የማስታወቂያዎች ፍትሃዊነት አለመኖር የግል የኅትመት ሚዲያዎችን ስጋት ውስጥ ከቷል

Views: 60

የኢትዮጵያ ፕሬስ ሌሎች ዓለማት ላይ እንዳሉት በመንግሥትም ሆነ በግለሰብ የመደገፍ አቅማቸው ዝቅተኛ ነው። በተለይ ደግሞ አንባቢ የሚባለው የማኅበረሰብ ክፍል እየተቀዛቀዘ በመጣበት በዚህ ወቅት መንግሥት ለኅትመት ውጤቶች ድጋፍ የማያደርግ ከሆነ እየተዳከሙ ከገበያው እንደሚወጡ አያጠያይቅም። ለዚህ የኅትመት ውጤቶች መዳከም ምክንያት ከሆኑት አንዱ ስለሆነው የማስታወቂያ አስነጋሪ ድርጅቶች ችግር ምን እንደሆነ እና መፍትሄዎቹን የአዲስ ማለዳዋ ሰላማዊት መንገሻ በስፋት ተመልክታዋለች።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ከዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ ዘመነ ኢሕአዴግ (የአሁኑ ብልጽግና) ድረስ በመንግሥታዊ ጭቆና ውስጥ የወደቀና በንስር ዓይን ሥር የኖረ ዘርፍ ነው። በኢትዮጵያ ከአወዳሽ ሚዲያው ውጭ ያለው ፕሬስ እንዳይወቅስ እና እንዳይከስ፣ ሕዝብን እንዳያነቃና ለመብት ጥያቄ እንዳያነሳሳ፣ መረጃ እንዳያሰራጭና ለውጥ እንዳይፈጥር መንገዱን የእሾህ ጋሬጣ ሲያበጁበት በኖሩት ገዢ መንግሥታት ሳቢያ ከዳዴ ጉዞ ፈቅ ሳይል አንድ ክፍለ ዘመን ይዟል።

በተለይም የኢሕአዴግ መንግሥት፣ በአገሪቱ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሕገ መንግሥታዊ በሆነበት ማግስት ሊያብብ የጀመረውን ፕሬስ በክፉ ዱላ ከመታውና ጋዜጠኞችን ማዋከብ የኅልውና ጥያቄ አድርጎ ከተነሳ ወዲህ፣ ይህ የፕሬስ በተለይም የነጻው ፕሬስ ዘርፍ ʻየደፈረ ብቻʼ የሚገባበት ʻቀይ ዞንʼ ሆኖ እንዲቆይ ምክንያት ሆኗል።

የመጀመሪያው ጋዜጣ ‘አእምሮ’ ከእጅ ጽሑፍ ወጥቶ በማሽን መታተም ከጀመረ (ከ1902 ወዲህ) ከመቶ ዓመታት በላይ ሆኖታል። ከዚያ በኋላ ‘ብርሃንና ሰላም’ የተባለው ጋዜጣም የተወሰነ ጊዜ መዝለቅ ችሎ ነበር። እስካሁን ድረስ መዝለቅ የቻለው እና “አዲስ ዘመን” የሚባለው በመንግሥት የሚታተም ጋዜጣ ሆኖ ለአንባቢያን የደረሰው በ1941 ነው። የዐፄ ኃይለሥላሴንና የደርግን ዘመን ተሻግረው አሁን የኢሕአዴግ ዘመን ድረስ የዘለቁትን እነ አዲስ ዘመንን የመሳሰሉ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጦችን ጨምሮ፣ በ1902 አሐዱ ተብሎ በዘመናዊ ኅትመት የተዘጋጀው ጋዜጣ ዕድገት በ2013 መድረስ የቻለበት የብዛት ጣሪያ በጣም ጥቂት ነው።

በ1985 በኢትዮጵያ ውስጥ 28 ጋዜጣና 65 መጽሔቶች የነበሩ ሲሆን፥ በ1986 ደግሞ ይህ ቁጥር አሻቅቦ 79 ጋዜጣና 38 መጽሔቶች በድምሩ 117 የኅትመት ውጤቶች ገበያውን አጥለቅልቀውት ነበር። በጊዜው የዜጎች የፖለቲካ ተሳትፎ የገነነበት፣ ሕዝቡ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ከምንጊዜውም በላይ ያገባኛል ያለበት ወቅት ስለነበር፥ አዲስ ከነበረው የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ ጋር ተዳምሮ ዛሬ ላይ መልሶ የሚደገም የማይመስል ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተንሰራፋ። ይህን ተገን ያደረገው የኢትዮጵያ ፕሬስ፣ በተለይም የግሉ ፕሬስ፣ በመንግሥት አሠራሮች ላይ ብቻ ሳይሆን በማኅበረ ምጣኔ ሀብት ተሳትፎውም የጎላ ድርሻ መያዝ ጀመረ። አሳታሚዎች በተለያየ አቀራረብ ይዘዋቸው ብቅ ከሚሉት የፕሬስ ውጤቶች ከሲሦ በላይ የሆኑት የፖለቲካ ይዘት ያላቸው ነበሩ። ጊዜው የጋዜጦች ብቻ ሳይሆን የመጽሔቶች አብዮትም የፈነዳበት ነበር።

ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት እየተከፈቱ ያሉ የብሮድካስት እና ፕሪንት ሚዲያዎች መበራከት ይበል የሚያሰኝ ነው። ሚዲያ ማለት ሕዝብ ችግሮቹን ይፋ የሚያደርግበት፣ መንግስትም ለሕዝብ መረጃዎችን የሚያስተላልፍበት ሰንሰለት ነው። ባደጉት አገራት እንኳን ብንመለከት የመንግስት ድምጽ ከሆኑት ሚዲያዎች ጀምሮ በየአካባቢው የሕብረተሰቡን ችግር የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙኃን በርካታ ናቸው። አሁን አሁን እየታየ ያለው የመገናኛ ብዙኃን መበራከት እንደ መልካም አጋጣሚ ቢወሰድም የሚያቀርቧቸው ዝግጅቶች ላይ የይዘት እጥረት በመኖሩ በማስታወቂያ እና በስፖንሰር ድጋፍ እያገኙ አይደለም። በርግጥ አንዳንድ ተቋማት ላይ የሚቀርቡ ለሕብረተሰቡ ጥቅም ያላቸው ፕሮግራሞች በማስታወቂያ እጥረት ሳቢያ ከገበያ ሲወጡ፣ ጥቅም እና ሀሳብ የሌላቸው ፕሮግራሞችን እያቀረቡ በማስታወቂያ እና ስፖንሰር የሚደገፉ መኖራቸው የማይካድ ሀቅ ነው። ከእነዚህ በማስታወቂያ ድጋፍ የማያገኙ መገናኛ ብዙኃን መካከል አንዱ የኅትመት ውጤቶች ናቸው።

በአገራችን የሚገኙ የኅትመት ሚዲያዎች መዳከም እየታየባቸው ነው። የኅትመት ሚዲያው የሚሰራው ለትርፍ ብቻም ሳይሆን መረጃዎችንና ዝርዝር ጉዳዮችን በጥልቀት በመዳሰስ ለሕዝቡ ለማቅረብ ነው። ለኅትመት ሚዲያዎች መዳከምና ከገበያ መውጣት እንደ ምክንያት ከሚነሱት መካከል አንዱ ማስታወቂያ አስነጋሪ ድርጅች አለመኖር ነው። እውነት ለመናገር እንደ አገር የተፈጠረው የወረቀት ዋጋ መወደድ በኅትመት ውጤቶች ላይ ጫና መፍጠሩ አልቀረም። ይህ የወረቀት መወደድን ተቋቁሞ ስራውን ለማስቀጠል ግን ማስታወቂያ አስነጋሪ ድርጅቶች ለኅትመት ውጤቶች የሚያደርጉት ድጋፍ አናሳ ነው። በተለይ ደግሞ እንደ ቅሬታ የሚነሳው የመንግስት ኅትመት ውጤቶች ላይ የሚለቀቁት እንደ ጨረታ፣ የስራ ማስታወቂያ እና የመንግስት ማስታወቂያዎች በግል ለሚታተሙ የኅትመት ውጤቶች ተደራሽ አለመሆናቸው ነው።

ከሶስት ዓመት በፊት የካቲት 2010 ግዮን መጽሔት በማለት የተጀመረው በአሁኑ ሰዓት ኢትዮ-ሐበሻ በማለት ደግሞ ወደ ጋዜጣ አድማሱን ያሰፋው አንዱ ተጽእኖ እየደረሰበት ያለ የኅትመት ውጤት ነው። የግዮን መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመወርቅ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ድርጅታችን ከመጽሔት አልፎ ጋዜጣ ማሳተም የጀመረው የሚመች ሁኔታ ኖሮ ሳይሆን በአገራችን የሚካሄደውን ምርጫ በተመለከተ ለመዘገብ እና ወቅታዊ የሆኑ መረጃዎችን ለማድረስ ከማሰብ ነው ብለዋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቂያዎችን ይሰጠናል የሚል ተስፋ እንደነበራቸው ይናራሉ። ነገር ግን እንኳን አዲስ ለተጀመረው ጋዜጣ ቀድሞ ለነበረው መጽሔት እንኳን የምርጫ ማስታወቂያዎች እንዳልደረሳቸው ይናገራሉ። ተቋማቸውም ቢሆን በዚህ ፍትሃዊ ያልሆነ የማስታወቂያ ክፍፍል ምክንያት የኅትመት መገናኛ ብዙኀን የወደፊት ተስፋው አስጊ ነው ብለዋል። የመጽሄቱም ሆነ የጋዜጣው ቀጣይነት አስጊ ነው ያልኩት በሙያው ብቃት አንሶን ሳይሆን ያለው የኢኮኖሚ ጫና ነው ሲሉ ፍቃዱ ተናግረዋል።

