ሳንጠላለፍ እንሸናነፍ!

Views: 50

6ተኛው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ እየተቃረበ ሲመጣ የእርስ በርስ ዘለፋውና ሀሜቱ እየበዛ መጥቷል። ከ1997ቱ በስተቀር ከዚህ ቀደም በተደረጉት ምርጫዎች ከረር ያለ ፉክክርም ሆነ እሰጥ አገባ ተደርጎ አያውቅም። ያም ቢሆን ግን የጎንዮሽ መናቆሩ በምርጫ ወቅት ጠፍቶ አያውቅም። ሕዝብ የፈለገውን እንዲመርጥ አማራጭ ነን የሚሉ ፓርቲዎች ስርዓት ባለው መንገድ ስለራሳቸው ብቻ ማስተዋወቅ እንዳለባቸው አዲስ ማለዳ ታምናለች። ስለምርጫ ክርክር በተነሳ ቁጥር እየተስተዋለ የመጣው ነገር አንዱ ሌላ ተፎካካሪን የማጠልሸት ተግባር ነው። የተቀናቃኝን ደካማ ጎን በማንሳት ራስን ከፍ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት እንደ ብልጠት እየታየ የፈጠራ ወሬም እየታከለበት ውጤታማ ለመሆን እየተሞከረበት ነው። አንድ ፓርቲ የሚጠበቅበት ስለራሱ በጎ ጎን ማስተዋወቅ፣ ራሱን ለመተቸት ደረጃ ከበቃም የሚወቀስበትን ዘርዝሮ አስተካክላለሁ ማለት ነው። ይህን ማድረግ ካልቻለ ዝም ማለት እንጂ ስለሌላው ፓርቲ የማውራት ሃላፊነትም ሆነ መብት ሊኖረው አይገባም። ሁሉም ስለራሱ ብቻ ማውራት ሲጠበቅበት ይህን ትቶ ስለሌላው ክፋት ለማስረዳት መሞከር መራጩን ከማታለል ተለይቶ የሚታይ አይደለም።

“እኔ እንዲህ አደርጋለሁ”፣ “ እንዲህ አይነት ፖሊሲ አለኝ” ብሎ በጎ በጎውን ማሳወቁ ተግባራዊ ካልተደረገ ለመሸናነፍ ሳይሆን ለመጠላለፍ በር ይከፍታል። መራጭ ህሊናውን ተጠቅሞ ከሰማው ማስተዋወቂያ ተነስቶ ራሱ ገምግሞ ይመርጣል እንጂ የሌላ ተፎካካሪን ግምገማ የሚሰማበት ምንም አይነት አመክንዮአዊ ነገር አይኖርም። “እገሌ እንዲህ አድርጓችኋል” ወይም “እንዲህ ሊያደርጓችሁ ነው” እያሉ ለሕዝቡ መደጋገም፣ ለሕዝብ እኔ ብቻ አውቅልሀለሁ ከማለት አባዜ ምንም አይለይም። አሁን አሁን እየተለመደ የመጣውን የፖለቲካ ፓርቲዎች አካሄድ ድግስ ደግሶ ብሉልኝ ከሚል ሰው ማመሳሰል ይቻላል። ደጋሹ ብፌ ዘርግቶ ከየአይነቱ ደርድሮ ተጋባዡ ሕዝብ ተጠርቶ እንደገባ ስለአመጋገብ አያስተምርም። “ከእንጀራ ዳቦ ብቻ ይሻልሀል፣ ይህን ይህንን ወጥ ብቻ አውጣ” ካለ የምግብ ምርጫ ሳይሆን አስገድዶ ማብላት ይሆናል። ይህ አይነት ተግባር ሕዝቡ የሚበላውን አይነትና መጠን መወሰን ብቻ ሳይሆን ከስር ከስር እየተከታተሉ እንዴት መብላት እንዳለበት በጅምላ ተመሳሳይ መንገድን ከመምራት አይተናነስም። ይህ የጋባዡ አካሄድ ቶሎ ካልተስተካከለ ቀጣዩ ጋባዥ፣ “ለእናንተ ብዬ” ብሎ “እኔ ብቻ ካላጎረስኩ” ብሎ ላለማሰለፉ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። በዚህ አይነት ልማድ የተማረረው፣ የምግብ ምርጫውን ራሱ የሚያውቀውና ሌላው እንዲያከብርለት የሚፈልገው ሕዝብ ከነጭራሹ ድግስ መሄድ ያቆማል። ምርጫው ተቀባይነት ስለማይኖረው ተሳታፊውም እያደር በመቀነሱ በኋላ ቢለመንም ስለማይመጣ ደጋሽም ይጠፋል።

