‹‹የእኛ ደፍሮ መናገር ነገ ለእነሱ እርማት ይሆናል››

Views: 24

በሱማሌ ክልል ለ27 ዓመት ገደማ በትጥቅ ትግል ውስጥ የቆዩ ናቸው። የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር ታጋይና አመራር ሆነው ጫካ ከቆዩ በኋላ ከ3 አመት በፊት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል። በ6ተኛው አገራዊ ምርጫ ለሱማሌ ክልል ምክር ቤት ይወዳደራሉ። ስማቸው አህመድ መሐመድ ይባላል። የኦጋደን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር(ኦብነግ) የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ኃላፊ ሲሆኑ፣ በቆራየሄ ዞን በኢሼኮች ወረዳ የክልል ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ ናቸው።

የፖለቲካ ትግላችሁ ምን ይመስላል?
አንድ የሶማሊ አባባል አለ። “ግሀነብ ከገባህ ቀዝቃዛ ቦታ የለውም” ይባላል። እሳት ውስጥ ከገባህ ቀዝቃዛ ቦታ የለውም። ትግል ቀላል ቦታ የለውም። እኔ የማምነው በትጥቅ ትግል ሲሆን ነው፣ ምክንያቱም በትጥቅ ትግል ሲሆን ነው የሚቀለው፤ በትጥቅ ትግል ጠላትክን ታውቃለህ ትጋደላለህ። ነገር ግን ለዓላማ ስትታገል ብዙ ተግዳሮቶችና እንቅፋቶች ይኖራሉ። ከነበረኝ ልምድ፣ ከነበረን የትጥቅ ትግል ጠንከር ያለ ትግል ነው የገባነው። ግን የሰው ህይወት ማዳን ነው።

ምን ያክል ዘመን በትጥቅ ትግል ቆያችሁ?
እኔ ራሴ 27 ዓመት ነው በትጥቅ ትግል ጫካ የቆየሁት። ድርጅታችን ከ1987 እስክ 2010 ባለው ጊዜ የትጥቅ ትግል ከመንግሥት ጋር ስናደርግ ነበር። እኛ 84 በመቶ አሸንፈን ሕዝባችንን እየመራን እያለን ነው ኢህዴግ ጦርነት የከፈተብን። በወቅቱ ጦርነት ከፍተን ጫካ መግባቱ ግዴታ ስለሆነብን፣ ያለምንም ድርድር በሰው ህይወት ትግላችንን እናራምዳለን ብለን ነው የገባነው።

ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ እንዴት ታዩታላችሁ?
አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫ ብሎ መሰየም እራሱ አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም የምርጫው ሂደት ብዙ ውይይቶችና ክርክሮች የተደረጉበት እና ምርጫ ቦርድ በርካታ ጥሩ የሚባሉ ሥራዎችን ቢሰራም፣ አሁን ባለው ሁኔታ ገዥው ፓርቲ ብልጽግና እንቅፋት እየሆነብን ነው። የተደረጉ ጥረቶችና ሙከራዎች የምርጫ ካርዶች ሲዘረፉ፣ እጩዎች ሲታሰሩና ግለሰቦች ስብሰባ ማደረግና ሕዝብ ማወያየት ሲከለከሉ፣ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ምርጫ ሊካሄድ አይችልም። ዛሬ በገዥ ፓርቲና በአስተዳደሩ ላይ ደፍረን መናገር ካልቻልን ነገ በእነሱ ታሪክ ላይ መጥፎ ነገር ማውራቱ ምንም ዋጋ አይኖረውም። የእኛ ደፍሮ መናገር ነገ ለእነሱ እርማት ይሆናል። ከሚያደርጉት ድርጊትና ስህተት ቢቆጠቡ እና ለአገሪቱ ቢያስቡ ጥሩ ነበር።

ፓርቲያችሁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምን ያክል እጩዎች አቀረበ?
በአጠቃላይ 263 እጩዎች አሉን። 161 የሚሆኑ እጩዎች ሱማሌ ክልል አትመዘገቡም ተብለው ተባረው እኔ ነኝ አዲስ አበባ ያስመዘገብኳቸው። ክልሉ እጩዎችን ማስመዝገብ አለመቻሉን ተከትሎ፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳውቀን እጩዎቻችን አዲስ አበባ እንዲመዘገቡ ቦርዱ ፈቅዶልናል። ቦርዱ ከዝቅተኛ ሠራተኛ ጀምሮ እስከ ቦርዱ ሠብሳቢ ድረስ እገዛ አድርገውልናል። በዚህ አጋጣሚ ምርጫ ቦርድን በእኔም በድርጅቴም ስም አመሰግናለሁ። ከዚያ በኋላ ጥሩ ነገሮችን እንዳደረጉና ብዙ ችግሮችን ለመፍታት እንደሞከሩ እናውቃለን፤ ግን ጫና እንዳለባቸውም እናውቃለን።