ሌሎች የመንግስት ኅትመት ሚዲያዎች ላይ ያለው የማስታወቂያዎች እና የመንግስት ጨረታዎች በፊት ከነበረው የመንግስት አወቃቀር እስከ አሁን በሞኖፖል ነው የተያዙት ሲሉ ፍቃዱ ገልጸዋል። የመንግስት ለውጥ ቢኖርም የኅትመት ሚዲያውን ግን ለመለወጥ የተደረገ ጥረት አለመኖሩንም አንስተዋል። በአገራችን የማንበብ ባህል የተዳከመ መሆኑ እየታወቀ ሕብረተሰቡ የማንበብ ልምዱን እንዲያዳብር እንደዚህ አይነት የኅትመት ውጤቶችን ማገዝ እንደሚያስፈልግም ፍቃዱ ጠቁመዋል። ሕብረተሰቡ ጋዜጣና መጽሔት እንዲያነብ የምናበረታታው ከሆነ ንቃተ ኅሊናው ስለሚያድግ ሌሎች ትላልቅ መጻሕፍትንም እንዲያነብ በር ከፋች መሆኑ መታወቅ አለበት ብለዋል።

ፍቃዱ እንደሚሉት ከሆነ የመንግስት ተቋማት ማስታወቂያ የሚሰጡበት መስፈርት ከተደራሽነት አንጻር እና ከኮፒ ብዛት ከሆነ ግዮን መጽሔት ከሚያሳትማቸው ኅትመቶች በታች ለሆኑት እየተሰጠ መሆኑን እንደ ችግር አንስተዋል።
በተለይ ደግሞ ምርጫ ቦርድ ማስታወቂያ እንዲሰጣቸው የጠየቁ ሲሆን እስካሁን ምላሽ እንዳላገኙ ታውቋል።

ግዮን መጽሔት ከተጀመረ እስከ አሁን ድረስ በግል በሚያገኛቸው ስፖንሰሮች ችግሮችን እየተቋቋመ ያለ ሲሆን፣ በመካከል ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ፍቃዱ በመታሰሩ ምክንያት ለ4 ወር ተቋርጦ ኪሳራ ገጥሞት ነበር። ነገር ግን ለሙያው ትልቅ ፍቅር ስላላቸው ይህንን ችግር በብቃት በመወጣት ዳግም በማንሰራራት ወደ ሥራ መግባት ችለዋል።

መንግትሥት ተለወጠ ይባላል እንጂ በመንግሥት ተቋማት ላይ ያሉ ሰራተኞች ለሕትመት ሚዲያ ያላቸው አመለካከት የበፊቱ ስርዓት ላይ እንደነበረው ነው። የስርዓት ለውጥ እንጂ የአስተሳሰብ ለውጥ አለመምጣቱን ፍቃዱ ገልጸዋል። አሁን በቅርብ በወጣ አዋጅ መሰረት ማንኛውም ሚዲያ ላይ የሚሰራጩ ማስታወቂዎች በፍትሃዊነት ላይ እንዲመሰረቱ ይደነግጋል። ይህንን መሰረት በማድረግ ማስታወቂያ እንዲሰጠን እንጠይቃለን፣ ነገር ግን ብንጠይቅም ምላሽ እንደማይሰጠን እያወቅን ነው ብለዋል። መንግስት እንኳን ማስታወቂያዎችን ሊሰጥ ቀርቶ የተለያዩ መግለጫዎችንም ለመጥራት ፍቃደኛ አለመሆኑን ነው ፍቃዱ የሚያነሱት።

