የእለት ዜና

አባይ በታሪክና በጥበብ ሥራዎች ሲቃኝ

“አባይን በጭልፋ”፣ “አባይ ማደሪያ የለዉ ግንድ ይዞ ይዞራል” ከሚሉ የቁጭት ቃላት ወደ ተስፋዉ ጉዞ መጓዝ ከጀመርን እነሆ አስር አመት ሞላን። ከግድቡ ጋር በተገናኘ ‹‹አባይ በህጻናት አንደበት ›› በሚል ርዕስ በጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት ሚያዝያ 15 ቀን አንድ መድረክ ተካሂዶ ነበር። ዝግጅቱ ግድቡ የመሰረት ድንጋይ ጋር የተጣለበትን በማስመልከት አመቱን ሙሉ ይቀጥላል ሲሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ና ሁነት አስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የሲቪል ማህበራት እና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አመነ በቀለ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ገልጸዋል።

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ተብሎ በተደረገ ጥንቃቄ 200 ህጻናት እና 40 የሚጠጉ ከተለያዩ ተቋማት የተጋበዙ እንግዶች በተገኙበት በጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት ታዳጊዎቹ የተለያዩ የሥነ- ጽሁፍ ስራዎቻቸዉን ማቅረባቸዉንንም አመነ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ገልጸዋል። “አባይ በህጻናት አንደበት” የሚለዉ ፕሮግራም የግድቡ መሰረት ድንጋይ ከተጣለ ከሰባት አመት በኋላ ዘግይቶ የተጀመረ መሆኑም ታዉቋል። ይህ ፕሮግራም በግድቡ ዙሪያ ከሚዘጋጁ ፕሮግራሞች አንዱ ነዉ።
የግድቡ አጀማመር ትዉስታ

መጋቢት 24 / 2003 የብዙ ትዉልዶችን ቁጭት እዉን ለማድረግና ኢትዮጵያንም ሆነ ጎረቤቶቿን ሊጠቅም የሚችል አንድ ትልቅ ብስራት በመላዉ ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ተሰማ። ያም በአባይ ወንዝ ላይ ግዙፍ የኤሌትሪክ ሀይል ማመንጫ ሊሰራ የመሰረት ድንጋይ መጣሉ ነበር። ታዲያ ይሄ የተስፋ ብስራት ጉዞዉ አልጋ በአልጋ አልነበረም። ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን መገንባት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በተለይ ግብፅ ተቃውሞዋንና ስጋቷን በተለያዩ መንገዶች ስትገልጽ እስከ ዛሬ ደርሳለች። ግብፅ ኢትዮጵያ የገንዘብ የምታገኝባቸዉን መንገዶች ሁሉ ስትዘጋ፣ ሱዳንና ሌሎች የተፋሰሱም ሆነ የማይመለከታቸዉ አገራት ጋር በመሄድ የግድቡን ግንባታ እንዲቃወሙ ስትማጸን ቆይታለች። ግብፅ በየሚዲያዉ፣ በጥበብ ሙያተኞች እና በተከታዮቻቸዉ አማካይነት የዉስጥ ግጭቶቻችንም በመጠቀም ጭምር ግድቡ እንዳይገደብ ኢትዮጵያዊያንን ተስፋ ለማስቆረጥ ብዙ ሰርታለች፤ እየሰራችም ነዉ።

“ትውልድ እንደ ጅረት የተቀባበለው” የሚለው በታዳጊ ህጻናት የተዜመው ዜማም በ2003 የግድቡን የመሰረት ድንጋይ መጣል ሃሳብ ተመርኩዞ ልብን የሳበ መነጋገሪያ የጥበብ ስራ እንደነበር ይታወሳል። ሌላው “ አባይ ነጋ ጠባ ሀብቱን ያፈሰዋል፣ ጭስ አልባው ነዳጅ ብለው ምን ያንሰዋል” ስትል ገነት ማስረሻ ያላትን ቁጭት ግድቡ ከመጀመሩ በፊት በለቀቀችው ዜማ ህዝቡ ከመደሰቱ ባሻገር ስሜቱን የቀሰቀሰለትና ታላቅ መነቃቃትን የፈጠረለት ሥራ ነበር።

