የቅስቀሳ ፖስተር ፎቶዎቹ ስለ ምርጫው ምን ይናገራሉ!?

Views: 33

የስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ቅስቀሳ ከሚካሄድባቸው መንገዶች መካከል የተፎካካሪ ፓርቲ የቅስቀሳ ፖስተሮችና ባነሮች ትልቁን ቦታ ይይዛሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የብልፅግና ፖስተሮች በዝተዋል ከመባል ውጪ ስለይዘታቸው ሲነገር አንሰማም፡፡ በየአደባባዩ ስለተሰቀሉ ባነሮች ተመሳሳይነት ከአላማቸው ጋር በማነጻጸር ግዛቸው አበበ ያስተዋለውን እንዲህ አስፍሮታል፡፡

ክፍል 1
መጭውን ምርጫ በስጋት እንዲታይ የሚያርጉ በርካታ ነገሮች መኖራቸውን በሚመለከት ብዙዎች እየተነጋሩበት ያለ ነገር ነው። መነጋሪያ ከሆኑት ጉዳዮች መካል ሦሥቱ የሚከተሉት ናቸው። የፖለቲካ ፓርቲ ቢባሉም በአንድ ግለሰብ ጀርባ የመሸጉ ጀሌዎቹ የሚራኮቱበት ግብግብ፣ በጀርባቸው ኃይማኖታዊ ጉዳይ ይዘው ወይም ግልጽ ሳያደርጉ አንድን ኃይማኖት ወክለው የሚራወጡ የፖለቲካ ቡድኖች፣ አንድን ብሄር በማዳን ወይም በመወከል ስም የህወሓት/ኦነግን የመሰለ ጸረ-ኢትዮጵያዊነት አጀንዳ አንግበው ኢትዮጵያዊነትን በሚያቀነቅኑ ቡድኖችና ግለሰቦች ላይ ጠላትነትን የሚያራምዱ የፖለቲካ ቡድኖች።

ከነዚህ ሦሥት አነጋጋሪ ጉዳዮች መካከል የሁለቱን እውነተኛነት በአዲሰ አበባ ለምርጫ ቅስቀሳና ዕጩወችን ለማስተዋወቅ በሚል በየቦታው ከተገተሩ ትልልቅና ትንንሽ ባነሮችና ፖስተሮች፣ እንዲሁም በየግድግዳውና በየፖሉ ከተለጠፉ ወረቀቶች መረዳት የሚቻል ሲሆን፣ ሦሥተኛውን የባለ ጠባብ አጀንዳወችን ጉዳይ ለማረጋገጥ ደግሞ በየክልሉ የተሰቀሉና የተለጠፉ የምርጫ ቅስቀሳ ፖስተሮችንና ባነሮችን በማየት መረዳት ይቻላል። በዚህ ጽሑፍ የግለሰቦችን ምስሎች በሰፊው መጠቀምን በሚመለከት ሰፋ ያለ ነገር ለማለት ይሞከራል።
በአዲሰ አበባ የብልጽግና፣ የኢዜማና የባልደራስ ፖስተሮችና ባነሮች የቡድኖቹን መሪዎች ፎቶ ይዘው እዚህና እዚያ ይታያሉ። የፎቶዎቹ በየቦታው መደንጎር ሦስቱ ቡድኖች እነዚህን መሪዎቻቸውን የጥንካሬ ምልክት አድርገው ከማሳየት አልፈው እነዚህን መሪዎቻቸውን የተመላኪነት ክብር እየሰጧቸው ይሆን ብሎ ለመጠየቅ የሚጋብዝ ነው። ሦሥቱ ፓርቲወች ቡድናቸው በዓላማውና በለአገርና ለሕዝብ በሰነቀው ህልም ሕዝብ ይመርጠናል ብለው ከማሰብ ይልቅ የነዚህን ግለሰቦች ፎቶ በየቦታው በመስቀል ሕዝብ ለግለሰቦቹ ብሎ ፓርቲውን ይመርጣል በሚል የቅዠት ዓለም ውስጥ የሚዋኙ ይመስላሉ።

