ስለኮቪድ የሚናፈሱ ወሬዎች

Views: 72

የኮሮና ቫይረስ የዓለማችንን ገጽታ ከቀየሩ ክስተቶች አንዱ ነው። ለኮሮና ቫይረስ ይኸ ነው የሚባል መድኃኒት ዛሬም ድረስ ባይገኝም ክትባቱ ግን በመላው ዓለም አገራችንን ጨምሮ እየተሰጠ ይገኛል። የኮሮና ቫይረስ ክትባት ላይ እየተዛመቱ ያሉ ወሬዎች በአገራችን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ጭምር የሚናፈሱ ናቸው። ህብረተሰቡ በሚናፈሱ አሉባልታዎች ምክንያት ለክትባቱ የነበረው ፍራቻ አሁን አሁን እየቀነሰ የመጣ ይመስላል። ለዚህም እንደማሳያ ክትባቱ በአገራችን መሰጠት በጀመረ በኹለት ወራት ውስጥ ከ1 ሚሊየን 700 ሺሕ በላይ ሰዎች መከተባቸው ነው።

አሁንም ግን የኮቪድ ክትባት ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች አልጠፉም። በተለይ ደግሞ ክትባቱ የሚሰጠው መጀመሪያ የኮቪድ ምርመራ ላደረጉ ሰዎች ባለመሆኑ ኮቪድ እንዳለባቸው ሳያውቁ ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች ለሞት እንደተዳረጉ አስተያየታቸውን ከሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰምተናል። ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች አንዲት አስተያየት ሰጭ አባቷን በቅርቡ በሞት ተነጥቃለች። “አባቴ ኮቪድ 19 ወደ አገራችን መግባቱን ከሰማንበት እለት ጀምሮ ከቤት ወጥቶ አያውቅም። ወደ ተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችም ሆነ ለሚያስፈልጉን ማናቸውም ነገሮች እኛ ነበርን ወደ ውጭ የምንወጣው። ተገቢዉን ጥንቃቄም እናደርግለት ነበር። ነገር ግን የኮቪድ ክትባት በወሰደ በአንድ ሳምንቱ ሕይወቱ አለፈች” በማለት ገልጻለች። እንደ እርሷ አስተያየት ከሆነ አባቷ የኮቪድ ክትባት በመውሰዳቸው ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን ታምናለች። ለዚህ እንደ ምክንያት ደግሞ አባቷ ከክትባቱ በፊት ሙሉ ጤነኛ እና ተጓዳኝ ህመም የሌለባቸው እንደነበር ታነሳለች።

በሌላ በኩል ምርመራ ሳይደረግላቸው ክትባቱ የሚሰጣቸው ግለሰቦች ቫይረሱ እያለባቸው ከተከተቡ ለሞት ይዳረጋሉ የሚል ያልተረጋገጠ ወሬ እንዳለ ይሰማል፡፡ ስለ ኮቪድ ክትባት ሌላኛው የሚነሳ ጉዳይ ደግሞ ክትባቱ በግል ተቋማት ውድ በሆነ ዋጋ እየተሸጠ መሆኑን አስተያየት የሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ። የዛሬ ኹለት ወር ገደማ በእርዳታ መልክ ወደ አገራችን የገባው የኮቪድ ክትባት፣ ክትባት ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንደየቅደም ተከተላቸው እየተሰጠ ይገኛል። ጤና ሚኒስቴርም ይህ ፅሁፍ እስለተጻፈበት ግንቦት 19 ድረስ ለ1 ሚሊየን 738 ሺሕ 550 ያክል ሰዎች ክትባት ማዳረሱን አሳውቋል።

ከኮቪድ ክትባት ጋር የተነሱ ቅሬታዎች ላይ ምላሽ ለማግኘት ወደ ጤና ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ስልክ በመደወል ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ይህ ጽሁፍ ወደ ማተሚያ ቤት እስከተላከበት ሰዓት ድረስ አልተሳካም። ሌላኛው ከኮቪድ ጋር እየተነሳ ያለው ጉዳይ ለኮቪድ ጽኑ ህሙማን ያግዛል የተባለ COROVIR (Remdesivir) የተሰኘ መድኃኒት ዋጋ ጉዳይ ነው። መድኃኒቱ የኮቪድ ጽኑ ታማሚ የሆነ ቤተሰብ ያላቸው ሰዎች ከ40 ሺሕ እስከ 70 ሺሕ ብር ድረስ እንደሚገዙት አስተያየት ሰጭዎች ያስረዳሉ። በካዲስኮ ሆስፒታል የኮቪድ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ዘለዓለም ተስፋየ እንደሚሉት COROVIR ከስሙ እንደምንረዳው ለኮሮና ሕክምና ተሻሽሎ የተሰራ መድኃኒት መሆኑን አስረድተው፣ ዋጋው እጅግ ውድ እና በእኛ አገር የጤና ሚኒስቴር ባወጣው የኮቪድ ሕክምና መመሪያ መሰረት ያልተፈቀደ ነው በማለት ገልጸዋል።

