹ ይታወቃል። እንዲሁም ‹ሰው ለሰው› እና ‹ዘመን› የተሰኙ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ በድርሰት እና በትወና የበለጠ የታወቀና የተደነቀ የጥበብ ሰው ነበር።
ከወራት በፊት ኢትዮጵያ የዓለም ሎሬት ዶክትር ጥበበ የማነብርሃንን በኮቪድ 19 ምክንያት አጥታለች። በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በሥነ ቆዳ ሕክምና (ዴርማቶሎጂ)፣ በኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ባለሙያም ሆነው ኢትዮጵያን ለሃምሳ ዓመታት አገልግለዋል። በቅርቡ በተቋቋመዉ የሰላም ኮሚሽን ውስጥም እያገለገሉ ነበር።

አንጋፋውን ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የሚዘነጉ አይደሉም። ፕሮፌሰር መስፍን በተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸው በጥናትና ምርምራቸው እንዲሁም ደፋር በሆኑ የአደባባይ ትችቶቻቸው እና ሦስት መንግሥታትን በማገልገልም በመሞገትም ይታወሳሉ። ኮሮና ጉምቱውን ፕሮፌሰር ሲያሳጣን እንደ አገር አንድ ትልቅ ዋርካ ወድቋል።

ከላይ ያወሳናቸው ኮቪድ በአገራችን ገብቶ ከነጠቀን አንጋፋዎቻችን ጥቂቶቹን ነው። እንዳልነው በየእለቱ እጅግ በርካታ በቤቶች ውስጥ ድንኳን ተጥለዋል፣ ያልተዘመረላቸው ባለውለታዎችና አገልጋዮችን ሕይወታቸው አልፏል፣ ቤተሰብ ተበትኗል፣ በየመንገዱ ጥቁር የሀዘን ልብስ የለበሰ ማየት በጣም የተለመደ ትዕይንት ሆኗል። ግን ማገገምም አለ። ብዙዎችም ከቫይረሱ አገግመዋል። ወዲህ ደግሞ ኮቪድን ተጋፍጠው ያገገሙ አንጋፈዎችን እናነሳለን።

የቫይረሱን ስርጭት ተከትሎ ብዙዎች ‹ኮቪድ 19 ገዳይ የሚሆነው በተለይ እድሜያቸው የገፉ ሰዎች ላይ ነው› የሚለውን አስተያየት ሲደጋግሙት ይሰማ ነበር። ቫይረሱ እድሜ የማይመርጥ እንደሆነ ኋላ ላይ ይታይ እንጂ፣ በእርግጥም በእድሜ የገፉ ሰዎች የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸው እሙን ነው።

ታድያ ግን በእድሜ የገፉና ይህን ቫይረስ ያሸነፉ አልጠፉም። በተቃራኒው ደግሞ በእድሜ አልገፉም የሚባልላቸው ወጣቶች በኮቪድ ሳቢያ ሕይወታቸው እንዳለፈ ተመዝግቧል። ኮቪድን ተጋፍጠው እንዳሸነፉት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ይፋ ካደረጉት የአገራችን ታላላቅ ሰዎች አንዱ አንጋፋው ኢትዮጵያዊ ሀኪም ዶክተር አበበ ሀረገወይን ናቸው። እርሳቸውም ለኹለት ወራት ከኮቪድ 19 ጋር ካደረጉት ውጊያ በኋላ ‹‹ከጽኑ በሽታ ለመዳን ጽኑ ሕሊና ይጠይቃል። ዘራፍና ትኩስ ቶሎ ፈንድቶ ቶሎ የማይበርድ ጊዜውን የሚፈጅ መሆን አለበት። አርምሞና ልምምድ ይጠይቃል። በተለይ ተፈትኖ የማለፍ ተለምዶ ይጠይቃል። ማማረርና መደበር፣ መጎሳቆልና ሰው ማካለብ ራሳቸው የበሽታ ማራዘሚያ መንፈስ ናቸው።›› ሲሉ ማገገማቸውን እና ለማገገማቸው ምክንያት የነበረውን ጽናታቸውን ገልጸዋል።
ዶክተር አበበ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው በኮተቤ የኮቪድ ማገገሚያ ሕክምናቸውን ሲከታተሉ እንደነበር እና በጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ገብተውም እንደነበር የሚታወስ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ በበርካታ ድራማዎች እና ፊልሞች ላይ የእናትነትን ገጸ ባህሪ በመላበስ በበርካቶች ዘንድ የእናት ያህል ተቀባይነትን ያገኘችው አንጋፋዋ አርቲስት ፍቅርተ ደሳለኝ ከኮቪድ 19 ጋር ተጋፍጠው ካሸነፉት ጎራ ትመደባለች። ፍቅርተ ኮቪድ 19 ወደ ኢትዮጵያ ገባ ከተባለ ጊዜ ጀምሮ ለሥራ እንኳን ከቤት ወጥታ እንደማታውቅ ገልጻለች።

