የእለት ዜና

ኢትዮ አማዞን የተሰኘ አዲስ የመገበያያ ድረ-ገጽ ወደ ሥራ ሊገባ ነው

ኢትዮ ካብ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር አዲስ የኦንላይን መገበያያ ድረ-ገጽ በመክፈት በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ በአሜሪካ አገር የኬሚስተሪ መምህር እና የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ወንደሰን ፍቅሬ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ድርጅቱ የኦንላይን ንግድ ሃሳቡን ከአማዞን የወሰደ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለውን ‹ኢትዮ አማዞን ዶት ኮም› የተሰኘ የዌብሳይት ዶሜን ስም መግዛቱም ተገልጿል። በዚህም ውጪ የሚገኙ ዳያስፖራዎች ከኢትዮጵያ የሚፈልጉትን እቃ ከድረ-ገጹ መሸመት ይቻላቸዋል ሲሉ ወንደሰን ተናግረዋል። ድርጅቱ በአሁኑ ሰዓት ዌብሳይቱን ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉንም ሥራዎች የጨረሰ ሲሆን በቅርቡ ወደ አገልግሎት እንደሚገባ ታውቋል።

በኢትዮጵያ እንደ ‹ብሩንዶ ዶት ኮም፣ አዲስ ብር እና ኦንላይን ሾፕ› የተሰኙ የአገር ውስጥ ግብይት ብቻ የሚፈጽሙ ድርጅቶች እንዳሉ ይታወቃል። ኢትዮ አማዞን በኢትዮጵያ የሚገኙ ነጋዴዎች የውጭ አገራት ገበያን እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው ሲሉ ወንደሰን ገልጸዋል። ሻጮች እቃዎቻቸው ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ በዌብሳይቱ አማካይነት ግብይት የሚፈጽመው በዶላር መሆኑን ሰምተናል።

ኢትዮ አማዞን በዋናነት የሚሰራው ከሻጮች እቃዎችን በመቀበል በኦንላይን ማሰተዋወቅ ሲሆን፣ ምርቱ በኦንላይን ከተሸጠ ገዢው ወዲያውኑ ብሩን በኢትዮ አማዞን በኩል ይልካል። በመቀጠል ባለው ውል መሰረት ሻጩ ለገዢው ማንኛውንም እቃ ወደ ውጪ የሚላክበትን መንገድ በመጠቀም ከ5 እስከ 7 ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ መላክ ይጠበቅበታል። በተባለው የጊዜ ገደብ የማይልክ ከሆነ ከኢትዮ አማዞን ጋር ባደረገው ውል መሰረት ሕጋዊ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ወንደሰን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። ገዢዎች የገዙት እቃ በተባለው ቀን የማይደርሳቸው ከሆነ የሚጠይቁት አትዮ አማዞንን በመሆኑ በተባለው ቀን ሻጮች መላክ ይጠበቅባቸዋል።

በአገራችን የተከሰተውን የኮቪድ ወረርሺኝ ተከትሎ አለም ላይ ያለው ማህበረሰብ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ባለበት ቦታ ሆኖ እየተገበያየ ይገኛል። ይህ በመሆኑም ኢትዮ አማዞን ዌብሳይት አብዛኛው አሜሪካ፣ ካናዳ እና አውሮፓ ያለው ዲያስፖራ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ምርቶችን በቀላሉ ለማግኘት እንዲችል የሚረዳው ነው።

ሻጮቹ ምርቶቻቸውን ዌብሳይቱ ላይ ያስቀምጣሉ። ዌብሳይቱ ላይ ለእያንዳንዱ ሻጭ የራሱ የሆነ ዳሽ ቦርድ ይኖረዋል። ዳሽ ቦርዱ ላይ ‹ዩዘር ኔም እና ፓስወርድ› ይኖረዋል። ሻጩ ያለውን ምርት በዌብሳይቱ ላይ በማስቀመጥ እቃው በተለያዩ አገራት ይተዋወቃል። ለምሳሌ እቃው 100 ብር የሚሸጥ ከሆነ 15 ብር ለኢትዮ አማዞን የሚከፈል ኮሚሽን ጨምረው ማስቀመጥ ይኖርባቸዋል። ዌብሳይቱ ላይ ግዢ ሲፈጽሙ ገዢዎች የመላኪያ ክፍያ ጨምሮ እንደሆነ ያሳያቸዋል በዛ መሰረት ይከፍላሉ ተብሏል።

ዌብሳይቱ ከገዢዎች የሚደርሰውን ክፍያ ለሻጮች በተለያዩ የአገር ውስጥ የክፍያ ስርዓቶች ማለትም እንደ ቴሌ ብር እና ኢ ብር በኩል እንደሚፈጽም ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል። ቴሌብር ከኢትዮ ካብ ጋር ለመስራት ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ ድርጅቱ ለሚሰራቸው ማንኛቸውም አገልግሎቶች ዲጂታል የገንዘብ ዝውውሮችን እንደሚጠቀም ሰምተናል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮ ካብ የሹፌሮች ደህንነትን የሚያስጠብቅ አዲስ የታክሲ አገልግሎት የጀመረ ሲሆን፣ አሽከርካሪዎች 20 ደንበኞችን ካጓጓዙ በኋላ ሙሉ የላቢያጆ አገልግሎት እንደሚሰጥ ወንደሰን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ደንበኞች የኢትዮ ካብን የታክሲ አገልግሎት መተግበሪያ ሲያወርዱ የሚያገኙትን ማጣቀሻ ለሌሎች በማጋራት ደንበኞችን በማስገባት የቦነስ(ስጦታ) ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል። በዚህም 10 ብር በአንድ ሰው ያገኛሉ። 50 ሰው ሲያሰዝመዘግቡ ደግሞ 500 ብር ስጦታ ይበረከትላቸዋል።

የኢትዮ ካብ 7445 አገልግሎት ለየት የሚደርገው 1 ጉዞ ሲያደርጉ 5 ኪ.ሜ ስጦታ እና 7 ጉዞ ሲያደርጉ 35 ኪ.ሜ ይበረከትላቸዋል። ይህንንም ወደ ሞባይል ካርድ እና ወደ ብር በመቀየር ለእርዳታ ድርጅት ማበርከት የሚችሉበት መንገድ አመቻችቷል ሲሉ ወንደሰን ገልጸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 133 ግንቦት 14 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!