‹‹ የምርጫ ሂደቱ በብዙ እንከኖች የተከበበ ዝቅተኛ መስፈርትን የማያሟላ ነው ››

Views: 213

ገለታው ዘለቀ በየነ ይባላሉ። የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የቢሮ ኃላፊ ናቸው። ፓርቲያቸውን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የምርጫ ከልል 20 ላይ ነው። ስለ 6ተኛው አገር አቀፍ ምርጫ አጠቃላይ ሂደት እንዲሁም ስለፓርቲያቸው ሁኔታ ከአዲስ ማለዳው ቢንያም ዓሊ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አገር አቀፉ ምርጫ ይራዘማል ስለመባሉ ምን አስተያየት አሎት?
የምርጫ መራዘም ከሚባለው ነገር ጋር መነሳት ያለበት የመጀመሪያው ነገር ምን ልንሰራበት ነው? የሚለው ነው። ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ ያለውን የኢትዮጵያን አጠቃላይ ሁኔታ ስንመለከት የምንሰማው “ጊዜ ያስፈልጋል” የሚለውን ነው። ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ሲመጣ “ለእንዲህ ተነስተው” እየተባለ “ጊዜ ያስፈልጋቸዋል” ቢባልም ሁኔታዎች እየባሱ አየተባባሱ ሲመጡ ታይተዋል። የምርጫ ጊዜው ቢራዘም በተራዘመው ጊዜ ምን ይገኛል የሚለው ነው የመራዘሙን ጥቅም የሚያሳውቀው። ቀኑ በ2 እና 3 ሳምንት ነው የሚራዘመው ሲባል ሰምቻለሁ። ቀኑ ቢራዘም ችግር የለም፣ ዋናው ምን ሊሰራበት ነው የሚለውን ማወቁ ላይ ነው። ለአጭር ጊዜም ቢሆን የሚራዘመው እውነት ምርጫ ቦርድ በዛ ጊዜ ውስጥ የሚፈታ እክል ገጥሞት ነው ወይ? የሚለው ይወስነዋል። ከዚህ ውጭ ረዘም ላለ ጊዜ መራዘሙን አልደግፍም። ጊዜ በተራዘመ ቁጥር ችግሮች እየተወሳሰቡ ስለሚመጡ፣ ይህ ምርጫ ቢያንስ ወደ ብሔራዊ መግባባት እንዲገፋ፣ ሕዝብ የመረጠው ተከብሮ አገሪቱ አዲስ ምዕራፍ ውስጥ እንድትገባ ስለሚያግዝ ምርጫው ጊዜ ሳይወስድ መደረግ አለበት። ምርጫ ቦርድ በጊዜ ሠሌዳው መሰረት ምን ማድረግ ፈልጎ ነው ይህን ሀሳብ ያነሳው የሚለው ነው መታየት ያለበት።

ምርጫው ረዘም ላለ ጊዜ ቢተላለፍ የሚያመጣው ችግር ምንድን ነው ይላሉ?
በተለመደው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት መስከረም ላይ አዲስ መንግስት መመስረት አለበት። ምርጫው ረዘም ላለ ጊዜ ከተራዘመ ሌላ መዘበራረቅ ያስከትላል። ክረምቱም ከገባ ለገበሬው አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ገጠር አካባቢ ድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በእግር ረጅም ርቀት ሊያስኬዱ ስለሚችሉ የወንዝ ሙላትን የመሳሰሉ ከዝናብ ጋር የተገናኙ ችግሮች አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ሊያስተጓጉሉ ይችላሉ። ይህ በመራጩ ላይ ብቻ ሳይሆን በታዛቢዎችና ምርጫ አስፈጻሚዎች ላይም ሊከሰት የሚችል ችግር ነው። ከምርጫው በፊትም ሆነ በዕለተ ቀኑ የአየር ጸባዩ የሚያመጣው ተጽእኖ ይኖራል። ይህን በመሳሰሉ ችግሮች ምክንያት ምርጫው ወደ ክረምቱ ከተወሰደ ችግር ይኖረዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ አዲስ ፓርላማ መስከረም ላይ ከመቋቋሙ በፊት መሰራት የሚኖርባቸውን ነገሮች በማስተጓጎል እክል ሊፈጥር ይችላል። በአጠቃላይ መራዘሙ ወራትን መውሰድ የለበትም።

