የእለት ዜና

በአገራችን የመጀመሪያው ዓለም-አቀፍ ሚዲያ ሊቋቋም ነው

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ‹ግሎባል ቴሌቪዥን ኔትወርክ ኦፍ አፍሪካ› የተሰኘ ዓለም-አቀፍ ሚዲያ ሊቋቋም እንደሆነ ለ15 ዓመታት የውጭ ሚዲያ ተወካይ እና የተቋሙ መሥራች የሆኑት ጋዜጠኛ ግሩም ጫላ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ይህ Global Television Network of Africa (GTNA) መቀመጫውን እና ዋናው መስሪያ ቤቱን በአዲስ አበባ የሚያደርግ ሲሆን፣ 5ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያርፋል ተብሎ ይገመታል። በአጠቃላይ ሙሉ የGTNA ግንባታን ለመስራት 450 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ የነገሩን ግሩም ሚዲያውን ለማቋቋም በርከታ አጋሮች ጋር በጋራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የገበያው ሁኔታ ተለዋዋጭ እንደመሆኑ መጠን ግንባታው እስኪጠናቀቅ ከተጠቀሰው ገንዘብ በላይ ሊፈጅ ይችላልም ተብሏል።

የሚዲያ ተቋሙ ሙሉ በሙሉ ስርጭቱን በእንግሊዝኛ ብቻ የሚጀምር ሲሆን፣ ለ24 ሰዓት ዜናዎች፣ ዶክመንተሪ፣ ቃለመጠይቅ፣ የባህል እና መዝናኛ ዝግጅቶችን እንደሚያካትት ታውቋል። ይህን ፍቃድ በተመለከተ አዲስ ማለዳ ግሩምን የጠየቀች ሲሆን፣ ይህ ሚዲያን ለማቋቋም ከሚያስፈልጉት ሕጋዊ ሂደቶች መካከል አንዱ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ፍቃድ መውሰድ መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት ሚዲያውን ለማቋቋም በሃሳብ ደረጃ ስለሆነ ባለሥልጣኑ የሚጠይቃቸው መስፈርቶች በሚሟሉበት ወቅት ፈቃድ ለመውሰድ መታቀዱን ግሩም ገልጸዋል። ይህን ተከትሎ GTNA መገንባት የሚያስችል የኢንቨስትመንት ፈቃድ ማግኘቱ ተጠቁሟል።

አዲስ ማለዳ የሚዲያ ፈቃድን በተመለከተ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱን የጠየቀች ሲሆን GTNA ፍቃድ አለመውሰዱን የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ ገልጸዋል። ይህ ሚዲያ ለኢትዮጵያውን ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ለሚገኙ አፍሪካውያን ድምጽ እንደሚሆን የተናገሩት ግሩም ፣ አፍሪካውያን ብሎም ኢትዮጵያውያን ሀሳባቸውን የሚገልጹበት፣ የውስጥ ችግሮችን በአደባባይ የሚያሳዩበት እና የፈጠራ ሃሳቦችን ለምዕራባውያን የሚያስተላልፉበት ተቋም ይሆናል ሲል ግሩም ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። በርካታ የአፍሪካ አገራት ሀሳቦቻችንን ለአለም የምናስተዋውቀው በውጭ ሚዲያ ተወካዮች አማካይነት ነው ያሉት ግሩም፣ አሁን ዘመኑ የሚጠይቀውን የሚዲያ ተደራሽነት መሰረት በማድረግ GTNAን ለማቋቋም ታስቧል።

GTNAን የመሰሉ ሚዲያዎች መቋቋም የነበረባቸው በፊት ነበር። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ጊዜው ሳይረፍድ መቋቋሙ ትልቅ ጥቅም አለው ተብሏል። ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሚዲያ ማዋቀር ረጅም ዓመት መውሰዱ አይቀርም። በመሆኑም ይህ ሚዲያ በ2 ዓመት ውስጥ ሁሉንም ደረጃዎች በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ይገባል ሲል ግሩም ተናግሯል። በነዚህ ኹለት ዓመታት ውስጥ ሙሉ ግንባታውን አጠናቆ ወደ ሥራ ለመግባት የተለያዩ አራት ደረጃዎች ይኖሩታል። የመጀመሪያው በማህበራዊ ድረ-ገጽ የተለያዩ ዝግጅቶችን ማሰራጨት ሲሆን፣ በኹለተኛ ደረጃ ለስቱዲዮ ግንባታ የሚያስፈልጉ ዘመናዊ እቃዎችን የት እንደሚገኙ ዳሰሳ ማድረግ እና ለስቱዲዮ መገንቢያ የሚሆነውን መሬት መረከብ ነው።

ሦስተኛው ሁሉንም ግንባታዎች በታቀደው ልክ መገንባት ሲሆን፣ በመጨረሻም የስርጭት ተግባሩን ማስኬድ ነው ሲሉ መስራቹ አስረድተዋል። እንደ እሳቸው ገለጻ ከሆነ GTNA በዚህ ዓመት የመጀመሪያውን ደረጃ ስርጭት በማኀበራዊ ድረገጾች ለማስጀመር አቅዷል።
መንግስት ጋር ያሉ የቢሮክራሲ ፈተናዎች በታቀደው ዓመት ስራውን ለማስጀመር እንቅፋት እንዳይሆንባቸው የሚመለከተው አካል የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል። ሚዲያውን ለማቋቋም የታቀደውን መሬት ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር እና መሬት አስተዳደር መልካም ምላሽ ማግኘቱን የገለጹት ግሩም፣ አዲስ አበባ ያለባትን የመሬት ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት በቅርቡ መሬት እንረከባለን የሚል ተስፋ አለኝ ብለዋል።

ይህን ቦታ በሚረከቡበት ጊዜ ሚዲያውን ከማቋቋምም በላይ የልህቀት ማዕከል፣ ኦዲዮ ቪዥዋል ላይብረሪ እና ላብራቶሪ በተጨማሪም ለጋዜጠኞች መኖሪያ ቤት ለመገንባት ታቅዷል ሲል ግሩም ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። ተቋሙ የሚያስፈልገውን የስቱዲዮ እቃዎች ለመግዛት የገበያው ሁኔታ ጥናት እየተደረገ ሲሆን፣ እቃዎቹ ከጣሊያን፣ ከዱባይ፣ ከቻይና እና ከአሜሪካ የሚገዙ ናቸው ተብሏል። ሚዲያ የሕዘቡን ሀሳብ ለማንጸባረቅ ከሚረዱ ተቋማት መካከል አንዱ ነው። ምዕራባውያን ያሏቸውን ሚዲያዎች በሙሉ በመጠቀም የሚያስተላልፉት መልዕክት ከራሳቸው አገር አልፎ አለም ላይ ተጽእኖ ይፈጥራል። ይህንን ታሳቢ በማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ ዓለም-አቀፍ ሚዲያ ተቋቋመ ማለት ከዓለም ጋር የምንዋጋበት መከላከያ ሰራዊት እንደማቋቋም ይቆጠራል ሲሉ ግሩም ተናግረዋል።

ይህ ሚዲያ ሲቋቋም ከማንኛውም ፖለቲካ፣ ብሔር እና ኃይማኖት የጸዳ ገለለተኛ ተቋም ይሆናል ተብሏል። አሁን ባለው ሁኔታ ሚዲያ ማቋቋም ከባድ ቢሆንም ኢትዮጵያ እንደዚህ አይነት ዓለም-አቀፍ ተቋም ካላት ያሉባትን ችግሮች በመቅረፍ ሀሳቧን ለዓለም እንደሚያስተዋውቅላት ተነግሯል።


ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!