ትንኮሳ የተቀላቀለበት ቅስቀሳ

Views: 34

6ተኛው አገራዊ ምርጫ የጊዜ ሠሌዳ ከወጣለት ወቅት አንስቶ እስካሁን ድረስ ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል። ምርጫውን ከሚያካሂደው ምርጫ ቦርድ ላይ ከሚሰነዘረው ይልቅ ፓርቲዎች እርስ በርሳቸው የሚካሰሱት ትልቁን ቦታ ይይዛል። ምርጫው ጋር በተገናኘ ከሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አብዛኞቹ በመንግስት ወይ በገዢው ፓርቲ አባላት ትናንሽ ፓርቲዎች ላይ እንደሚፈጸሙ ይነገራል። የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብት ኮሚሽን ባዘጋጀው መድረክ ላይ በርካቶች የደረሰባቸውን ተጽዕኖ አሰምተዋል። እነሱ የተናገሩትን ተከትሎ የአዲስ ማለዳው ቢኒያም አሊ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አነጋግሮ ስለወቀሳዎቹ ተጽእኖ የሚከተለውን አሰናድቷል።

በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ በገዢ ፓርቲ ተጽእኖ ስር ያልወደቀ ምርጫ የለም። ከኃይለሥላሴ የእንደራሴዎች ሹመት ጀምሮ በደርግ ዘመን የነበረው የሸንጎ አባላት ምርጫ በሕዝብ ሳይሆን ሥልጣን ላይ ባለው አካል ይከናወን እንደነበር ግልጽ ነው። ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በተካሄዱት ምርጫዎች ሕዝብ ምረጥ ተብሎ አማራጮች ቢቀርቡለትም፣ ተቃዋሚዎች ላይ ጫና በመፍጠር ወይም ሕብረተሰቡ ፈርቶም ይሁን ለአገር ሠግቶ እነሱ የፈለጉትን እንዲመርጥ የተደረገባቸው አሊያም የተጭበረበሩ እንደነበሩ ይታመናል። የ1997ቱ ምርጫ በዓይነቱና በሕዝብ ተሳትፎ የተለየ ቢሆንም ጉልበት ያለው መንግስት ስልጣኑን ሕዝብ ለፈለገው ፓርቲ በፍላጎት እንደማይሰጥ በግልጽ የታየበት ነበር። ያንን እንደማስረጃ አድርጎ በ2002 እና በ2007 የተካሄዱት ምርጫዎች ላይ ሕዝቡ ተሳትፎ እንዲያደርግ ቢጋበዝም፣ “ላይሆን ነገር ሕዝብ እንዲልቅ ምክንያት አንሁን” በሚል እሳቤ ብዙዎች ሳይሳተፉ ቀርተዋል። የገዢው ፓርቲ ተጽእኖና የተቃዋሚዎች ቸልተኝነት ሕዝቡ በምርጫ ተስፋ እንዲቆርጥ በማድረጉ ምርጫውን “መቶ በመቶ አሸነፍን” አስብሎም የዓለም መሳለቂያ አድርጎን ነበር።

የዘንድሮው 6ተኛው አገራዊ ምርጫ በኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት በተያዘለት ጊዜ አይደረግም ከመባሉ አንስቶ ብዙ ትችቶች ተሰንዝረውበታል። በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓት እንደሌላ አገር የራሴን ምርጫ አደርጋለሁ ብሎ ሲገዳደር በሃሳቡ ቢወቀስበትም ከማካሄድ አልተቆጠበም ነበር። ድርጊቱ ከማዕከላዊው መንግስት ከማላተም ውጭ ያመጣለት ፋይዳም አልነበረም። አንድ አመት ተጨማሪ የዝግጅት ጊዜን ያገኘው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም፣ ይጠበቅበት የነበሩ ሥራዎችን እንዳላከናወነ የሚናገሩ አሉ። የሕዝብ ቁጥራችን በከፍተኛ መጠን ጨምሮ፣ የከተማ ፍልሰትም በተጋነነ ፍጥነት በብዙ እጥፍ ጨምሯል በሚባልበት በዚህ ጊዜ ምርጫው ከ14 ዓመት በፊት በተወሰደ መረጃ መሰረት ይደረጋል መባሉ ከተለያዩ ፓርቲዎች ትችት አሰንዝሮበት ነበር። የሕዝብ ቆጠራን ማካሄድ ካለመቻሉ ባሻገር ወቅታዊ የምርጫ ቀጠናም ማዘጋጀት ሳይቻል በመቅረቱ በፊት በተዘጋጀው መሰረት እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወቃል።