የምርጫ ቅስቀሳውንና ክርክርን በተመለከተ ሂደቱን እንዴት ያዩታል?
እዚህ አዲስ አበባ የሚካሄደውን ቅስቀሳ በተመለከተ በተለይ የእኛ ፓርቲ ላይ ያሉ ወከባዎች በጣም ይበዛሉ። ለምሳሌ፣ ባነሮቻችንን ማበላሸትና የምንተክላቸው ድንኳኖች ጋር ፖሊስ እየመጣ ወከባ መፍጠርን የመሳሰሉት ችግሮች ይገጥሙናል። ይህ ቢገጥመንም ቅስቀሳ እያደረግን ነው። ከዚህና ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተገናኘ የታዩትን ከባድ ችግሮች በማስመልከት ባልደራስ ጥናት አስጠንቶ አቅርቧል። ጥናቱ የሚያሳየው አጠቃላይ ቅድመ ምርጫ ሂደቱ የመጨረሻውን ዝቅተኛ መስፈርት እንዳላሟላ ነው። የዚህን ምርምር ውጤት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ሆነ ለብሔራዊ ኮሚቴው እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሕዝብ አቅርበናል። ሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ ባልደራስ ላይ የተለየ ጥቃት በብልጽግና በኩል ተፈፅሞብናል። ለምሳሌ፣ አዲስ አበባን በሚመለከት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ብልጽግናና ኢዜማ ለክርክር በተገናኙበት ወቅት ባልደራስ ክርክር ማድረግ አልቻለም ነበር። ባልደራስ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ መቅረብ አይችልም ተብሏል። በዚህ አይነት መንገድ እንዳንከራከራቸውና ድምጻችንን እንዳናሰማ ክልከላ እየተደረገብን ያለበት የቅድመ ምርጫ ሂደት ላይ እንገኛለን። የምርጫ ሂደቱ በብዙ እንከኖች የተከበበ ዝቅተኛ መስፈርትን የማያሟላ ነው።

ቅስቀሳውን በተመለከተ የአቅም ልዩነቱ ምን ያህል ነው? ለፓርቲዎች የሚሰጠው ገንዘብስ በቂ ነው?
ምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎች የሚሰጠው ገንዘብ አለ። ገንዘቡ መሰጠት ያለበት ቀድሞ ነበር። የምርጫው ዋዜማ ላይ ወይም ከተጠናቀቀ በኋላ ሰጥቶ በብሩ እንዲጨፈርበት አይደለም ዓላማው። ገንዘቡ ስራ እንዲሰራበት በተለይ የምርጫ ቅስቀሳ እንዲሰራበት ነው የሚሰጠው። ብዙ ከሰራን በኋላ በቅርቡ ትንሽ ገንዘብ ለሁላችንም ተለቆልን የቀረው ይለቀቅላችኋል ተብለን ነበር። ኹለተኛው ዙር እስካሁን አልደረሰንም። ይህን የሚያደርጉት ለምን እንደሆነ ሊገባን አልቻለም። ሀብቱ የኢትዮጵያውያን ሀብት ነው። አላማው ዴሞክራሲን ለማበረታታት ሆኖ ሳለ መድብለ ፓርቲን ለማስለመድ ፓርቲዎች ያለባቸውን ችግር እንዲቀርፉ እንዲሁም በተመጣጣኝ ሁኔታ ቀስቅሰው ሕዝብ አውቆ እንዲመርጥ ነው። ብሩን እጃቸው ላይ ይዘው በማስቀረታቸው የማይቸገረው ብልጽግና ብቻ ነው። ፓርቲው የመንግስትን ካዝና ስለሚጠቀም የምናያቸው ባነሮች ብዙ ብር የሚያስወጡ ናቸው። ሌላው ፓርቲ ኹለት መኪና ይዞ ለመንቀሳቀስ የሚያንገዳግደው ነው። ይሰጣል የሚባለው ገንዘብ ካለ አሰቀድሞ ለምርጫ ቅስቀሳ እንዲውል ማድረግ ሲገባ እስካሁን ድረስ መዘግየቱ እኔን በጣም ያሳዝነኛል።

