አዲሱ የኮቪድ ዝርያ ሌላኛው ስጋት!

Views: 34

የኮቪድ 19 ክትባት ተገኝቶ ዓለም እፎይ ከማለቷ፣ እንደ አዲስ የተገኙት የኮቪድ ዝርያዎች ሌላ እራስ ምታት ይዘውባት ከተፍ ብለዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ ከወደ አገረ እንግሊዝ አዲስ የኮሮና ቫይረስ የመገኘቱ ዜና ከተሰማ ወዲህ ወደ ሕንድም ዘልቆ እያመሳት የሚገኘው ይኸው አዲሱ የኮቪድ ዝርያ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ ይህ በሆነበት በዚህ ወቅት በደቡብ ምስራቅ እስያ ከምትገኘው ቬትናም የተገኘው የኮቪድ 19 ዝርያ በእንግሊዝ እና በሕንድ ተገኘ የተባለውን ኹለት አይነት ዝርያ ቀይጦ የያዘ አዲስ ዝርያ መሆኑ የአገሪቱን መንግሥት እና ሕዝብ አስደንግጧል።

ቢ.1.617.2 የሚል መለያ የተሰጠውና ባለፈው ጥቅምት ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በሕንድ የተገኘው ዝርያ በዩናይትድ ኪንግደም ከተገኘው ‘ኬንት’ ቫይረስ የበለጠ ተላላፊ ነው ተብሏል። እንደ ባለሙያዎች ከሆነ በዩናይትድ ኪንግደም የተገኘው ኬንት የተሰኘው ቫይረስ ቢ.1.1.7 በሚል መለያም ይታወቃል። በቬትናም የተገኘው አዲሱ ዝርያ መለያ ያልተሰጠው ሲሆን እንደ ቬትናም የጤና ሚኒስቴር ገለጻ ከሆነ አዲሱ የቫይረስ ዝርያ ቀድሞ ከነበረው ዝርያ በተለይ በአየር የበለጠ ተላላፊ መሆኑን አሳውቀዋል።

አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በፈረንሳይ፣ በካናዳ፣ በዴንማርክ፣ በጀርመን፣ በጣሊያን፣ በኔዘርላንድስ፣ በኦስትሪያ ፣በሲዊዲን መገኘቱን ሪፖርት ተደርጓል፡፡ በተለይ ደግሞ በእንግሊዝ የአገሪቱ የስታትስቲክስ ጽህፈት ቤት እንደሚገምተው በኮሮናቫይረስ ከተያዙት ሰዎች መካከል ኹለት ሦስተኛው አዲሱ ዝርያ ሳይገኝባቸው እንደማይቀር ነው።

አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ አህጉራችን አፍሪካ በሚገኙ የተለያዩ አገራት መግባቱ ታውቋል፡፡ በተለይ ደግሞ በኬኒያ ስርጭቱ ተስፋፍቷል። በዚህ በኮቪድ- 19 የሚጠቁ አብዛኛዎቹ ሰዎች የሚያሳዩት ምልክት ልክ ጉንፋን ወይም ኢንፍሉዌንዛ የያዛቸው ሰዎችን ይመስላል። ይሄው ምልክትም ወድያውኑ የሚታይ ሳይሆን ከኹለት እስከ14 ቀናት ቆይቶ የሚታይ ነው። ምልክቶቹም ትኩሳት፤ ሳል ወይም የመተንፈስ እጥረት እንደሆነ በአሜሪካን አገር የሚገኙ ሐኪሞች ገልጸዋል።

ከተለመዱት የኮሮና ምልክቶች ማለትም የጉሮሮ ቁስለት ፣ ሳል (አብዛኛውን ጊዜ ደረቅ)፣ የትንፋሽ ማጠር፣ የደረት ህመም፣ ትኩሳት፣በድንገት የማሽተት እና/ወይም የመቅመስ ስሜት ማጣት በተጨማሪ የራስ ምታት፣ አጠቃላይ የሰውነት መድከም፣ የምቾት ማጣት ስሜት፣ የጡንቻ ሕመም፣ የንፍጥ መብዛት፣ የአንጀትና ሆድ እቃ ህመም ምልክቶች (ማቅለሽለሽ፣ማስታወክ፣ ተቅማጥ፣ የሆድ ህመም)፣ የቆዳ ሽፍታ የአዲሱ የኮቪድ ቫይረስ ምልክቶች መሆናቸውን ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

እነዚህን ምልክቶች የሚያሳየው እና የህመም ስሜቱም ሆነ ገዳይነቱ መጀመሪያ ከምናውቀው የኮቪድ ዝርያ እጅግ የከፋ መሆኑ የተነገረለት አዲሱ ዝርያ አብዛኛውን ጊዜ የሚተላለፈው ረዘም ላለ ጊዜ በሚኖር የቅርብ ንክኪ አማካኝነት ነው። ማለትም በቫይረሱ ከተጠቃ ሰው ጋር መከላከያ ሳያደርጉ ከ1 ነጥብ 5 ሜትር ባነሰ ርቀት ከተቀራረቡ፣ በፈሳሽ ጠብታዎች አማካይነት፣ ቫይረሱ ያለበት ሰው ከተነፈሰ፣ ካወራ፣ ካስነጠሰ ወይም ካሳለ፣ ቫይረስ ተሸካሚ ጠብታዎች በቅርብ ርቀት ወደሚገኝ ሰው የመተንፈሻ (አፍንጫ፣ አፍ ወይም ዓይን) ሕብረ ሕዋስ ሊደርሱ ይችላሉ። በጣም ረዥም ርቀት ላይ በጠብታዎች (ብናኞች) አማካይነት ቫይረሱ የመተላለፍ እድሉ ጠባብ መሆኑም ተገልጿል።