አሁንም ግን ከሚጠበቅባቸው ገና 50 በመቶ አልፈፀሙም ብለን እናምናለን። ግን ሊያደርጉ የሚገባቸው ነገሮች አሁን አሉ። ይህንን ማድረግ አለባቸው ካልተደረገ ግን ሌላ ስም ሳንሰጥ አንቀርም።

የቅስቀሳና የክርክር ሂደቱን እንደት ይገመግሙታል?
በዚህ ላይ ኹለት ነገሮችን ማንሳት እወዳለሁ። እኛ አገር ውስጥ ከገባንና ከተደራጀን በኋላ ገዥው ፓርቲ ሜዳውን ነጻ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነልንም። እንድንቀሰቅስና ሕዝባችንን እንድናደራጅ ባደረግነው ጥረት ብዙ ያጋጠሙን ችግሮች አሉ። የታሰሩ የተደበደቡ አሉ። እኔ እራሴ በደጋሀቡር ከተማ በድንጋይ ተፈንክቻለሁ። የድርጅት ቅስቀሳ ሳደርግ ነው ይሄ የገጠመኝ።

በመጀመሪያ ደረጃ እነሱ እንድንቀሳቀስና እንድንደራጅ አልፈቀዱልንም። አባሎችን ማሰር፣ ቢሮዎችን መዝጋትና መኪናዎችን መገደብ በየቀኑ እያደረጉት ነው። በኹለተኛ ደረጃ እኛ የመራጮች ምዝገባ ሲካሄድ ካየን በኋላ በጊዜያዊነት ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ እንቅስቃሴ አቁመናል።

በሚደረጉ ክርክሮች ላይ እየተሳተፋችሁ ነው?
ክርክር እየተካሄደ ነው ብለን እናምናለን፤ ነገር ግን በፍትሐዊነት ተግባራዊ እየሆነ አይደለም። ለምሳሌ ባለፈው ወር በአዳማ በሶማሊኛ የሚደረግ አንድ ክርክር ነበር፣ እኔ ከአዲስ አበባ መኪና ተከራይቼ ለክርክሩ ሄጃለሁ። ነገር ግን ችግር ገጥሞናል። ከሰላሳ ደቂቃ በኋላ ይተላለፋል ቢሉም አልሆነም። አሁን ከኹለት ሳምንት በፊት እንዳወኩት ያደረግነው ክርክር በቀጥታ እንዳይተላለፍ ከሶማሊ ክልል ኃላፊዎች ተደዉሎ ታዟል። ክርክሩ እንዲታረም(ኤዲት እንዲደረግ) የፈለጉት ካልሆነ ግን እንዳይተላለፉ ብለው አዘዙ።
ከዚያ በኋላ እኛ ክርክሩን ሙሉ በሙሉ ሳይስተካከል ካላስተላላፋችሁትና ኤዲት ከተደረግ እንከሳችኋለን ብለናቸው አሁን ዘግይቶም ቢሆን እንዲተላለፍ ተደርጓል።

የክርክር እና የማስተዋወቅ ሂደቱ ሊያልቅ ከመሆኑ አኳያ ከምርጫ ቦርድ የሚለቀቀው ገንዘብ በቂ ነው ትላላችሁ?
ገንዘብ ተለቋል ሲባል ሰምቻለሁ። እኔ ግን የገንዘብ ጉዳይ ላይ ስለማልሠራ ይህንን ጉዳይ ብዙ አላውቅም።
ከዓለም አቀፍ ጉዳዩች አኳያ ሰሞኑን ከአሜሪካ ጋር የተፈጠረው ክስተት አለ። ግብጽ እና ሱዳን ጋርም እንደዚሁ በዓባይ ግድብ ጉዳይ ላይ አለመግባባት አለ። በነዚህ ጉዳዮች የፓርቲያችሁ አቋም ምንድን ነው?
ይህ ነገር እልባት ማግኘት አለበት። እንደ አገር ዓለም እኛን ይፈልገናል፤ እኛም ዓለምን እንፈልጋለን። እኛ በዲፕሎማሲያ መንገድ ይህንን ችግር መፍታት አለብን። ሉዓላዊነት እና ነጻነት መከበር አለበት። አገሪቷም የዓለም ሕግጋት እና ደምቦችን መከተል አለባት። ይህንን ነገር እንደ ዜጋ እኔ የማየው መፈታት አለበት ብዬ ነው።

