“ግንቦት 20ን በዓል ነው ብሎ ማክበሩ ወንጀል ነው” የግንቦት 20 እና የመስከረም 2 ተቃርኖ

Views: 96

ኢትዮጵያ ብዙ ሺሕ ዓመታት ተከብራ የኖረችበት የዘውድ ስርዓት በተማሪ አመጽ ተጀምሮ በወታደር አድማ ከተወገደ 46 ዓመታት ተቆጥረዋል። የሺሕ ዘመናቱ ስርዓት የተወገደውና በኋላ ደርግ የተባለው ወታደራዊ ቡድን ስልጣኑን የተቆናጠጠው መስከረም 2፣ 1967 ነው። ይህ ቀን የሕዝብ በዓላትና የእረፍት ቀንን ለመወሰን ተብሎ በወጣው አዋጅ ቁጥር 16/1967 ላይ ብሔራዊ በዓል ተብሎ ከሌሎች ከተዘረዘሩ በዓላት እኩል እንዲከበር ተደንግጓል።

ኢትዮጵያ ከምታከብራቸው ኃይማኖታዊና አገራዊ በዓሎች ተርታ የተሰለፈው ይህ ቀን የአብዮት ቀን ተብሎ ይጠራ ነበር። ከዘመን መለወጫ ቀን በነጋታው መስቀል አደባባይ በሚካሄድ ወታደራዊ ትዕይንት ይከበር የነበረው ይህ በዓል የአደባባዩን ሥም አብዮት አደባባይ እስከማስባል ደርሶ ነበር።

ሻዕቢያና ወያኔ ይባሉ የነበሩት አማፂያን ጥምረት ፈጥረው የደርግ መንግሥትን በጉልበት እስካስወገዱበት 1983 ድረስ ደርግ የበዓል ፍላጎቱን ሕጋዊ እንዳደረገ ቆይቷል። አማጽያኑ ኢህአዴግ ተብለው ስልጣን ከጨበጡ ወዲህ ግን፣ ሕግ ሳያወጡ ተጀምረው የነበሩትን ለማቋረጥና ያለቁትን ለማፍረስ እንዲሁም ሥያሜዎችን ለመቀየር ጊዜ አልፈጀባቸውም። ከዚህ ተግባራቸው መካከል አዲስ አበባን የተቆጣጠሩበትን ግንቦት 20 ቀንን በዓል ሆኖ እንዲከበር ያደረጉበት ሕግን ያልተከተለ አካሄድ በዋናነት ይጠቀሳል። ይህን ሲያደርጉ መስከረም 2ን ሳይሽሩ እንዲረሳ አድርገውታል።

ከ1984 ጀምረው ግንቦት 20ን በቀኑ ምንም ሥራ ሳይሰራ፣ ትምህርትም ተዘግቶ፣ በየቀበሌው ሰንጋ እየተጣለ በፌሽታ ሲያከብሩት ቆይተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የበዓል ስሜቱ በአገር ደረጃ እየተቀዛቀዘባቸው ስለመጣ “መቀሌ በሥራ ተከብሮ ዋለ” ብለው እስከመዘገብ ደርሰው ነበር። ደረግ በዘውዳዊው ስርዓት የነበረውን የበዓላት ቀን መቁጠሪያ አዋጁን ሽሮ መስከረም 2 እንዲከበር እንዲሁም የድል በዓል ከሚያዚያ 27 ወደ መጋቢት 28 እንዲለወጥ አድርጎ ነበር። ምክንያቱ ለአፄ ኃይለ ሥላሴ ካለ ጥላቻ ሊሆን ቢችልም ቢያንስ ሕጋዊነት ለማላበስ ተሞክሮ ነበር።

ኢህአዴግ በማናለብኝነት ይሁን ባለማወቅ እስከ 1988 ምንም ዓይነት በዓላትን የተመለከተ ሕጋዊ ለውጥ ሳያደርግ በዘልማድ መስከረም 2ን በግንቦት 20 ተክቶ ሲያከብር ቆይቷል። ስልጣን በያዘ በ5ኛው ዓመት ግን የሕዝብ በዓላትና የእረፍት ቀንን ለመወሰን ተብሎ የወጣው አዋጅ መሻሻል አለበት ብሎ ረቂቅ አቅርቦ አጸድቆ ነበር። በዚህ ማሻሻያ አዋጅ ላይ ግን ስለመስከረም 2 መሻር ምንም ያለው ነገር የለም። ግንቦት 20ም ብሔራዊ በዓል ነው ተብሎ አልታወጀም። ይህ የሚያሳየው ተረስቶ ሳይሆን ለውጥ ማድረግ አለመፈለጉን ነው። አንዳንዶች ጫካ የገቡበት የሺሕ ዘመናት ስርዓት የቆመበትን ሽሮ ደርግ 17 ዓመት ብቻ ቆይቶ የተወገደበትን መተካቱ፣ በመካከላቸው ጭቅጭቅ ሊያስነሳባቸው ስለሚችል አንድነታቸውን ለመጠበቅ ትተውት ነው ይላሉ።

