የአሜሪካ ማዕቀብ እንደ መልካም አጋጣሚ?!

Views: 96

የአሜሪካ የሰሞኑ ማዕቀብ ኢትዮጵያንና ኤርትራን በእጅ አዙር ለመግዛት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። በተለይ ኢትዮጵያ ምርጫ ልታካሂድ በተቃረበችበትና የግድቡን ኹለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማካሄድ እየተሰናዳች ባለችበት ጊዜ መሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ስቧል። የአሜሪካና የኢትዮጵያ ግንኙነት ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ ቢሆንም ድንገት እዚህ ደረጃ መድረሱ አሳሳቢ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በአሜሪካ እና ኢትዮጵያ ታሪካዊ ግንኙነት እንዲሁም በማዕቀቡ ዙሪያ ተሻለ አሰፋ ይህንን ጽሁፍ አቅርበዋል።

ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረው የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ ይፋዊው የዲፕሎማሲ ግንኙነት በብዙ ከፍታዎች እና ዝቅታዎች የታጀበ ለመሆኑ ብዙ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል። ከአዎንታዊው ለመጀመር በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ሮበርት ስኪነር በሚባል የአሜሪካ የዲፕሎማሲ ወኪል አማካይነት የኹለቱን አገራት ግንኑነት ለማጠናከር የንግድ ስምምነት ተፈርሟል። ከዓመታት በኋላ በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመን የ‹ሰላም ጓድ› መርሃ ግብር በማስጀመር በተለይ በትምህርት፣ በጤና፣ በገጠር ልማት እና አነስተኛ የንግድ እንቅስቀሴዎችን በመደገፍ ግንኙነቱ ኹለንተናዊ አስተዋጽዖ ማበርከቱ በታሪክ ድርሳናት ሁሌም ይታወሳል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ተጠናክሮ መቀጠሉም ይታወቃል። በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አሜሪካ ታካሂደው ለነበረው ዓለም ዐቀፍ የጸረ ሽብርተኝነት ጦርነት ኢትዮጵያ አጋር በመሆን ሠርታለች። በተጨማሪም የአሜሪካ መንግሥት በድህነት ቅነሳ፣ የምጣኔ ሀብት ልማት ጨምሮ በመንግሥት አስተዳደር እና በማኅበራዊ ዘርፎች ኢትዮጵያ ለምታካሄዳቸው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች ኹነኛ አጋር በመሆን ድጋፍና እርዳታ በማበርከት ቀጥላለች።

ይህ ማለት ግን የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ሁልጊዜም የሰመረ ነበር ማለት እንዳልሆነ መሰመር አለበት፤ ብዙ ማሳያዎች መጥቀስም ቢቻልም አንዳንዶቹን ለአብነት ማስታወሱ ተገቢነት ይኖረዋል።
በ1969 የዚያድ ባሬ ወራሪ መንግሥት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት አሜሪካ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን አለመሆኗ ብቻ ሳይሆን የወራሪውን መንግሥት በጦር መሣሪያ አቅርቦትና ሥልጠና ረድታለች። ይህም ሳያንስ ኢትዮጵያ ለተጋረጠባት የሉዓላዊነት፣ አገር መደፈር የመሣሪያ ግዢ ከአሜሪካ ጋር ብትፈጽምም በአሜሪካ ሸፍጥ ምክንያት መሣሪያውን ለማግኘት አልቻለችም ነበር።

ያለፉት ሦስት ዓመታት
ህወሓት ቅድመ 2008 የኢሕአዴግ ዘመን ከልካይ የሌለበት አንጋሽም ነጋሽም እንደነበር ይታወቃል። የ2007 አጠቃላይ ምርጫን ተከትሎ ኢሕአዴግ መቶ በመቶ ‹ባሸነፈ› ማግስት በተነሳና እስከ 2010 በዘለቀው ሕዝባዊ ተቃውሞና አመጽ፥ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ አካሂጄዋለው ባለው ጥልቅ ተሃድሶ፣ ተለውጫለሁ በማለት የአመራር ለውጥ አድርጎ ዐቢይ አሕመድ’ን (ዶ/ር) የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር፣ በኋላም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በማድረግ ወሳኝ የፓርቲና የመንግሥት ሥልጣን እንዲቆጣጠሩ አደረገ።
በኢትዮጵያ የተካሄደውን ለውጥ በጥንቃቄ ትከታተለው የነበረው አሜሪካ በለውጡ መጀመሪያ አካባቢ በኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረግ ሽግግር እንደምትደግፍ ማስታወቋም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