ከ2 ሳምንት በኋላ እንዲካሄድ በድጋሚ የተራዘመው ምርጫ እስኪደርስ በሂደቱ ስለተፈጠሩ ክስተቶች የተለያዩ ፓርቲዎች ቅሬታዎቻቸውን ለምርጫ ቦርድ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ምርጫ ከዋናው በተለየ ቀን መደረጉ ተገቢ አይደለም ብለው በርካታ ፓርቲዎች ቅሬታ አስገብተው የነበረ ሲሆን፣ ቦርዱም ጥያቄያቸውን ተቀብሎ ቀኑን አንድ ላይ አድርጎ የቀድሞ ውሳኔውን በቅርቡ ቀይሯል። ፓርቲዎች ይህ መደረጉ ያስደሰታቸው ቢሆንም ብዙ ተቀባይነት ያላገኙ ጥያቄዎችና ሥጋቶች አሁንም እንዳሉባቸው ይናገራሉ።

ከገዢው ፓርቲ ውጭ ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከሚያነሷቸው ቅሬታዎች ዋና ዋናዎቹ፣ በመንግስት ጫና እየተደረገብን ነው፤የአባላቶቻችንና ደጋፊዎቻችን ሠብአዊ መብት እየተጠበቀ አይደለም፤ እንዲሁም ዕድሎች በፍትሐዊነት አልተሰጡም የሚሉ ገዢው ፓርቲ ላይ ያነጣጠሩ ቅሬታዎች ናቸው። ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ በበኩሉ የሥም ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶብኛል ከማለት ውጭ ሁሉንም በጅምላ ወይ በተናጥል ያብጠለጥላል እንጂ ስሞታ ይዞ ለምርጫ ቦርድ ወይም ለሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ሲያቀርብ ተሰምቶ አያውቅም።

ልዩነቱ የራሱ ምክንያት እንዳለው ቢታመንም፣ ከምርጫው በፊት ያለው ሂደት ካልተሻሻለ አጠቃላይ ምርጫው ፍትሐዊ ነው ለማለት እንደሚያስቸግር የሚናገሩ አሉ። አንዳንዶቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድም ሆነ በገዢው ፓርቲ አካሄድ ላይ ቅሬታ ቢኖራቸውም፣ አጠቃላይ የምርጫውን ሂደት ላለማስተጓጎልና ሕዝቡ ይበልጥብናል እያሉ ችለው እያለፉ መሆናቸውን ይናገራሉ። ሲጀመር ተመዝግበው ከነበሩ ከ100 በላይ ፓርቲዎች አሁን 47 ቢቀሩም ጥቂት ቀናት ቀርተውም ቢሆን የተወሰኑት ቅሬታቸውን ከማቅረብ አልቦዘኑም።

የፓርቲዎቹን ቅሬታ እየተቀበለ ከሚያስተናግደውና ውሳኔ ከሚሰጠው ምርጫ ቦርድ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን(ኢሠመኮ) ቅሬታቸውን በደብዳቤም ሆነ በቃል የሚያቀርቡ በርካቶች ናቸው። በኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ(ዶ/ር) ለሚመራው ለዚህ ተቋም፣ በሕዝባችን ወይም በፓርቲያችን ላይ ግፍ ተፈፀመ፤ እንዲሁም በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈፀሙ ነው የሚሉ ቅሬታዎች አሁንም ይገቡለታል። ኮሚሽኑ የቀረበለትን ቅሬታም ሆነ ጥቆማ መሠረት አድርጎ በተለያዩ አካባቢዎች እየተገኘ በማጣራት እርምጃ እንዲወሰድ የሚያስችል መረጃ በሪፖርት መልክ ቢያወጣም አንዳንዶች በቂ አይደለም ይላሉ። በፊት ከነበረው አኳያ አሁን ያለውን አመራሩንም ሆነ ስራውን በርካቶች ቢያደንቁም፣ በፅሁፍ ከማሳወቅ ያለፈ እርምጃ የማስወሰድ አቅምና ሥልጣን የለውም እያሉ የሚተቹትም አሉ።

