‹‹ ወታደር ከመሆን ሴት መሆን ይከብዳል ››

Views: 192

ሰላም ማጣት ሁሉንም ያውካል። የሰላም ጥቅም ግልጽ የሚሆነውም ሲደፈርስ ሳይሆን አይቀርም። ታድያ ሰላም ሲጠፋ፣ ከባድ ግጭትና አለመረጋጋት ሲኖር የሰዎች የመንቀሳቀስና በደኅና ወጥቶ የመግባት መብት ይነፈጋል። መብትን ከመነፈግ በላይ ደግሞ ጭራሽ ጥቃት ይደርሳል፤ ተሸሽገው ካሉበት፣ ተጠልለው ከሚገኙበት ዘው ብሎ ይገባል።

ጾታዊ ጥቃት አንዱ በግጭትና አለመረጋጋት መካከል የሚከሰትና የማይጠፋ ኹነት እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል። በአዘቦቱም የአስገድዶ መድፈር ዜና እንግዳ ባይሆንም፣ በግጭት ወቅት ግን ይከፋል፤ ይበረታል። ምክንያቱም ግርግር ነውና አስጣይ፣ ተከላካይ፣ ዳኛና ጠበቃ አይኖሩም። ድርጊቱም በማኅበረሰብ ውስጥ እኩይ ምግባር ካለው ጀምሮ በጸጥታ አስከባሪነት ለሕዝቡ አለሁኝ እስከሚል ወታደር ድረስ፣ በማናቸውም ሊፈጸም ይችላል።

የዓለም መንግሥታትም ቀደም ብሎ ከሆነውና ከብዙ አገራት ልምድ ተነስተው ጾታዊ ጥቃት እንደ ጦር መሣሪያ እያገለገለ ነውና ልብ በሉ ካሉ ዓመታት አልፈዋል። ይህ የሚደርስባት የማይመስላት ኢትዮጵያ ጾታዊና ወሲባዊ ጥቃት እንደ ጦር መሣሪያ ውሏል፣ አልዋለም ብላ አጥርታ አታስቀምጥ እንጂ፤ ጥቃቶች በጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም በተለያዩ ግለሰቦች እየተፈጸሙ እንደሆነ በተለያዩ ተቋማት የወጡባት ዘገባዎች ያመላክታሉ።

የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ከዚህ ጋር በተያያዘ የተሠሩ የተለያዩ ጥናቶችን እና ዘገባዎችን በማጣቀስ ከግጭት ጋር በተገናኘ የደረሱ ጾታዊ ጥቃቶችን እና እነዛን ለመከላከል ወደፊት ይወሰዳሉ ስለተባሉ እርምጃዎች በማንሳት ጉዳዩን የአዲስ ማለዳ ሐተታ አድርጋዋለች።

ፊሊፕ ጆርጅ ዚምባርዶ የተባሉ አሜረካዊ የሥነ ልቦና ባለሞያ እና በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ኤምሬተስ ፕሮፌሰር፣ ‹ዘ ሉሲፈር ኢፌክት› የተሰኘ በማረሚያ ቤቶች የተደረገ ጥናትን መሠረት አድርጎ የተዘጋጀና ብዙ ያወዛገበ መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ አስፍረዋል፤ ‹‹በእናንተ ላይ ጥይት አናባክንም። አስገድዶ መድፈር እንፈጽምባችኋለን፣ እሱ ይከፋባችኋል።››
ዘ ሰርክል የተባለ ድረገጽ ያስነበበው አንድ ዘገባ ደግሞ እንዲህ ሲል ይጠቅሳል፤ ‹‹ዘመናዊ በሚባለው በአሁኑ ወቅት ወታደር ከመሆን ይልቅ ሴት መሆን በእጅጉ ከባድ ነው››

