የአሜሪካውያን እቅድ፡ ኢትዮጵያን እንደ ሆንዱራስ፤ ዐቢይን እንደ ዜላያ

Views: 55

ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አሜሪካውያንን መንግሥት ከመገልበጥ ሙከራ አያስቆምም

አሜሪካ በበርካታ አገራት የውስጥ ጉዳይ መግባት ብቻ አይደለም በመንግሥት ግልበጣ እየተሳተፈች በብዙ አገራት መከራን እንዳመጣች ይታወቃል፡፡ በተለይ በደቡብ አሜሪካና አፍሪካ አገራት ተደጋጋሚ መፈንቅለ-መንግሥቶችን እያካሄደች በእጅ አዙር በርካታ አገራትን ትመራለች፤ አልሆን ካላትም ታወድማለች፡፡ ሠሞኑን በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ጥላ በውስጥ ጉዳይ ለመግባት ስትጥር ትታያለች፡፡ የአሜሪካን ተግባር በሆንዱራስ መንግሥት ላይ ከፈጸመችው ጋር እያስተያዩ አዲሱ ደረሰን እንዲህ ከትበውታል፡፡

አሜሪካውያን መንግሥት ከማስተዳደር ይልቅ መንግሥት መገልበጥን ተክነውበታል ብንል ማስረጃ ማግኘት የምንችልበት ዘመን ላይ ነን ያለነው። አፍጋኒስታን፣ ሶማሊያ፣ ኢራቅ፣ የመን፣ ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ ኤርትራ፣ ዚምባብዌ… በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት በአሜሪካውያኑ ጥርስ ተነክሶባቸው መንግሥታቸው የፈራረሰባቸው አሊያም የተዳከመባቸው አገራት ናቸው።

ያሁኑ እና የቀድሞ ባለሥልጣናት የቪዛ ክልከላ እና የጸጥታ ትብብርን እንዲሁም የዓመታዊ በጀት ድጎማ ክልከላን ያካተተው ማዕቀብ መወሰኑን ተከትሎ፣ ከእነዚህ አገራት ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ ትካተት ይሆን? የሚል ስጋት በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ አይደለም እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፤ ያን ያክል አይዳፈሩንም የሚል ፉከራ በሌላ በኩል ስንሰማ የቆየንበትን ሳምንት ነው ያሳለፍነው። የፖለቲካ ትንተናውም እንደዛው ተጧጡፎ ነው የሰነበተው። አሜሪካውያኑ በህውሓት ወዳጆች እጃቸው ተጠምዝዟል፤ የለም ትክክለኛ የሰብዓዊ መብቶች ሞጋቾች ስለሆኑ ነው፤ የለም…የለም የጆ ባይደን ቻይናን ከአፍሪካ የማባረሪያ ፖሊሲ እየተተገበረ ስለሆነ ነው። ኧረ በፍጹም! የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኢጋድ ውጪ በቀጠናው የፈጠሩት ኤርትራን ያካተተ አሰላለፍ ቀጠናው በጠቅላላ ከቁጥጥራቸው ውጪ እንዲወጣ አድርጓል… ሌላም… ሌላም!

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ማዕቀቡን፣ ምክንያቱን እና ውጤቱን መተንተን አይደለም። ያንን ለየዘርፉ ሙያተኞች መተውን መርጫለሁ። ይልቁንም ዓላማዬ አሜሪካውያኑ ሲወርዱ ምን ያክል እንደሚወርዱ ማሳየት ነው። የአሜሪካውያኑ ጣልቃ መግባት የሚያስገርመው፣ ጓደኞቻቸው ባያምኑበትም፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተዉ ቢሉም፤ ሕዝባቸው ቢቃወምም ከማድረግ አለመመለሳቸው ነው። ሌላኛው የሚያስገርመው ደግሞ ፍጹም በተሳሳተ መረጃ አገር ከማፈራረስ አለመመለሳቸው ነው፤ ሳዳም ሁሴን ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ አደራጅቷል የሚለው መረጃ ኢራቅ ከፈራረሰች በኋላ የተሳሳተ መሆኑ ተረጋግጧል። በዚህ አጭር መጣጥፍ በተለይ ሆንዱራስ ውስጥ የሠሩትን ግፍ ጥሩ ማሳያ ነው በሚል እንደምሳሌ መጠቀም ፈልጌያለሁ።

