የውጪ ጣልቃ ገብነት እና የኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታ

Views: 342

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ኹለት ከባድ ችግሮች ውስጥ ትገኛለች፤ አንደኛው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኹለተኛው ደግሞ 6ተኛው አገራዊ ምርጫ ነው። እነዚህ ሁለት ትላልቅ ጉዳዮችን ተከትሎ የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት በግልጽ እየታየ ይገኛል።

በእርግጥ ምርጫ በየትኞቹም የአፍሪካ አገራት ላይ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ችግር ሳይፈጥር አልፎ አያውቅም። በዚህ ጉዳይ ተደጋጋሚ ሃሳብ እየሰነዘሩ የሚገኙት የአውሮፓና የአሜሪካ አገራት ናቸው። እነዚህ አገራት እኛ ያልተካተትንበት ጉዳይ በአፍሪካ መፈጸም የለበትም የሚሉ ይመስላሉ። እልፍ ሲልም በጥብቅ የተሳሰረ ወዳጅነታቸው ለማሳየት በዓባይ ጉዳይ ከግብጽ ወግነው እንዲህ አድርጉ እንዲያ እንዳታደርጉ የሚል ቀጭን ትዕዛዝ በመስጠት ፈላጭ ቆራጭ እየሆኑ ነው። ከዚህ እልፍ ሲልም ማዕቀብ ሊጥሉብን ችግራችን ላይ እየተሳለቁ ይገኛሉ።

በያዝነው ሳምንት መነጋገሪያ ከሆኑ አጀንዳዎች ቀዳሚ የነበረው ይኸው የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ነው። የአሜሪካ ኤምባሲ አውጥቶት የነበረው መግለጫ በርካታ ቅሬታዎችን ሲያስነሳ ቆይቷል።
ከትግራይ የኤርትራ ጦር ጨርሶ እንዲወጣ፣ በወልቃይትና ራያ እያስተዳደሩት ያሉት የአማራ ክልል ታጣቂዎችና አስተዳደሮች እንዲወጡ የሚያዝ አይነት ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ በማውጣቷ ከመንግስት ደጋፊዎችም ሆነ ተቃዋሚዎችና ግለሰቦች ተቃውሞ ገጥሞታል።

ይህንን አነጋጋሪ ጉዳይ አዲስ ማለዳ በስፋት ዳሰሳ ያደረገች ሲሆን ከአንዳርጋቸው ጽጌ ተከታዩን ምላሽ አግኝታለች።
ፖለቲከኛና ጸሐፊ አንዳርጋቸው ጽጌ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ባንዲራ እስከ ማቃጠል እንደርሳለን የሚለው ንግግር ለምን እንደዚህ እንዳነጋገረ አልገባኝም ብለዋል። አንድ ግለሰብ ወይም ሕዝብ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመቃወም በማሰብ የተናገረው አድርጎ መውሰድ ይገባ ነበር። ባንዲራ መቅደድ እና ማቃጠል የሰላማዊ ሰው ትክክለኛ የትግል መገለጫ እና ቁጣ ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ ነው ብለዋል።

መግለጫውን ያወጡት ለኢትዮጵያ እርዳታ ሰጪ የሚባሉ የአውሮፓ አገራት፣ አሜሪካ እና ኢስያ አለም ላይ ካሉት ሃያላን መንግስታት መካከል ናቸው። እነዚህ አገራት ስለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት፣ ስለ ዲሞክራሲ እና ስለ ሰላም ማውራት የሚያስችል ምንም የሞራል አቅም የሌላቸው ናቸው ሲሉ አንዳርጋቸው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ላይ ያወጣው መግለጫ የራሷን ችግር በራሷ የመፍታት መብቷን የሚጋፋና ሉአላዊነቷን የጣሰ እንደሆነ አብራርተዋል።
ጉዳዩ መንግሥት ብቻ ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን በዋናነት በነጻነትና በጀግንነት በኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ነው። ድርጊቱ ኢትዮጵያዊያንን የመናቅ፣ ታሪካቸውን የመዘንጋትና ያልተገባ አመለካከት መኖሩን ያሳዩበት አጋጣሚ መሆኑን ነው አንዳርጋቸው የተናገሩት።