በግጭትና አለመረጋጋት እንዲሁም ጦርነቶች መካከል፣ ሴቶች በማንኛውም ሰው ላይ የሚደርሰው ተጽእኖ የሚያርፍባቸው ከመሆኑ በተጨማሪ ለጾታዊ ጥቃት ተጋላጭ ናቸው። ከግጭት በኋላ የሚቀበሉት ቤተሰብን የመሰብሰብና አስፈላጊውን ሁሉ የማሟላተ አስገድዶ መድፈር ይደርስባቸዋል፣ ልጆቻቸው ሲገደሉም ሊያዩ ይችላሉ።

ጦርነትና የሴቶች ጥቃት
በቀደመው ጊዜ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ይካሄዱ በነበሩ ጦርነቶችና ግጭቶች መካከል በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃት ታስቦበት የሚፈጸም ሳይሆን የጦርነት አንድ የጎንዩሽ ጉዳት ተደርጎ ይወሰድ ነበር።
በ1990ዎቹ በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በቦስንያ በነበረ ግጭት ነው በተለይ ከአስገድዶ መድፈር ጋር በተያያዘ የወጡ ዘገባዎች በዝተው የተገኙት። ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ተጠልለው በሚገኙባቸው ካምፖች ውስጥ የተሰሙትን የጥቃት ታሪኮች የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ እንደ ‹የጦርነት የጎንዮሽ ጉዳት ብቻ› ሊያልፈው አልቻለም። ጥቃቶቹ እንደውም በተጠና መንገድና ይሁነኝ ተብሎ የተፈጸሙ መሆናቸው ተነገረ።

የተባበሩት መንግሥታት ቀደም ብሎ በነበሩ ግጭትና ጦርነቶች መካከል የደረሱ ጾታዊ ጥቃቶችን መለስ ብሎ ዳስሷል። በዚህም አካሄዱን ለመለየት አስቸጋሪ ይሁን እንጂ ግጭቶችን ተከትለው ከሚወጡ መደበኛ ዘገባዎች መካከል አስገድዶ መድፈር አንዱና ሁሌም ያለ መሆኑ እርግጥ ነው ሲል አስታወቀ። በኋላም በየመን፣ ደቡብ ሱዳን እና ኢራቅ የሴቶች ስደትና ሽሽት እውነትም በሴቶች ላይ ጥቃት ማድረስ እንደ አንድ የጦርነት መሣሪያ እንደሚቆጠር አመላካች ሆነ።

ታድያ እነዚህ ከግጭት ጋር የተገናኙ ጾታዊ ጥቃቶች በሴቶች ላይ ጎልተው ይታዩ እንጂ በወንዶችም ላይ የሚደርሱ መሆናቸውን ‹ግሎብ 23› የተሰኘ ድረገጽ ባስነበበው ጽሑፍ አትቷል። ለዚህም የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክን ጨምሮ በሶሪያ፣ ስሪላንካ፣ ፔሩ እና ቦስንያ ተከስተው የታዩ ጾታዊ ጥቃቶች ማሳያ ናቸው።

እነዚህን በተለያዩ አገራት የተፈጠሩ ክስተቶችን ተከትሎ በ2002 ዓለማቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ጾታዊ ጥቃት የጦርነት እንዲሁም በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው ብሎ አወጀ። ይህም የሆነው ዓለማቀፍ ፖሊሲዎች ጾታዊ ጥቃቶች እንደ ጦር መሣሪያ እያገለገሉ መሆናቸውን ካረጋገጡ በኋላ ነው። የተባበሩት መንግሥታትም በ2008 መደበኛ በሆነ መንገድ አስገድዶ መድፈር እንደ ‹ጦር መሣሪያ› እየዋለ እንደሆነ አስታወቀ።

በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሴራሊዮን የነበረውና ከዐስር ዓመት በላይ በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ብዙዎች የተፈናቀሉበት፣ ከባድ ጉዳትን ያስተናገዱ እንዲሁም የሞቱበት ከመሆነኑ በተጨማሪ፣ በአገሪቱ ካሉ ሴቶች አንድ አራተኛ የሚሆኑት ሴቶች ተደፍረዋል። በተጓዳኝ በሩዋንዳ ለዓመታት በዘለቀ የእርስ በእርስ ግጭት ከ250 ሺሕ በላይ ሴቶች ተደፍረዋል። በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክም በ2011 በነበረው ግጭት በየአንድ ሰዓት 48 ሴቶች አስገድዶ መድፈር ይደርስባቸው ነበር።

ለምን?
ለምን አስገድዶ መድፈር እንደ ‹ጦር መሣሪያ› እንዲያገለግል ሆነ? መነሻው ምንድን ነው? ግርግር ለሌባ ስለሚያመች ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለ? እነዚህ ጥያቄዎች በብዙዎች አእምሮ ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ናቸው።

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በጦርነት ወቅት የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች ይልቁንም አስገድዶ መድፈር እንደ ኹከት መፍጠሪያ ይቆጠራል። አሸባሪዎችና ታጣቂዎች እንዲሁም የባላንጣ ወገን ወታደሮች ሴቶችን አስገድዶ በመድፈር ሕዝብን ያሸብራሉ።

ዶውን ስቴቨንሰን የተባሉ በዩናይትድ ኪንግደም የሊድስ ዩኒቨርሲቲ መምህር የጾታ ጥቃት ለምን የጦር መሣሪያ ሆነ በማለት ይጠይቃሉ። ወይዘሮዋ መልሰው ለዚህ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ ‹‹አስገድዶ መድፈር የሚያስከትለው ዘርፈ ብዙ ተጽእኖ አንድን ተጠቂ ብቻ ሳይሆን ቤተሰብና ማኅበረሰብን ሊከፋፍል የሚችል ኃይል ይሰጠዋል።›› ይላሉ።

አስገድዶ መድፈር እንደ ሥልታዊ መንገድ እየተወሰደ ነው ያሉት መምህሯ፣ ይህም የሆነው ጥቃቱ በማኅበረሰብ ውስጥ ዘላቂ የሆነ ኪሳራን እንደሚያሳድር ስለሚታወቅ ነው ብለዋል። የሚያስከትለው ዘላቂ የሆነ ድንጋጤና ዝለትም ጥቃት በደረሰባቸው ሴቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ ሕይወት በሚቀርቧቸው ወንዶች እና በዙሪያቸው ባለው ማኅበረሰብና ለቀጣይ ትውልድ ጭምር የሚተርፍ ነው።
እኚሁ መምህርት የሩዋንዳን የ1994 ዘር ጭፍጨፋ መነሻ አድርገው በሠሩት ጥናት፣ የተጠና እና ወታደራዊ የሆነ አስገድዶ መድፈር ዘርን ለማጥፋት ተፈጽሟል ብለዋል።

ጥቃቶችን የሚፈጽሙ አጥፊዎች በባህል ሴቶች ያላቸው ክብር እንዲሁም የወንዶች የከለላነት/ጠባቂነት እሴት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳርፋሉ። ለምሳሌ በሩዋንዳ በነበረው ግጭት ወላጆችና የቤተሰብ አባላት ባሉበት እያዩ አስገድዶ መድፈር፣ እንግልት እና ግድያ እንዲፈጸም ያደርጋሉ። ይህንንም የሒውማን ራይትስ ወች በ1996 ባወጣው ዘገባ ያስነበበው ነበር።

