የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎና የፖለቲካ ፓርቲዎች

Views: 20

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ሴትን ከፖለቲካ ጋር በተገናኘ ማንሳት በእኛ በኢትዮጵያውያን ዝቅተኛ አመለካከት የሚሰጠው ጉዳይ ነው። በተለይ ደግሞ ሴት የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የምትሳተፍ ከሆነ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለው መገረም የገዘፈ ነው። በእርግጥ በኅብረተሰቡ ዘንድ እንደዚህ ዓይነት ዝቅተኛ የሆነ አመለካከት እንዲኖር ያደረግነው እኛ ሴቶች መሆናችን ሀቅ ነው። ለምሳሌ፣ ቤት ውስጥ ያለውን በርካታ ኃላፊነት የምትወስደው ሴት በመሆኗ የምታወራው እና ጉዳዬ ብላ የምትይዘው ምናልባት የአስቤዛ እና የቤተሰብ አስተዳዳሪነትን ጉዳይ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የምትገኝ ሴት ጊዜና ኃላፊነት ተርፏት አገሪቷ ላይ የሚከናወነው የፖለቲካ ሽኩቻ ሊያሳስባት አይችልም።

እስቲ ቤታችን ውስጥ ያሉ ወጣት እና አዋቂ ሴቶችን እንመለከት። ቴሌቪዥን ሲከፍቱ ምን ማየት ይቀናቸዋል? ጣቢያው ላይ ማንኛውም የፖለቲካ ወሬ ካለ ወደ መዝናኛ ወይም ደግሞ ማኅበራዊ ጉዳይ የሚዘገብበት ሚዲያ በማዞር ምርጫቸውን ይቀይራሉ።
ይህ የሚያሳየው ሴቶችም ብንሆን ፖለቲካውን ደፍረን መሳተፍ እንደማንፈልግ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ብንመለከት በቀድሞ ዘመነ መንግሥታት የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ አሁን ካሉት የተሻለ ነበር ማለት ይቻላል። በአሁኑ ሰዓት መንግሥትን በተለያዩ ሚዲያዎች ከሚተቹትም ሆነ ፖለቲካው ላይ ንቁ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል ደግሞ የዓባይ ሚዲያ ጋዜጠኛ እና መምህር መዓዛ መሐመድ፣ የቀድሞ የኢሳት ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ እንዲሁም መምህርት እና ጸሐፊ መስከረም አበራ ይገኙበታል። በተጨማሪም ቆንጂት ብርሀን የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲን (ኢሕአፓ) በመምራት በፖለቲካው በግንባር ቀደምትነት ከምናገኛቸው መካከል አንዷ ነች።

ከእነዚህ ሴቶች በተጨማሪ ሳናነሳው የማናልፈው የአዲስ አበባ ነዋሪ ላልሆኑ በርካታ ግለሰቦች ያለ ሕግ አግባብ መታወቂያ እየተሰጠ ነው በማለት ደፍራ የተናገረችው ሰናይት ታደገ ትገኛለች። እነዚህ ሴት ፖለቲከኞች ከኅብረተሰቡ፣ ከቤተሰብ እና ከፖለቲካ አካላት የሚደርስባቸውን ማንኛውንም ተጽዕኖ ተቋቁመው የቆዩ ናቸው። የእነዚህ ደፋር ሴቶች አስተዋጽኦ ደግሞ አሁንም የተቀዛቀዘውን የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማነቃቃት እድል ይፈጥራል። ከዚህ በተጨማሪ በዚህ ዓመት ስለሚካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ የማታውቅ ሴት የለችም። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በምርጫው ላይ ከሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በአመራርነት የሚገኙ ሴቶች በጣም አንሶ ይስተዋላል። ይህንንም ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎች የሴቶችን ተሳትፎ መጨመር እንዳለባቸው ሲያሳስብ ከርሟል። ይህን ተከትሎ በተለያዩ ፓርቲዎች ሴቶች በዕጩነት እንዲቀመጡ ሲደረግ ማየት ችለናል።

ገዢው ብልጽግና ፓርቲም ቢሆን ሴቶች በተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ላይ ተሳታፊ በማድረግ ተሳትፏቸውን እየጨመረ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ይስተዋላል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን በትላልቅ የአመራር ቦታዎች ላይ የሚገኙ፣ በፖለቲካ ጉዳዮች መንግሥትን የሚሞግቱ ሴት አክቲቪስቶች ቁጥር በእጅጉ አናሳ ነው። ይህንን ተሳትፎ ለመጨመር ሴቶች በራሳችን ተነሳሽነት በማንበብ፣ መረጃ በመከታተል፣ ሕጎችን በመረዳት እና የአመራርነትን ቦታ በመረከብ አቅማችንን ማሳየት ይጠበቅብናል።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com