ብልጽግና በየቦታው የገተራቸውን የቅስቀሳና የዕጩ ማሳወቂያ ፖስተሮች ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዲሸከሙ ፈርዶባቸዋል። የጠቅላዩ ምስሎች በየቀበሌው ካድሬዎች ወይም በየክፍለ ከተሞቹ ፖለቲከኞች እየተመረጡ የታተሙ ስለሆኑ ብዙዎቹ ፎቶዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩን የኮትና የከረባት ማስታወቂያ የሚሰራ አርቲስት ወይም ለቁንጅና ውድድር ቀረበ ጎረምሳ አስመስሏቸዋል። ብልጽግና በጠቅላይ ሚ/ሩ ምስሎች ፋንታ ሰርቻቸዋለሁ የሚላቸውን ተቋማት፣ መናፈሻወችና የመሰረተ ልማት አውታሮች ለቅስቀሳው አለመጠቀሙ ጠቅላዩን ሕዝብ ስለሚወዳቸው በእሳቸው ስም ዕጩወቼን በሙሉ ይመረጡልኛል የሚል 2010 ዓም ላይ ቆሞ የቀረን ስትራቴጂ ለመጠቀም የፈለገ ይመስላል።

መንግስት አለ ከተባለ ኢትዮጵያችን በጣም በተዝረከረከና ደካማ በሆነ መንግሥታዊ አመራር በፈጠራቸው በርካታ ችግሮች ውስጥ መዘፈቋን መካድ አይቻልም። ምንም እንኳ የገዥው ቡድን አመራሮችና አባላት መጭው ዘመን ብሩህና የብልጽግና መሆኑን እየተናገሩ በመዝፈንና በመቧረቅ ላይ ቢሆኑም በእነሱ አመራር ዘመን በበርካታ አካባቢወች እንዲሁም “ከ” እና “ወደ” አዲስ አበባ የሚያጓጉዙ አገር አቋራጭ መንገዶች ሳይቀሩ አስተማማኝ የሆነ ሰላም አጥተው ግድያዎችን፣ አፈናዎችንና ዝርፊያዎችን ደጋግመው እያስተናገዱ ነው። የአመራር ችግሩ አገሪቱን ምስቅልቅሏን ባወጣና ከፍተኛ ጦርነትን እንዲካሄድ ባስገደደ ጥበብ የለሽነት የተበከለ ከመሆን አልፎ፣ በዓለም ዓቀፍ መድረክም ታይቶ በማያውቅ ደረጃ የደከመና የተናቀ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ተመዝግቧል። እናም እኛ የእነ ብሬዤኔቭን ፎቶ ይዘን “የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ይውደም!” ብለን በጨፈርንበት አደባባይ ዛሬ ልጆቻችን የፑቲንን ፎቶ ይዘው “አሜሪካ እጅሽን ሰብሰቢ!!” ብለው ለመዝፈን በቅተዋል። በደርግ ዘመን እኛ “የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ይውደም!” እያልን ስንጨፍር ግብጾች ‘አሜሪካን ለማውደም ስትሄዱ እግረ መንገችሁን እኛን ረምርማችሁን እንዳታልፉ’ ብለው ተሳልቀውብናል። ዛሬስ ምን እያሉን ይሆን? ግብጾች በሱዳን ተደጋጋሚ የጦርነት ልምምድ እያደረጉ ነው።

ከጥቂት ቀናት በኋላ ኢትዮጵያ የ2014 ዓም ዓመታዊ በጀቷን ትቀምራለች፡፡ ከሚታየው የኑሮ ውድነትና የኢኮኖሚ መንገዳገድ በመነሳት ለ2013 ዓም ከ600 ቢሊዮን ብር ላቅ ብሎ የተሰላው በጀት ለቀጣዩ ዓመት ከ800 ቢሊዮን እስከ 1 ትሪሊዮን ብር መመደብን የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል። በየዓመቱ በጀት ሲመደብ የሚሰማው ወደ ግማሽ የሚሆነውን ከብድርና ከዕርዳታ ይሸፈናል የሚል መግለጫ ዘንድሮም ሊሰማ ይችላል። በኦሕዴድ/ብልጽግናው መሪ “…ቢቀርብንም የነቀዘ ስንዴዋ ነው…” ተብላ ማስተዋል የጎደለው ሽርደዳ የተዘሰረዘረባት አሜሪካ፣ የአሜሪካ አጋሮችና ተባባሪዎች የሆኑት እነ ካናዳና የአውሮፓ አገራት፣ የአሜሪካ መሳሪያዎችና ታዛዦች የሆኑት የዓለም ባንክ (WB) እና የዓለም ገንዘብ ድርጅት (IMF) ናቸው የብድሩንም ሆነ የዕርዳታውን የአንበሳ ድርሻ የሚሸፍኑት። በጠቅላይ ሚ/ሩ ጎረምሶች ተብለው የተዘለፉትም እነሱ ሊሆኑ ይችላሉ። ብልጥና አስተዋይ የሆነ መሪ ‘የጎረምሶቹን’ ጉርምስና መከላከል የሚሞክረው ዱላቸውን ሲያነሱ ሳይሆን እየሸለሙና በየሰበቡ ገንዘብ እየሰጡ ለማጃጃል ሲሞክሩ ነበር። የኃያላኑ አገራት መሪዎች፣ የኃያላኑ በተለይም የአሜሪካ መሳሪያ የሆኑት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትም ሆኑ አንዲት የንጉስ እናት የምትባለው የዓረብ ሴትዮ አምስት ሳንቲም እንዲሁ ያለ ዓላማ አይሰጡም። ለምኖ ለማግኘት የተፈጠረ ሰው ሊኖር ቢችልም ያለ አንዳች ጥቅም ገንዘቡን ለሌላ የሚሰጥ የውጭ መንግሥት ወይም ባለሥልጣን ታይቶ አይታወቅም።