ይኸው ዓይነት ጥቃት በኹለተኛው የዓለም ጦርነት ላይ የዋለ ሲሆን፣ የጃፓን ኢምፔሪያል ወታደር ሠራዊት በዐስር ሺሕ የሚቆጠሩ የቻይና ሴቶችን በቡድን ሆነው ይደፍሩ ነበር። የቤተሰብ አባላት እርስ በእርስ ግንኙነት እንዲያደርጉ በማስገደድ በግድያ በማስፈራራት፣ በቤተሰብ አባላት መካከል ያለውን ትስስርና አንድነት እንዲሁም ማኅበረሰቡን በጠቅላላ ለመከፋፈል ተጠቅመውበታል።
ታድያ ጥቃቱን የሚፈጽሙት አጥፊዎች በዚህ ተግባራቸው ጥቃት የሚደርስባቸውን ሴቶች ማሸማቀቅና በሚዋጉት ኃይል ላይ የበላይነትን እንዳሳዩ ይቆጥራሉ። ያም ብቻ ሳይሆን ሴቶችን ይጠብቃሉ የሚባሉ ወንዶች ማለትም ባል፣ አባት ወይም ወንድም ላይ የበላይነታቸውን ማሳየትና እንዲያፍሩ ማድረግ ግባቸው ነው።

ሌላው በኮንጎ የነበረውን እንዲሁም በሌሎችም ጦርነትና የእርስ በእርስ ግጭት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች የተከሰተውን መነሻ በማድረግ ጥናት ያዘጋጁት ኤሪክሰን ባዝ እና ማሪያ ስተርን የተባሉ ሰዎች እንደጠቀሱት፣ ይህን መሰል ጾታዊ ጥቃቶችን በቀላሉ ‹የታሰበበትና የጦርነት ዓላማ ያለው› ብቻ ተብሎ መጠቀስ የለበትም፣ ከዛም በላይ ውስብስብ ነው ይላሉ።

ለኹለቱ ሰዎች ‹አስገድዶ መድፈር እንደ ጦር መሣሪያ› የሚለው አነጋገር ችግር የሚያመጣ ነው። ምክንያቱም በዓለማቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን ያገኘ በመሆኑ በወታደራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በመደበኛነት ከላይ ወደታች እንደሚወርድ አቅጣጫ ሊቆጠር ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

በማሳያነት የሚያነሱትም በሩዋንዳ የሆነውን ነው። የጾታዊ ጥቃት በወታደርና ፖለቲካ አመራሮች ቀጭን ትዕዛዝ እየተላለፈ የሚፈጸም ድርጊት ነበር ይላሉ። በአንጻሩ ግን ከላይ እንደ ወታደራዊ አቅጣጫ ባይወርድ እንኳ በወታደር ቤት ያለ የአሠራርና የስርዓት መፍረስ ይህን ሊያስከትል እንደሚችል ሳይጠቅሱ አላለፉም።

በድምሩ የተጠቀሱት ጥናቶችና የባለሞያዎች ዕይታዎች እንደሚያስረዱት፣ ተዋጊዎች ጠላታችን ባሉት ወገን ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃትን የሚፈጽሙት ለምን ነው ከተባለ፤ መልሱ የጥቃቱ ተጽእኖ አንዲት ሴት ላይ ብቻ ሳይሆን ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ እንዲሁም አገር ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ በሚገባ የተረዱ በመሆናቸው ነው።

ይህ ታድያ ጦርነት ካበቃም በኋላ ዘልቆ የሚቀጥል ነው። ያልተፈለገ እርግዝና፣ በግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችና ከጦርነት በኋላ በሚኖረው ማኅበረሰብ ውስጥ መገለል ይኖራል፤ ይከሰታል።