ከውጭ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ከምዕራባውያን በተለይም ከአሜሪካ ጋር ያለን ግንኙነት ምን መምሰል ይኖርበታል ትላላችሁ?
ከውጭ ጉዳይ ጋር በተመለከተ ለኢትዮጵያ ተብሎ ተለየ ነገር አይመጣም። የአውሮፓ ህብረትን ካየን በብዙ አገሮች የምርጫ ትዝብቶችን ይሰራል። እነሱ የሚሉት የቅድመ ምርጫ ሂደቱ በብዙ ችግሮች የተተበተበ ነው፤ የተቀመጠ መስፈርትንም አያሟላም ነው። እኛም በጥናታችን የደረስንበት ይሄንኑ ነው። ከዚህ በላይ ግን አውሮፓ ህብረት ምርጫውን ይታዘብ አይታዘብ የሚለው የራሱ ውሳኔ ነው። ነገር ግን፣ መስፈርትን አያሟላም ያሉት እኛም ያረጋገጥነው ስለሆነ ልክ ነው። እነሱ አጋዥ እንዲሆኑ ነው በሂደቱ ላይ የሚሳተፉትና የሚታዘቡት። ምርጫው ዓለም አቀፍ መስፈርትን ያሟላ መሆኑን የምንገመግመው ዋናው እኛው ነን።

ኢትዮጵያውያን ያሉንን ሲቪክ ማኀበረሰቦችን፣ ሽማግሌዎቻችንን፣ የኃይማኖት ተቋማትን፣ ተጠቅመን ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ማስኬድ ይገባናል። ከዛ ውጭ እንደሌላው ዓለም ምርጫው ቅቡልነት ያለው እንዲሆንና ተቀባይነት ያለው መንግሥት ለመመስረት ሌሎች ታዛቢዎችን መጥራት ተገቢ ነው። እነሱም ሌላው አገር የሚያደርጉትን በሁሉም የሚጠበቅን ያደርጋሉ። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት አንደከዚህ በፊቱ ስጋቶች ያሉበት ያመስለኛል።የምርጫ ማጭበርበር ፍላጎት ሊኖረው ይችላል። በዚህ አይነት ምክንያት ከታዛቢዎች ጋር የተጋጨ ይመስላል።

በ1997 እንደምናስታውሰው አና ጎሜዝ የመራችው የምርጫ ታዛቢ ታሪካችን ላይ በጥሩ ተፅፏል። በጊዜው ለሀቅ ቆመው ለምንድን ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫውን የተነጠቀው? ብለው ከሕዝቡ ጎን በመቆማቸው አርሶ አደሩ ሳይቀር “ሀና ጎበዜ” ብሎ ስም እስከማውጣት በመድረስ ሲያደንቅ ነበር። አሁንም ቢሆን እኛ ዓለምአቀፍ ታዛቢዎች ገለልተኛ ሆነው መኖራቸው አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን። እነሱ ቅድመ ምርጫው ከተበላሸ ድህረ ምርጫውም ጥሩ አይሆንም የሚል አመለካከት ነው ያላቸው። መንግሥት ሂደቱን ያስተካከል ማለታቸው ተገቢ ነው። መንግሥት አስተያየታቸውን ሰምቶ ማስተካከል ያለበትን ማረም ነው እንጂ ወደ ስድብና አላስፈላጊ ዘለፋ መሄዱ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም።

ትግራይን በተመለከተ እነ አሜሪካ ጣልቃ ይገባሉ መባሉን እንዴት ትመለከቱታላችሁ?
ትግራይን በተመለከተ እንደዜጋ ያሳስበኛል። ህወሓት ኢትዮጵያን በጥብጧል መመታት አለበት ብለን በቡድንም በግልም እንደፓርቲም ስንታገል ነው የኖርነው። ህወሓት ሲመታ ግን፣ “ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ” እንደሚባለው ሕዝቡ አብሮ መከራ እንዲያይ አንፈልግም። ሕዝቡ አካላችን እንደመሆኑ እዛ አካባቢ ያሉ ኢ-ፍትሐዊ ተግባሮች በሙሉ መወገዝ አለባቸው። እርዳታ እንዳይደርሳቸው የሚደረግባቸው ሁነቶች መኖራቸውን፣ የመሳሰሉ ተግባራት እንደሚፈጸሙ ማስረጃዎች አሉ። መንግሥት ለዛ ሕዝብ ተገቢውን ጥንቃቄና ከለላ አድርጎ ፅንፈኞቹን መዋጋት መቀጠል አለበት። ህወሓትን ሲያስወግድ እግረመንገዱን ንጹሃን ገበሬዎች እንዳይጎዱ ሕዝቡ ረሀብ ላይ እንዳይወድቅ ትኩረት መደረግ ነበረበት። እኛ እንደፓርቲ የትግራይ ጉዳይ እያሳሰበን ነው ያለው።

