የበረኸኛው የአቶ ጌታቸው ረዳ እንጉርጉሮዎች! ክፍል 2

Views: 161

ህወሓት በስልጣን ዘመኑ በጠላትነት ፈርጆ ያላጠቃው ሕዝብም ሆነ የፖለቲካ ቡድን አለ ማለት አይቻልም። የኤርትራውን ሻዕቢያ ጠላት አድርጎ በቡድኑና በሕዝብ ሀብት ላይ ያደረሰው ውድመት በቀላሉ የሚረሳ አልነበረም። በቅርቡ በህወሓት ላይ ወታደራዊ እርምጃ መወሰዱን ተከትሎ የበቀል እርምጃ በኤርትራውያን የተወሰደበት ምክንያት የህወሓት አመራሮች በፊት በነዙት የጥላቻ ቅስቀሳ ለፈጸሙት ጥፋት ምላሽ እንደሆነ ይነገራል። አሁንም ተመሳሳይ ጥፋት የሚያስከትል ቅስቀሳ በአማራ ላይ ማሰራጨታቸውን ቀጥለዋል። ይህ ተግባራቸው በትግራይና በኤርትራውያን መካከል የፈጠረውን አይነት የማይበርድ ቁርሾ ከአማራ ሕዝብ ጋር እንደሚፈጥር ግዛቸው አበበ በጽሁፋቸው እንዲህ አቅርበውታል።

ክፍል 2
ህወሓትና ጸረ-አማራ ዛቻዎቹ…..
አቶ ጌታቸው ረዳ ብአዴን/ብልጽግናን እንደ ዘገምተኛ ድርጅት አድርገው በመቁጠር አማራ ክልልን በፈለጉበት ጊዜና ቦታ በጦር እንቅስቃሴ ሊያመሰቃቅሉት እንደሚችሉ በግልጽ ተናግረዋል። እንደተናገሩትም ከአንዴም ሁለት ጊዜ ታጣቂዎቻቸውን ወደ አዋሳኝ የአማራ ክልል ወረዳዎች ልከው ወረራ ፈጽመዋል፤ ገድለዋል፤ ንብረት አውድመዋል። ይህን መሰሉ የህወሓት አካሄድ ድርጅቱ ገና ከመፈጠሩ በአማራ ሕዝብ ላይ የጠነሰሰውንና በስልጣን ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታት ራሱ ሲፈጽመው የነበረውን፣ እሱ የፈጠራቸውም ሆኑ የእሱ ተቃዋሚወች ነን የሚሉ አክራሪ ብሔርተኛ ድርጅቶች በነጻት እንዲያካሂዱት የፈቀደውን ጸረ አማራ ዘመቻ ለመቀጠል ያለውን ፍላጎት የሚያሳይ ነው። ህወሓት የካቲት 1968 ዓም በነደፈው ማንፌስቶ ላይ “የአማራ ብሔር እረፍት አታገኝም” ሲል ያሰፈረውን ዛቻ ተግባራዊ ከማድረግ እንደማያርፍ የአቶ ጌታቸውም ሆነ የሌሎች የህወሓት አውራዎች ቃለ ምልልሶች፣ እንዲሁም በትግራይ ሚዲያ ሃውስ ላይ እየቀረቡ ተመሳሳይ ሃሳቦችን የሚሰነዝሩ ፖለቲከኞች፣ የሐይማኖት አባቶች ነን የሚሉ ግለሰቦችና ጋዜጠኞች፣ ወዘተ. አነጋገሮች ያረጋግጣሉ።

የእነ አቶ ጌታቸው ረዳ ጸረ-አማራ ቀረርቶ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ለመረዳት በህወሓትና በሻዕቢያ መካከል ሰፍኖ የኖረው የጠላትነት መንፈስ በኤርትራና በትግራይ ሕዝብ መካከል ምን እንዳስከተለ መለሰ ብሎ ማየት ተገቢ ነው። አቶ ጌታቸው ረዳ በድርጅታቸውና በሕዝባዊ ግንባር መካከል ነግሶ የኖረው አንዴ የባሪያና የጌታ ኣይነት ሌላ ጊዜ የደመኛ ጠላቶችን የመሰለ ግንኙነት በሂደት በኤርትራና በትግራይ ሕዝቦች መካከል ከፍተኛ ቁርሾ መፍጠሩን ሊክዱ አይችሉም። ብዙዎች የትግራይ ምሁራንና ፖለቲከኞች እንደሚሉት በአሁኑ ጊዜ የመረረ ጥል ያለው በህወሓትና በሻዕቢያ መካከል ብቻ አይደለም። በድርጅቶቹ የበረኸኛነት ዘመን በሻዕቢያ ጥረት ተጀምሮ ከባድመ ጦርነት ጀምሮ ደግሞ በህወሓት ጥረት ሰማይ የደረሰው ጥላቻንና ንቀትን የመዝራት ዘመቻ ሁለቱን ሕዝቦች እንደ ደመኛ ጠላት እንዲተያዩ፣ አንዱ ሕዝብ ሌላውን እንደ አጥፊው አድርጎ እንዲያስብ አድርጎታል።