ኮሚሽኑ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አድርጎ ነበር። የፖለቲካ ፓርቲዎች በአጀንዳዎቻቸው እንዲያካትቷቸውና ቃል እንዲገቡ የሚጠበቅባቸውን 6 ነጥቦች ለማስተዋወቅ፣ እንዲሁም እርስበርስ ለማወያየት ነበር ጉባዔው የተሰናዳው። በዚህ ፕሮገራም ላይ የተገኙት ሁሉም ማለት ይቻላል “ትንንሽ” የሚባሉና በአብዛኛው ሕብረተሰብ የማይታወቁ ክልላዊ ፓርቲዎች ናቸው። በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚወዳደሩ ጥቂት ፓርቲዎች በስተቀር በአንፃራዊነት ከፍተኛ ስምና ዝና ያላቸው ብዙ እጩዎችን ያስመዘገቡ ፓርቲዎች አልተገኙም። በውይይቱ የተገኙ፣ “እኛ ምስኪኖች ብቻችንን ተገኝተን ዓላማው ውጤታማ ይሆናል ወይ?” ብለው እስኪጠይቁ ድረስ የግዙፎቹ አለመገኘት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። በተለይ በአብዛኞቹ ክርክሮች አለመገኘትን በማብዛቱ የሚታወቀው ብልጽግና በዚህኛው ውይይትም አለመሳተፉ ለሚቀርቡበት ስሞታዎች ምላሽ እንዳይሰጥ አድርጎታል። ከሕግ አንጻር ክስ የቀረበበት ወገን ምላሽ ሣይሰጥ ዕድሉን ካሳለፈ አምኖ እንደተቀበለ ይቆጠራል። ብልጽግና ፓርቲም የሚቀርቡበትን ክሶችም ሆነ ስሞታዎች በየወቅቱ እየተገኘ ማስተባበልም ሆነ ማክሸፍ ካልቻለ የተባለው እውነት እንደሆነ ሕዝቡ ሳያጣራ ማመኑ አይቀሬ ነው።

በዕለቱ የነበረውን መድረክ የመሩት ኮሚሽነር ዳንኤል፣ “በጣም መጠነ ሠፊ የሠብዓዊ መብት ስጋት ውስጥ እንገኛለን” በማለት ጉባኤውን ጀምረው የተሳታፊዎቹን አስተያየት ሰምተዋል። ጊዜ እስኪያጥር ድረስ ተጋባዦቹ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ወክለነዋል ስላሉት ሕዝብም ይሁን ስለአባላቶቻቸው በርካታ ቅሬታዎችን አቅርበዋል። የተወሰኑት ከዚህ በፊት በተለያየ መንገድ የተሰሙ ቢሆኑም አንዳንዶቹ የመሰማት እድል ያላገኙ ነበሩ።