በውጫዊ ገጽታና እጆች ላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሲያስሉና ሲያስነጥሱ፣ ቫይረሱን የያዙ ጠብታዎች እጆቻቸው ወይም ውጫዊ ገጽታዎች ላይ ሊያርፉ ይችላሉ። ሌላ ሰው እነዚህን ጠብታዎች በእጆቹ አንስቶ አፍ፣ አፍንጫ ወይም ዓይኑን ከነካ በቫይረሱ ሊያዝ ይችላል።
አንድ ሰው የህመም ምልክቶች እንዳሉበት ሳያስተውል ሌሎች ሰዎችን ሊበክል ስለሚችል በትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። የዚህ ምክንያት ደግሞ፣ አንድ የታመመ ሰው ምልክቶቹ ከመታየታቸው ከኹለት ቀናት በፊትና ከታዩ ከ10 ቀናት በኋላ በሽታውን ማስተላለፍ መቻላቸው እንደሆነ በባለሙያች ተገልጿል።

በአገራችን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በየቀኑ የሚመዘገብ የሞት መጠን፣ በተለይ በያዝነው ሳምንት፣ እየቀነሰ እና ከአስር በታች እየወረደ መምጣቱ እንደ መልካም ዜና ቢቆጠርም፣ አዲሱ የኮቪድ ዝርያ ወደ አገራችን ይገባ ይሆን የሚለው ደግሞ ሌላኛው ስጋት ሆኗል።
ዶክተር ዘለዓለም ተስፋየ በካዲስኮ ሆስፒታል የኮቪድ ሐኪም ናቸው፡፡ አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ መግባቱ እና አለመግባቱ ታውቆ ይሆን? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ይህንን በምን ልናረጋግጥ እንችላለን በማለት ነበር ምላሻቸውን የሰጡን። እንደዚህ አይነት አዳዲስ ግኝቶችን ለማወቅ በጣም ሰፊ የሆነ ጥናት ማድረግ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ እንግሊዝ፣ ብራዚል እና ሕንድ ያሉ አገራት አዲሱን የኮቪድ ዝርያ ለይተው አውቀውታል። የተለየ ሳይንሳዊ ስያሜም ሰጥተውታል፡፡ ወደ እኛ አገር ስንመጣ ግን ይህንን ለማድረግ መሟላት ያሉባቸወ ብዙ ነገሮች ይኖራሉ። ትላልቅ የሆኑ ላቦራቶሪዎች ያስፈልጉናል፣ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ያስፈልጉናል፣ የበለጠ እየሠራን የምንገኘው ምርመራው ላይ ብቻ ነው፤ ለዚህ መንግሥት የግሉ የጤና ተቋም እገዛ በራሱ ያስፈልገዋል ብለዋል።

ዶክተር ዘለዓለም አክለውም አሁን ያለው የኮቪድ ምርመራ በራሱ ባልተሟሉ የመመርመሪያ ቁሳቁሶች እየተደረገ ይገኛል፡፡ ለምርመራ ናሙና ከተወሰደ በኋላ ውጤቱ የሚደርስበት ጊዜም ይዘገያል። በበሽታው ተይዞ ሊሆን ይችላል ተብሎ የተጠረጠረ ሰው የምርመራ ውጤቱ ቶሎ የማይደርስ ከሆነ እና ጥንቃቄ ካላደረገ ወደ ቤተሰቦቹ ሲቀላቀል የኮሮና ቫይረስ ሊያስተላልፍ ይችላል።

እንደ ሐኪሙ ገለጻ አንድ የቫይረስ ዝርያ ባህሪውን ቀይሮ እንደ አዲስ ሲከሰት ከባድ ሕመም ያስከትላል፤ ገዳይነቱም ይጨምራል፤ጊዜ ሳይሰጥ ፈጣን ሆኖ እርዳታ ካልተገኘ በቶሎ ሕይወት እንዲያልፍ ያደርጋል፤የመተላለፍ እድሉም በዛው ልክ የጨመረ ይሆናል፡፡ ለዚህ እንደ ምሳሌ ብራዚልን ማንሳት እንችላለን፡፡ አዲሱ የኮቪድ ዝርያ በብራዚል ከተገኘ ወዲህ የሚመዘገበው አዲስ የኮቪድ ታማሚ ቁጥር እና የሟቾች ቁጥር በዛው ልክ ጨምሯል፤ በሕንድም ተመሳሳይ ነው ብለዋል።

አዲስ በሽታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምልክት ሊያሳይ ይችላል፤ በአጭር ጊዜ ጽኑ የሆነ ሕመም ያስከትላል፡፡ በፍጥነት እየተዛመተ ከሄደ እና እየበረታ ከመጣ የህክምና መስጫ ተቋማት ካላቸው አቅም በላይ ይሆናል፡፡ የህመሙ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የኦክስጂን መጠን ይፈልጋል፤ ከፍተኛ የሆነ የኦክስጂን ፍላጎት እያለ የኦክስጂን አቅርቦቱ አናሳ ከሆነ የሞት መጠኑ ከፍተኛ ይሆናል በማለት ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com