አባይ በታሪክና በጥበብ ስራዎች ሲቃኝ
ከጥንት ጀምሮ ትዉልዱ ስለ አባይ ብዙ ብሏል። ከእነ ሄሮደተስ አንስቶ በርካታ የዉጪና የአገር ዉስጥ የታሪክ ተመራማሪዎች በየኖሩበት ዘመን ጽፈዉ አልፈዋል። በተለይም የታሪክ አባት(The father of history) በመባል የሚታወቀዉ ጥንታዊዉ የግሪክ የታሪክ ተመራማሪ “ግብጽ ያለ አባይ ሕይወት የላትም›› የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ ነበር። የጥበብ ሰዎችም ብዙ ብለዋል፤ በተረትና ምሳሌ ተናግረዋል፤ ቅኔ ዘርፈዋል፤ ድርሰት ጽፈዋል። ሰዓሊዎች በብሩሻቸዉ አሳይተዋል፤ ፎቶ ግራፍ አንሺዎች በካሜራቸዉ አስዉበዉ አንስተዉታል፤ ተዋንያን ተጠበውበታል፤ ቲአትርም ተሰርቶበታል። ታላቁ ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን የቅኔ ችሎታዉን ጥግ አሳይቶበታል። ድምፃዊት እጅጋየው ሽባባዉ በበኩላ “የማያረጅ ዉበት…”ስትል አዚማለታለች። እረኞች በየሜዳዉና ሸንተረሩ ተቀምጠዉ በዋሽንታቸዉ ኩራታቸውን ፣ቁጭታቸዉንና ፍቅራቸዉን ከበጎቻቸው እና እርሻቸው አሻግረዉ አንጎራጉረዉለታል።

በሌላ በኩል፣ የተለያዩ የኢትዮጵያ መሪዎች የአባይን ወንዝ ባለቤትነት ከማስጠበቅ አኳያ ጦርነት አካሂደዋል። ለምሳሌ እ.አ.አ በ1848 ደባርቅ በተባለ ሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ላይ አፄ ቴዎድሮስ( ካሳ ሀይሉ) የአባይን ወንዝ ከመነሻዉ እንይዛለን ብለዉ ከመጡት ግብፃዊያን ጋር ጦር ተማዘዋል። አፄ ዮሀንስ ፬ በ1875/76 በዚሁ የአገራችን ሰሜናዊ ክፍል ጉንደትና ጉራ ላይ ተዋድቀዋል። ቅኝ ገዢዎችም የአባይን ወንዝ መነሻ አገር ለመያዝ፣ በተለይም እንግሊዝና ፈረንሳይ በ1898 ኦምዱርማን በሚባል የሱዳን ግዛት ዉስጥ ያደረጉት ፍጥጫ የዚሁ የናይል ወንዝ ተፋሰስ አገሮችን የመቆጣጠር አካል እንደነበር የታሪክ ማህደር ያስረዳል።

አባይ አሁን ላይ
እንብላ እንጂ ልብላ የማያውቀዉ የኢትዮጵያ ህዝብም ሌሎች የተፋሰሱ አገሮችን በማይጎዳ መልኩ ግድቡን እየሰራ ይገኛል። ይህ በኢትዮጵያዊያን አቅም የሚገነባ ታላቅ የዚህ ትዉልድ አሻራ ነዉ። ትዉልዱ አክሱምን፣ ላሊበላን፣ ጎንደርን፣ሐረርን የገነቡትን ከማወደስና ከማድነቅ አልፎ የራሱን የእጅ ስራ ዉጤት በመስራት ላይ ይገኛል። አሁን ላይ ያለዉ ትዉልድም ይህንኑ ግድብ ሰርቶ ለማጠናቀቅ የተለያዩ ፈተናዎችን በመጋፈጥ መስራት ከጀመረ አሥር አመት ሞላዉ። ይሁንና ፈተናዎቹ በአጭሩ ሊቋጩ አልቻሉም። ምክንያቶቹ ደግሞ አባይ ወንዝ ድንበር ተሻጋሪ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነዉ።

የአባይ ወንዝ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ስፍራዎች በመነሳት የአገሪቷን ለም አፈር እና ውሃ ያለ ማንም ከልካይ በመሸከም እየወሰደ፣ ከዘመን ወደ ዘመን ቤቱን አራቁቶ የሰው ጓዳ ሊሞላ ፣ምስጋና ላያገኝ አመድ አፋሽ ሆኖ በግብጽ በርሀ ላይ ተንከራቶ ሜዲትራኒያን ባህር ይገባል ። አባይ የተፋሰሱን 11 የአፍሪካ አገሮች የሚያቋርጥ የአለማችን ረጅሙ ወንዝ ነዉ። ከግሽ አባይ የሚነሳው ጅረት፣ ሜዳውን፣ ሸለቆውን፣ ገደሉን እየተጥመዘመዘ ባህር ከመግባቱ በፊት አስራ አንድ አገሮች እያካለለ 4,132 ማይል ሲጓዝ ውሎ ያድራል። ለእዚህ ወንዝ ኢትዮጵያ 86 በመቶ የሚሆነውን የውሀ መጠን ብቸዋን ስታበረክት፣ ግብጽና ሱዳን ደግሞ ለወንዙ ምንም ዉሃ የማያበረክቱ የወንዙ ከፍተኛ ተጠቃሚ የተፋሰሱ አባል አገራት ናቸዉ።