የምርጫ ስነምግባር ህጉ አንዱ በሌላው ላይ አሻጥርም ሆነ የጥላቻ ንግግር እንዳያደርግ ቢከለክልም ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም። ተቆጣጣሪው አካል የእያንዳንዱን ፓርቲ አባላት አስተያየትም ሆነ የድርጅቱን እንቅስቃሴ ተከታትሎ እየፈተሸ መስመር ማስያዝ አስቸጋሪ ሊሆንበት ይችላል። በዚህ ረገድ ሁሉም ማድረግ ያለበትን ከሌለበት ለይቶ እንዲያውቅና ደጋፊዎቹን እንዲያሳውቅ ይጠበቃል። የደጋፊ ተግባር ቡድኑን ማስቀጣት እንደሚችል ቢያንስ ከእግርኳስ ህግ መማር ግድ ይላል። ሁሉም ራሱን እንዲቆጣጠር ማድረግ የሚያስፈልገው ጨዋ ለመባል ሳይሆን ባለፈው ግማሽ ክፍለዘመን እንደተጠፋፉት ፓርቲዎች ላለመተላለቅ ሲባል መሆን አለበት። መሪዎች ሲሰዳደቡ ደጋፊዎች በቃላት ብቻ አያቆሙም። መናናቅ ካሳዩ ሕዝቡ እስከመገዳደል ሊሄድ እንደሚችል ሊታወቅ ይገባል።

በቀድሞ ዘመን “አንተ ምራ፣ አንተ ቅደም” የሚል ባህል ስለነበረን “እኔ ልሁን” በሚል ፉክክር ምን ሊፈጠር እንደሚችል የማወቁ ሰፊ ልምድ የለንም። የወደደው ሲዘለፍ ደስ የሚለው ወይ በትእግስት የሚያልፍ ያን ያህል በሌለበት ሀገር አንድ እንኳን ደጋፊ ያለውን ግለሰብ ስም ማጠልሸት ይበልጥ ስለሚያራርቅ ጉዳቱ ከፍተኛ ይሆናል። ፓርቲዎች ባይሞጋገሱም እርስ በርስ እየተከባበሩ መዝለቁ ሕዝብን ለመሳብና የሕብረተሰቡን ስነልቦና ለመረዳት እንደሚጠቅም አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።

በዘንድሮው ምርጫ እየታዩ ካሉ አላስፈላጊ የእርስ በርስ ነቀፌታዎች ውስጥ በርክቶ የሚታው ስልጣን ላይ ባለው ፓርቲ የሚሰነዘረው ነው። ተፎካካሪ ፓርቲዎች እርስ በርስ ከሚናቆሩት ይበልጥ በየፊናቸው ፓርቲው ላይ የሚሰነዝሩት ቢበልጥም አንዳንዶች እርስ በርሳቸው ያላቸው ጥላቻም ተወዳዳሪ የለውም። ስልጣን ላይ ባለ ፓርቲ የሚደረግ ውንጀላም ሆነ ነቀፌታ ከሁሉም የሚብሰው በደጋፊዎቹ ጉልበትን መሰረት ያደረገ እርምጃ ሊያስወስድ መቻሉ ነው። “ተቃዋሚ” ሳይሆን “ተፎካካሪ” ነው የምንላቸው ሲባል ሕዝቡ ደስ ብሎት እንዳልነበር፣ ብዙ ሳይቆይ ከእኛ ፖሊሲ በስተቀር የሌሎቹ ድርሰት ነው የሚል ማስረጃ የሌለው ዘለፋ መከተሉ ብዙዎችን አስገርሞ ነበር። ይህንን ማረም ሳይቻል በቅርቡም የሚረባ ፖሊሲ እንደኛ ያለው የለም እስከመባል ተደርሷል።