መንግስት መጀመሪያውኑ ህወሓት ጡንቻ እስኪያወጣ ሮኬት እስኪገዛ ድረስ መጠበቅ አልነበረበትም። ዝም ብሎ በመቆየቱ ነው እንደዚህ አይነት ጦርነት ውስጥ ሊገባ የቻለው። በወቅቱ ከነደብረፂዮን ጋር በየከተማው እየዞሩ ሲደንሱ የነበሩ ሰዎች ናቸው ከጊዜ በኋላ ጦርነት ውስጥ የገቡት። በወቅቱ ችግሩን መፍታት ሲቻል አካባቢው ለከፍተኛ ችግር እንዲጋለጥ ተደርጓል። በትግራይ ጉዳይ አሜሪካም ሆነች አውሮፓ ህብረት ምን አለ ሳይሆን እንደኢትዮጵያዊነታችን የትግራይ ችግር መፈታት አለበት። የአካባቢው ሁኔታ አሳሳቢ ከሆነባቸው ምክንያቶች መካከል መረጃ እንዳይወጣ መደረጉ አንዱ ነው። ሚዲያዎች በነጻነት እንዳይዘግቡት እየተደረገ መሆኑን አንድ ከዛው የመጣ ሰው ነግሮኛል። እንደሰማሁት ከሆነ ትግራይ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ችግር ነው ያለው። እርዳታ እንኳን እንዳይደርሳቸው የሚደረጉ አሉ። የትግራይ ሕዝብ አካላችን እንደመሆኑ ችግሩን አስበን ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። ለትግራይ ትኩረት ይሰጥ የሚልን ልንጠላ አይገባም። መንግስትም መደገፍ ነው ያለበት።

ከዚህ በተረፈ በሌሎች የውስጥ ጉዳዮቻችን የሚመለከተን እኛ ኢትዮጵያውያንን ነው። ችግሮችን እኛው መፍታት አለብን የምንለው ያሉብን ስርአታዊ ችግሮች ስለሆኑ ነው። ከትግራይ ክልል ጋር ያለው የመሬት ችግር የኔ ብቻ ነው የሚል የፌደራሊዝም ስርአቱ የወለደው ችግር ነው። ሕገ-መንግስቱን በማሻሻል የሚፈታ ነው። የውጭ አገራት በእንደዚህ አይነት ጉዳይ ላይ እላፊ ይሄዳሉ። ዓለምአቀፍ ተቋማትም ጫና ይፈጥራሉ። ይህ ውስጣዊ ችግራችንን በማስተካከል የሚቀር ነው። በየቦታው ያሉ ችግሮቻችን ሊፈቱ የሚችሉት ቁጭ ብለን መነጋገር ስንችል ነው። ያለውን ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ማስረዳትም ያስፈልጋል።

ምርጫው ፍትሃዊ ይሆናል ብለው ይገምታሉ?
ምርጫ ፍትሃዊ ይሆናል ብለን የምንገምተው የቅድመ ምርጫ ሂደቱን አይተን ነው። አሁን በቅርቡ ባልደራስ የሰራው ጥናት እንደሚያሳየው በጣም ብዙ ችግሮች እንዳሉ ነው። ሂደቱ ዝቅተኛውን መስፈርት አያሟላም ማለት ግልጽ ነው። ያልተዘራ አይታጨድም። እና አሁንም በምርጫው ተስፋ የምናደርገው ሕዝብ ከዚህ ሁሉ በላይ ነው ብለን ስለምናምን ነው። ሕዝቡ ድምጹን ማስከበር የሚችልበት የዴሞክራሲ ትግል መድረክ የሆነ የምርጫ ወቅት ምዕራፍ ላይ ነው የምንገኘው። ስለዚህ አገሪቱን ወደ ብሔራዊ መግባባትና ጥምር መንግስት ምስረታ ሊገፋ የሚችል አንድ መንስኤ ይሆናል የሚል ትልቅ ተስፋ ነው ያለኝ።