ምዕራባዊያኑ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ የሚያሳድሩትን ተጽእኖ እና የሉአላዊነት ጉዳይ ሕዝቡ ሊቃወም ይገባል።
“ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ቆመው ክብራቸውንና አንድነታቸውን የሚጋፉ አካላትን በማውገዝ በአገራቸው ጉዳይ የማይደራደሩ መሆናቸውን በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት፣ የአፍሪካ ህብረትና የኢጋድ መስራች ከመሆኗ ባለፈ በማንኛውም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብታ ባታውቅም በክፉ ቀን ከጎኗ የሚቆም ወዳጅ አልነበራትም ብለዋል።
አሜሪካና መሰሎቿ የሚያስተላልፉት መልዕክት ከራሳቸው ጥቅም አኳያ የተቃኘ መሆኑን በመጠቆም መስማት የሚመርጡት የፈለጉትን ጉዳይ ብቻ ነው ብለዋል።
የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ምስረታው አገረ መንግሥቱን ያላከበረ ከሆነ መደፋፈር ስለሚሆን በወጣው መግለጫ ልክ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአገራዊ ጥቅም ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነትም ሆነ ውድድር ሊኖር እንደማይገባና በዚህ ጉዳይ ላይ “የፖለቲካም ሆነ የኃይማኖት ልዩነት ሳይገድበን በጋራ መቆም አለብን” ብለዋል።
ከኹለተኛው ዓለም ጦርነት ጀምሮ በዓለም ላይ የተፈጠሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና የዲሞክራሲ ስርዓት የተዛቡባቸው ሁኔታዎች በሙሉ እነዚህ ሀያላን የሚባሉ አገራት ጣልቃ የገቡባቸውና የተለያዩ አገር አምባገነኖችን በመደገፍ አገርን ያፈረሱባቸው እንደሆኑ ይታወቃል።

እንደ አንዳርጋቸው ገለጻ ከሆነ አገራቱ ለኢትዮጵያ እርዳታዎችን እንዳያቋርጡ መንግስት ለመቃወም ይፈራል።
ስለዚህ እኛ መብታችንን ተጠቅመን እንቃወማለን ብለዋል። በተጨማሪም ግንቦት 13 አርብ ከ10 ሰዓት እስከ 11 ሰዓት በውጪ እና በአገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በየአካባቢያቸው ‹‹እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ›› በሚል ባንዲራ የሚውለበለብበት መርሃ-ግብር ተካሂዷል።

አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በቀጣይ ሳምንት ትላልቅ ሰልፎችን በማደራጀት የምንጓዝበት ሁኔታ ይፈጠራል ሲሉ አንዳርጋቸው ገልጸዋል።
የሰልፉም ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ የውጭ አገራትን የሚያወግዝ ንቅናቄ ነው።

የንቅናቄው መርሃ ግብር ‘ብሔራዊ ክብር በሕብር’ በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ሲሆን ከኢትዮጵያ ሲቪክ ማኃበራት፣ አርቲስቶችና ከማሕበረሰብ አንቂዎች የተውጣጡ አካላት እንደሚያስተባብሩት ታውቋል።

በንቅናቄውም በመላው አለም ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ዲጂታል የፊርማ ማሰባሰብ ፕሮግራም ይካሄዳል ተብሏል።
አስተባባሪዎቹ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞችና የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሉአላዊነትን የሚዳፈሩ መግለጫዎች አንዳንድ የውጭ አገራት እያወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት፣ የሕግ የማስከበር ዘመቻና የዜጎች መብት የሆነውን የምርጫ ስርዓት አስታከው ጫና ለመፍጠር እየሰሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም አሁን የምናየው ለዘብ ያለ ይምሰል እንጂ የቅኝ ገዥነት ቀጣይ አመለካከት ነው የሚሉት ደግሞ ፖለቲከኛ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)ናቸው። እነዚህ አገራት በቅኝ ግዛት ጊዜ የነበረውን የበላይነታቸውንና አምሮታቸውን ሳይወጡ በዛው ስሜት ውስጥ ያሉ ይመስላሉ ሲሉ አረጋዊ ተናግረዋል።