በህወሓት ላይ እየተወሰደ ባለው ወታደራዊ እርምጃ መንግሥት የአሜሪካ እና የሱዳን ጣልቃ ገብነት አለብኝ እያለ ነው ይህንንስ እንዴት ያዩታል?
እንደ አንድ ዜጋ የአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ ላይ ሌሎች አገሮች ጣልቃ መግባት የለባቸውም ብየ አምናለሁ። ግን ይህንን ማጣራት እና እውነት መሆኑን እና አለመሆኑን መለየት አለብን። እንደ አንድ ፖለቲከኛ የመንግሥት ኃላፊዎች የሚያወሩትን ሁሉ ትክክል ነው ብሎ ለማመንም ትንሽ ይከብዳል። ነገር ግን የአገርን ሉዓላዊነት በሚነካ ነገር የትኛውም የዓለም አገር ከየትኛውም ጋር አይወዳደርም። ይኸ እውነት ከሆነ እና አሜሪካን እና ምዕራባዊያን አገራት ድንበር ጥሰው ወደ አገራችን የሚገቡ ከሆነ መንግሥት እውነት አለው፤ ሀቅ ነው ንግግሩ እንላለን። ሀሰት ከሆነ እና ሕዝቡን ለማነቃቃት ከሆነ ደግሞ ይኸ ወሬ ወደ የትም አይወስደንም፤ ወደ እውነተኛው መንገድ እንምጣ ብለን እናምናለን።

በተለያዩ ቦታዎች ያሉ ተፈናቃዮች በምርጫው አይሳተፉም፣ ሰላም የለባቸውም በተባሉ ቦታዎችም ምርጫው ለሌላ ቀን ተሸጋግሯል። ይኸንንስ ጉዳይ እንዴት ትመለከቱታላችሁ?
በአገሪቱ ውስጥ ብዙ ተፈናቃዮች አሉ። በትግራይ አሉ፤ በኦሮሚያ ውስጥ አሉ፤ በሱማሌ ክልልም አሉ። ችግራችን የት ነው፤ ያልተሰደደ ኢትዮጵያዊ የሌለበት ቦታ የለም። ነገር ግን አብዛኛው የሱማሌ ስደተኞች ያሉት በጎረቤት አገሮች ነው። ኢትዮጵያ ስለነዚህ ሕዝቦች ስታነሳም አላየንም። በጣም ከሚያሳዝኑኝ ነገሮች ተሰደው አገራቸውን ለቀው ወደ ኬኒያ፣ ሱማሊያ፣ የመን፣ ኤርትሪያ፣ ጂቡቲ ያሉት ሱማሌዎች በጦርነቱ ጊዜ የተፈናቀሉት በራሳቸው ጊዜ ተመልሰው የመጡት ደግሞ የመልሶ መቋቋሚያ አልተደረገላቸውም። ለምን? ብንል አብዛኛዎቹ የታጋዮቹ ዘመዶች፣ ባለቤቶች እና የድርጅታችን አባሎች ስለነበሩ ነው። ምናልባት ተመልሰን እንዳንመጣ እና ደጋፊዎቻችን እንዳይበዙ የገዢው ፓርቲ የሱማሌ ክልል አስተዳደር ኃላፊዎችም እንደዛ አይነት አስተሳሰብ ነው የወሰዱት ብለን ነው እኛ እስከዘሬ ድረስ እየጠረጠርን ያለነው። ነገሩን እየገመገምን ነው። ለምን በመቶ ሺዎች እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኛ ዜጎች ተፈናቅለው ተመልሰው እንዲመጡ አይበረታታም። ከውጭ አገር ተምረው ሰርተፊኬት ይዘው ተመልሰው ሲመጡ ለሰርቲፊኬታቸው ቅቡልነት ስለማያገኝ ሥራ ማግኘት አልቻሉም። ክልከላ እየተደረገባቸው ነው። የኔ ወንድም የዩንቨርሲቲ ተማሪ ነው፤ ከታወቀ የኬኒያ ዩኒቨርሲቲ ተመርቋል፤ የማስትሬት ዲግሪ አለው ግን አንቀበልም አሉት።

በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠር ስደተኛ በአገራዊም ሆነ በክልል ምክር ቤቱ ተወካይ ማግኘት አለበት ስለመባሉ ምን ትላላችሁ?
ይህንን ጥያቄ ገዥው ፓርቲ ቢጠየቅ መልካም ነው።
ተመልሰው አገራቸው መጥተው ድምጻቸውን ይስጡ ብለን ስለእነርሱ ከማውራታችን በፊት አገር ውስጥ ያሉት ድምጻቸው እየተነፈገ እና ካርዳቸው እየተነጠቀ፣ መብታቸው እየተገፈፈ የሌሎችን ማውራት ሌላ ነገር ነው።