በዲፕሎማሲ ሀ ሁ፣ አገራት ከማንኛውም አገር ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት ቅድሚያ አገራዊ ፍላጎታቸውን፣ ከዛም የጋራ ጥቅማቸውን ባስጠበቀ ሁኔታ እንደሚያካሂዱ ይታወቃል። ኢትዮጵያ የአሜሪካ ስትራቴጂያዊ አጋር ትሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲገብርላትም ትፈልጋለች፤ በተለያዩ መልኮችም ተጽዕኖዎቿን ታሳርፋለች።

ይህንን በምሳሌ ለማስረዳት አሜሪካ ራሷን ብቸኛዋ የዓለም ፖሊስ አድርጋ ስለምትቆጥር፣ በተለያዩ ወቅቶች በአገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ በመግባትና በመፈትፈት መንግሥት ፈንቅላለች፤ ጥቅሟን የሚያከብርላትን የአሻንጉሊት መንግሥትም አንብራ ታውቃለች፤ አገራትን አፍርሳለች ወይም በተዘዋዋሪ እንዲፈርሱ አድርጋለች። በአፍጋኒስታን እና በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ በየጊዜው የምታራምዳቸውን አቋሞች እዚህ ላይ ልብ ይሏል።

ኢትዮጵያን በተመለከተ ‹ሲጠሩት አቤት፣ ሲልኩት ወዴት?› የሚል አሽከር መንግሥት እንዲኖር በቀጥታም ይሁን ስውር እጆቿን በመጠቀም እንዲፈጠር አድርጋለች። የህወሓት – ኢሕአዴግ መንግሥት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ኢትዮጵያን አጋር በማድረግ ኤርትራ ከዓለም እንድትነጠልና ማዕቀብ እንዲጣልባት አድርጋለች። እንዲሁም በሥመ ጸረ ሽብርተኛ አጋርነት በሶማሊያ የኢትዮጵያ ጦር መዝመት ሰበቡ አሜሪካ ለመሆኗ እማኝ መጥቀስ ጊዜ ማባከን ይሆናል፤ ግልጽ የሆነ ጉዳይ በመሆኑ።

አሜሪካ ፖሊሲዋ እስከተከበረ እና የምትሰጠው ትዕዛዝ እስከተፈጸመ ድረስ ከአገራት ጋር የሚኖራት ግንኙነት ለሕዝብ ግንኙነት ፍጆታ እንደሚውሉና እቆረቆርላቸዋለሁ ለምትላቸው ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እና ለሰብአዊ መብቶች መከበር ቁብ አትሰጥም። ለዚህ ትልቁ አስረጅ ሆኖ የሚቀርበው ምርጫ አድርገው የማያውቁ፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ምናቸው ላልሆነና የዜጎቻቸውን ሰብአዊ መብቶች የሚጥሱ ሀብታም የመካከለኛው ምሥረቅ የአረብ አገራትን መጠቀስ ይቻላል። ህወሓት ባነበረው መንግሥት ለይስሙላ የተካሄዱ ምርጫዎች፣ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን እስርና ማሳደድ፣ የተፈጸሙ ጅምላ ግድያዎችና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ጆሮ ዳባ ልበስ ብላ ለሦስት ዐሥርት አመታት ዋነኛ አጋር ሆና ዘልቃለች። ምክንያቱም የኢትዮጵያ መንግሥት ታዛዥና አሽከር መንግሥት ስለነበረ!

የሕዳሴው ግድብ እና የትግራይ ሕግ ማስከበር በአሜሪካ ዐይን
አሜሪካ የሕዳሴው ግድብ ግንባታን በተመለከተ በታዛቢነት ሰበብ (አደራዳሪ እስከመሆን የደረሰ ዐይናውጣነት በታየበት ሁኔታ) የግብጽ ወገንተኛ መሆኗን አሳይታለች። ኢትዮጵያ የሦስትዮሽ ድርድሩን አሜን ብላ የማትቀበል ከሆነ ደግሞ ግድቡን በቦንብ ማጋየት እንደሚቻል የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት የነበሩት ዶናልድ ትራም መፎከራቸው ጸሐይ የሞቀው ሃቅ ነው።

