ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንዲቆሙ ምሁራን ጠየቁ

Views: 69

በኢትዮጵያ ላይ የውጭ ጫና እየበረታ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚቆሙበት ጊዜ አሁን እንደሆነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ባላት አቅም እና እውቀት ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ መቀጠሏን እና ለሁለተኛው ዙር የግድቡን የውሃ ሙሌት ለማከናወን በምትዘጋጅበት በዚህ ወቅት አለም አቀፍ ጫና እየበረታ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች እየተባባሰ በመጣው አለመረጋጋት ላይ የምእራባውያን ጫና በታከለበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵውን በጋራ የሚቆሙበት ጊዜ አሁን ነው ይላሉ።
የኢትዮጵያን ሰላም እና እድገት የማይፈልጉ የውጭ ሀይሎች ኢትዮጵያን ለማተራመስ ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹት ምሁሩ በአገር ውስጥ የማንስማማባቸው አንዳንድ ጉዳዮች ቢኖሩም እንኳ እንዚህን ሁሉ ወደ ጎን በመተው አንድነታችንን በማጠናከር የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ልናስጠብቅ ይገባል ብለዋል።
አገሪቱ በአሁን ሰአት ካለችበት ችግር እና ከውጭ አገር ጣልቃ ገብነት ለመታደግ ኢትዮጵያውያን የውስጥ ችግሮች ላይ ትኩረት ባለማድረግ፣ እንዲሁም የትውልድ ተወቃሽ እንዳንሆን አገራችንን ልንጠብቅ ይገባል የሚሉት ደግሞ በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የአለም አቀፍ እና ማህበራዊ ጉዳዮች መምህር እና ተመራማሪ ያዕቆብ ወርቁ (ዶ/ር) ናቸው።
የእኛ የእርስ በእርስ መጠላለፍ እና የጎሪጥ መተያየት ጠላቶቻችን እንደፈለጉ እንዲያጠምዱን ወጥመድ ይዘረጋል በማለት ለችግሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሰሞኑን አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የጣለችው ማእቀብ በቀጥታ የራሷን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ነው የሚሉት ያእቆብ አርሳኖ በተለይም አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ላይ ያላትን ተሰሚነት ለማሳደግ በቀጥታ ለመጠቀም የፈለገችው ግብጽን ነው ብለዋል።
ግብጽ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል የነበረውን የተኩስ አቁም ስምምነት አሸማጋይ በመሆን የነበራትን ተሳትፎ ያመሰገነችው አሜሪካ ናት።
ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ለግብጽ ምላሽ የሰጠችው አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጠር እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለማስተጓጎል እየሰራች እንደምትገኝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ያዕቆብ አርሳኖ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ የጣለችው ማእቀብ በትግራይ ክልል በተደረገውን የህግ ማሰስከበር ዘመቻ ላይ እና በክልሉ የሰብአውዊ መብት ረገጣ አለ የሚለውን ሰበብ ተከትሎ ቢሆንም በዋናነት ግብጽን ወግነው እንደሆነ ማሳያ ነው ብለዋል ያዕቆብ ወርቁ።
በታሪክ ኢትዮጵያ በርካታ የውጭ አገር ጣልቃ ገብነትን አስተናግዳለች በዚህ ጉዞዋ ከውጭ የሚቃጡ ጥቃቶች በህዝቦቿ አንድነት ተመክቶ አሁን ካለችበት ደርሳለች ያሉት ያዕቆብ አርሳኖ፣ በቀጣይም ጫናው ከዚህ በላይ ሊበረታ ስለሚችል ህዝቡ ውስጣዊ አንድነቱን በማጎልበት መንግስትም የአገሪቱን ሰላም እና አንድነት ለማስጠበቅ አበክሮ መስራት እንዳለበት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ምሁራን አሳስበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com