ግዮን መጽሔትን በአሁኑ ሰዓት በግል ማተሚያ ቤት የሚያሳትም ሲሆን፣ ይህ ደግሞ የሆነው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ዋጋ በመወደዱ መሆኑን ፍቃዱ ገልጸዋል። እንደ ተጨማሪ ምክንያት ያነሱት ደግሞ ኅትመቱ በተፈለገው ቀን እንደሚወጣ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። በመሃል ሌሎች የመንግስት ሰዎች ከመጡ የግል ስራዎችን ትተው ሊሰሩ ስለሚችሉ በወቅቱ አይደርስልንም ብለዋል። እነዚህንና ሌሎች ቢሮክራሲዎችን ለመራቅ ወደ ግል ኅትመት ቤቶች ለመሄድ ተገደናል ብለዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አሳታሚዎች ወደ ግል ማተሚያ ቤቶች ለመሄዳቸው ምክንያቱ የዋጋ መጨመር መሆኑን አዲስ ማለዳ ለብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ጥያቄ አንስታ ነበር። የማተሚያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት እና ማኀበራዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሙያና የጽ/ቤት ኃላፊው ወኪል የሆኑት መሳይ ታደሰ እንደተናገሩት፣ ተቋማችን ሁሉንም ሥራዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሰራ ነው ብለዋል። ምናልባት ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት የወረቀት ዋጋ በጣም በመወደዱ ምክንያት የኅትመት ዋጋዎች መጨመር አንዳንዶችን ከገበያ ያወጣበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። አንዳንዶቹ ደግሞ በራሳቸው ፍላጎት ዋጋውንና ጥራቱን በማወዳደር ወደግል ማተሚያ ቤቶች ሄደዋል።

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከወረቀት ዋጋ መወደድ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ጫና ለመቀነስ በራሱ ኃላፊነት ሚዲያዎቹ ላይ ዋጋ ሳይጨምር እያሳተመ እንደሚገኝ መሳይ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የግል ማተሚያ ቤት ላይ ለመሄድ ያነሰ ዋጋ ካገኙ ብርሃንና ሰላም እንዲያሳትሙ አይገደዱም። እንደሚታወቀው የወረቀት ዋጋ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መጥቷል። ብርሃንና ሰላም እንደ ኅትመት ተቋም ማንኛውንም ስራ እኩል በማየት የሚሰራ ተቋም ነው ብለዋል።

ይልቁንም ሥራዎች እንዲመጡ ይፈለጋል ነው ያሉት መሳይ። በአሁኑ ሰዓት በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ውስጥ የሚታተሙ የግል እና የመንግስት ኅትመቶች 16 መሆናቸው ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የግዮን መጽሔት ፍቃዱ እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ብዙ ገንዘብ የሚያተርፍ በመሆኑ ለመንግስት ተቋማት የሚመች አሰራር ነው ያለው። በአሁኑ ወቅት የወረቀት ዋጋ መወደድ ምንም ጥያቄ የለውም፤ ነገር ግን መንግስት ለጋዜጣ እና መጽሔት የሚጠቅሙ ወረቀቶች ላይ የጣለው ቀረጥ ያለአግባብ መሆኑን ሳያነሱ አላለፉም። ለኅትመት ሚዲያ የሚጠቅሙ ወረቀቶች ላይ የተጣለው ቀረጥ እንደ መደበኛ መጻሕፍት ኅትመት ነጻ መሆን ይገባዋልም ብለዋል።

በፊት የነበረው የመንግሥት ስርዓት ሚዲያውን ለማዳከም በተለያዩ መንገዶች ጫና ሲፈጥር ቆይቷል። አሁንም ያ ጫና አልበረደም ያሉት ፍቃዱ በተለወጠው የመንግሥት ስርዓትም ተግባራዊ መደረጉ ለኅትመት ሚዲያው ማነቆ ነው ብለዋል። እነዚህን ለኅትመት ሚዲያ ማነቆ የሆኑ የወረቀት መወደድ እና የመንግሥት ማስታወቂያዎች ፍትሃዊነት አለመኖር መንግሥት እንዲያስብበት ጥያቄ አቅርበዋል።

ግዮን መጽሔት የመንግሥት ድጎማ እንደማያስፈልገው የገለጸው ፍቃዱ ቢያንስ ቢያንስ የኅትመት እና የቢሮ ኪራይ መሸፈን የሚያስችል ማስታወቂያዎችን እንዲያገኙ ሁኔታዎች ቢመቻቹ ኢኮኖሚውን ተቋቁሞ መወጣት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
የኅትመት ዋጋ መወደድ ያልተፈታ ጉዳይ ሆኗል የሚሉት የኅትመት ክትትልና ስርጭት ባለሙያ የሆኑት በዛብህ ተክሉ ናቸው። የኅትመት ዋጋ ስለጨመረ ጋዜጦች ላይ ዋጋ ጨምሮ መሸጥ ከባድ መሆኑንም ያነሳሉ። በዛብህ እንደምሳሌ የጠቀሱት አንድ ጋዜጣ 30 ብር ሸጦ ለማትረፍ ቢታሰብ ማንም እንደማይገዛ ይታወቃል። አንድ ግለሰብ ጋዜጣ 30 ብር ከሚገዛ ዳቦ ገዝቶ ወደ ቤቱ መግባትን ይመርጣል። በተጨማሪም ደግሞ ያለው የኢኮኖሚ ጫና ረክሶም እንዲገዙ አይገፋፋም። ስለዚህ ይህ ግለሰብ ጋዜጣውን ከመግዛት ይልቅ በ1 ብር ተከራይቶ ማንበብ አማራጭ ያደርገዋል።

