እንድምታው የበዛው የአሜሪካ ማዕቀብ

Views: 73

ባሳለፍነው ሳምንት ከወደ አሜሪካ የተሰማው በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰት አለ በሚል ሽፋን፣ ለትግራይ እና ሌሎች ክልሎች ቀውስ ተጠያቂ ናቸው ያለቻቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትን፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና የህወሓት አባላትን ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚከለክል የቪዛ ገደብ ወይንም ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።
ይህን መሰል ማዕቀብ እና ክልከላ በዓለም አቀፍ ሕግ እንዴት ይታያል የሚለውን ጨምሮ ኢትዮጵያ ከሌሎች የዓለም አገራት ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ላይ፣ እንዲሁም በአገሪቱ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ በተመለከተ የዘርፉ ባለሙያዎችን በማነጋገር የአዲስ ማለዳው ወንድማገኝ ሀይሉ በሀተታ ዘ ማለዳ ተመልክቶታል፡፡

ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው ዘመናት ሁሉ ፍላጎቶቻቸውን እና ጥቅሞቻቸውን ለመጫን የፈለጉ የውጭ ኃይሎች ሲፈትኗት እንደቆዩ ይታወቃል። የአገሪቱን ሉአላዊነት ለመዳፈር የሞከሩ ኃይሎችን ሕዝቦቿ የበዙ ጫናዎችን ተቋቁመው አሳፍረው በመመለስ እና ክብሯን በመጠበቃቸው ሁሌም ስሟ የሚነሳ አገር ሆናለች። ለዚህም የጥቁር ሕዝብ ጀግኖች ያስመዘገቡት ድል ዋና ማሳያ ነው። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን በዘመናዊ ቅኝ ግዛት እሳቤ በተቃኙ የውጭ ኃይሎች አገሪቱ ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ትግል ተከትሎ ፈተናው እጅጉን እያየለባት መጥቷል።

ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ ከወደ አሜሪካ የተሰማው በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰት አለ በሚል ሽፋን እና ለትግራይ እና ሌሎች ክልሎች ቀውስ ተጠያቂ ናቸው ያለቻቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና የህወሓት አባላትን ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚከለክል የቪዛ ገደብ ወይንም ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል። ማዕቀቡ በባለሥልጣናት ላይ ከተጣለው የቪዛ ክልከላ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ መንግሥት በሚሰጥ የምጣኔ ሀብት እና የጸጥታ ዕርዳታ ላይ ገደብ መጣሉን የአሜሪካ መንግስት ማስታወቁ አይዘነጋም።

የዓባይ ፖለቲካ እና የባዕዳን ተልእኮ ጸሀፊና ጋዜጠኛ ስላባት ማናዬ ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ለበርካታ አመታት ጠንካራ የሚባል ግንኙነት ቢኖራቸውም አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር መፈለጉን ይናገራሉ። ከነዚህም ምክንያቶች መካከል ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ የፈጠሩት ጥምረት በተለይም ይህ ጥብቅ ግንኙነት ምስራቅ አፍሪካ ላይ ተጠናክሮ ከወጣ በአገራት መካከል ጣልቃ እየገባን የራሳችንን ፍላጎት የማስጠበቅ ሚናችን ይቀንሳል የሚል ስጋት ስላደረባት ነው በማለት ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል።

አያይዞም የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካ አሁን ላይ ከፍተኛ ኃያላን አገራት ሩሲያ፣ቻይና እና ፈረንሳይን ጨምሮ የአረብ አገራት ከፍተኛ የጦር ሰፈር እና የወደብ ፖለቲካ ቅርምት እያደረጉበት እና እሽቅድድም እያካሄዱ ያሉበት ወቅት መሆኑን ያነሳው ስላባት፣ አሜሪካ የምሥራቁን በተለይም በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ በኩል የቀይ ባህርን በበላይነት የመቆጣጠር ከፍተኛ ፍላጎት ስላደረባት ይህን ውሳኔ ኢትዮጵያ ላይ መወሰኗን አብራርተዋል። ጋዜጠኛ ስላባት አያይዞ ኒውክለር ለሰላማዊ ኃይል ፍላጎት ማስጠበቂያ የሚል ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ስለተፈራረመችው ስምምነት ግንቦት 20፣2018 ላይ ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባወጣው ጽሁፍ ላይ ኢትዮጵያ የኒውክለር ኃይል ባለቤት የመሆን ጅማሮ ላይ ናት ማለቱን ተከትሎ ከምእራብ ዘመሙ የርዕዮት ዓለም አፈንግጦ በሩሲያ ሊደገፍ ይችላል የሚለው ሌላኛው ስጋት እንደሆነባት አንስተውልናል።