ግብጽ፣ኢትዮጵያና ሱዳንን ጨምሮ ላለፉት አስር ዓመታት ያህል በአባይ ወንዝ ጉዳይ ላይ ከስምምነት ለመድረስ ሲደራደሩ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን ሦስቱንም አገራት የሚያስማማ ሁሉን አቀፍ መግባባት ላይ መድረስ አልተቻለም። ግብጽና ሱዳን በቅኝ ግዛት ዘመን ገዢዎቻቸው የተፈራረሙትን የእነሱን ፍላጎት ያማከለዉን የ1929 እና የ1959 ስምምነት እንደመነሻነት እያነሱ የግድቡ ስራ እንዲደናቀፍ ምክንያት ሲፈጥሩ ይታያሉ። በተጨማሪም ግብጽና ሱዳን በግድቡ ዙሪያ የሚኖሩ ስምምነቶች ላይ ከመወያየትና መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ ስብሰባዎችን ረግጠዉ በመዉጣት ስምምነቶችን አለመፈረማቸዉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከዚህም ባሻገር፣ በአገራቸዉ ዉስጥ የሚነሱ የተለያዩ አብዮቶችንና የህዝብን ጥያቄዎችን ከመመለስ ይልቅ የአባይን ጉዳይ በማንሳት አጀንዳ ሲጠመዝዙ ይስተዋላሉ። ኢትዮጵያ ተፈጥሮ በለገሳት ሀብቷ እንዳትጠቀም የተለያዩ እንቅፋቶችን በማዘጋጀትና ከወዳጅ አገሮቿ ጋር ጭምር ችግር እንዲገጥማት ሲሞክሩ ይስተዋላል። ለበርካታ ዘመናት ያለተፋሰስ አገሮቹ ጥያቄ እና ማን አለብኝነት ግብጽ እና ሱዳን የአባይን ወንዝ እንደፈለጉ ሲጠቀሙበትም ኖረዋል። በተለይም ግብጽ ህይወት ያለ አባይ የማይታሰብባት በረሀማ አገር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የስልጣኔ ምንጫዋም ነዉ። ለኢትዮጵያ ደግሞ የእድገት ተስፋዋ ነዉ። ስለዚህም ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ የግድቡ አስተባባሪዎችም ትዉልዱን ለማንቃት የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛሉ። ታዳጊ ህጻናትም ስለ ግድቡ በቂ መረጃ እንዲኖራቸዉ ለማስቻል ብር ከማዋጣት ጀምሮ በተለያዩ መድረኮች ላይ ልዩ ልዩ የሥነ- ጽሁፍ ስራዎችን በየትምህርት ቤታቸዉ መድረኮች እያቀረቡ ይገኛሉ።

ከእዚህም ጋር በተያያዘ የግድቡ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን ጊዜ በማስመልከት ግድቡ እስኪያልቅ የሚዘልቁ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ባለስልጣን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ አስታዉቀዋል። አመቱ መጨረሻ ላይ ፕሮግራሙ ሲጠናቀቅም በተለያዩ የሥነ-ስሁፍና ዉድድሮች ያሸነፉ ከግልና ከመንግስት ትምህርት ቤት የተዉጣጡ ታዳጊዎችን በመሸለም ይጠናቀቃል ተብሏል። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም በግድቡ ዙሪያ የሚነሱብንን ችግሮች ለመቅረፍ ከዉስጥም ከዉጪም ያለን ኢትዮጵያዊያን በጋራ መቆም ይገባናል ሲሉ አሳስበዋል። በተለይም የሚዲያና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የተለያዩ የዉጪ ቋንቋዎችን በመጠቀም ፣በግድቡ ዙሪያ የዉጭ ሚዲያዎችና ባለስልጣናት የሚያሥተላልፉትን የተዛባ መረጃ ለማስተካከል ትክክለኛውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ እንዳለባቸው ተነግሯል።<hr/>ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com