ይህን የፈጠረው የጋዜጦቹ መወደድ ሳይሆን የኢኮኖሚው መዳከም ነው ሲል በዛብህ ያነሳል። ተከራይቶ በሚያነብበት ወቅት ተጠቃሚ የሚሆነው አዟሪው ነው። በዚህ መሀል አሳታሚውም ሆነ አከፋፋዩ አይጠቀምም። አሳታሚው አሳትሞ ለአከፋፋይ ይሰጣል። አከፋፋዩ ለአዟሪው ይሰጣል። አዟሪው ደግሞ ከኅትመቶቹ ሽያጭ ሳይሆን ከሚያከራው ላይ የዕለት ገቢ ያገኛል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አዟሪዎች የሚሰሩት ሥራ የመጻሕፍት ሥራ አሳታሚዎችንና አከፋፋዮችን የሚጠቅም አይደለም የሚሉት በዛብህ፣ ከአሳታሚው ጀምሮ አዟሪው ጋር አስኪደርስ ያለው ትርፍ የ1ብር ከ50 ሳንቲም ነው ይላሉ። አንድ ጋዜጣ ከአሳታሚው 9ብር ከ50 ሳንቲም ካወጣ፣ አከፋፋዩ ጋር 11 ብር ይሄዳል። በመጨረሻ አዟሪው ከ12 ብር እስከ 13 ብር ይሸጠዋል። ይህ ደግሞ ትልቁ ትርፍ 2 ብር እንኳን አይሞላም ማለት ነው። ትርፉ በቂ ስላልሆነ የኅትመት ውጤቶች መዳከም ያሳያሉ ሲል በዛብህ ነግሮናል። ይህንን ተከትሎ አንድ ጋዜጣ አዟሪ 80 ብር ለማትረፍ 200 ጋዜጦች መሸጥ ይኖርበታል።

በዚህ ዘመን 80 ብር ይዞ ቁርስ፣ ምሳ ና እራት በልቶ፣ ቤት ኪራይ መክፈል አይቻልም። ስለዚህ ያለው አማራጭ ማስነበብ ነው። በሚያስነብበት ወቅት ከ200 እስ 300 ብር ማግኘት ይችላል። ይህን ተከትሎ የሚመጣው የአሳታሚዎች መጎዳት ከኢንዱስትሪው እንዲወጡ ያደርጋቸዋል ሲሉ በዛብህ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ አዟሪዎች ከአከፋፋዩ የኅትመት ውጤቶቹን የሚወስዱት በዱቤ ነው። ለምሳሌ የ150 ብር ጋዜጣ ከፍሎ ወስዶ 170 ብር ከማትረፍ ከመርካቶ ካልሲ ይዤ መጥቸ 200 ብር ብሸጥ ይሻለኛል ብሎ ያስባል። ስለዚህ በነጻ ከወሰዱ በኋላ አስነብበው እና ሸጠው የሚያገኙትን ትርፍ ይዘው ዱቤ ይከፍላሉ። ስለዚህ የትርፍ ማነስ አንዱ የኅትመት ውጤቶች ማነቆ መሆኑን በዛብህ ይገልጻሉ። ከዚህ ሁሉ ችግሮች ጀርባ ያለው ትልቁ ማነቆ ትውልዱ ማንበብ አለመውደድ ነው።

አሁን ያለው ትውልድ ከማንበብ ይልቅ መረጃዎችን ከፌስቡክ በቀላሉ ማግኘት ይፈልጋል። ያነባሉ ተብለው የሚገመቱት እድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው ደግሞ ባለው የኢኮኖሚ መዳከም ጋዜጣ ገዝቶ መሄድ አቁመዋል። እነዚህ ችግሮች ጨምሮ በአገሪቱ የተከሰተው የወረቀት ዋጋ መናር የኅትመት ውጤቶች እንዲዳከሙ አድርጓል።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com