ሆንዱራስ…
ሁንዱራስ በመካከለኛው አሜሪካ የምትገኝ በስተሰሜን የካሪቢያን ደሴቶች፣ በስተደቡብ ደግሞ የፓሲፊክ ውቂያኖስ የሚያዋስናት አገር ናት። ሆንዱራስ ከስፔን ቅኝ ግዛት በ1821 የተላቀቀች ሲሆን፣ ከዚያም እስከ 1823 ድረስ የመጀመሪያው የሜክሲኮ ኢምፓየር አካልም ነበረች። ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላት ሆንዱራስ፣ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት በታችኛው ረድፍ ላይ የምትገኝ እና ከአምስት ዜጎቿ አንድኛው ጭልጥ ባለ ድህነት ውስጥ የሚገኝባት አገርም ናት። አገሪቱ የከበቧትን ደሴቶች በየዓመቱ ከሚጎበኙ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ቱሪስቶች የምታገኘው ገቢ ዋንኛ መተዳደሪያዋ ነው።

ሆንዱራስ በብዝኀ ፓርቲ እና በፕሬዝዳንታዊ ስርዓት የምትዳደር አገር ናት። የሆንዱራስ ፕሬዝዳንት የመንግሥትም የአገረ-መንግሥቱም ራስ ነው። የሥራ አስፈጻሚውን ድርሻ ሥልጣን ተረክቦ መንግሥት የመሰረተው ፓርቲ ሲወስድ፣ የሕግ አውጪነቱን ድርሻ ደግሞ የሆንዱራስ ብሔራዊ ሕግ አውጪ ምክር ቤት ይወስዳል። ሆንዱራስ ከአምስት በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሯትም በዋንኛነት ፖለቲካዋን ሲዘውሩ የከረሙት ግን የብሔራዊ ፓርቲው እና የሊብራል ፓርቲው ናቸው።

ማኑዔል ዜላያ…
ማኑዔል ዜላያ በ1952 በካታካማስ የተወለደ የሆንዱራስ ፖለቲከኛ ሲሆን፣ አገሩን ከ2006 እስከ 2009 ድረስ በፕሬዝዳንትነት አገልግሏል። የሊብራል ፓርቲው ዜላያ ሥልጣን ላይ የወጣው በ2005 በተደረገው ምርጫ ከፍተኛ ፉክክር አድርጎ የነበረውን እና የአክራሪውን የብሔራዊ ፓርቲ እጩ ፖርፎሪዮ ሎቦ ሶሳን አሸንፎ ነው። በ2009 ማኑዔል ዜላያ ቢጃማውን አንኳን ሳይቀይር ወደ ጎረቤት አገር ሄዶ ነብሱን እንዲያተርፍ ያስገደደው መፈንቅለ መንግሥት ተደረገበት።

ሆንዱራስ በ2005 ፍጹም ዲሞክራሲያዊ የሆነ፣ ዲሞክራሲያዊ መሆኑም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በአውሮፓ ሕብረት እና በሰሜን፣ በመካከለኛው እና በደቡብ አሜሪካ አገራት ጭምር የተመሰከረለት፣ ምርጫን አካሄደች። ምርጫው ከፍተኛ ፉክክር የሞላበት የነበረ ቢሆንም በስተመጨረሻ የከበርቴው ገበሬ ልጅ ዜላያ ማሸነፉ ተነገረ። ተሸናፊውም ጽዋቸውን አምነው ተቀብለው ማኑዔል ዜላያ ወደ ሥልጣን መጣ።

