ሳንካ የበዛበት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ

Views: 58

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻነት ቀንዲል በመሆን ለአፍሪካ ሕብረት ምስረታ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክታለች። ሕብረቱም ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ዋና መቀመጫው አድርጓታል። የአድዋ ድልን ተከትሎ የጥቁር ህዝብ ኩራት፣ የነጮች አፍ ማስያዣ በመሆን እና ለቅኝ ግዛት አልንበረከክም፣ እጅ አልሰጥም በማለት ነጻነቷን በማወጅ ኢትዮጵያ ለብዙ አመታት የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል ሆና ቆይታለች። ከዚህ ባሻገርም የኢጋድ ዋና መስራች በመሆን፣ እንዲሁም የሱዳን እና የሶማሊያ ፖለቲካ እንዲረጋጋም የላቀ ሚና እንደነበራትም ይታወቃል።

ታዲያ በተለያዩ አገራት ፍትህ እንዲነግስ እና ሰላም እንዲወርድ የጎላ ሚና የነበራት፣ እንዲሁም የዲፕሎማሲ ማዕከል እንደነበረች የሚነገርላት ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የውስጥ ሰላሟ እየተናጋ፣ ከጎረቤት አገራት ጋር የጎሪጥ እየተያየች፣ የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት እና የበዙ ጫናዎች አቅሟን እያዳከሙት እንደሄዱ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ምሁራን አንስተዋል።ለዚህም በዋናነነት የውስጥ ሰላም መደፍረስ እና ደካማ የዲፕሎማሲ ስርአት መከተሏን እንደችግር ሲናገሩም ይደመጣል።

ዲፕሎማሲ ወይንም የኹለትዮሽ ግንኙነት ማለት አገራት በሰላማዊ መንገድ እርስ በእርሳቸው አገራዊ ጉዳዮቻቸውን የሚፈጽሙበት እና ሰጥተው በመቀበል መርህ የየአገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩበት መንገድ እንደሆነ እሙን ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፉት ዘመናት ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን አገራት ጋር የነበራት ዲፕሎማሲያዊ ወይንም የኹለትዮሽ እና የሕዝብ ለሕዝብ (PUBLIC DIPLOMASY) ግንኙነት ታሪካዊ ዳራ እንዴት እንደነበር ለማስታወስ ያክል አዲስ ማለዳ ምሁራንን ጠይቃለች።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ያእቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናትም ሆነ ከጥቂት ጊዜያት አስቀድሞ ከምዕራባውን ጋር የነበራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ትክክለኛውን የዲፕሎማሲ መርህ የተከተለ ነው። ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር የሚበጃትን የኢንቨስትመንት እና ምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊ ፣የቴክንክ ተራድኦ አንዲሁም ሰብአዊ ድጋፎችን ከምዕራባውያን በማግኘት የተጠናከረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደነበራት ለአዲስ ማለዳ አስታውሰዋል።
ጉዳዩ የሰጥቶ መቀበል ስለሆነ እነሱም ቢሆኑ ኢትዮጵያ በተናጥልም ሆነ በጋራ የሚፈልጉትን ሁሉ እንድትደግፋቸው እና እንድትሰራላቸው ይፈልጋሉ።

ለምሳሌ ያክል፣ ባለፉት ሀያ አምስት እና ሀያ ሰባት አመታት ለእነሱ የጸጥታ ስጋት ችግር የሆኑትን በአፍሪካ ቀንድ እና በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ይስተዋሉ የነበሩትን አለመረጋጋት እንድትመክትላቸው ጠይቀዋል። ሰራዊቷን እያሰማራች አሸባሪዎች የተባሉትን በመዋጋት አስተዋጽኦ አበርክታለች።በተለይም ከ9/11 የአሜሪካ የአሸባሪዎች ጥቃት በኋላ ከኢትዮጵያ በጽኑ የሚፈልጉት አሸባሪዎችን እንድትመክትላቸው እንደነበር ያእቆብ አርሳኖ ተናግረዋል።