አሁን ኢትዮጵያን ለማስፈራራት እና የግብጾችን ዓላማ ለማሳካት፣ የህዋሓት ጁንታው ዓላማን ከግብ ለማድረስ የሚያደርጉት ማስፈራሪያ ነውም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ግድቡንም ብቻ ሳይሆን ነጻነቱን የሚያስከብር ካስፈለገም መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀቱን በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በእውቀት በየቀኑ እያደረገ ካለው አስተዋጽኦ መታወቅ ይኖርበታል ብለዋል። ስለዚህ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ማንም አገር ወዳድ የሆነ ሰው የማይቀበለው እና ወዳቂ ሀሳብ ነው ብለዋል።

እንደ አረጋዊ ገለጻ ከሆነ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ የሚያስፈልገው አንድነታችን ነው። በሚረባውም በማይረባውም እየተለያየን ውስጣችንን ማዳከም የለብንም። የውስጥ ችግራችንን እውቀት በተሞላበት ውይይት መፍታት እንችላለን።

የውስጣችንን ችግር ከፈታን የውጭውን ተጽእኖ በቀላሉ መፍታት እንችላለን። የውስጣችንን ትናንሽ ችግሮች አጉልተን የምናሳይ ከሆነ እና አላስፈላጊ ተቃውሞዎችን እየፈጠርን እና ለባዕዳን ሃይሎች በር እየከፈትን ከምንሄድ በጋራ መግባባት ይኖርብናል። ጊዜው ለውጥ የተደረገበት በመሆኑ ማንም ሰው ተደራጅቶም ሆነ ሳይደራጅ ሀሳቡን መግለጽ እና መናገር ይችላል ብለዋል።
ስለዚህ ለአገር ና ለሕዝብ የሚጠቅም ጠንካራ ሀሳብ ያለው ይዞ መጥቶ ደካማውን ሀሳብ እያሸነፈ በአንድነት እየተባበርን የውጭውን ተጽእኖ መቋቋም ቀላል ነው።

በተለያዩ መንገዶች ሰልፎች መካሄዳቸው በራሳቸው መፍትሄ አያመጡም። ነገር ግን ሰልፎቹ የአንድነታችን ምልክት ሆነው ከታዩ፣ የውጭ አገራት የአገር አንድነት እና ሉዓላዊነት ላይ እንዲያተኩሩ ያደርጋል ሲሉ አረጋዊ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

የአንድነት ሰልፎች ከተካሄዱ ሀሳቦችን በግልጽ በመናገር የጋራ መግባባት መፍጠር ይቻላል።
ይህ ደግሞ ለሚቀናቀኑ ሀይሎች መልዕክት እና ማስጠንቀቂያ ይሆናቸዋል። ኢትዮጵያውያን የአገራችንን ክብር ለማስጠበቅ ማንኛውም መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ ነን። እነርሱ ደግሞ ስግብግበነት ዓላማ ይዟቸው ሲመጡ ሽንፈት ማከናነብ ይኖርብናል ሲሉ አረጋዊ ገልጸዋል።

የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመቃወም የምናደርገው የጋራ መግባባት ለአገሪቱ ሰላም መፈጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር ናት፤ ያሉት አረጋዊ የውስጥ ችግሮቿን በራሷ ትፈታለች እንጂ የሕዝቦቿን እና የመንግሥትን ሉዓላዊነት የሚጥስ የውጭ ኃይል ጣልቃ ገብነት ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ስለ ኢትዮጵያ የማይመለከተውን ጉዳይ ይዞ ከማላዘን ይልቅ፣ ለዜጎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፎችን በማሰባሰብ ሊተባበር ይገባልም ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com