ሌላኛው እንደ ምክንያት ከተነሳው መካከል በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ሙሉ በሙሉ በሯን ትከፍታለች በሚል የመጣ የተሳሳተ ምልከታ ነው። በዚህም ረገድ በመንግስት ባለቤትነት ውስጥ ያሉትን ከፍተኛ የኮርፖሬት ተቋማትን ወደ ግል ለማዞር (privatize) ለማድረግ እንዲሁም ለመጠቅለል የነበራት ከፍተኛ ፍላጎት በመክሸፉ መሆኑን ጠቅሷል። ከዚህ ባለፈም ሩሲያና ቻይና በአፍሪካ ላይ የሚያደርጉትን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለመግታት ኢትዮጵያን ማዳከም የሚል ውጥን አሜሪካ እንዳላትም ስላባት ገልጿል። ኢትዮጵያ በጂኦግራፊ አቀማመጧ የታደለች፣ እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅና ቀይ ባህር አከባቢ በርካታ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚከወንባት አገር ከመሆኗ አንጻር የአሜሪካ እና ቻይና ፍልሚያ በኢትዮጵያ ላይ በርትቷል።

በጥቅሉ እነዚህ የተበጣጠሱ ካርታዎች ሲገጣጠሙ አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ ለምን ጫና መፍጠር ጀመረች ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያስቀምጥ ነው ሲል ስላባት ያስረዳል። ይህ አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ የጣለችው ማዕቀብ በሁለትዮሽ እና የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ ሊፈጥር የሚችለውን አሉታዊ ተጽእኖ ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል ብለዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ደመቀ ሀጪሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከአንድ ምዕተ አመት በላይ ያስቆጠረ መሆኑን ገልጸው፣ በተለይም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ጊዜ በ1942 እና 1944 እንግሊዞች ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር በተንቀሳቀሱበት ወቅት ጫናውን ለመቀነስ ከአሜሪካ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ፈጥረው እንደነበር አስታውሰዋል።

አያይዘውም ከዚህ ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ባሻገር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አከባቢ ባሉ አገራት፣ በተለይም በሶማሊያ ሽብርተኝነትን በመከላከል እና የአሜሪካን አጀንዳ በማስፈጸም ረገድ በርካታ ሥራዎችን ሠርታለች ብለዋል። ከዚህ የተነሳም ባለፉት 30 ዓመታት ህወሓት ከዲሞክራቶች ጋር የነበራቸውን ጥብቅ ግንኙነት ተከትሎ አሁን ኢትዮጵያ ላይ ብዙ ጫና ለማሳደር ሙከራ አድርገዋል። በኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 የተደረገው የፖለቲካ ሽግግር እስካሁን ውጤታማ እንዳይሆን እና የቀድሞ ስርአት እንዲቀጥል ለአሜሪካ የሀሰት ትርክትን በመንዛት አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ ጫናዎችን እንድታሳድር ያደረጉት የህወሓት ቡድን ተጽእኖ ፈጥሮ ነው ብለዋል የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ።

አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና የህወሓት አባላት ወደ አገር እንዳይገቡ የከለከለችበት የቪዛ ዕቀባም የአሜሪካን የአመራር ስርአት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው። መሬት ላይ ያለውን እውነታ በእርግጥ አውቀውታል፣ ተረድተውታል ወይ የሚለውን ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባ መልኩ የተደረገ ማዕቀብ ነው ብለዋል። አሜሪካ ይህንን ማዕቀብ ከመጣሏም በፊት የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በሚዳፈር መልኩ “ይህንን አድርጉ፣ ያንን አታድርጉ” በሚል ብሂል የአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ስትገባ መቆየቷም አግባብ እንዳልሆነ ምሁሩ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