አሸባሪዎችም ለኢትዮጵያ የማይተኙ መሆኑን በማስመልከት የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ተሰማርቶ ሰራዊቱን ወደ ሶማሊያና ዳርፉርን የመሳሰሉ አፍሪካ አገራት በመላክ አሸባሪዎችን በማጥቃት ተሳትፎ አድርጓል። ከዚህ ባሻገርም በሰሜን እና ደቡብ ሱዳን መካከል ያለውንም ችግር ለማረጋጋት የኢትዮጵያ መንግስት ጉልህ ሚና እንደነበረው በመጥቀስ፣ ለምዕራባውያን የጸጥታ ችግር መፍትሄ በመስጠት የኢትዮጵያን የእስካሁን ዲፕሎማሲዊ አካሄድ አስታውሰዋል። ከለውጡ መንግስት በኋላም ቢሆን ምዕራባውያን ከዚህ ቀደም በለመዱት መንገድ መሄድ ምርጫቸው በመሆኑ፣ በተለይም አሜሪካ ይህንኑ ተግባር ኢትዮጵያ እንድታረጋግጥ እና አጠናክራ እንድትቀጥል ጽኑ ፍላጎት እንዳላትም ተናግረዋል። ይሁን እንጂ አሁን ያለው አስተዳደርም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አንጻር እንጂ አሜሪካ ብቻዋን የምትጠቀምበት እና የምትገለገልበት መንገድ ማመቻቸት እና ማገዝ አይችልም በማለት አገሪቱ የትኩረት ፊቷን ወደራሷ እንድታዞር ካደረገ ሶስት አመታት ተቆጥረዋል ብለዋል።

አሁን እየተፈጠረ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ጭቅጭቅ፣ ንትርክ እና አለመግባባት የተፈጠረውም በዚሁ ምክንያት ነው ይላሉ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ። ህወሓት በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተፈጠሩ ግጭቶች ስር የሰደዱ በመሆናቸው አስካሁን ድረስ ሊቀዘቅዙ አልቻሉም። የህወሓት ኃይል ከተደመሰሰ በኋላ “ተጎድተናል፤ ተበድለናል” የሚሉ የአቤቱታ ድምጾች በዓለም ዙሪያ ተስተጋብተዋል ያሉት ያእቆብ፣ እውነታውን ሳይረዱና ሳያረጋግጡ በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ተመርተው በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰት አለ በሚል ሰበብ አጸፋዊ ምላሽ ይሆን ዘንድ አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ጥላ ጫና አሳድራለች በማለት አሁናዊ ሁኔታውን ያስረዳሉ።

ለዚህ ሳንካ እና ውጥረት ለበዛበት ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያ የሰለጠኑ እና ተጽእኖ ፈጣሪ ዲፕሎማቶችን በማሰማራት የአገሪቷን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ትኩረት ሰጥታ መሰራት እንዳለበትም የመፍትሄ አቅጣጫ ጠቁመዋል። ጠንካራ አቋም፣ ልምድ እና የዲፕሎማሲ ክህሎት ያላቸው ዲፕሎማቶች በግላቸውም ሆነ በአገሪቱ መንግሥት መመሪያ መሰረት መሬት ላይ ያለውን እውነታ እና አሁናዊ የኢትዮጵን ሁኔታ በሚገባ ለዓለም አገራት በማስረዳት ሉዓላዊነትን የማስጠበቅ ግዴታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለገጠሟት ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች ምላሽ ለመስጠት በኹሉም ግንባሮች ንቁና ብቁ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል የሚሉት ደግሞ ሌላኛው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ መምህሩ ደመቀ አጪሶ (ዶ/ር) ናቸው።

ኢትዮጵያ በተለይ በዚህ ወቅት ከውጭ ኃይሎች ግፊያና ጉሸማ ሲበረታባት፣ እየከበደ የመጣውን ተጽዕኖ ለመመከት የዲፕሎማሲ አቅሟን መፈተሽ ይኖርባታልም ብለዋል። ኢትዮጵያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በምዕራባውያን ኃይሎች ከፍተኛ ጫና እየተደረገባት ነው ያሉት ምሁሩ፣ በኹሉም የዲፕሎማሲ ግንባሮች እየተደረገ ያለው ጫና በውስጣዊ አንድነትና ጥንካሬ እንዲረግብ ካልተደረገ፣ በተለያዩ ማዕቀቦች በመሽመድመድ የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተን አደጋ ማጋጠሙ አይቀሬ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን እና ሌሎች አገራት ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በዘላቂ ጥቅም ላይ ካልተመሰረተ የአገራት መሪዎች በተቀያየሩ ቁጥር ወጣ ገባ እያለ ሊቀጥል ይችላል።

ኢጋድ፣ የአፍሪካ ሕብረት እና ሌሎች የዓለም አቀፍ ተቋማትን ከዘላቂ ጥቅም አንጻር መጠቀም ከተቻለ፣ እንዲሁም በአገር ሉዓላዊነት የማይደራደሩ ዲፕሎማቶች በብቃት የሚሰማሩ ከሆነ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ይቃናል የሚል ሀሳብ ምሁሩ ጠቁመዋል።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዝዳንት ማሙሸት አማረ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ልምድ እና እውቀት የሌላቸው በመሆናቸው፣ በተለይም አምባሳደር ተብለው በየ አገራቱ የሚሾሙ ሰዎች የዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ፣ መገናኛ ብዙኃኑ፣ ምዕራባውያን፣ የተባበሩት መንግስታት ተቋማት እና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ምን እንደሚናገሩ እና እንደሚጽፉ በውል መረዳት የሚሳናቸው ናቸው ብለዋል።