ይህ የአሜሪካ ከግብጽ ጋር መወገን በአንድ በኩል ግብጽ በመካከለኛው ምሥራቅ ለአሜሪካ ወሳኝ አጋር በመሆን እየዋለች ያለውን ውለታ ለመካስ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ ደካማና ለአሜሪካ መንግሥት ሎሌ የሆነ መንግሥት እንዲኖር በማድረግ አሜሪካ በምሥራቅ ብሎም በመላው አፍሪካም የሚኖራትን ተጽዕኖ ማሳደግ ላይ ያለመ ይመስላል።

ይሁንና የዐቢይ አሕመድ መንግሥት በአገር ውስጥ ያለው ደካማነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዘመነ ህወሓት – ኢሕአዴግ እንደነበረው ታዛዥ መንግሥት ሆኖ አላገኙትም። አንዳንድ በሚያደርጋቸው የልማት እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ትልልቅ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ የአሜሪካንን ሆነ ሌሎች ምዕራባውያን እገዛ ሳያስፈልገው ማሳካቱ ‹ይህቺ ባቄላ ያደረች እንደሆነ አትቆረጠምም› ነው የሆነባቸው። ስለዚህ አሜሪካ አንድም የኢትዮጵያን መንግሥት እንደቀደመው ህወሓት – ኢሕአዴግ ማስገበር አሊያም በማዳካም ወደሚፈለገው መስመር እንዲገባ ማስገደድ እንዳለባት ወስናለች።

የኢትዮጵያ መንግሥት በህወሓት ላይ ያካሄደውን የሕግ ማስከበር እርምጃ በተመለከተ አሜሪካ እያራመደች ያለው ፖሊሲ የአንድን ሉዓላዊት አገር የተዳፈረ ነው። በርግጥ ጦርነት በሚካሄድበት አገር የሰላማዊ ዜጎች መጎዳትን ማስቀረት ባይቻልም ለመቀነስ ኹለቱም ወገኖች ዓለም ዐቀፍ የጦርነት ስምምነቶች ማክበር ግዴታቸው ነው። ይሁንና የአሜሪካ አስተዳደር በአንዲት ሉዓላዊት አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት አልፎ የአንድን ወገን ጩኸት ብቻ በማስተጋባት የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር ደክሟል። ቀደም ሲል በተባበሩት መንግሥታት ጸጥታ ምክር ቤት ኢትዮጵያ ላይ ልታስወስድ የነበረው እርምጃ በሩሲያ እና ቻይና ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣናቸው መክኗል። በመሆኑም አሜሪካ የተናጠል እርምጃ እንድትወስድ ተገድዳለች። ካናዳን ጨምሮም ሌሎች ምዕራባውያንም እንዲሁ አሜሪካ በከፈተችው ቦይ ይፈሳሉ ተብሎም ይጠበቃል።

የአሜሪካ ማዕቀብ ምንነትና አንድምታ
ሰኞ፣ ግንቦት 16 አንቶኒ ብሊንከን በሚመሩት የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ በኩል የወጣው መግለጫ ‹‹ትግራይ ውስጥ በተፈጠረው ቀውስ›› ተዋናይ ናቸው የተባሉትን በሥም ያልተዘረዘሩ የኢትዮጵያንና የኤርትራ የቀድሞ እና አሁን በሥልጣን ላይ ያሉትን፣ የጸጥታ ኀይሎች አባላት፣ የአማራ ክልልና ልዩ ኀይል አባላት እንዲሁም የሕወሓት አባላት የጉዞ ቪዛ ክልከላ እንደተጣለባቸው አስታውቋል። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ላይ የምጣኔ ሀብትና ከጸጥታ በተገናኙ የሚደረጉ ዘርፈ ብዙ ድጋፎች እንዲገቱ፣ እንዲሁም ወታደራዊ ግዢዎችን በዚሁ መስመር ለማስኬድ ወስኗል። ይሁንና ማዕቀቡ የሰብአዊ ድጋፋና ወሳኝ እርዳታዎችን እንደማይመለከት አመላክቷል።