ጠቅላይ ሚ/ሩ ሠላም ከጠማቸውና የኑሮ እፎይታ ከናፈቃቸው ዜጎች በየቦታው ጥያቄ በቀረበላቸው ቁጥር የሰፈር ሚሊሻ አይደለሁም፤ ጠቅላይ ሚ/ር ሁሉን ስራ አይሰራም፤ ስንቱን መዋቅር ላጸዳና ላሻሽል ነው፣ በየጎዳናው ማንቁርት እያነቀ የሚጥል ኃይል በተለያዩ አገራት እያሰለጠንኩ ነው ወዘተ. እያሉ የመቶዎቹንና የሽዎቹን ሞት፣ የሚሊዮኖቹን መፈናቀል፣ የዐስሮች ሚሊዮኖቹን በስጋትና በሰቀቀን መኖር እያቃለሉ ስለሚያልፉ፣ ቡድናቸው ብልጽግናም የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ሁሉ ችላ ብሎ ሥልጣንን በማስቀጠል ሩጫው ላይ አተኩሮ ይታያል።

የአንድን ግለሰብ ፎቶ እዚህና እዚያ በመሰተር ምርጫውን የማሸነፍ ስትራቴጂ የሚከተለው ሁለተኛው ቡድን ኢዜማ ነው። ኢዜማ ብርሃኑ ነጋን (ፕ/ር) ምርጫን ለማሸነፍ አስማተኛ ካርድ እድርጎ የሚያይ ቡድን ነው። ኢዜማ እንደ ብልጽግና የማይተች፣ የማይገመገም፣ በሄደበት ሁሉ የሚከተሉትና ለተናገረው ሁሉ የሚያጨበጭቡለት መሪ ያለው ቡድን ነው። የኢዜማው ፕሮፌሰር በብዙ መንገዶች በብልጽግና ቡድን ውስጥ አሉ ከሚባሉ ‘ትልቅ’ ሰወች የተሻሉ ቢሆኑም፣ ፕሮፌሰሩ በተገኘው ስልጣን ላይ ሁሉ ጉብ ማለታቸው ሥልጣን ለማግኘት ወይም ሥልጣንን ላለማጣት በተደጋጋሚ ቁርቁስ ውስጥ የገቡ ሰው መሆናቸው የአምባገነንነትን በር በማናኳኳት ላይ ያሉ ሰው እንደሆኑ ተደርገው በብዙዎች ዘንድ እንዲጠረጠሩ እያደረጋቸው ነው። የኢዜማው መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ማንኛውንም ስልጣን እንካ ሲባሉ አይመቸኝም፣ አልወጣውም፣ ከእኔ የተሸለ ሰው ፈልጉ ማለት ፍጽሞ የማይወዱ ሰው ናቸው። ይህን ባህሪያቸውን የሚያጋልጠው አንዱ ታሪካቸው ያለ ምንም ብቃት፣ ያለ ምንም ተሞክሮና ያለ ምንም ሃሳብ የብዙዎችን የሕይወትና የአካል ግብር የሚጠይውን የሽምቅ ተዋጊ ቡድን መሪነት ያለ ምንም ማንገራገር መቀበላቸው ነው። ፕሮፌሰሩ ለዚህ መሪነት የተመረጡት በኤርትራ በረሀ በሌሉበት ጊዜ ሲሆን፣ በምርጫው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረው ፕሮፌሰሩን ለመመረጥ ያበቁት የኤርትራ ባለሥልናትና ከውጭ አገራት ወደ ኤርትራ የተጓዙ የቡድኑ አባላት ናቸው። የፕሮፌሰሩን መመረጥ በሚመለከት ከፍተኛ ተቃውሞ ሲዘነር የብርሃኑ ነጋን የ1960ወቹን ኢሕአፓነት ሕይወት በማውሳት ጦርን ለመምራት ብቁ ናቸው ለማት ተሞክሯል። ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ለሽምቅ ውጊያ መሪነት ሲመረጡ አሜሪካ ውስጥ እያስተማሩና ራሳቸውም ፕሮፌሰር ለመሆን እየተማሩ ነበረ። እናም ብርሃኑ ነጋ ዶላር ለማግኘት ፈረንጆቹን ለማስተማር መጽሐፍትን ሲቆፍሩ ኤርትራ በረሀ አለ የሚባለው ተዋጊ ምሽጉን ይቆፍር ነበር፡፡ ብርሃኑ ነጋ ፕሮፌሰር ለመሆን መጽሐፍት ሲቆፍሩ የግንቦት ሰባት ተዋጊ መቃብሩን ይቆፍር ነበረ። የዚህ ዓይነቱ እነ ጅሎና እነ አጃጅሎ የመሰረቱትን ማኀበር የመሰለ ቡድን ከኤርትራ ሳይወጣ፣ ወጣ ካለም ታሪክ ሳይሠራ እየተቀጠፈ በርካታ ዓመታትን በኤርትራ ምድር ከርሞ የኢትዮጵያ ወጣቶች ነጻ አውጥተውት ከበረሀ ወደ ከተማ ገብቷል።

