ማዕቀቡና አጀቡ

Views: 117

የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት ላይ የአሜሪካ መንግስት የጣለው ማዕቀብ ለቀናት መነጋገሪያ ሆኗል። የአባይ ግድብ ውዝግብን በማስመልከት አሜሪካ ከግብፅ ጎን መሰለፏን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት ግንኙነት ውጥረት የነገሰበት ነበር። በህወሓት ባለስልጣናት ላይ እርምጃ መወሰድ ሲጀምር ከሮ የነበረው ግንኙነት ይበልጥ ተወጥሮ አሁን ተበጥሷል። ግንኙነቱ ሻክሮ በነበረበት ወቅት ውጥረቱን ለማርገብ ተደርገው የነበሩ ሙከራዎች የአሜሪካንን ልብ ማለስለስ ሳይችሉ ቀርተው ይበልጥ እንድታስፈራራን አድርጓታል። ከህወሓት ጋር ካልተደራደራችሁ ሞቼ እገኛለሁ ያለችው አሜሪካ እንዴት ብትደፍሩኝ ነው የምለውን የማትቀበሉት ብላ ማእቀብ ጥላለች።

ማዕቀቡ እንደተጣለ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች እንደመሰላቸው ሲተቹትና ሲደግፉት ሰንብተዋል። ከመንግስት ባለስልጣናት መካከል የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ታዬ ደንደዓ ያለምንም ማመንታት፣ “ማዕቀቡ የትራንስፖርት ወጪያችንን ለመቀነስ ያግዘናል” በማለት እያመሰገኑ አሹፈውበታል። የኦሮሚያ ክልል ትሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፣ “የሚቀርብን የነቀዘው ስንዴያቸው ማራገፊያ መሆን ነው” ብለው ማዕቀቡን አጣጥለውታል። የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አገኘሁ ተሻገርም፣ “አያውቁኝ አላውቃቸው፣ አሜሪካ ሄድኩ አልሄድኩ ምን ሊቀርብኝ? ከህወሓተ ጋር ድርድር የሚባል ነገር የለም፣ ጦሬንም ከወልቃትና ራያ አንዲት ኢንች ንቅንቅ አላደርግም” ማለታቸውን የሰማው ናትናኤል መኮንን ሀሳባቸውን በፅሁፍ አጋርቶታል። ከነዚህ ባለስልጣናት ይበልጥ ሙክታሮቪች ኦስማኖቫን የመሳሰሉ የማህበረሰብ አንቂዎች የአሜሪካንን እርምጃ ከመኮነን አልፈው ተሳልቀውበታል።

በሌላ በኩል፣ “አሜሪካ ደግ አደረገች፣ ይህ መንግስት ሲያንሰው ነው” እያሉም የፃፉም ነበሩ። ሕዝብ በአገሩ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አቅቶት በሰላም እጦት እየተሰቃየና መንገድ እየተዘጋበት በሚጉላላበት በዚህ ወቅት፣ ጥቂት ባለስልጣናት አሜሪካ እንዳትገቡ ስለተባሉ ይህን ያህል መጮሁና ሕዝብን መቀስቀሱ ተገቢ አይደለም በማለት ማዕቀቡን ተከትሎ የተፈጠረውን አጀብ ያወገዙም አሉ። ቪዛ ተከለከልን ብሎ ምግብ እንደተከለከለ ህፃን ማልቀስ እንደማገባ በመጥቀስ ገና ብዙ ነገር ሊመጣ ስለሚችል ተዘጋጅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል ሲል አንድ ግለሰብ አስጠንቅቋል። አሜሪካ የጉዞ ማእቀብ መጣሏ ያን ያህል ሊያሳስብ አይገባም ነበር ያሉ በበኩላቸው፣ ባለስልጣናቱ ይበልጥ የሚያሳስባቸው የእነሱ አሜሪካ መሄድ አለመሄድ መሆን አልነበረበትም ብለዋል። የአሜሪካ እርምጃ ተገቢ ነው ብለው ከህወሓት ደጋፊዎች ውጭ የደገፉት ስለመኖራቸው ማረጋገጥ ባይቻልም፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጭምር አውግዘውታል። መንግስትን የሚቃወሙ የተወሰኑ ግለሰቦች የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል እሳቤ፣ “ደግ አደረጓችሁ” የሚል ይዘት ያለው መልዕክት አስተላልፈዋል።

መንግስት ጥሩም ሰራ መጥፎ እንደሀገር የሚጎዳን ነገር ከተደረገ ሁላችንም በየፊናችን ማውገዝ ይጠበቅብናል። የአሜሪካ ፍላጎት በጉዞ ማዕቀብ የሚሳካላት ስለማይሆን ሁላችንንም የሚጎዳ ቀጣይ መዘዝ እንደሚያመጣ ሁሉም ሊረዳ እንደሚገባ አስተያየታቸውን ብዙዎች ሰጥተዋል። አንዳንዶች ነገሩን ለማርገብ ከመሞከር ይልቅ እኛም አፀፌታውን እነሱ ላይ ማዕቀብ በመጣል መመለስ አለብን ብለዋል።

ያም ሆነ ይህ ሀገርና ክብር ለድርድር የማይቀርቡ በመሆናቸው፣ አይደለም ጥቂት ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ ሁላችንም ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ቢፈጸም እጅ ሰጥተን ታዛዣቸው እንደማንሆን ግልፅ ነው። አፄ ቴዎድሮስ ላይ ቁርሾ የነበረባቸው የእንግሊዝ ጦርን እየመሩ ሲመጡ እሳቸውን በመክዳት አሳልፈው ሠጥተው በኋላ ላይ ካዘኑት እና አፄ ዮሐንስን ጠልተው ከደርቡሽ ጋር ብቻቸውን ተዋግተው እንዲሰዉ ምክንያት ከሆኑት፣ እንዲሁም አፄ ኃይለሥላሴን በመቃወም አውቀውትም ይሁን ሳያውቁ ጠላትን አግዘው በስራቸው ካሳፈሩን አያት ቅድመአያቶች ልንማር ይገባል። ወንድማማቾች ሲጣሉ ጎረቤት ይገላግላል እንጂ የሩቅ ባዳ ይዞ የሚመጣ ከሆነ የተጣሉትን ማስታረቁ አይቀርም።


ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com