አክለውም ይህ ማዕቀብ ወቅቱን እና ጊዜውን ያላገናዘበ ነው ያሉት ደመቀ (ዶ/ር) በጠራ መረጃ ያልተደገፈ፣ሚዛናዊነት የጎደለው እና ገለልተኝነት የሌለበት ነው በማለት እቀባውን አጣጥለውታል። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ግድያዎች፣ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች እና የዘር ጭፍጨፋዎች በተፈጸሙበት ጊዜ ይህን መሰል ጠንካራ እርምጃ እንዳልወሰዱ ጠቅሰው፣ ይህም ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ያስነሳል ሲሉ ደመቀ አንስተዋል። ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ኹለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ለማከናወን እየተዘጋጀች ባለችበት እና ሥድስተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ ደፋ ቀና በምትልበት በዚህ ወቅት ይህ ማዕቀብ መጣሉ ለረጅም ጊዜ ወጣ ገባ የሚለውን እና በብዙ ችግሮች ተተብትቦ የመጣውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት የሚያሻክር መሆኑን ደመቀ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ አብራርተውል።

አሜሪካ ይህን ገለልተኝነት የሌለበት ውሳኔ ማሳለፏ ኢትዮጵያ ሌሎች አገራት ጋር ያላትን ጥብቅ ቁርኝት ሊያጠለሽ ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን አስቀምጠዋል። ኢትዮጵያም በተቻላት መጠን ሉአላዊነቷን እና ነጻነቷን በማይነካ መልኩ አሜሪካ ከኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እጇን እንድታነሳ በሰላማዊ መልኩ መደራደር አለባት ያሉት ምሁሩ፣ ከሌሎች አገራትም ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት ጠቁመዋል። ቀድሞውንም ቢሆን ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተለያዩ ችግሮች የተተበተበ በመሆኑ አሁን ደግሞ ይበልጥ አዘቅት ውስጥ የገባች ይመስላል የሚሉት ደግሞ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ እና የመድረክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ናቸው።

የአገር ውስጥ የፖለቲካ ጉዳዩ እና የውጭ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የአንድ ሳንቲም ኹለት ገጽታ ናቸው ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፣ የውስጡን የስልጣን ሽኩቻ ማረጋጋት ካልተቻለ እና በየጊዜው ሕዝብ ከመንግስት ጋር የሚጋጭ ከሆነ ሌሎች የውጭ አገራት ለኢትዮጵያ ያላቸው አመለካከት የጠለሸ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱንም ሊያሻክር ይችላል ብለዋል። ሱዳንም ብትሆን ዛሬ ላይ ይዛ የመጣችው ፋይል ከዛሬ አንድ መቶ ሀያ አመታት በፊት በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት የነበረውን ሲሆን፣ ይህም የሆነበት ምክንያት ኢትዮጵያ በተለያዩ በአገር ውስጥ እና በውጭ ችግሮች የታጀበች መሆኗን ስለምታውቅ ነው ሲሉ ሀሳባቸውን አስቀምጠዋል።

ስለዚህም የአገሪቱን ህልውና ሊጎዳ የሚችለውን ይህንን የመሳሰሉ የውስጥ የፖለቲካ ችግሮችን መፍታት ከተቻለ የውጭ ችግሮችን እና ጫናዎችን በቀላሉ መከላከል ይቻላል ባይ ናቸው። የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌ በበኩላቸው ከላይ ከተነሱት ሃሳቦች በተለየ መልኩ ሀሳባቸውን አስቀምጠዋል። እንደ አቶ ሙሉብርሃን ሃሳብ ከሆነ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ለአያሌ አመታት መልካም የሚባል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የነበራቸው ቢሆንም፣ አሜሪካ የቀድሞውን የኢሕአዴግ መንግሥትን እንደፈለገች የምትዘውርበት ሁኔታ ነበር።