በየሄዱበት አገር ዜግነታውን በቀየሩ በርካታ ሰወች ሲተራመስ የኖረው ግንቦት ሰባት ወደ አገር ቤት ገብቶ አንዳንድ አባላቱ በሳምንታትና በወራት ዕድሜ ወደ ፈረንጅ አገር ሲመለሱ አንዳንዶቹ እዚህ ቀርተው ኢዜማን መስርተዋል። ከመስራቾቹ ጥቂት የማይባሉት ዜግነታችሁን አስተካክሉ (ኢትዮጵያዊ ሁኑ) ሲባሉ አሻፈረኝ ብለው የፈረንጅ አገር ዜግነታቸውን ይዘው ከቡድኑ እንዲርቁ ተገድደዋል። ይህን መሰሉ አካሄድ ኢትዮጵያን ከዶላርና ከፓውንድ አሳንሶ ከማየት የሚመጣ መሆኑን መጠራጠር ተገቢ አይደለም። የዜግነት ፖለቲካን የሚያራምድ የፖለቲካ ፓርቲ መስራችና መሪ ነኝ የሚሉት ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከረር አድርጎ ቡድኑ ራሱን ኢትዮጵያዊ ካልሆኑ ሰዎች እንዲያጠራ ከማዘዙ በፊት ቡድናቸው የዜግነት ጉዳዮችን ችላ ብሎ ማንንም በአባልነትና በአመራርነት የማቀፉን ተገቢነት በሚመለከት ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበረ። የፕሮፌሰሩ መልስ የቁጣ ቃና የነበረውና “የዜግነት ፖለቲካ ሲባል የግድ ኢትዮጵያዊ መሆን አለበት ማለት አይደለም” ሲሉ ተሰምተዋል።

የግንቦት-7/ኢዜማ ሰዎች በምርጫው ሕግ ውስጥ ለመምረጥና ለመመረጥ በዜግነት ኢትዮጵያዊ መሆንን ግድ የሚለውን አንቀጽ ችላ ብለው የተወሰኑ ጊዜያትን አሳልፈዋል። የግንቦት-7/ኢዜማ ሰዎች በፓርቲዎች መመስረቻ ሕግ ውስጥ አንድ ፓርቲ መመስረት የሚገባውና በአባልነት ማቀፍ የሚችለው ኢትዮጵያዊ የሆኑ ሰዎችን ብቻ መሆኑን፣ ገንዘብ መሰብሰብ የሚገባውም ከኢትዮጵያውያን ብቻ መሆኑን የሚደነግገውን አንቀጽ በማን አለብኝነት እየጣሱ የተወሰኑ ጊዜያትን ተራምደዋል።