ዜላያ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የገበሬውን የምግብ ምርት እንዲጨምር በማድረግ፣ እንዲሁም ሆንዱራስን በደን መልሶ ማልበስ ሥራ ተጠምዶ ከፍተኛ አድናቆትን ያገኝም ጀመር። ለድሃው ያደላል የሚባልለትና ብዙ ሚሊዮኖችን የቤት ባለቤት አድርጎ ከድህነት አውጥቷል ተብሎ የሚነገርለትን የሁጎ ቻቬዝ ፕሮግራም አድናቂም ሆነ። በግንኙነታቸውም የመካከለኛው አሜሪካ አገራት ኅብረትን ተቀላቀለ።

በዚህና በሌሎች ሥራዎች ተጠምዶ አራት ዓመታት አገሩን መራ። በ2009 ሊደረግ በታቀደው ምርጫ ላይ ዜላያ ሌላም ነገር አቅዷል። ዜጎች የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንዲደረግ ድምጽ እንዲሰጡ የሚያስችል ሕዝበ ውሳኔ ማዘጋጀት። ይህ ሕዝበ ውሳኔም ዜላያ በሚጠብቀው መልኩ ከተጠናቀቀ ዜላያን ለኹለተኛ ጊዜ እንዲወዳደር ይፈቅድለታል። የሕዝበ ውሳኔው ውጤት ዜላያን አሸናፊ እንደሚያርግ የሕዝቡ ድጋፍና ደስታ ይናገራል።

ዋሽንግተን 2009…
የባራክ አቦማ አስተዳደርን የውጪ ጉዳይ ግንኙነት እንዲዘውሩ የ‹ስቴት ዲፓርትመንት› ኃላፊ ሆነው የተመረጡት ሂላሪ ክሊንተን የዜላያን ጉዳይ እንዴት እንደሚያደርጉት ከስለላ ድርጅት ሹማምንቶቻቸው ጋር መክረው ጨርሰው ተዘጋጅተዋል። የቻቬዝ አድናቂ መሆን፣ በዛ ላይ መካከለኛው አሜሪካ አገራትን ጥምረት መቀላለቀል ለአሜሪካውያኑ የማይታለፍ መስመር ሆኖባቸዋል። በገዛ ማድነቁ፣ በገዛ መቀላቀሉ፣ አሜሪካያኑ ምናገባቸው አትሉኝም?!

በሌሎች አገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ተወዳዳሪ እንደማይገኝላቸው በሊቢያም በድጋሚ ያስመሰከሩት ሂላሪ ዜላያ መወገድ እንዳለባቸው ተስማምተው ጨርሰዋል። ሕዝበ- ውሳኔውን ማስቀደም አለብን በሚል ዝግጅቱ ተጧጡፏል።
በወቅቱ በሆንዱራስ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት አሜሪካዊው ግለሰብ ስለ ሂላሪ እቅድ ይሰሙና ለአለቃቸው ኢ-ሜይል ያደርጋሉ። አምባሳደሩ ዜላያ ፍጹም ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተመረጡ፣ አገሬው የሚወዳቸው መሆናቸውን ጠቅሰው የመፈንቅለ መንግሥቱን ጉዳይ ሂላሪ መልሰው እንዲያስቡበት ይማጸናሉ። ሂላሪ ቀጠን ባለ የአለቃነት መልዕክታቸው ‹‹አገሬው ቢወዳቸው እኛ ምን አግብቶን፤ እኛ አልወደድናቸውም። አርፈህ ተቀመጥ! ሁሉን ነገር ሲአይኤ ይጨርሰዋል።›› የሚል አጭር መልስ ይሰጧቸዋል።