ከጥቅምት 2013 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ በሚካሄደው ጦርነት አቶ ጌታቸው ረዳና ጓዶቻቸው ወደ ትግራይ ምድር ዘልቆ የገባው የኤርትራ ጦር ከተራ የቤት እቃዎች ጀምሮ የፋብሪካ ማሽነሪዎችን፣ የቢሮ ቁሳቁሶችን፣ የዩኒቨርሲቲ ንብረቶችን፣ ወዘተ. ዘርፎ እያጓጓዘ መሆኑን ደጋግመው ነግረውናል። ለዘረፋ ያልተመቸውን ንብረት ደግሞ በቦምብና በእሳት እያጋየ መሆኑንም ተናግረዋል። እነ አቶ ጌታቸው ረዳ ሻዕቢያ ትግራይን የማውደም፣ የማደህየትና በስልጣኔ በብዙ ዓመታት ወደ ኋላ የመጎተት ዕቅድ ይዞ መውረሩን ነግረውናል። የሻዕቢያ ጦር ዕድሜያቸው 12 ዓመት ከሆናቸው ጀምሮ ሁሉንም የትግራይ ወንድ ለመግደል ዘመተብን ሲሉም ተሰምተዋል። ይህ ሻዕቢያ የትግራይን ወንዶች ሊጨርስ ትግራይን ወረረ የሚል ወሬ ለቃለ ምልልስ በቀረቡ የህወሓት ሰወች፣ በትግራይ ሚዲያ ሃውስ፣ በርዕዮት ሚዲያ፣ በኢትዮ ፎረም፣ ወዘተ. በተደጋጋሚ ተነግሯል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የአማራ ሚሊሻ፣ ፋኖና ልዩ ኃይል የ5 ዓመት ዕድሜ ካላቸው ጀምሮ ሁሉንም የትግራይ ወንጆች የመጨረስ ዘመቻ እያካሄደ ነው መባሉ እየተደጋገመ ነውና የአማራንና የትግራይን ሕዝብ ጥርስ ለማናከስና አንዱ የሌላው ጸር ሆኖ የሚታይበትን ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው።

ትግራይ በኤርትራ ጦር ሙሉ በሙሉ ወደመች፤ ተዘረፈች የሚለውን ነገር ሲነግሩን አቶ ጌታቸው ረዳና ደጋፊ ሚዲያዎቻቸው የማይነግሩን ነገር አለ። ነገሩ ብድር የመመለስ ዘመቻ መሆኑን መካድ አይቻልም። የባድመውን ጦርነት ተከትሎ በህወሓት መራሹ ጦር እጅ ውስጥ በገባው የኤርትራ ምድር መጠነ ሰፊ ዝርፊያና ውድመት ተፈጽሟል። የዝርፊያው ሰለባ ሻዕቢያ ብቻ አልነበረም፤ የኤርትራ ሕዝብም ጭምር ነበረ። በ1991/92 ዓ.ም. ሽሬን፣ አክሱምን፣ ዓድዋንና ዓዲግራትን የመሳሰሉ ከተሞች ወደ ሃይፐር-ማርኬትነት ቀይረው እንደነበረ ማን ይረሳዋል። በዚህ ጊዜ በነዚህ ከተሞች ሲቸበቸቡ የነበሩት የወርቅ ጌጣ-ጌጦች፣ ቴሌቪዥኖች፣ ቴፕ-ሪከርደሮች፣ ፍሪጆችና ሌሎችም የቤት ቁሳቁሶች ከየት የመጡ ናቸው? ለመሆኑ ሽያጩን ሲያካሂዱና ገንዘብ ወደ ኪሳቸው ሲከቱ የነበሩት እነማን ናቸው? የጦር አዛዦች አይደሉምን?!