ፓርቲዎች ሽንፈትን ለመቀበል ምን ያህል ዝግጁ ናቸው ይላሉ?
እኛ አገር የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በሚገባ ገና አልተገነባም። የሕግ ከለላም ስለሌለው ግማሹ በብሔር ላይ የተመሰረተ ሲሆን ግማሹ በብሔራዊ ደረጃ የተመሰረተ ከምርጫ በኋላ ሊጠፋፋ የሚችል ነው። ለምሳሌ፣ አንዱ የስርዓት ለውጥ ቢያመጣ ሌላውን ያጠፋዋል። የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ገንብተው በጋራ ተስማምተው የሚኖሩ አገራት ናቸው ምርጫን በተስፋ የሚጠብቁት። ምርጫ እኛ አገር ብዙ ስጋቶች አሉበት። በድህረ ምርጫ ችግር እንዳይፈጠር ብሔራዊ መግባባት መቅደም አለበት ብለን ስንወተውት የነበረው ለዚህ ነው። ይህን ሀሳባችንን ዶ/ር ዐቢይ ምንም ሳይሰማው ወደ ምርጫ ውስጥ ነው የገባው። የመሸናነፍ ልምድን አላዳበርንም። በታሪካችን እንደሚታወቀው አንዱ ለአንዱ ተሸነፍኩ ብሎ በሰላም ሥልጣን ያስረከበበት ጊዜ የለም። ወደ ሰላማዊ ሽግግር ለመተላለፍ ትግላችን መቀጠል አለበት። የፖለቲካ መስመሮቻችንን ማስተካከል አለብን። ችግሩ የሽግግር ስራ አለመሰራቱ ነው። ይህ ቢሰራ ኑሮ ዋስትና ይኖር ነበር። አንዱ ሲያሸንፍ ሌላውን የማያጠፋበት ዋስትና ያስፈልጋል። በሽግግር ጊዜ ሁሉንም ፓርቲ የሚያሳትፍ ስርዓት ያስፈልጋል። በዚህ መንገድ ያሉብንን ስጋቶች ቀንሰን የመድብለ ፓርቲ ስርአትን የምናዳብርበት ጊዜ መሆን አለበት።

የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ምርጫ ከአገር አቀፉ ጋር አንድ ላይ መሆን አለመሆኑ የሚያመጣው ልዩነት ምን ነበር?
ጊዜው አንድ ቀን እንዲሆን እኛ ከዚህ በፊት በጣም ታግለናል። መጀመሪያ ቀኑ እንዲለያይ የተደረገበት ምክንያት አልገባንም ነበር። ሁሉም በተመሳሳይ ቀን መታደም ሲኖርበት መለያየቱ ችግር ያስከትላል። ለተለያዩ ግጭቶች፣ ለድምጽ ዝርፊያና ለመሳሰሉት ሊዳርግ ይችላል። በዚህ የተነሳ ለምርጫ ቦርድም ደብዳቤ አስገብተን በስተመጨረሻ ተገቢ ውሳኔ ተገኝቷል። በዚህም ደስተኞች ሆነናል።

ከሌሎች ፓርቲዎች የሚለያችሁ ዋና ዋና ነገር ምንድን ነው?
እኛ ዋናው አቋማችን የማትከፋፈል ኢትዮጵያ መገንባት አለባት የሚል ነው። ሕገ መንግስቱ የተከፋፈለች ናት ቢልም ለእኛ ኢትዮጵያ የማትከፋፈል ናት። አሁን ባለን ሕብረት ውስጥ ልዩ ጥቅም የሚባል ነገር አይገባም። የልዩ ጥቅም ጥያቄው እራሱ እኩልነትን ይጻረራል የሚል ጽኑ አቋም ነው ያለን። ከዚህ በተረፈ አዲስ አበባ የፌደራሉ መቀመጫ የሆነች ራሷን በራሷ የምታስተዳድር ክልል መሆን አለባት። ከአጠቃላይ ታሪኳም ሆነ ለፌደራሉ መንግስት ካላት አስተዋጽኦ አንጻር ራሷን የቻለች ክልል የመሆን መብት አላት የሚል መዋቅራዊ ጥያቄ አለን። ስልጣን ብንይዝ የምናደርገው አንዱ ይህን ነው። ከዚህ ባሻገር እኛ ቀኝ ዘመም ፓርቲ ነን። ከብዙ ፓርቲዎች የሚለየን ይህ ነው። አብዛኞቹ ማለት ይቻላል ግራ ዘመም ናቸው። እሴቶቻችንና ታሪኮቻችን በልማት ምክንያት መረሳት የለባቸውም ብለን እናምናለን። አሻራዎቻችን መጥፋት የለባቸውም የሚል ትግል ውስጥ ነው ያለነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com