ባለፉት ሦስት አመታት በኢትዮጵያ የመጣውን የለውጥ መንግስት ተከትሎ እንደ ከዚህ ቀደሙ እጅን ለመጠምዘዝ እና የራሷን ፍላጎትና ጥቅም ለማስጠበቅ አገራችን ምቹ ስላልሆነችላቸው ነው ይህን እርምጃ የወሰደችው ብለዋል። ይሁን እንጂ አሜሪካ ለብዙ አመታት ለኢትዮጵያ ስታደርግ የቆየችውን ሰብአዊ እና የምጣኔ ሀብታዊ ድጋፍ ላይ ማዕቀብ መጣሏ የኢትዮጵያን ህልውና ሊጎዳ አይችልም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ይሁንና በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት እና ሌሎች ድጋፎች ላይ የተጣለውን ማዕቀብ መቋቋም የሚቻለው የውስጥ ችግሮቻችንን በመፍታት እና አንድነታችንን በማጠናከር ነው ያሉት አቶ ሙሉብርሃን፣ የኢትዮጵያን ህልውና አጠናክረን ማስቀጠል ይኖርብናል ብለዋል።

አያይዘውም የኢትዮጵያን የድህነት እና የተመጽዋችነት ታሪክ ፈጽሞ ሊለውጥ እንዲሁም ወደ አዲስ የእድገት ምዕራፍ ሊያሸጋግር የሚችለውን የታላቁን ህዳሴ ግድብ ኹለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ስናከውንና ግድቡን ስናጠናቀቅ ያን ጊዜ አሜሪካ እና ሌሎች የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ አገራት ኻፍረትን ይከናነባሉ ብለዋል። በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰት አለ በሚል ሽፋን እና ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ኢትዮጵያን ለመጉዳት የሸረበችው ሴራ የትም ሊያደርሳት አይችልም የሚል አቋምም ይዘዋል። አክለውም የተጣለውን ማዕቀብ ተከትሎ ኢትዮጵያ ከጎረቤት እና ሌሎች የአለም አገራት ጋር ያላትን የሕዝብ ለሕዝብ እና የኹለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ሊያሻክር ይችላል ተብሎ የተፈራውም ቢሆን፣ ኢትዮጵያ መሬት ላይ ያለውን እውነታ እና ምንም አይነት ጥፋት እንደሌለባት ለዓለም አቀፉ

ማኀበረሰብ በማስረዳት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን አጠናክራ መቀጠል ትችላለች ብለዋል ሙሉብርሃን ኃይሌ። ለዚህም በተለያዩ አገራት ያሉ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለባቸው ጠቁመዋል። እነዚህ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ የማንሰራ ከሆነ ግን የፈሩት ይደርሳል ሊሆንብን ስለሚችል ትኩረት ልንሰጠው ይገባልም ብለዋል። አሜሪካ ከጣለችው የጉዞ ክልከላ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ በሚሰጥ ማንኛውም ኢኮኖሚያዊ እና የጸጥታ ድጋፎች ላይ ዘርፈ ብዙ ገደቦች መጣሉን ተከትሎ የመከላከያ ንግድ ቁጥጥር ፖሊሲም ከዚህ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ይደረጋል መባሉም ይታወቃል።

የተጣለው ማዕቀብ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ባሻገር በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት እና ግለሰባዊ ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል የሚል የተቃርኖ ሃሳብ ያላቸው ደግሞ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርኸ ተስፋ (ዶ/ር) ናቸው። በዚህም ረገድ ኢትዮጵያ ለልማት ፕሮጀክቶች ከአሜሪካ የምታገኛቸው የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፎች ሊቋረጡ እንደሚችል የገለጹት ቆስጠንጢኖስ አሜሪካ እጇ ረጅም ስለሆነ በአውሮፓ ያሉ የልማት አጋሮቿን በእጅ አዙር ለኢትዮጵያ ድጋፍ እንዳያደርጉ፣ ከወለድ ነጻ የብድር አገልግሎት እና የቴክኒክ ድጋፍ እንዳይሰጡ፣ እንዲሁም እነሱም በተመሳሳይ ማዕቀብ እንዲጥሉ እጃቸውን በመጠምዘዝ ተጽእኖ ልታሳድር እንደምትችል ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