ዶክተሩ የኮቪድ ሕመም ለያዘው ሰው መድኃኒቱን መስጠት በሸታው ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይሄድ እንደሚረዳ አስረድተው፣ በውጭ አገራት ለኮቪድ በሚደረግ ሕክምና መድኃኒቱ ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሚገኝ፣ እንደ ምሳሌም የቀድሞው የአሜሪካን ፕሬዝዳን ዶናልድ ትራምፕ በኮሮና ተይዘው በነበረበት ጊዜ መድኃኒቱ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል። በኛ አገር ግን ኮሮቪር የተሰኘውን መድኃኒት አስመልክቶ ምንም አይነት ጥናት እና ምርምር ባለመደረጉ፣ እንዲሁም በበቂ ሁኔታ መድኃኒቱ ስለማይገኝ ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ብለዋል። ነገር ግን፣ ከላይ ለመናገር እንደሞከርኩት ከውጭ አገር በተገኘ ልምድ አንዳንድ የጤና ተቋማት ላይ መድኃኒቱ እየተሰጠ እንደሆነ እና አንዳንድ ፋርማሲዎች ውስጥ በውድ ዋጋ እየተሸጠ እንዳለ መስማታቸውንም ዶክትር ዘለዓለም ተናግረዋል። በኮቪድ ታማሚ ቤተሰቦች ያሏቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በኢንተርኔት በሚያዩት በሚሰሙት እና በሚያነቡት ተነስተው መድኃኒቱን ከውጭ አገራት በማስመጣትም ሆነ አገር ውስጥ በውድ ዋጋ በመግዛት ኮቪድ ታማሚ ለሆኑ ዘመዶቻቸው እንድንሰጥላቸው ይጠይቁናል ሲሉ ገልጸዋል።

ዶክተሩ አክለውም ሕክምና እምቢታን ስለማይጠይቅ መድኃኒቱን ወስደን የምንሞክርበት ጊዜ አለ ብለዋል። አንድ ታማሚ ይህንን በመርፌ የሚሰጥ መድኃኒት ሰባትም ሆነ ስምንት ጊዜ ሊወስድ ይችላል። አንዱ መድኃኒት 100 ሚሊ ግራም ነው ብለዋል። ዋጋውም እንደሰሙት ከሆነ ስምንቱን ለመግዛት 80 ሺሕ ብር ድረስ ወጭ ማድረግ ይጠይቃል የመድኃኒቱ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣም ተናግረዋል። ዶክተሩ በመንግሥት ደረጃ ያሉ የኮቪድ ማገገሚያ ማዕከላት ጭምር መድኃኒቱን እንደሚጠቀሙም ገልጸዋል። የሕክምናውን መመሪያ እና ሕግ ተከትለን እንስራ ካልን ግን ብዙ መከተል ያለብን ቅመ ሁኔታዎች አሉ። ምክንያቱም መድኃኒቱ ጉበትን ሊጎዳ ስለሚችል ለታካሚው ከመስጠታችን በፊት የጉበቱን ጤነኛነት መርምረን መስጠት ሊኖርብን ይችላል በማለት ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዓለም የጤና ድርጅት መመሪያ ይህ መድኃኒት የተፈቀደ ሲሆን፣ በተለይ ኮቪድ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘባት ቻይና መድኃኒቱን እየተጠቀመችበት ትገኛለች ብለዋል። የዓለም የጤና ድርጂትን መመሪያ እንደ መነሻ ብንወስድም በእኛ አገር የኮሮና ሕክምና መመሪያ Hydroxychloroquine ቢሰጥ ይመከራል ተብሎ እንደተካተተው ሁሉ COROVIR ባለመካተቱ እና ከዋጋው አንጻር መሰጠቱ ሕጋዊ አይደለም ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል።ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com