አንዳንድ ከፍተኛ የጦር ሹማምንት በነዚህ የትግራይ ከተሞች ውሽሞችን አስቀምጠው ከኤርትራ በመጡ ቁሳቁሶች የተደራጀ ካፍቴሪያ፣ ሆቴልና ሌላም የንግድ ተቋም ከፍተው አስረሽ ምችው ይሉ እንደነበሩ የነዚህ ከተሞች ነዋሪ የሆኑ ተጋሩዎች በሀዘኔታ ሲነጋሩበት የነበረ ነገር ነው። ይህን መሰሉ ዝርፊያ በአንዳንድ ስግብግብ ጦር መኮንኖች የግል ፍላጎት የተመራ ሳይሆን በድርጅት ደረጃ እንዲፈጸም የተደረገ የጥላቻ ዘመቻ ውጤት መሆኑን መጠራጠሩ ተገቢ አይደለም።

ህወሓት ኢትዮጵያዊነታቸውን ያልተዉ የኤርትራ ተወላጆችን ጭምር፣ ሕጻንና አዛውንት ብሎ ሳይለይ ኮማንዶዎች፣ ሰላዮችና ወዘተ. ናቸው እያለ በባድመ ጦርነት ዋዜማ ባዶ አጃቸውን ከኢትዮጵያ እንዲባረሩ በማድረግ የጀመረውን ሕዝቦችን በጅምላ በበቀል በትር የማጥቃት ዘመቻ በኤርትራ በሚኖሩ ኤርትራውያን ላይም በገዛ አገራቸው ደግሞታል።

በእርግጥ የባድመ ጦርነት ገና ከጅምሩ የበቀል ጦርነት ነበረ። የኤርትራ አየር ኃይል ወደ መቐለ ዘልቆ አይደር ትምህርት ቤትን ደጋግሞ መደብደቡ፣ ወደ ዓዲግራት ሰማይ ዘልቆም ከተማዋን የቦምብ ዒላማ ማድረጉ የጠላትነቱን ደረጃ የሚያሳይ ነው።

የኤርትራው ሳዋ፣ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ብቻ ሳይሆን ከ10ኛ ክፍል በኋላ ሁሉም የኤርትራ ተማሪዎች ገብተው ቀሪ ትምህርታቸውን እና ሁለገብ ስልጠና የሚወስዱበት ግዙፍ ካምፕ ነው። ይህ ካምፕ የኤርትራ አየር ኃይል መዳከሙን ተከትሎ የህወሓት የበቀል በትር ካረፈባቸው ቦታወች እንዱ ነው። ህወሓትም ሳዋን በአየር ሲደብድብ የተወሰኑ አንቶኖቮች ቦምብ ሲጥሉ ሌላ አንቶኖቮቭ በምድር ላይ የሚሆነውን ፊልም ይቀርጽ ነበረ። አንቶኖቮቹ ስራቸውን ዘና ብለው እንዲሰሩም በበርካታ ተዋጊ ጀቶች ይጠበቁ ነበረ። በዚህ መንገድ በሚገባ የተቀረጸው ፊልም በባለሙያ ተከሽኖ በኢቲቪ እንደ መዝናኛ ሆኖ መቅረቡ የሚረሳ ጉዳይ አይደለም። ከዚህ ሌላ ቁስለኛ የኤርትራ ወታደሮችን የጫኑ ኦራሎችና የሕክምና ማዕከላት በአየር ድብደባ እንዲጋዩ ተደርገው፣ ምስሎቹ ሻዕቢያ የራሱን ቁስለኞች አቃጥሎ ፈረጠጠ ወደሚል ድራማ ተቀይረው በቴሌቪዥን መሰራጨታቸው ሌላው ከወዲህ በኩል የተሰነዘረ የብቀላ ተግባር ነበር።

ከጦርነቱ ቀጠና ውጭ የሚካሄደው ጥቃት ቀጥሎ፣ የኤርትራን ሀብት ንብረት የማውደሙ ተግባር የተካሄደበት ሌላው ቦታ ሂርጊጎ ነው። ሂርጊጎ ምጽዋ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፣ በዚህ ቦታ ለመላዋ ኤርትራ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማሰራጨት ተብለው የተተከሉ በርካታ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫወች ይገኛሉ። ይህ ቦታ በተዋጊ ጀት ተደብድቧል። የመጀመሪያውን ድብደባ ተከትሎ የአሜሪካ መንግስት ለህወሓት/ኢሕአዴግ መንግስት ማስጠንቀቂያ ባይሰጥ ኖሮ ውድመቱ ሙሉ ይሆን ነበረ።