አዲስ ማለዳ ከዲፕሎማሲያዊ እና ከምጣኔ ሀብቱ ጫና ባሻገር በባለሥልጣናቱ ላይ የተጣለው የቪዛ እገዳ ወይንም ማዕቀብ በሕግ አግባብ እንዴት ይታያል ስትል የሕግ ባለሙያን ጠይቃለች። የዓለም አቀፍ ሕግ አማካሪ እና ጠበቃ የሆኑት ጥጋቡ ደሳለኝ አሜሪካ ወደ ራሷ ሉአላዊ ግዛት እንዳይገቡ ማንኛቸውንም ባለሥልጣናትንም ሆነ ግለሰብ የመከልከል መብት እንዳላት አስረድተዋል። ለዚህም እንደማሳያ ሊሆን የሚችለው የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራንፕ ወደ ሥልጣን በመጡ ሰሞን ከአፍሪካም ሆነ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ይመጡ የነበሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ ስትከለክል እንደነበር አስታውሰዋል።

አሜሪካ የሰብአዊ መብት አስከባሪ ነኝ የምትል እና በዓለም መንግስት የማኀበረሰብ ግንኙነት ላይ የጎላ ሚና አለኝ ብላ የምታስብ አገር ናት ብለዋል። አክለውም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና አውሮፓ ህብረት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላላት ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠረው ችግር በኢትዮጵያ መንግስት፣ በአማራ ልዩ ኃይል አዛዦች እና የህወሓት አመራሮች ላይ ሚና እንዳላትም አስረድተዋል። ለዚህም ባለሥልጣናቱን እና የህወሓት አመራሮችን ወደ ሉዓላዊት ግዛቷ እንዳይገቡ ማድረጓ የሕግ ጥሰት ፈጽማለች የሚያስብላት አይደለም ብለዋል፤የህግ ባለሙያው ጥጋቡ ደሳለኝ።

ይሁን እንጂ ትግራይ ውስጥ በሕግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት የተፈጠረውን ችግር በተባበሩት መንግስታት፣ በሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ እና በሚዲያዎቿ በኩል ያለውን እውነታ ሳታጣራ ማዕቀብ በመጣል ጫና ለማሳደር መሞከሯ ሊያስወቅሳት እና ሊያስተቻት ይችላል ብለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት አሜሪካ የጣለቻቸው ገደቦች ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት ያላገናዘበና ለአሜሪካ መንግስትና ሕዝብ ጭምር የማይጠቅም ነው። አገራቱ በቀጣናው ሠላምና ደህንነት በማስጠበቅ እንዲሁም ሽብርተኝነት ለመከላከል በትብብር የሚያከናውኑት ሥራ ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

የቪዛ ገደቡና ሌሎች ተዛማጅ እርምጃዎች በኢትዮጵያ መንግስት ተቀባይነት እንደሌላቸውና አሜሪካ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያበቃ ምክንያት እንደሌላት አምባሳደር ዲና ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያለውን ጉዳይ ‘ማጋጋል’ አትፈልግም፤ የሁለትዮሽ ግንኙቱ እንዲበላሽ አትሻም፤ አሜሪካ ውሳኔዋን ዳግም ታጤነዋለች ብለን ተስፋ እናደርጋለን ሲሉም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ነጻነት የማይታለፍ ቀይ መስመር፣ በገንዘብም የማይቀየር የሕልውና ጉዳይ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ዲና ይህንን ሁሉም ሊያውቀው የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል። በሌላ በኩል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በትግራይ ክልል ያሉ እውነታዎችን እየካደ መሆኑን፣ ይህም ያለውን ሁኔታ ካለማወቅ የመነጨ ሳይሆን ጉዳዩን ከራስ ጥቅም ጋር በመያያዙ እንደሆነ አክለዋል።
በትግራይ ክልል ከሠብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነትና አቅርቦት እንዲሁም ከሠብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ ይነሱ የነበሩ ጉዳዮች ምላሽ ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com