በኢትዮጵያ በተከሰቱ ግጭቶችስ?
የኢፌዴሪ መንግሥት በትግራይ ክልል የ‹ሕግ ማስከበር› እንቅስቃሴ ከጀመረ ግማሽ ዓመት እየተጠጋ ነው። ይህም በጥቂት ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ ቢገመትም እያደር እየበረታ ከባድ አለመረጋጋት ተከስቷል። በዚህም ላይ የጎረቤት አገር ኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው ገብተው ትግራይ ክልል በብዛት መገኘታቸው ሁኔታውን አስቸጋሪ፣ ውስብስብና ከባድ አድርጎታል።
ይህን ተከትሎ ከደረሱ ውድመቶች፣ ከጠፉ ሕይወቶችና ሊደርሱ ይችላሉ ተብለው ከሚጠበቁ እንደ ረሀብ ከመሰሉ ተጨማሪ ጥፋቶች ጎን ለጎን፣ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች አሳሳቢ ሆነዋል። የተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በትግራይ ክልል ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው፣ ተገድደው የተደፈሩ፣ ይህን መሰል ጥቃት ቤተሰባቸው ባሉበት እየተመለከቱ መፈጸሙን የተናገሩ ሴቶችን አቅርበዋል። ይህም በወታደሮች (በኢትዮጵያ እንዲሁም በኤርትራ ወታደሮች) የተፈጸመ እንደሆነ ተጠቅሷል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የወንጀል ምርመራን በሚመለከት ዘገባ አውጥቶ ነበር። ይህን እንደማሳያ ብናነሳ፣ በዚህ ዘገባውም የአስገድዶ መድፈር ወንጀልን በሚመለከት በአጠቃላይ 116 ተበዳዮች ለፖሊስ ቃላቸውን ሰጥተዋል ሲል አስታውቋል። በወንጀሉ የተሳተፉ የፌዴራል ፖሊስ እና መከላከያ አባላት ተለይተው ጉዳዩ በክልሉ ዐቃቤ ሕግ እንዲመረመር እንዲሁም የሠራዊት አባላት የሆኑት በወታደራዊ ግዳጅ ላይ እያሉ የፈጸሙበት በመሆኑ በወታደራዊ ፍርድ ቤት እንዲታይ ተላልፈው ተሰጥተዋል ብሏል።

የተባበሩት መንግሥታትም ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆነ ዘገባን ይፋ አድርጓል። ነገሩ ‹ጥቃቶች የሚፈጸሙት መለዩ በለበሱ የጸጥታ ኃይሎች ነው› የሚለውን መግቢያ አያድረገው እንጂ፣ የጸጥታ ኃይሎች ጾታዊ ጥቃት መፈጸማቸው ጉዳዩን የጦር ወንጀል ያደርገዋል የሚል ነው። በዘገባው የሰብአዊ የሰብአዊ እርዳታ ቢሮ (ኦቻ) በኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ክልል በመሚደረገው ጦርነት ጾታዊ ጥቃት እንደ ጦር መሣሪያ እያገለገለ ነው ማለቱን የጀርመን ድምጽ (DW) አስነብቧል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው እንደተናገሩት፣ በክልሉ የመብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙ አውስተው ምርመራ ተደርጎ ጥፋተኛ ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል። አያይዘውም ወሲባዊና ጾታዊ ጥቃቶች መፈጸማቸውን የሚያሳዩ ዘገባዎች እንዳሉና፣ የመከላከያ አባል ሆኖ ይህን ጥፋት ያደረሰ ወታደር በሕግ እንደሚጠየቅ ገልጸዋል።
አሁንም ግን ቁጥሮች በግልጽ እየተነገሩ አይደሉም። ያም ብቻ ሳይሆን ትግራይን ጨምሮ መፈናቀል ባለባቸው አካባቢዎች እየደረሱ ያሉ ጾታዊ ጥቃቶች እንደ ጦር መሣሪያ እያገለገሉ ስለመሆኑ እንዲሁም የጦር ወንጀል ስለመፈጸሙ እንዲህ ነው ብሎ የሚናገር የለም። ‹‹የደንብ ልብስ የለበሱ አካላት ጥቃቱን ፈጽመዋል ተብሏል›› ይባል እንጂ፣ እንደውም ‹‹የወታደር ልብስ የለበሱት ሕወሓት ከእስር የፈታቸው እስረኞች የወታደር ልብስ ለብሰው ነው›› የሚል ነጥብም ሲነሳ ተሰምቷል።

ሁሉም ግን የጠራ አይደለም። ስለሴቶች የሚሠሩ ማኅበራት፣ በሴቶች ሥም የተቋቋሙ ተቋማት፣ ከመረጃ እጥረት አልያም በአንዳች ምክንያት በጉዳዩ ላይ ሐሳባቸውን ሲሰጡ አይሰማም፤ ሐሳብ ከመስጠት የተቆጠቡም ይመስላል።