አክለውም በዓለም አቀፍ እና ሌሎች ቋንቋዎች ስለ አገራቸው መሞገት የማይችሉ እና ጠንካራ አቋም የሌላቸው የመንግስት ተሿሚ ካድሬዎች ናቸው በማለት የዲፕሎማቶችን ደካማ ጎን አንስተዋል። የዲፕሎማቶች እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አቅም ማነስ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የነበራት ክብር እና ዝና ብሎም ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ያበረከተችውን አስተዋጽኦ እንዲደበዝዝ ምክንያት ሆኗል ይላሉ። ይህም በእውቀት እና ክህሎት ሳይሆን በዘር እና ቋንቋቸው የተመረጡ ዲፕሎማቶች ከመሆናቸው የተነሳ ኢትዮጵያ ያላትን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የቴክኖሎጂ የሥልጣኔ እና የባህል ጉዳዮችን ለሌሎች አገራት ማስተዋወቅ አልቻሉም ሲሉም ተደምጠዋል። ይህም አገራት ፊታቸውን እንዲያዞሩብን አድርጓል፤ ጫናዎች እንዲበዙብንም ዋና ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

በእንደዚህ አይነት ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነም “ኢትዮጵያ ደክማለች፤ አቅም አጥታለች” በማለት ሌሎች አገራት መሰል ድርጊቶቸን እንዲያደርጉ በር ይከፍታል ባይ ናቸው። በተለያዩ ችግሮች ለተተበተበው ዲፕሎማሲ ከሰላማዊ ሰልፍ፣ ከመግለጫ እና ሚዲያ ጋጋታ ይልቅ ወደ ውስጥ መለስ ብሎ የአገር ውስጥ ሠላምን እና አንድነትን ማጠናከር፣ እንዲሁም ብቁ ዲፕሎማቶችን ማሰማራት አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል። የኦሮሞ ጻነት ግንባር (ኦነግ) ምክትል ሊቀመንበር ቀጀላ መርዳሳ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ፤ ቀደምት ነገሥታት የደም ዋጋ ከፍለውባት ያቆሟት የነጻነት ቀንዲል የሆነችው አገር አሁን ላይ በውስጥም ሆነ በውጭ ወራሪ ጥቃት ችግር ላይ ወድቃለች ብለዋል።

ያለፉት ነገስታት የአገሪቷን ሉአላዊነት ሳያስደፍሩ ከተለያዩ ምዕራባውያን ጋር የጦር መሳሪያ ድጋፍን ጨምሮ በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የጠበቀ ግንኙነት እንደነበራቸው አስታውሰዋል። የመኢአዱን ማሙሸትን ሀሳብ በመጋራት ስለ ኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ድክመት የተናገሩት የኦነግ መሪ፣ በተለያዩ አገራት ያሉት የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ብዙዎች የብሔር መነጽር ስላጠለቁ ለአገር ሳሆን ለቡድን እና ለግል ጥቅማቸው፣ እንዲሁም ለብሔራቸው የቆሙ ናቸው በማለት ለዲፕሎማሲው መላላት ችግር ያሉትን እንደምክንያት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከግለሰብ ጥቅም ይልቅ አገራዊ ጉዳይን ማዕከል ያደረገ መሆን አለበትም የሚል ሀሳብ ያነሳሉ። የኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ፣ የምዕራባውያንን አገራት ጨምሮ፣ ከሁሉም አገራት ጋር በትብብር፣ በመረዳዳት መንፈስ እና ሰጥቶ መቀበልን ማዕከል ባደረገ መልኩ ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖራት እንደምትፈልግ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስረድተዋል። የአሜሪካን ማዕቀብ በተመለከተ፣ ለአንድ መቶ ሀያ አመታት በተለያዩ መስኮች በጋራ ለሰራነው ለእኛ አና ለአሜሪካ የማይመጥን ነው።