አጠቃላይ የእስካሁኑን ሂደት አይተው ከምርጫው በኋላስ ምን ይሆናል ብለው ይገምታሉ?
ምርጫው ፍትሃዊ፣ ነጻ እና ሚዛናዊ እንዲሆን ያለው ሥርዓት መቀየር አለበት። በተለይ ደግሞ በእኛ ክልል የምርጫ ጣቢያ ሠራተኞቹ በዝምድና የተቀጠሩ፣ በሙስና የተቀጠሩ፣ ምንም ሥነ ምግባር ያልተረዱ አሉ። ካርዶቹ ተሰርቀዋል ሳይሆን ተዘርፈዋል። ግምጃ ቤት አስቀምጦ ነው ገዥው ፓርቲ በዋርዲያ እያስጠበቀው ያለው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ምርጫ እንደሚካሄድ አላውቅም፤ እንዴት እንደሚሆን አላውቅም። አንድ ነገር ካልተቀየረ ፍትሃዊ ምርጫ አይኖርም።

ምን ምን ይደረግ ትላላችሁ?
በመጀመሪያ ደረጃ እኔ ለሱማሌ ክልል ነው ትኩረት የምሰጠው እና የማውቀው። በምወዳደርበት ቦታ የምርጫ ካርዶቹ ይሰረዙ፤ ሠራተኞችም ይቀየሩ እና ሌላ ገለልተኛ የሆኑ ሰራተኞች በመንግሥት ሥር ያልሆኑ ሰራኞች ይቀጠሩ። የምንተማመንበት መረጃዎች በግዜው ይፋ ይሁኑ እና በዚህ አይነት መልክ እንወዳደር ብለን እናምናለን። ያለበለዚያ በሱማሌ ክልል የሚወዳደር ሌላ ፓርቲ አይኖርም ይህንን ነው የማረጋግጥላችሁ።

ፓርቲያችሁ ከሌሎች ፓርቲዎች በምን ይለያል?
በብዛት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሳሳይነት አላቸው። ሊለያዩ የሚችሉባቸው ትንሽ ነጥቦች ናቸው። በፓርቲ ተወዳድሬ አገርን እመራለው የምትል ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ ተመሳሳይነት አለው፤ ግን በማንፌስቶ ላይ ልዩነት አላቸው። አንዱ ለትምህርት ትኩረት ሲሰጥ፣ ሌላኛው ለሰብዓዊ መብት ትኩረት ይሰጣል። እኛ የምንለየው የሰብዓዊ መብቶችን ዋጋ ስለምናውቅ ነው። ምክንያቱም ሰው ሲያልቅ እና ሲሞት ብዙ ጊዜ አይተናል። እናም የመኖር ዋጋ ምን እንደሆነ እናውቃለን። ሰብዓዊ መብት ደግሞ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ጉዳይ ነው። ሰው እንደ ድንጋይ ዝም ብሎ ተቀምጦ አይኖርም። ትልቅ ዋጋ እና ክብር ተሰጥቶት መኖር አለበት። እርግጠኛ ሁኘ የምነግርህ ከገዥው ፓርቲ በጣም እንለያለን። መብት እየረገጡ፣ ሰውን ያለአግባብ ያለፍርድ ቤት ማዘዣ እያሰሩ፣ እየደበደቡ፣ ሕዝቡ መብቱ በጣም እየተነጠቀ፣ ከነርሱ በጣም እንለያለን ብየ አስባለሁ። እኛ አንደኛ፣ ኹለተኛ እና ሦስተኛ ቅድሚያ የምንሰጠው በማኒፌስቷችን ላይ እንዳለው ለሰብዓዊ መብቶች ነው። አብዛኛዎቹ የእኛ ደጋፊዎች ምናልባት ከ60 በመቶ በላይ ደጋፊዎቻችን ሴቶች እና ወጣቶች ናቸው። ቅድሚያ የምንሰጠውም ለሴቶች እና ለወጣቶች ነው።

አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ለመሸነፍ ዝግጁ ናቸው ብለው ያምናሉ?
ማንኛውም የሰው ልጂ ውድድር ውስጥ ሲገባ የማሸነፍ ተስፋ አለው። እንደውም የግል ኑሮ ላይ የማሸነፍ ተስፋ አለን። ሁሉም ድርጂት እንደዛ ሀሳብ አለው ለማለት እወዳለሁ። እኛ ግን ከሕዝባችን ለሕዝባችን ወደ ሕዝባችን ስለሆንን ዱሮም ተሞክሮ ስላለን ሙሉ በሙሉ እንደምናሸንፍ እናምናለን። ብንሸነፍም እንቀበላለን፤ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ከሆነ።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com