የበቀሉ አዙሪት ሲቀጥል በወረራ ውስጥ የወደቁ የትግራይና የኤርትራ ከተሞችም የብቀላ ዱላወች አርፈውባቸዋል። የትግራይዋ ዛላንበሳ ቃል በቃል በዶዘር ታርሳለች። የኤርትራዎቹ ተሰነይና ባረንቱን የመሳሰሉ ከተሞች መሰረተ ልማታቸው ወድሟል፤ አገልግሎት መስጫ ተቋሞቻቸው የቦምብ እራት ሆነዋል፤ ዘመናዊ ሆቴሎቻቸው እንዲፈራርሱ ተደርጓል፤ የሻዕቢያ ቤቶች የተባሉ የግል መኖሪያ ቤቶች ፈራረሰዋል። የጥቅምት 2013 ዓ.ም. ጦርነት ተከትሎ ደግሞ ትግራይ ውስጥ ተመሳሳይ ነገር በኤርትራ ጦር ተፈጽሟል።

በኤርትራዋ ዓልጊድር የተፈጸመው ውድመት ለየት ያለ ነበረ። ሕዝባዊ ግንባር ስልጣን እንደያዘ ብዙም ሳይዘገይ በጋሽ-ባርካ ምድር የሚመረተውን ከፍተኛ የጥጥ ምርት ለኤርትራ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ግብኣት ከመሆን አልፎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ እንዲሆንለት አጓጊ ዕቅድ ነድፎ ነበረ። ይህን ዕቅድ ለማሳካት ወደ 50 ሚሊዮን ዶላር እንዳወጣበት የሚነገርለትን በጣም ግዙፍና ዘመናዊ የጥጥ መዳመጫና ማደራጃ ፋብሪካ ዓልጊድር ላይ ተከለ። ፋብሪካው ተገንብቶ ምርት ማምረት ከጀመረ ብዙም ጊዜ ሳያስቆጥር የባድመ ጦርነት ተጀመረ። በምዕራብ ኤርትራ የገባው የኢትዮጵያ ጦር ከወረራቸው ከተሞች እንዷ ዓልጊድር ሆነች። ይህን ወረራ ተከትሎ የህወሓት የውድመት ዒላማ ከተደረጉት ተቋማት አንዱ ይህ ግዙፍ ፋብሪካ ነው። የትግራዩ ጦርነት ተቀስቅሶ የኤርትራ ጦር የትግራይን ፋብሪካዎችና እያወደመና እየዘረፈ ነው የሚለውን ወሬ መስፋፋት ተከትሎ የኤርትራ አክቲቪስቶችና የሕዝባዊ ግንባር ደጋፊዎች በማኀበራዊ መገናኛ ዘዴወች የባድመውን ጦርነት ተከትሎ ኤርትራ ውስጥ የተካሄደውን ንብረት የማውደም ዘመቻ የሚያሳዩ በርካታ ምስሎችን መልቀቅ ጀመሩ። ከነዚህ ምስሎች ጥቂቶቹ በበርካታ ቦምብ የጋየው የዓልጊድሩ ፋብሪካ ናቸው። ከመደርመስ በተረፈው የዓልጊድር ፋብሪካ ግዙፍ ግንብ ላይ የሚከተለው ጽሑፍ ሰፍሮበታል-

‘ለጓድ ኢሳያስ አፈወርቂ! ይህ በታላቅ ወጭ የገነቡትን ተቋም ስላደስንልወት ታላቅ ደስታ ይሰማናል…… ገባወት?’
ይህ ጽሑፍ የተጻፈው በተመረጠና ፊደላትን ቆሎ አስመስሎ በሚያስቀምጥ ሰው መሆኑ የታሰበበት፣ የጠላትነትና የብቀላው ክፍል መሆኑን ያሳል። አሁን ደግሞ የመውደም ተራው የትግራይ ፋብሪካወች፣ የመሳለቅ ተራው የሻዕቢያ ሆነ።

በ1991 ዓም የሽሬን ሕዝብ ያስቆጣ አንድ ድርጊትን እንዘክር። በወቅቱ የሰሜን ምዕራብ ትግራይ አስተዳዳሪ የነበረው ግለሰብ በሽሬ ከተማ ውስጥ ነጭ ዲ.ኤክስ. መኪና ይዞ መታየት ጀመረ። መኪናዋ ከየት መጣች የሚለው ጥያቄ ምላሽ ያገኘው ብዙም ሳይቆይ ነበረ። መኪናዋ ከኤርትራ ተዘርፋ የመጣች ነበረች። ሕዝቡ ማጉረምረም አበዛ። የተማረከች የሻዕቢያ ንብረት ከሆነች ለመንግስት ገቢ መደረግ ሲገባት አስተዳዳሪው የግሉ አደረጋት የሚል እሮሮ በዛ። አስተዳዳሪው ለጦርነቱ ስኬት ላበረከተው አስተዋጽኦ በመንግስት እንደተሸለመ ተደርጎ ወሬ ቢነዛም የሕዝቡ ማጉረምረም አልበረደም። ብዙም ሳጥቆይ መኪናዋ ከሽሬ ጎዳናዎች ተሰወረች።