ይህን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በሚገባ የተረዳው ይመስላል። መጋቢት 20 እና 21 በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ የቤይጂንግ ፕላትፎርም ተግባራዊነትን የ26ኛ ዓመት ጉዞውን በሚመለከት የሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ያዘጋጀው መድረክ ነበር። በዛ ላይ የተገኙት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በስብሰባው ቢደረግ ብለው ካነሷቸው ነጥቦች መካከል አንዱ ከዚሁ ጋር የተገናኘ ነበር።
በግጭት መካከል ወድቀው በጸጥታ አካላትም ይሁን በማንኛውም ሰው ጥቃት የሚፈጸምባቸውና ለዚህ ሰለባ የሆኑ እህቶች/ሴቶች አሉ ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ሕዝብ ድርጊቱን በአንድ መንፈስና ድምጽ ሆኖ እንዲያወግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

ግጭት በሚኖር ጊዜ የሕግ ስርዓት ስለሚፈርስ ጾታዊ ጥቃቶች በጸጥታ ኃይሎች ብቻ ሳይሆን ግርግርን ለመጠቀም በሚሹ ሰዎችም ሊፈጸሙ እንደሚችሉ አውስተዋል። በተጨማሪም የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች የሚጠለሉባቸው ቦታዎች ወይም ጣቢያዎች (Safe House) ጥበቃ የሚያገኙበትና ደኅንነት እንዲሰማቸው ሊያደርግ የሚገባ ነው። ስለዚህም በማናቸውም ዓይነት ሁኔታ ቢሆን በወንድ ጸጥታ ሠራተኞች፣ በወንድ ፖሊሶች ሊደፈሩና ሊፈተሹ እንደማይገባ ጥሪና መልዕክት እንዲተላለፍ አሳስበዋል።

‹‹ይህን የምለው ስላጋጠመን ነው።›› ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ‹‹ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች የተጠለሉበት ቦታ ወንድ የጸጥታ ሠራተኞች ገብተውበታል። ወንጀል ተፈጽሞ ከሆነ ሊፈተሸ ቢገባ እንኳ መፈተሸ ያለባቸው በሴት ሠራተኞች ሊሆን ይገባል እንጂ እንዲገቡ ሊፈቀድ አይገባም።›› ብለዋል።

ይህን በትግራይ ክልል ከባድ የሆነ ግጭትና ወታደራዊ እንቅስቃሴ በመኖሩ አነሳን እንጂ፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተመሳሳይ የሴቶች ላይ ጥቃት ይፈጸማሉ፤ ተፈጽመዋልም።

ተግባራዊነቱን የምንናፍቀው አዲስ ጅምር
የኢፌዴሪ የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር በዐስር ዓመት የልማት እቅዴ መሠረት የሴቶችን ጥቃት ለማስቆም የሚረዳ ቋሚ አሠራር ስርዓት ለመዘርጋት ግብረ ኃይል ማቋቋም ይገኝበታል ብሏል። ይህም በቋሚነት የሴቶችን ጥቃት የሚከላከል ግብረ ኃይል ይሆናል ነው የተባለው።

ታድያ በግንቦት ውር መጀመሪያ ላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህን እቅድ የማሳካት ጉዞውን በስምምነት ፊርማ ጀምሯል። ፊርማው በፖሊስ ዩኒቨርሲቲ እና የተባበሩት መንግሥታት ሕዝባዊ ፈንድ (The United Nations Population Fund-UNFPA) ጋር ተፈራርመዋል። ይህመ ፊርማ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ለጾታዊ ጥቃቶች ምላሽ ለመስጠትና ለመከላከል ሲሆን፣ ይህንን በብቃት ሊያከናውኑ የሚችሉ የጸጥታ ኃይሎችን ለማሰማራት የሚያስችል ነው ተብሏል።

የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ መንግሥት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን ያለመታገስ መርህ እንዳለው አንስተው፣ ጾታዊ ጥቃትን በመከላከልና ምላሽ በመስጠት በደንብ የሠለጠነ ልዩ አቅምና ችሎታ ያለው የፖሊስ ኃይል ያስፈልጋል ብለዋል።

ታድያ በዚህ የስምምነት ፊርማ መሠረት የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፖሊሶች በዛ መልክ የሠለጠኑ እንዲሆኑ ለማስቻል ያገኘውን ድጋፍ ተጠቅሞ ወደሥራ ያስገባል። ሥልጠናው የሚቀድም ይሆናል የተባለ ሲሆን፣ አስፈላጊ ግብዓት እንዲሟላ ለማስቻል ዩ.ኤን.ኤፍ.ፒ.ኤ. ድጋፍ አድርጓል። ለዚህ የጸጥታ ኃይሎች ሥልጠና እና ማሰማራት ተግባር እንዲውል አምስት ሚሊዮን ብር በድጋፍ ተገኝቶ መመደቡንም ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።

የሥልጠናው ዓላማ ታድያ ፖሊስ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለመመከት እንዲቻል አቅም እንዲያጎለብት እንዲሁም ተያያዥና ወቅታዊ ዓለማቀፍ ሁኔታዎችን እንዲረዳ ማድረግ ነው።
በመድረኩ ሥልጠናውን በሚመለከት አጠር ያለ ማብራሪያ የሰጡት የሚኒስትሯ አማካሪ ታምራት ዘላለም (ረዳት ፕሮፌሰር) ሲናገሩ፣ ጾታዊ ጥቃት የትም የሚፈጸም ሆኖ ሳለ ልዩነቱ ምላሽ አሰጣጥ ላይ ነው ብለዋል። ጾታዊ ጥቃት ከደካማ ማንነትና ከመጥፎ መንፈስ የሚመነጭ ነው ያሉት ታምራት፣ ስምምነቱን ተከትሎ ይህን ለመከላከል ኹለት አካሄዶች ተግባራዊ ይሆናሉ ብለዋል።

አንደኛው አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች የሚተገበር ሲሆን ሌላው መረጋጋት በሌለባቸውና ጾታዊ ጥቃቶች በብዛት የሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ነው። ኹለት ምዕራፍ እና ብዙ ደረጃዎች አሉት ያሉ ሲሆን፣ የመጀመሪያው በዋናነት በትግራይ ክልል እንዲሁም በቀጣይ በቤኒሻጉል የሚተገበር ነው ብለዋል። መደበኛና ማኅበረሰብ ዐቀፍ ፖሊሶች ሥልጠናውን እንዲወስዱ እንደሚደረግና በሂደት በፖሊስ ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ስርዓት ውስጥ እንዲካተት መታሰቡንም ነው ያነሱት።

ከዚህ በእርግጥ ለውጥ እንዲመጣ የሚጠበቅ ነው። ተጽፈውና ተፈርመው የአቧራ ካባ እንደለበሱ ሰነዶች ሳይሆን ይህ ስምምነት ተግባራዊነቱ ተጨባጭ ከሆነ፣ ምንአልባት ለውጥ ሊታይ ይችላል። በተለይም አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ይህን ማጽናትና ሴቶችን ከጥቃት መጠበቅ ያስፈልጋል። አሁን በግጭት መካከል ሆነው ግጭቱ ከሚፈጥርባቸው ሰዋዊ ስሜት፣ ጭንቀትና አለመረጋጋት ባለፈ ለጾታዊ ጥቃት ሰለባ ሆነው ተጨማሪ ጠባሳ እያረፈባቸው ላሉ እህቶች፣ እናቶችና ሴት ልጆች ግን አቤት ማለትና ድምጻቸው መሆን፣ ድርጊቱን ማውገዝም ያሻል።


ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com