ለተሳታፊዎች ከተሰጡት እድሎች የመጀመሪያውን ያገኙት የወለኔ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት ፈይሰል አብዱልአዚዝ ናቸው። “ኮሚሽኑ ጥርስ የሌለው አንበሳ ነው” በማለት አስተያየታቸውን የጀመሩ ሲሆን፣ አብዛኛው ሕግ የሚጣሰው በተቃዋሚዎች ሳይሆን በራሱ በመንግሥት ቢሆንም እኛ አቅምና ሚዲያ ስለሌለን ድምጻችንን ማሰማት አልቻልንም ብለዋል። ያሉት ሚዲያዎች ለተወሰነ ወገን የሚያገለግሉ ናቸው ያሉት ሊቀመንበሩ፣ ባለው ሁኔታ ምክንያት ባንዳንድ ቦታዎች ነገሮችን ለማቋረጥ እንደተገደዱ ተናግረዋል። የብልጽግና ተወካዮች በውይይቱ ላይ ተገኝተው ባይሰሙም ሕዝቡ ላይ የሚፈጸምን ማስፈራራት ማስቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ሕብረት ሊቀመንበር የሆኑት ገብሬ በርሔ በበኩላቸው፣ የሠብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ከአገር ውስጥ ተቋማት ከምንሰማው ይልቅ በአብዛኛው ከውጮቹ ነው የምንሰማው ብለዋል። ለዚህ አስተያየታቸው በኋላ ላይ ምላሽ የሰጡት ኮሚሽነሩ፣ “እኛ እንደሚዲያዎች የእሽቅድምድም ሥራ አንሰራም” በማለት የተቋማቸውን ተልዕኮ አስረድተዋል። በሌላ በኩል የክልል መንግሥታት አወቃቀርን በተመለከተ ገደብ ያለው ሥልጣን የላቸውም፤ ልዩ ኃይል የሚባልም በሕግ አይታወቅም በማለት ሊቀመንበሩ መፍትሄ ያሉትንም አሰምተዋል። “የተመጣጠነ ኃይል ያላቸው ክልሎች መሆን አለባቸው” በማለት የሚይዙት ትጥቅ በሕግ መወሰን እንዳለበት አስገንዝበዋል። ከምርጫው መቃረብ አኳያ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች መንስዔዎቻቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሳይሆኑ ሶሻል ሚዲያው ጋር ነው ያሉ ሲሆን፣ ችግሩን ለመቅረፍ ገለልተኛ የሆኑ የሚዲያ ተቋማት ማቋቋም ያስፈልጋል ብለዋል።

የአርጎባ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካይ መሐመድ ሙሳ ስደተኞችን በተመለከተ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ ተፈናቃዮች በየቦታው ተበትነው ባሉበት በዚህ ወቅት ምርጫውን ለማከናወን መታሰቡን በመጥቀስ ለወደፊት ምን ለማድረግ እንደታሰበ ጠይቀዋል። ከመንግሥትም ሆነ ከገለልተኛ ተቋማት ብቻ ሳይሆን ከእኛ ከፓርቲዎችስ ምን ይጠበቃል ብለዋል። በሕዝባቸው ላይ አደገኛ ቅስቀሳ ሲደረግ እንደነበር የተናገሩት እኚህ ተወካይ፣ ምን እንደሆነ ዘርዝረው ባያሳውቁም ተግባሩ እንዲቆምላቸው ጠይቀዋል። ኢሠመኮን በተመለከተ፣ ወንጀል ሲፈጸም ፈጻሚዎቹን “ከተግባራቸው ይቆጠቡ” ከማለት ባሻገር ለውጥ የሚያመጣ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይገባዋል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት ባንድራ በላቸው፣ “ብሔርን ከብሔር የሚያጋጩ ግልጽ ቅስቀሳዎች እየተደረጉ ይገኛሉ” በማለት በአካባቢያቸው ያሉ የገዢው ፓርቲ ተወካዮችን ወንጅለዋል። ጦርና ጋሻ ይዘው “ና ውጣ” እያሉ የእኛ ሕዝብ ላይ ድንጋይ እስከማስወርወር ሲደርሱ የጸጥታ ኃይሎች ዝም ብለው ማየታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እጃችን ላይ አለ ብለዋል። ፓርቲያችን ተሰርዟል እያሉ የብልጽግና ሰዎች ይቀሰቅሱብናል። የምርጫ ወረቀቱ ላይ ያለውን የእኛን ምልክት አውጥተው ሌላ የሌለንበትን የውሸት አሳትመው በማዘዋወር፣ የእኛ ፓርቲ እንደሌለ አድርገው ሕዝቡን ለማሳመን እየሞከሩ ነው የሚል ወቀሳቸውን አቅርበዋል።

የደቡብ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀመንበር አለሳ መንገሻ መድረኩ የተዘጋጀበት ዓላማ ላይ በማተኮር ያስተዋሏቸውን ችግሮችንም ጠቅሰዋል። ከፓርቲዎች በኩል የታየ ያሉት ችግር ግጭት ቀስቃሽ ንግግሮችን በተመለከተ ነው። ከመንግሥት በኩል ሕግን አለማክበር በዋናነት የታየ ችግር እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን፣ ገለልተኛነትን በተመለከተ የጸጥታ ኃይላት አወቃቀር እንዲታሰብበት ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።