በርግጥ የአሜሪካ መንግሥት እርምጃን ሁሉም ይደግፈዋል ማለት እንዳልሆነ የሪፐብሊካን ሴናተር ጅም አንሆፍ የተቃውሞ ድምጽን በማስረጃነት መጥቀስ ይቻላል። ሴናተሩ በቲውትር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈው የቪዛ እገዳን እቃወማለሁ በማለት ኢትዮጵያ ኹከትና ብጥብጥን ለማስቆም እየሠራች ባለችበት ሁኔታ የእኛን ድጋፍ ትሻለች ብለዋል። ‹‹እንደነዚህ ዓይነት እርምጃዎች ወደ ሰላማዊ መፍትሄ እንድንቀርብ አያደርጉም›› ሲሉ እርምጃውን በጥብቅ አውግዘዋል።
የሆነው ሆኖ የአገራቱ የኹለትዮሽ ግንኙነት እዚህ ደረጃ መድረሱ መጠኑ ይለያይ እንጂ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። ተወደደም ተጠላ አሜሪካ ልዕለ ኀያል አገር በመሆኗ ግንኙነቱ ወደ በለጠ መካረር እንዳይሄድ የኢትዮጵያ መንግሥት በጥንቃቄ መያዝ አለበት። አሜሪካ ጨምሮ ምዕራባውያን አገር ማፍረስ ምን እንደሆነ በተግባር በሊቢያና ሶሪያን አሳይተውናል።

እዚህ ላይ አንዳንዶች የአሜሪካን መንግሥት የወሰደውን እርምጃ የኢትዮጵያ መንግሥት ደካማ የዲፕሎማሲ እና የሕዝብ ግንኙነት ውጤት አድርገው ይወስዱታል። በርግጥ ይህ የራሱ መጠነኛ አስተዋጽዖ ሊኖረው ቢችልም እዚህ ግባ የሚባል ነው ብዬ አላምንም። ምክንያቱም የአሜሪካ ማዕከላዊ የስለላ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ በምልዓት አያውቀውም ማለት የዋህነት ይመስለኛል። ይልቅ ዋናው ምክንያት አሜሪካ ደካማና ሎሌ የኢትዮጵያ መንግሥት መፈለጓ ይመስለኛል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት ሌሎች የአፍሪካ አገራትን በተመሳሳይ መስመር በማሰለፍ ‹ሲጠሯቸው አቤት፣ ሲልኳቸው ወዴት› ያልሆኑ መንግሥታትን እንዲያቆጠቁጡ ‹መጥፎ› አርዓያ ይሆንብኛል ከሚል ስጋትም ጭምር ነው።

ምን ይደረግ?
ወቅታዊው የኢትዮጵያን ሁኔታ ስንገመግመው በውስጣዊ የፖለቲካ ችግር የምትባትት፣ ደካማ መንግሥት ያላት እና የኑሮ ውድነት እና ድህነት ወገቡን ያጎበጠው ሕዝብ ያለባት መሆኑን መካድ የሚቻል አይመስለኝም። ‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ› እንዲሉ፥ በተለይ ከሕዳሴው ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ የውጪ ተጋላጭነት የበረታበት ዘመን ነው።

ይሁንና በምንም ዓይነት ችግር ውስጥ እንሁን ኢትዮጵያውያን የምንታወቅበት አንድ ነገር ደግሞ አለን – ለውጪ ጠላት ያለን አይበገሬነት። ኢትዮጵያውያን አባቶቻችንና እናቶቻችን ለነጻነታቸው እምቢኝ በማለት ተዋድቀዋል፤ ነጻነታችንን አስጠብቀውልን እኛ ጋር ደርሷል።
ስለዚህ እያንዳንዳችን ኢትዮጵያውያን አሁን ምን ማድረግ አለብን ለሚለው ጥያቄ፥ ምላሼ የውስጥ ችግራችንን እያስታመምንና ፖለቲካዊ መፍትሄ እያበጀን በብልሃት መያዝ ይገባናል። በዚህ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ መወጣት ያለበት መንግሥት ነው። በሌላ በኩል የውጪ ጠላት በግልጽም ይሁን በስውር ‹ጦርነት› ሲከፍትብን መንግሥትም ሆኑ ሌሎች የፖለቲካ ኀይሎች ሕዝብን በማስተባባር ማንኛውንም ጥቃት ለመቋቋምና ለመከላከል በአብሮነት እንዲቆም ማድረግ ይገባል። ሕዝብን ይዞ መሸነፍ የማይቻል ብቻ ሳይሆን የማይታሰብ መሆኑ መታወቅ ይገባል!

እዚህ ላይ ከወዳጅ አገራት ጋር የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጥበቅ ተገቢነቱ ሊሰመርበት ይገባል።
በመጨረሻም ይህንን በኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠውን ከባድ አደጋ ወደ መልካም አጋጣሚነት ለውጦ ለነጻነታችን የማንደራደር፣ አይበገሬዎች መሆናችንን በተግባር በድጋሜ የምናረጋግጥበት እንዲሁም በምግብ ራሳችንን በመቻል ለሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶቻችን አርዓያ መሆን የምንችል ሁነን መገኘት ይገባናል።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!


ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com