ሆንዱራስ 2009…
ዜላያ ተጨማሪ ጊዜን በኃላፊነት እንዲቆይ የሕዝቡን ይሁኝታ የሚያገኝበት ቀን ደርሷል። ያም እንደሚሆን ቅንጣት ታክል የሚያጠራጥር ሁኔታ አልነበረም። በአክራሪው ብሔራዊ ፓርቲ ሹማምንት፣ በወታደራዊ ክንፉ ሹማምንት እና በዋሽንግተን ባለሥልጣናት ጥምረት የተጠነሰሰው መፈንቅለ መንግሥት ሴራ ተጠናቆ የዜላያ መኖሪያ በር ላይ ደረሰ።

የወታደራዊ ክንፉ ሹማምንት ወደ መኖሪቸው ገብተው ከሥልጣናቸው እንደተወገዱና ቤተሰባቸውን ብቻ ይዘው ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ከተከተሏቸው ወደ ጎረቤት አገር እንደሚያሸሹዋቸው ነገሯቸው። ዜላያ በቢጃማቸው ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ወደ ጎረቤት ኮሎምቢያ ተሰደዱ።

የሰሜን፣ መካከለኛው እና ደቡብ አሜሪካ መንግሥታት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት መንግሥታት በአንድ ድምጽ መፈንቅለ መንግሥቱ ሕገ ወጥ ነው፤ ዜላያም ወደ ቦታቸው መመለስ አለባቸው አሉ። ሂላሪ ክሊንተን እና የወታደራዊው ክንፍ ሹማምንት ወዳጆቻቸው ጆሮ ዳባ ልበስ አሉ።

ወዳጅ ይሆነናል ያሉትን እና የሆንዱራስ የወታደራዊው ሹማምንት ያመኑባቸውን ሮቤርቶ ሚቼሌቲን በጊዜያዊ ፕሬዘዳንትነት ሾሙ። ሆንዱራስ ዜላያ ከተሰደዱ በኋላ በወንጀል ትናጥ ጀመር። በርግጥ ዜላያ በሥልጣን በነበሩበት ወቅት ወንጀል አልነበረም ለማለት አይደለም፤ የትኛውም አገር ወንጀል አለ። ነገር ግን አዲሱ ፕሬዝዳንት ከተተኩ በኋላ ባሉት ዓመታት ወንጀል ከ50 በመቶ በላይ ጨመረ። ቅቡልነትን ለማግኘት ሲንገዳገድ የኖረው የአዲሱ ፕሬዝዳንት አስተዳደር ይባስ ብሎ የድብቅ ገዳይ ወታደሮችን አሰማራ።

ዜጎች ወንጀል ሰርታችኋል በሚል በየአስፓልቱ እየገደለ የሚጥል የፖሊስ ስርዓት ተገነባ። በጣም የሚያስገርመው ደግሞ ለዚህ የፖሊስ ኃይል በድብቅ እርዳታ የምታደርገው አሜሪካ መሆኗን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ማግኘት መቻሉ ነው። ሆንዱራስ ላይ በራሱ ሕዝብ የሚናጥ ያልወደቀ፣ ግን ወደፊት የማይራመድ መንግሥት ተመሥርቶ እነሆ ዐሥር ዓመታት ተቆጠሩ። ቀጥ ብሎ መሄድ የተሳነው፣ የእኔ ነው የሚለው ራዕይ የሌለው፣ ገደል አፋፍ ላይ እንዳለ ዝም ብሎ የሚንገዳገድ… ወይ የማይወድቅ፤ አሊያም የማይቆም መንግሥት። አካሉ ሆንዱራስ፤ የሥትንፋሱ ይሁኝታ ግን በዋሽንግተን ያለ መንግሥት። ሂላሪ ክሊንተን እቅዳቸው ሰመረ።

