የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ መራዘም ምን ይዞ ይመጣል?

Views: 182

ኢትዮጵያ ሥድስተኛ አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፋ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። አሁን ላይ ሥድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ አብዛኛዎቹ ሥራዎች የተከናወኑ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያች የምርጫው ዋና አስተናባሪ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በገጠሙት የቅደመ ምርጫ መጓተቶች ምክንያት ምርጫውን ቀድሞ ቀጠሮ በያዘበት ቀን ማካሄድ እንደማይችል ባሳለፍነው ሳምንት ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ነው።

ሥድስተኛው አገራዊ ምርጫ የሚካሄድበት መደበኛው ጊዜ 2012 የነበረ ቢሆንም፣ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ወደ 2013 ተራዝሞ መቆየቱ የሚታወቅ ነው። ከ2012 ወደ 2013 በኮቪድ 19 የተራዘመው ምርጫ በአገር አቀፍ ደረጃ ግንቦት 28/2013 እንዲሁም በአዲስ አበባና እና በድሬድዋ ከተማ አስተዳደር ሰኔ 5/2013 እንድካሄድ በኢትዮጵያ ብሐየራዊ ምርጫ ቦርድ ቀን ተቆጥሮለት ነበር።
ይሁን እንጅ ቦርዱ ምርጫውን በተያዘለት ጊዜ ማለትም ግንቦት 28 እና ሰኔ 5/2013 ለማካሄድ የሚስችል ቅድመ ዝግጅት አለመጠናቀቁን ተከትሎ ምርጫውን በሦስት ሳምንታት እንደሚራዘም ባለፈው ሳምንት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በነበረው ውይይት አስታውቋል። በመሆኑም ግንቦት 28 ቀን ሊካሄድ የነበረው አገራዊ ምርጫ ሰኔ 14/2013 እንደሚካሄድ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ቦርዱ የድምጽ መስጫ ቀኑን ያራዘመው የድምጽ መስጫ ቀን ከመድረሱ በፊት ቀድመው መጠናቀቅ ያለባቸው የቅድመ ምርጫ ተግባራት በታቀደላቸው የጊዜ ሰሌዳ አለመጠናቀቃቸው መሆኑን ገልጿል።
ለምርጫው መራዘም ምክንያት የሆነው አልተጠናቀም የተባለው ቅድመ ምርጫ ሂደት፣ በተለይ የጸጥታ ችግር ባለባቸው እና ተፈናቃይ ዜጎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የምርጫ ቁሳቁሶች አለመድረስ፣ የፖለተካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ አለማካሄድና የመራጮች ምዝገባ በተያዘለት ጊዜ አለመካሄዱ ጎልቶ የሚታይ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል።

አሁንም ድረስ ችግሩ ያልተፈታ እና በተራዘመው ጊዜም ሊፈታ እንደማይችል ስጋታቸውን የሚገልጹ አካላት አሉ። በተለይ የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተንቀሳቅሰው ሥራቸውን መስራት ባልቻሉበትና ሕዝቡ የምርጫ ድባብ ባላየበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ ተገቢ አይደለም የሚሉ አካላትም አሉ።

የምርጫ ጊዜው መራዘም የተጓተተውን የምርጫ ቅደመ ሂደት ያሻሽለዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የሚገልጹም አሉ። የምርጫው መራዘም በተለይ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አከባቢዎች ተገቢ መሆኑን የሚያምኑት የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ መብራቱ አለሙ(ዶ/ር) ናቸው።

መብራቱ እንደሚሉት ከሆነ በተለይ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ዜጎች ተፈናቅለው እና አሁን ላይ የጸጥታ ችገሩ በተባባሰበት ሁኔታ ምርጫ ማድረግ የሚስችል ሁኔታ አለመኖሩን በመግለጽ መራዘሙ ተገቢ መሆኑን ያምናሉ። ይሁን እንጅ ተንቀሳቅሶ ሥራዎችን መስራት ካልተቻለ የምርጫ መራዘም ብቻውን ለውጥ አንደማያመጣ ይገልጻሉ።

በሌላ በኩል፣ የምርጫ መራዘሙን የተለያዩ ምክንያቶችን በማስቀመጥ የሚቃወሙ ፓርቲዎች አሉ። የምርጫ መራዘሙን በምክንያት ከሚኮንኑት መካከል በምርጫው ተሳታፊ ከሆኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ እጩ በማስመዝገበ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው እናት ፓርቲ ይገኝበታል።

የእናት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ሰይፈ ስላሴ አያሌው(ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ የምርጫው መራዘም አሁን ካለው አገራዊ ሁኔታ ጋር በሕዝቡ ዘንድ ጥሩ ስሜት እንደማይፈጥር ይገልጻሉ። የምርጫው መራዘም የተጓተተውን የምርጫ ሂደት ለማስተካከል ቢያስችልም፣ ምርጫው በሕዝቡ ዘንድ የፈጠረው ስጋት ስላለ ምርጫው መጥቶ ባለፈልን የሚል ስሜት እንደሚታይ ጠቁመዋል።
እንደ አገር ሕዝቡ ምርጫውን በጉጉት የሚጠብቅ እንዳልሆነ የሚገልጹት ሰይፈ ስላሴ፣ በዚህ ሁኔታ የምርጫው መራዘም የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽኖ እንደሚፈጠር ይገልጻሉ። በሌላ በኩል የምርጫው መራዘም አሉታዊ ጎን የሚሉት የድምጽ መስጫው ቀን ከኹለት እስከ ሦስት ሳምንት መራዘሙ ክረምት የሚገባበት ወቅት መሆኑን በማንሳት ነው።