በአዋጅ ቁጥር 29/ 1988 የተሻሻለው የድል በዓል ቀን ብቻ ነበር። እነሱም ላስወገዱት ደርግ ከፍተኛ ጥላቻ ስለነበራቸው ቡድኑ የቀየረውን ቀን ወደነበረበት ሚያዝያ 27 በሕጋዊ መንገድ መልሰው ሌላውን ባለበት ትተውታል። ስለዚህ እስካሁን የመስከረም 2 በዓልነት አልተሻረም፤ ግንቦት 20ም ሕጋዊ ብሔራዊ በዓል ሆኖ አያውቅም። በተግባር ግን የተገላቢጦሹ ሲከናወን ለማስቆም የሞከረ አልነበረም። ሕዝቡም በፍርሃት ይሁን በትዕግስት ሳይቃወም እስካሁን በዛው መንገድ ቆይቷል።

በብሔራዊ በዓላት ጉዳይ ያነጋገርናቸው ጠበቃ ካፒታል ገብሬ እንደነገሩን ግንቦት 20 የሕዝብ በዓል ተደርጎ የታወጀበት ሠነድ ስለመኖሩ እስካሁን የሰሙት ነገር የለም። ሕግ እንደሚያዘው ሕዝብ እንዲያውቀው በነጋሪት ጋዜጣ ይፋ ሣይደረግ በድብቅ ተወስኖ ካልሆነ በስተቀር፣ ይህን የሚያክል ግዙፍ የሕግ ተቃርኖ ለዘመናት መፈጸሙ አስገራሚና አሳፋሪ ነው ብለዋል። እሳቸው ይህን ጉዳይ ለማጣራት ከአቃቤ ሕግ ባለስልጣናት ጀምሮ የተለያዩ የሙያ አጋሮቻቸውን ቢያማክሩም አንድም ግንቦት 20ን ሕጋዊ የሚያደርግ አዋጅ ስለመኖሩ አውቃለሁ የሚል ሰው አላገኙም።

ምንም የሕግ መሠረት ሳይኖረው በዓሉ እስከዛሬ መከበሩ በራሱ ሕገወጥ ድርጊት ነው ብለዋል። ለማመን የሚከብድ ነው ያሉት ይህ ሕገ ወጥነት፣ በተሳሳተ መንገድና በስህተት መቆየቱን ብቻ ሳይሆን እንዲህ ይሰራል ብሎ ለመቀበል እንደሚያስቸግር ነግረውናል። ቀኑ ሕጋዊ የበዓል ቀን ሆኖ ሳይታወጅ ሀገሪቷ ትልቅ ገቢ እንድታጣ የሚያደርግና የማኀበረሰቡ ሕይወት እንዲናጋ መደረጉ በራሱ ወንጀል ስለሆነ ሊያስጠይቅ ይገባል ይላሉ።

በዓላትን የማወጅ ስልጣን የተሰጠው የፌደራሉ ምክር ቤት በግልጽ ባላወጀበት ሁኔታ ቀኑን በዓል ነው ብሎ ሰራተኛን እንዲቀሩ ማድረግ በራሱ አለቆችን ያስጠይቃል። ሰራተኞችም በዓል ነው ብለው ቀርተው ቢቀጡ መከራከር አይችሉም። ይህ ብቻ ሳይሆን ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሰረት ሳይኖረው ካላንደር ላይ ግንቦት 20 ቀን የእረፍት ቀን እንደሆነ እና እንደበዓል ለይተው የሚያወጡ አካላት ሊያስጠይቃቸው ይችላል። ሕጋዊ በዓል ያልሆነው ቀን እንደሆነ ተደርጎ በእነሱ ምክንያት በመሰራጨቱ ብቻ የደረሰ ጉዳት መኖሩን ማረጋገጥ ከተቻለ በሕግ ሊያስጠይቅ እንደሚችል ጠበቃ ካፒታል ነግረውናል።