የአሜሪካን ማዕቀብ ተከትሎ በተለያዩ የሙያ ዘርፍ ያሉ ሰዎች ለማዕቀቡ መነሻ ምክንያት ከሚሉት ውስጥ ስለ ኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ በሚገባ አለማሳወቅ እና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ አለመሰራቱ እንደሆነ አምባሳደሩ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። በሺህ ዘጠኝ መቶ ስልሳ የኮሪያ ዘመቻ ላይ ከዘመቱት አገራት መካከል ኢትዮጵያ በቀደምትነት ትጠቀሳለች ያሉት አምባሳደር ዲና፣ ከአፍሪካም ብቸኛዋ አገር ናት በማለት ስለቀደመው ዲፕሎማሲ አንስተዋል። ከዚያም ወዲህ ከአሜሪካ ጋር በጸረ ሽብር እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ በትብብር ስትሰራ መቆየቷን ገልፀው፣ ይህ ጠንካራ ግንኙነት በጥቃቅን ጉዳዮች ምክንያት እንዲከሽፍ አንፈቅድም በማለት የኢትዮጵያን አቋም ገልጸዋል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በምዕራባውያን በተለይም በአሜሪካ እየተነሱ ያሉት ጉዳዮች በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል የሕግ ማስከበር ሂደትን ተከትሎ የሰብአዊ እርዳታ ለማድረግ በር ይከፈትልን የሚል እንደሆነ አንስተዋል። ይህ ደግሞ የምዕራቡም ዓለም ሆነ የአሜሪካ ጉዳይ ሳይሆን የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እና በራሷ የምትፈጽመው ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።

የሰብአዊ መብት ጥሰትንም ሆነ ተራድኦን በተመለከተ ኃላፊነቱን የኢትዮጵያ መንግስት ብቻውን እንደሚወጣ ተናግረዋል። የዲፕሎማሲ ክሽፈት እና የዲፕሎማቶች የብቃት ማነስ ነው ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ችግር የሆነው የሚሉ የበዙ ድምጾች በየጊዜው እንደሚሰሙ የተናገሩት አምባሳደሩ ይህንንም በሁለት ጉዳዮች ከፍለው አብራርተዋል። እንደ ምሳሌም ያነሱት ለአገር ያገባኛል ይመለከተኛል በሚል የመቆርቆር መንፈስ ወቅታዊውን ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት ለአገር ጠበቃ የቆሙ እንዳሉ፣ እንዲሁም የሕግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ የተፈጠሩ ክፍተቶችን በማንሳት የሚተቹ እንዳሉ አንስተዋል። እንደማንኛውም ተቋማት ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ፍጹም ነው ማለት እንደማይቻል ገልጸው፤ ያሉትንም ክፍተቶች ለመሸፈን ብቃት ያላቸውን ዲፕሎማቶችን በማሰማራት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ሰሞኑን ደግሞ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ኢትዮጵያ ከአገራት ጋር የምታደርገው የዲፕሎማሲ ግንኙነት የትኛውም ጽንፍ ላይ የወደቀ አይደለም ብለዋል። ኢትዮጵያ ከማንኛውም አገራት ጋር የምታደርገው ግንኙነት መለኪያው እንደሰማይ ሩቅ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፣ አንዳንድ አገራት ቀድሞ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ይደረግባቸው እንደነበረው ጫና አሁን ስለማይደረግባቸው ኢትዮጵያ ወዳጅነቷን ከየትኛውም የአለም አገራት ጋር በነጻነት እንደምታደርግ ጠቅሰዋል። የወዳጅ አገራት ምርጫ የለንም ያሉት አምባሳደር ዲና፣ ግንኙነቱ የጋራ እንደመሆኑ መጠን በኹለቱም አገራት ያለው ግንኙነት አብሮ የመጠናከር እና አብሮ የመሥራት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ካልተገደደች በቀር የምርጫ መስፈርት እንደሌላት እና ከኹለም አገራት ጋር ግንኙነቷን የማጠናከሩን ሥራ እየገፋችበት እንደምትገኝም ገልጸዋል።

በሳምንቱ የአስር አገራት አምባሰደሮች የሹመት ደብዳቤ ያቀረቡ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴም በየአገራቱ ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በኢትዮጵያ በኩል ፍላጎት መኖሩን እና ወቅታዊውን የአገሪቱን ሁኔታ እንዳስረዷቸው አመልክተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም ከሞሮኮ አቻቸው በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን አንስተዋል። የኹለቱን አገሮች ግንኙነት ለማጠናከር ብሎም ከዚህ በፊት የተደረጉ የኹለትዮሽ ሥምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑም መነጋገራቸውን አምባሳደሩ ገልጸዋል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ከተለያዩ አገራት ጋር የኹለትዮሽ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት ተግባራት መከናወናቸውንም አምባሳደሩ አክለው አስረድተዋል። በተለያዩ አካላት ሥለ ዲፕሎማሲው የተነሱት ችግሮች ምን ያስከትሉ ይሆን የሚለውና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስቀመጠው የመፍትሄ አቅጣጫ ምን ውጤት ያመጣ ይሆን የሚለው ጥያቄ ጊዜ የሚፈታው ጉዳይ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com