የድምጽ መስጫ ቀን ክረምት ወደሚገባበት ጊዜ መቃረቡ በምርጫ ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተጽኖ እንዳይፈጥር ሰይፈስላሴ ስጋት አላቸው። ቦርዱ ውሳኔውን ባሳለፈበት ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይህንኑ ሀሳብ አንጸባርቀዋል። በዚህም የምርጫ ድምጽ መስጫው ቀን የግብርና ሥራውን በማያስተጓጉል መንገድ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዋች ጠይቀዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ካነሷቸው ሀሳቦች መካከል፣የኦሮሚያ ነጻነት ንቅናቄ (ኦነን) ፓርቲ በበኩሉ የተራዘመው የመራጮች ድምጽ መስጫ ቀኑ ከመጭው ክረምት በኋላ እንዲሆን ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት ደግሞ ምርጫው ከተራዘመ አይቀር አሁን እየተነሱ ያሉ የዲሞክራሲ እና የተሳትፎ ጥያቄዎችን በሚመልስ መልኩ ቢራዘም የተሻለ እንዲሆን ለምርጫ ቦርድ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። የአፋር ህዝብ ፓርቲ ደግሞ የምርጫ ድምጽ መስጫ ቀን ከተራዘመ የመራጮች ምዝገባ ቀንም ሊራዘም እንደሚገባ ጠይቋል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ በበኩላቸው፣ ፓርቲዎቹ ያነሷቸው ጥያቄዎች ለቦርዱ ቀጣይ ውሳኔዎች ግብዓት መሆናቸውን በመጠቆም የተነሱ ሀሳቦችን ከግምት ውስጥ በማስገባት በቀጣይ ውሳኔ እንደሚሰጥ ጠቁመው አልፈዋል።

ለመራጮች ምዝገባ በቂ ጊዜ መሰጠቱን የተናገሩት ሰብሳቢዋ የምዝገባ ጊዜው በድጋሚ ሊራዘም እንደማይችል ገልጸው፣ ፓርቲዎች ተጨማሪ ጥያቄዎች እና የውሳኔ ሀሳቦች ካሏቸው በጽሁፍ ለቦርዱ ለማስገባት እንደሚችሉ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ቦርዱ አዲስ አበባ እና የድሬድዋ ከተማ አስተዳደሮች የድምጽ መስጫ ቀን ከአገር አቀፍ ድምጽ መስጫ ቀን ጋር በመለያየቱ በተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በርካታ ቅሬታዎችን ሲያስተናግድ ቆይቶ በመጨረሻ የኹለቱ ከተማ አስተዳደሮች ምርጫ ወደ አገራዊ ድምጽ መስጫ ቀን ተቀልብሶ ምርጫው በአንድ ቀን እንድካሄድ ወስኗል።

የአዲስ አበባና የድሬድዋ ከተማ አስተዳደር ድምጽ መስጫ ቀን ከተቃወሙትና በተደጋጋሚ ቦርዱን ሲጎተጉቱ ከነበሩት ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ እናት ፓርቲ እንደነበር አስታውሰዋል። ሰይፈ ስላሴ አክለውም የድምጽ መስጫ ቀን በአንድ አገር ውስጥ ኹለት ቀን ማድረግ ትልቅ ችግር እንደሚፈጥር ገልጸዋል። አገር አቀፍ ምርጫ ውጤት ይፋ አድርጎ ሌላ የከተማ አስተዳደር ምርጫ ማካሄድ የ1997 ምርጫ የተከሰተውን አይነት ችግር እንዳይፈጥር እናት ፓርቲ ስጋት እንደነበረው ጠቁመዋል። ቦርዱ የፓርቲዎቹን ጥያቄ በመስማት ውሳኔውን ማስተካከሉ ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአዲስ አበባና ድሬድዋ ከተማ አስተዳደር የድምጽ መስጫ ቀን በአንድ ቀን እንዲሆን ፓርቲዎች ባቀረቡት የጽሁፍ ጥያቄ መሰረት የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዲቅሳ የፓርቲዎች ጥያቄ ታይቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት ባቀረቡት ሀሳብ መሆኑን ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ(ባልደራስ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በቃሉ አጥናፉ(ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ሥድስተኛው አገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያ አሁን ካለቸበትን ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተደራርቦ መምጣቱ ስጋት ያንዣበበበት ምርጫ እንዳደረገው እየተገለጸ ይገኛል። አሁን የውስጥና የውጭ ችግሮች በተበራከቱበት ጊዜ ምርጫ መካሄዱ በፓርቲዎችም ይሁን በሕዝብ ዘንድ ስጋት የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል።

ለዚህ ስጋት ደግሞ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከወዲሁ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ሰይፈ ስላሴ ይጠቁማሉ። በተለይ ገዥው ፓርቲ ችግሮቹን በአግባቡ በመረዳት ምርጫው ለተጨማሪ ቀውስ ምክንያት እንዳይሆን መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል። እንዱሁም ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ በመንቀሳቀስ ምርጫው ተጨማሪ ችግር እንዳይፈጥር በጥንቃቄ መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com