ሂላሪ ክሊንተን በውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ኃላፊነት ጊዜያቸው ሠራሁ ብለው ‹ሲቪ›ያቸው ላይ ከሚጽፏቸው ነገሮች ትላልቆቹ የሊቢያን እና የሆንዱራስን መንግሥት መገልበጣቸው ነው፤ ደግሞም ጽፈዋል። ሂላሪ ‹‹ከባድ ውሳኔዎች›› በሚል ርዕስ በከተቡት መጽሐፋቸው ላይ የሆንዱራሱ ዜላያ ላይ የሠሩት ሥራ በተሻለ መንገድ መሠራት የሚቻል እንደነበረ በመጥቀስ እጃቸው እንደነበረበት ያመኑበትን ዓረፍተ ነገር አስቀምጠው ነበር።
‹‹በተሻለ መንገድ፣ በባሰ መንገድ መሥራት። ሲጀመር ሰው አገር ሴራ መሥራትን ምን አመጣው?›› አትሉኝም?!  በመጽሐፉ ኹለተኛ ዕትም ላይ ለተመለከተው ግን ያ ዓረፍተ ነገር መጥፋቱን ያስተውላል።
‹‹ምነካሽ ሂላሪ ሴራውን እኛ እንደሠራነው በዓለም አደባባይ ማመን ምን ይሉታል?!›› ተብለው በባለቤታቸው ቢል ክሊንተን ተመክረው ይሆናል።

ባራክ ኦባማ ለኹለተኛ ጊዜ ሲመረጡ ኹለት መንግሥታትን ከመገልበጥ በዘለለ የረባ ሥራ ያልሰሩት ሂላሪ ክሊንተን በጆን ኬሪ ተተኩ። ጆን ኬሪ በነበራቸው ጊዜ የኢራንን የኒውክሌር ስምምነት አስፈጸሙ። ሥራ ማለት ይህ ነው! ያው በሥራቸው እንጂ በአሜሪካዊነታቸው እንዳልተቸናቸው ለማመላከት ብዬ ነው። (ምጽ!)

አሜሪካውያኑ በኢትዮጵያ…
ኢትዮጵያም የአሜሪካውያኑን ቆሻሻ አፍንጫ ኩሽናቸው ውስጥ ከገባባቸው አገራት አንዷ መሆኗን ማስረጃ እያገኘን ነው። አሜሪካውያኑ ከጊዜ ጋር እሽቅድድም ላይ ያሉ ይመስላሉ። በመግለጫ ጋጋታ ነብሳችንን ካወጡን በኋላ ማዕቀብ፤ ይህንን ጽሁፍ እየጻፍኩ ባለኹበት ዕለት ደግሞ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሥም የወጣ መግለጫ…ማስፈራሪያው በርትቷል!

የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ባለቤትነት ጭምጭምታ፣ የኢትዮ-ኤርትራ የወታደራዊ ግንባር ፍንጭ፣ የግብጽ ኩርፊያ እና የእስራኤልና የሐማስን ፍጥጫ በማስቆም ያሳየቸው ሚና፣ የሕዳሴ ግድብ የሚፈጥረው ውስጣዊ አቅም፣ የአክራሪ ጎጠኞች መታሰር እና መደምሰስ… አሜሪካውያንን የሚያሰጋ ብዙ ነገር አለ። እነዚህን ምክንያቶች አሳልጦ የሚያስተባብር በቂ የህወሓት ገንዘብም አለ። ሁሉም ምክንያቶች ተጣምረው ነው የአሜሪካውያንን የኢትዮጵያ ላይ ፖሊሲ እየዘወሩ ያሉት። አንድ ነገር በማድረግ ብቻ የሚወጡት ፍጥጫ አይሆንም። አንድ ነገር በማድረግ እንወጣው ከተባለ ግን- ያ አንድ ነገር-ሉዓላዊነትን በተመለከተ አንድ መሆን ነው።
አዲሱ ደረሰን በኢሜል አድራሻቸው
addisuderesse@gmail.com ማግኘት ይችላሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com