የደብረፂዮን መጨረሻ

Views: 321

ለዓመታት የህወሓት መሪ ሆነው ቆይተው በስተመጨረሻ የአሸባሪ መሪ ተብለው ተገደሉ ስለተባሉት ደብረፂዮን(ዶ/ር) አሟሟት መነጋገሪያ የሆነ መረጃ ሰሞኑን ወጥቶ ነበር። ምስላቸውን ከማሳየት ውጭ ለወራት ድምፃቸውን አጥፍተው የቆዩት እኚህ የቀድሞ ባለስልጣን አንድ ጊዜ ሞቱ ቆይቶም በድጋሚ ተገደሉ እየተባለ ሕልፈታቸው መነጋገሪያ ከሆነ ሠነባብቷል። ጭንቅላታቸው ተቆርጦ አካላቸው ብቻ ተገኘ እየተባለ ቢወራም፣ ለማስረጃ አስከሬንን ለማሳየት ነውር ሆኖ ነው እንዳይባል የስዩም መስፍንን በድን እያዘዋወሩ ሲያሳዩ ስለነበር አያሳምንም።

ወሬውን በገለልተኛ አካል ማረጋገጥ ባይቻልም ተገደሉ ተብሎ በወታደራዊ ደህንነት ሰው በኩል ወጣ የተባለው የአገዳደላቸው ዘመቻ ለብዙዎች የሳምንቱ አርዕስተ ወሬ ሆኖ ነበር። በሕይወት ያሉ በርካታ የህወሓት ሰዎች ሲያዙ ማሳየት፣ የተገደሉትንም መንግስት በይፋ እያሳወቀ መረጃው ከተለያየ ወገን እንዲረጋገጥ ሲደረግ ቢቆይም፣ የአሁኑ ላይ ግን እንደበፊቶቹ አለመደረጉ ጥርጣሬ እንደፈጠረባቸው የሚናገሩ አሉ። በሌላ በኩል ገና ያልተገኙት ጌታቸው ረዳን የመሳሰሉ የአሸባሪ ድርጅቱ መሪዎች ቦታና መልክ እየቀያየሩ አለን አልፈራንም ለማለት ዛቻ ቀላቅለው እንደሚናገሩት፣ ደብረፂዮን አለሁ ብለው መናገር አለመቻላቸውን ለመገደላቸው እንደማሰረጃ የሚያቀርቡት አሉ።

አለሁ ብሎ ለሕዝብ መታየቱ ታጣቂዎቻቸው እንዳይበተኑና ከደጋፊዎቻቸው የሚያገኙት የገንዘብ ፍሰት እንዳይቋረጥ ቢጠቅምም ሁሉም አመራሮች መታየት የለባቸውም ብለው የሚከራከሩም አሉ። ከዚህ ቀደም ከዘራ ይዘው፣ የነተበች ጃኬት አድርገው ድልድይ እያቋረጡ ታጅበው ሲያዘግሙ የሚያሳየው ምስል በደጋፊዎቻቸው ሲተች ነበር። ጌታቸው ረዳ ተጎሳቁሎ የሚታይበት ምስል መቀለጃ መሆኑንም ተከተሎ፣ በፕሮፓጋንዳ ጉልበት እላይ ደርሰው የተፈጠፈጡት ህወሓቶች እንዲስተካከል አድርገው የሚያስደስት ነገር ባይኖርም በፈገግታ እየተዝናና ለማሳየት ተሞክሮ ነበር። አሁን ደብረፂዮን ሞቱ መባሉን የሚረጋግጥም ሆነ የሚያስተባብል አለመኖሩ አሁንም ለመላ ምት በር እንደከፈተ ነው። ጃል መሮ አልሞትኩም ብሎ ለሕዝብ እንደታየው እሳቸው ያልቀረቡት ተደብቀው ነው ለማለት ያስቸግራል።

የአደዳደላቸው ሁኔታ ዝርዝር መውጣቱ እውነትነቱን ያረጋግጣል የሚሉ የመኖራቸውን ያህል ዘመቻው በጨለማ ተጀምሮ የተጠናቀቀበት ሰኣትን በተመለከተ የሚጣረስ ነገር አለው ብለው የሚሞግቱም አልጠፉም። የአገዳደላቸው መንገድ ምንም ይሁን ምን ራሳቸውና አካላቸው የተለያየ ቤተክርስቲያን ተቀብሯል ስለተባለ አውጥቶ በዲ ኤን ኤ ምርመራ ለማረጋገጥ ባሕላችንም ሆነ እምነታችን አይፈቅድም።

መንግስት ያሉበትን ለማወቅ ሆን ብሎ ወይ ደጋፊዎቹ ለፕሮፓጋንዳ ብለው የነዙት ወሬ ሊሆን እንደሚችል ሀሳባቸውን የሰነዘሩ አሉ። በተቃራኒው የህወሓት ሰዎች መንግስትን ውሸታም ለማስባል ሆን ብለው አስወርተው በኋላ አሳይተው ለማሳጣት ሊሆን ስለሚችል መጠበቁ ይሻላል ያሉም ነበሩ።

አንዳንዶች ተገድለውም ይሁን አይሁን ዋናው መታየት ያለበት የደጋፊዎቻቸው ሁኔታ ነው ይላሉ። የህወሓት ሰዎች ሲያዝኑ ወይም ሲቆጩ አሊያም አፀፋውን ሲዝቱ ስላልተሰማ ወሬውን ለማመን አስቸጋሪ ያደርገዋል ይላሉ። ተገደሉበት የተባለው መንገድ እውነት ከሆነ በሁለቱም በኩል ያሉ እማኞች በወጥነት ከተነገረው በተጨማሪ ከቤት ቤት በሸክም ሲንከራተቱ ያዩትን መመስከራቸው አይቀርም። በሠው ልጅ ሕልፈት ደስተኛ መሆን ተገቢ ባይሆንም፣ ጦርነት የገጠመ ሊገድል ወይም ሊገደል እንደሚችል ስለሚጠበቅ ነገሩን ማጋጋል ተገቢ አይሆንም።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com