ግንቦት 20ን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የአሐዱ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥበቡ በለጠ በበኩላቸው፣ ዘንድሮ ግንቦት 20ን በዓል ነው ብሎ ማክበሩ ወንጀል ነው ብለውናል። ግንቦት 20 መጣ ሲባል በጣም ይከፋኛል ያሉት እኚህ ጋዜጠኛና የታሪክ ተመራማሪ በዓል ተብሎ የሚዘከረው ቀን ረብሻ ነበር ብለውታል።

ትሕነጎች ‹‹እኛ ጀግኖች ነን›› በማለት የጦር ሰራዊት ትግልን፣ የደርግ መማረክን በአጠቃላይ የእርስ በእርስ መተላለቅን እንደ ጀብድ የሚያከብሩበት ቀን ነው። ግንቦት 20 ከ1984 ጀምሮ ያለማቋረጥ ቢከበርም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር መከበሩ እንዳሳዘናቸው ነግረውናል። ህወሓት አሸባሪ ተብላ በተፈረደችበት በዘንድሮው ዓመት ቀኑ ሥራ ተዘግቶ የሚከበረው ስርዓቱ ያደረሰው ግፍ ተረስቶ ይመስለኛል ያሉ ሲሆን፣ የተለመደው አካሄድ መቀጠል እንደሌለበት ሐሳባቸውን ገልፀዋል።

እርግጠኛ መሆን ባይቻልም በመንግሥት በኩል ዘንድሮ ለመጨረሻ ጊዜ እንደ በዓል ሥራ ተዘግቶ እንደሚዋል መረጃ እንደደረሳቸው ጠቁመውናል። ቀኑ መዘከሩም ሆነ በመንግሥት ደረጃ መከበሩ ተገቢ ያልሆነው እርስ በርስ የተላለቅንበት፣ የአየርና የባህር ኃይላችን የወደሙበትን፣ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ያለቁበትን ስለሚያስታውስና ብዙዎች የሚከፉበት ስለሆነ ነው ብለውናል። የአሁኑን መንግሥት እያገለገሉ ያሉ እነ ጀነራል ካሳዬ ጨመዳን የመሳሰሉ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን እንዲሁም ብዙኀኑ በጦርነቱ ያለቀና የተጎዳ ቤተሰብን በማሰብ ቀኑ መዘከር እንደሌለበት ነግረውናል። ነገር ግን በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ ተካቶ፣ ኢትዮጵያ ከዛ ቀን ወዲህ ለበርካታ ዓመታት እንዴት እንደጠፋች ትውልድ እንዳይደግመው መማሪያ ሊሆን ይገባል።

ስርዓቱን ያመጡት ግለሰቦችና ቡድናቸው ሙስናን በአገር አቀፍ ደረጃ ያሰለጠኑ፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣን በስፋት ያስከተሉ፣ በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ውድመት ያመጡና ሁላችንንም የጎዱ እንዲሁም ብሔርተኝነት ያነገሱ በመሆናቸው ከማስተማሪያነት በዘለለ የመጡበት ቀን መታሰብ የለበትም ብለውናል።

ግንቦት 20ም ሆነ መስከረም 2 ለእኔ ተመሳሳይ ናቸው ያሉን እኚህ የታሪክ አዋቂ፣ ኃይለ ሥላሴን ጨምሮ በርካታ ትላልቅ ሰዎችን ያጣንበት መስከረም ኹለትም መታወስ የለበትም ይላሉ። ኹለቱን ቀናት ከማክበር ይልቅ የካራማራ ድል እንደሀገር አንድ የሚያደርገን በመሆኑ በእነሱ ቦታ ሊተካ ይገባል ብለውናል። የእለቱን የወደፊት እጣ ፋንታ ሕጋዊ ስርዓቱን በመጠበቅ መንግሥት ሊያስብበትና በቶሎ ሊወስን ይገባል ያሉን ሲሆን፣ አሁን ያለው መንግሥት ዘንድሮ ግንቦት 20ን ከሥራ እና ከትምህርት አቅቦ ያስዋለበትን ምክንያት አስረድቶ ሕዝብን ይቅርታ በመጠየቅ ቀኑን በዓል አድርጎ ማክበሩንና ማስከበሩን ቢያቆም መልካም እንደሆነ ነግረውናል።


ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com