የትግራይ ሕዝብ በአብዛኛው ዝርፊያውን በቅሬታና በተቃውሞ ያስተናገደው ቢሆንም፣ ሕግ-ማስከበር የተባለውን የጥቅምት 2013 ዓም ጦርነት ተከትሎ ወደ ትግራይ በገባው የኤርትራ ጦር በትግራይ ያሉ ፋብሪካዎችና መኖሪያ ቤቶች ጭምር መዘረፋቸውን ሲሰማ እነዚህን መሰል ምስሎች እየተጠቀሙ ብድር በምድር እያሉ የጨፈሩ ኤርትራውያን እንደነበሩት ሁሉ የመበቃቀል አዙሪት እንዲቆም የወተወቱ ኤርትራውያንም አሉ። የትኞቹ ወገኖች እንደሚበዙ ለማወቅ ጥልቅ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም፣ የህወሓትና የሕዝባዊ ግንባር ጥል የሕዝብ ጥል ወደ መሆን እያደገ መሆኑን ለመረዳት አዳጋች አይደለም። የባድመውን ሆነ ጥቅምት 2013 ዓ.ም. የተጀመረውን ጦርነት ተከትሎ በውጭ አገራት የሚኖሩት የትግራይና የኤርትራ ተወላጆች ሁለት ዓይነት ገጽታ ታይቶባቸዋል። የበቀል በትሮችን ተከትሎ በየተራ የጨፈሩ የመኖራቸውን ያህል ሁለቱ ሕዝቦች ጥላቻቸውን ትተው ተባብረው እንዲኖሩ ድምጻቸውን ያሰሙም አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ለዚህኛውና ለዚያኛው ወገን ተቀጥረው ለገዛ ሕዝባቸው ጠላት ሆነው የፈረንጆቹን ጎዳናወች በጩኸት የሚያናውጡ ጉዶችም አልታጡም። አሁን ሊነሳ የሚገባው ‘ከወዲህ ወገን ተራቸው ደርሶና ጉልበት አግኝተው ኤርትራን በማውደምና በመዝረፍ ለመበቀል የቋመጡ ልቦች ስንቶቹ ይሆኑ?’ የሚለው ነው።

ይህን መሰሉን ቁጥሩ ቀላል በማይባል የትግራይና የኤርትራ ሕዝብ ልብ በተለይም በወጣቶች ልብ የተቀረጸው የጠላትነት ስሜት ነው አቶ ጌታቸው ረዳና ድርጅታቸው በአማራና በትግራይ ሕዝቦች መካከል እንዲፈጠር በጣም ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ያሉት።

የአሁኑን በትግራይ የሚካሄድ ጦርነት ተከትሎ አቶ ጌታቸው ረዳና ትግራይ ሚዲያ ሃውስ ብቻ ሳይሆኑ የብልጽግና ሹመኞች ሆነው መቐለ ላይ የተቀመጡ ብዙ ባለስልጣናትም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በየሰበቡ አማራውን ሕዝብ ወይም የአማራን ልዩ ኃይል፣ የአማራ ሚሊሻና ፋኖ እያነሱ ማውገዛቸው የተለመደ ነገር እየሆነ ነው።

አንዳንዴም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ‹የአማራ ጥቅም አስከባሪና የአማራን የበላይነት ለማስመለስ የሚሰሩ› አስመስለው በመናገር ለትግራይ ሕዝብ ‘በዚህም ሆነ በዚያ ጠላትህ አማራና አማራ ብቻ’ ነው የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ እየሞከሩ ነው። ይህን መሰሉ አካሄድ የሚያቆመው ካልተገኘ በኤርትራና በትግራይ መካከል የነገሰው መጠፋፋት፣ የመጠቃቃትና ዘላለማዊ ጠላት ሆኖ የመተያየት አዙሪት በአማራና በትግራይ ሕዝብ መካከልም ሊነግስ ይችላል።

ጥቅሙና የመጨረሻ ግቡ ባይታወቅም ህወሓት በዙሪያ ገባው የሚገኘው ወገንና ወንድም ሕዝብ የትግራይ ሕዝብ ጠላት እንዲሆን በርትቶ እየሰራ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com