ነገር ግን ለሀይማኖታዊ ጉዞ ወደ ይርጋለም በሄደችበት አጋጣሚ ኮቪድ ሳይዛት እንዳልቀረ ከታዲያስ አዲስ ጋር ባደረገችው ቆይታ ገልጻለች። ፍቅርተ ኅብረተሰቡ ኮሮና በዚህ ደረጃ እየተስፋፋ እና ገዳይነቱ እየጨመረ መምጣቱ እየተነገረ ለምሳሌ እንደ መስፍን ጌታቸው ያሉ የሚሞቱ የማይመስሉ ሰዎችን ከጎናችን እያጣን ለምን አንጠነቀቅም? በማለት መልእክቷን አስተላልፋለች። ፍቅርተ በቤቷ ውስጥ በኦክስጂን የታገዘ ሕክምና አድርጋ ከቫይረሱ እንዳገገመች ገልጻለች።

ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አንጋፋ የመጀመሪያዋ ሴት የረጂም ልቦለድ ጸሐፊ ፀሐይ መላኩ ናት። በማኅበራዊ ትስስር ገጿ ላይ ‹‹የኮሮና ወጀብ ጠልፎኝ ጥቂት መንገድ ወስዶኝ ነበር። በሥቃዩ አዙሪት ውስጥ ገብቼ መከራውን ቀምሻለሁ። ሥቃዩ እጅግ አስጨናቂና ከባድ ነው። በዚህ ውስጥ ሆኜ አምላኬን ተማፀንኩት። እሱም በጽኑ ክንዱ ስቦ አወጣኝ። ለዘላለም ይመስገን።›› ስትል ከኮሮና ጋር የነበራትን ትንቅንቅ አስፍራለች።

የኮቪድን አስከፊነትም ‹‹ውድ ወገኖቼ! ይህንን የቸነፈር ጊዜ ለመሻገር ከምሁራን የሚሰጠውን ቅን ሐሳብና ምክር ልንቀበልና ልንጠነቀቅበት ይገባል። መኖርን ለመኖር ተጠንቅቃችሁና ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ተብለናልና።›› በማለት ለማኅበረሰቡ መልእክቷን አስተላልፋለች።

ኮቪድ 19ን ተጋፍጠው ድል ያደረጉ የአገራችን ሰዎች በርካቶች ቢሆኑም በኮቪድ ድል የተነሱም ስፍር ቁጥር የላቸውም። በኢትዮጵያ ኮቪድ 19 ዛሬም በየእለቱ የሰዎችን ሕይወት መንጠቁ አልቀረም። በዓለም ዐቀፍ ደረጃም ቢሆን ኮቪድ መልኩን ቀይሮ ድጋሚ አገርሽቷል። እንደ ህንድ እና ብራዚል ባሉ አገራትም የሟቾች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ይገኛል።

በእኛም አገር የኮቪድ 19 ምርመራ እጅግ የተጠናከረ እና በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች የሚካሄድ ቢሆን ኖሮ፣ በቫይረሱ የሚያዙ ዜጎች ቁጥር አሁን እየተነገረ ካለው ቁጥር የበለጠ እንደሚመዘገብ የሕክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ስልክ ላይ ጥንቃቄ የተሞሉባቸው እንቅስቃሴዎችን እንድንተገብር የሚያስረዱ መልእክቶችን በመላክ እያሳሰበን ቢገኝም፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው መዘናጋት ግን እንደቀጠለ መሆኑን ለመታዘብ ችለናል።

 ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com