በሌላ በኩል፣ ስራ ላይ ያልታየን ፓርቲ በማንነት መነፅር እያዩ የአባላቶቹን ስብጥር በመላምት እያቀረቡ መገምገምና መራጭን ማወናበድ ትክክል አይሆንም። አንዳንዶች ማሸነፍ የምንችለው እኛ ነን፣ እንዲሁም መንግስት መመስረት የምንችለው እኛ ብቻ ነን ሲሉ ይደመጣሉ። ይህ ሕዝብን አማራጭ የለህም የሚል ይዘት ያለው የሚመስል አባባል ተገቢ አይሆንም። የሚያሸንፉትን ወንበር አይተው ግለሰቦችም ሆኑ ፓርቲዎች ጥምረት በመፍጠር መንግስት መመስረት አይችሉም የሚል መልዕክትን ያስተላልፋል። በምርጫ የሚወዳደር ሁሉ መንግስት የመመስረት አላማ እንደማይኖረው ከግል ተወዳዳሪዎች አላማም መረዳት ይቻላል። በፓርቲም ሆነ በግል የሚወዳደሩ የወከላቸውን ማህበረሰብ ድምፅ እንዲያሰሙ እንጂ የራስን ወይም የቡድንን አጀንዳ መንግስት ሆኖ ለማስፈፀም አይደለም። በሌላ በኩል፣ እንዲህ አይነት ማህበረሰቦች ይበልጥ ያሉበት ነው እየተባለ የሆነ ፓርቲ በዘር ወይም በሃይማኖት እንዲፈረጅ ማድረጉም ተገቢ አይሆንም። ምርጫ ቦርድ ህጋዊ ነው ብሎ እስከፈቀደ ድረስ ቅሬታን በተገቢው መንገድ ማቅረብ እንጂ ለህዘብ ማናፈሱ ይበልጥ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። የዚህ ዘር ወይም የእገሌ ሃይማኖት ፓርቲ ነው ብሎ እያበሻቀጡ መግለፁ መረጃው እውነት ቢሆን እንኳን ማንነታቸውን መሰረት አድርገው ለመምረጥ ለሚፈልጉ የማሕበረሰብ ክፍሎች ማስታወቂያ ይሆናል እንጂ ተግባሩን አይቀንሰውም። ማጥላላት ወደትክክለኛ አካሄድ ከመመለስ ይልቅ የአፀፋ ጥላቻን ይፈጥራል። ግለሰቦች በዘርም ይሁን በሃይማኖት ለይተው እንዳይመርጡ ማድረግ አይቻልም፣ ህጋዊም አይሆንም። ይህ እንዳይሆን ማስተማር እንጂ ሰው ብሄሩን እንዲደብቅ ሃይማኖቱንም እንዲሸሽግ ማድረግ አይቻልም።

መራጭም በፈለገው መመዘኛ አይቶ ይወክለኛል ያለውን የሚያምነውን ከመምረጥ ሊታገድ እንደማይገባ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች። በአንፃሩ የሚለያዩ ይህን መሰል መስፈርቶችን ፓርቲዎች በፖሊሲቸው ማስቀመጥም ሆነ ዘርና ሃይማኖትን መሰረት አድርገው በይፋ መንቀሳቀስም ሆነ መደራጀት እንደሌለባቸው ግልጽ ነው።

በስነልቦና ባለሙያዎች እንደሚነገረው ሰው በአደባባይ የተቸውን ይጠላል፣ ያደነቀውን ደግሞ ይወዳል። ማንኛውም ግለሰብ የሚጠላው ሰው የሚነግረውን ሳይሆን የሚወደው ሰው የተናገረውን ሰምቶ በቶሎ እንደሚቀየር እሙን ነው። ጠላት ብሎ የፈረጀው ወገን ቢተቸው የተቺውን ደካማ ጎን ፈልጎ ይነቅፋል ያጣጥለዋል እንጂ፣ ግትርነቱን ትቶ ለመሻሻል እንደማይሞክር ከልምዳችንም እናውቃለን። በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን አልሸነፍ ባይነት ባህሪ ከልክ በላይ ስለተጠናወተን ይህን ባህሪያችንን ሳንተው የሚያሸናንፍ የእርስ በርስ ውድድር ውስጥ መግባት አልነበረብን ይሆናል። ይህ ባህሪያችን እያለ መሰዳደቡ አልበቃ ብሎ ወደመጠላለፉም ገብተናል። የእጩዎች መገደል መታሰር መንገላታትና ንብረት መውደም እየተደጋገመ መጥቷል። የፓርቲ አባላት ላይ ያልቆመው ይህ ተግባር ወደ መራጮችም ካመራ ቆይቷል። ሕዝብ በኖረበት እንዳይመርጥ ጥቃት በመሰንዘር መግደሉና ማፈናቀሉ እንደቀጠለ ነው። ሕዝብ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ እንዳይመርጥ ማድረግና በህገወጥ መንገድ የራስ የተባሉ ወገኖች ይበልጥ እንዲመርጡ ለማድረግ እየተሞከረ ይገኛል። “ሳይቃጠል በቅጠል” እንደሚባለው በቀረው ጊዜ ለማሻሻል ካልተሞከረ መዘዙ ከባድ ይሆናል። ምርጫው ወደ ፍጥጫ ከመቀየሩ በፊት ሁሉም ሊያስብበትና ወደ ትክክለኛው መስመር መግባት እንዳለበት አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com