የውጭ አገር ዜግነታቸውን አስበልጠው ቡድኑን ጥለው የወጡ የግንቦት-7/ኢዜማ ሰወች ኤዜማንና ፕሮፌሰሩን ተመርጠው የጣምራ ዜግነት ሕግ እንዲወጣ፣ በምርጫውና በፓርቲወች መመስረቻ ሕግ ውስጥ የሚገኙትን የሌላ አገር ዜጎችን ከፓርቲ አባልነት፣ መራጭና ተመራጭ ከመሆን የሚያግዱትን አንተቀጾች ሰርዘው ለኪሳቸው የሃብታም አገር ዜግነትን፣ ለስልጣን ጥማቸው ኢትዮጵያዊነትን ይዘው ለመምነሽነሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ የብዙወች ጥርጣሬ ነው። ይህ ማለት ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በፈረንጅ ዩንቨርስቲወች በዕውቀታቸው እየሰሩና ዶላር እያካበቱ በኤርትራ ምድር የመሸጉ ምስኪኖችን በሪሞት ኮንትሮል ለመምራት የሞከሩበትን የወራት ጨዋታ የመሰለ በሁለት እግር ሁለት ዛፍ የመውጣት ቅዠት እግርን ከአራት ኪሎ እስከ ዋሽንግተን ወይም እስኪ ለንደን በማንፈራጠጥ አገርን መጫወቻ ማድረግ ይቻላል ማለት ነው።

የብርሃኑ ነጋን (ፕ/ር) ፎቶ በየጎዳናውና በየአደባባዩ በመስቀል ሊኮፈሱ የሚሞከሩ የኢዜማ አመራሮች አባላት በአንድ ወቅት ‘ፕሮፌሰሩ ኢዜማ ናቸው ብልጽግና? ኢዜማ የብልጽግና ተለታፊ ነውን?’ ተብሎ እስኪጠይቅ ድረስ ፕሮፌሰሩ የጠቅላይ ሚ/ሩ አወዳሽና አምላኪ ሆነው ሲታዩ ዝም ባሉበት መንፈስ የዜንግነቱን ጉዳይ በቸልታ ይመለከቱት ይሆናል። ነገር ግን የግንቦት ሰባት አመራር የነበሩትን ታደሰ ብሩን (ዶ/ር) በልቶ ደብዛቸውን ስላጠፋውና ጭጭ ስላሰኛቸው ጅብ ማሰብ ይገባቸዋል። ዶክተሩ በአንድ ወቅት ዜግነት የሰጣቸው የእንግሊዝ መንግስት በአሸባሪነት ጠርጥሯቸው አርፈው እንዲቀመጡ መማስጠንቀቁን፣ የቁም አስረኛ አድርጎ ከተፈቀደላቸው ቦታ ውጭ የትም መላወስ እንደማይችሉ ከነገራቸው በኋላ ራሳቸውን ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ ተገድደዋል።

ኢትዮጵያዊ የሆኑና የየትኛውንም የውጭ አገር ዜግነት ጥቅም ያልቀመሱ የኢዜማ አባላትና አመራሮች አንድ ሰው የእንግሊዝን ዜግነት ሲወስድ ለእንግሊዟ ንግስትና ለወራሷቿ ብቻ ታማኝ አገልጋይ ለመሆን ቃል እንደሚገባ፣ አንድ ሰው የአሜሪካን ዜግነት ሲወስድ ከአሜሪካ ውጭ ለማንኛውም አገር (ለኢትዮጵያም ጭምር) ያለውን ታማኝነት ለመሻር ቃል እንደሚገባ አውቀው የብርሃኑ ነጋንና የውጭ ዜጋ የሆኑ ጓዶቻውን ሴራ መዋጋት ይገባቸዋል። አምልኮተ ብርሃኑ ነጋ ገደብ ካጣ መጨረሻው ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ጠላት ሆኖ መቆም መሆኑን ማወቅ አለባቸው።
ግዛቸው አበበ በኢሜል አድራሻቸው
gizachewabe@gmail.com ማግኘት ይችላሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com