የአገው ብሔረሰብ ሸንጎ ሊቀመንበር በበኩላቸው ስለቅማንት ሕዝብ አንስተዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ እንደሌላው ሕዝብ እየታየ አይደለም ያሉት ሊቀመንበሩ፣ ሕዝብ ሲጨፈጨፍ ኮሚሽኑ በድፍረት ሲቃወም አናየውም ቢሉም ኮሚሽነሩ በስተመጨረሻ በሰጡት አስተያየት፣ “እኛ የምንፈራው የለም፣ ከፍርሀት ርቀን ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው” ብለዋል። እንወክለዋለን ስላሉት የዋግኽምራ ሕዝብም ሲናገሩ፣ ከህወሓት ጋር ባለ ግጭት ሳቢያ አካባቢው ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ ነው ብለዋል። ከእሳቸው ቆይቶ በኋላ ላይ እድል ተሰጥቶ የተናገሩ የማሕበረሰቡ አባልና የፓርቲው ተወካይ፣ በአካባቢያቸው የኤርትራ ጦር እንዳለ ተናግረዋል። “እኛ አካባቢ ምርጫ አለ መባሉ ያስቀኛል” ያሉ ሲሆን፣ “ሽፍታዎችን መንግሥት እያደራጀ ነው” በማለት ፋኖ በመባል የሚታወቁ የሕዝብ ታጣቂዎች ላይ ያላቸውን ቅሬታ አቅርበዋል።

የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባርን ወክለው የተገኙት አህመድ መሐመድ በበኩላቸው፣ በሱማሌ ክልል በመንግሥት አካላት የሚፈጸምን ኢ-ፍትሐዊ ተግባር ኮንነዋል። “እውነት ብንናገር እንቃጠላለን፣ ከዚህ ወጥቼ ቃሊቲ ላለመውረዴ ምንም ዋስትና የለኝም” ያሉት እኚህ አመራር፣ ክልላችን ውስጥ ዕጩ ማስመዝገብ ስላልቻልን ከ160 በላይ የሚሆኑትን አዲስ አበባ መጥተን ነው ያስመዘገብነው ብለዋል። አሁን ያለው የክልሉ አመራር ከበፊቱ ይለያል ብዬ አላምንም ያሉት አህመድ፣ ሠው ሲታፈን መፈንዳቱ እንደማይቀር አሳስበዋል። እንደአመራሩ ንግግር “የምርጫው ውጤት አልተነገረም ግን ታውቋል፤ አሁን የሚካሄደውን ምርጫ Election ሳይሆን ሰሌክሽን(selection) ነው ማለት ይቀላል።” ከሠብዓዊ መብት ጋር በተገናኘ ስልጠና ለጉልበተኛው መሆን እንደነበረበትና የምርጫ አካሄዱ ካልተቀየረ ይጠቅማል ብለው እንደማያስቡም አሳውቀዋል። ኮሚሽኑንም በጽሁፍ እንጂ በድርጊት ላይ የላችሁበትም ያሉት እኚህ የኦብነግ አመራር፣ ስልጣን ላይ ያሉትን ለመውቀስ ድፍረት አላችሁ ወይ? ብለው ጠይቀዋል።

ከወላይታ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር የመጡት ሻምበል ኤርሚያስ ገዢው ፓርቲ መቀስቀስ ሳይሆን ማስፈራራት ነው የያዘው ብለዋል። በተለይ በገጠራማው አካባቢ፣ “ማዳበሪያ አታገኙም፣ እኛን ካልመረጣችሁ እንዲህ ትሆናላችሁ” እያሉ ሕዝቡን በማስፈራራት ላይ ናቸው ሲሉ የመንግስት አመራሮችን ወቅሰዋል።

ከትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የመጡት ተሻለ ንጉሴ በበኩላቸው በትግራይ እየተፈጸመ ያለው የሠብዓዊ መብት ጥሰት የትም ከተፈጸመ ጋር አይወዳደርም በማለት የሁሉም ጣሪያ ነው ብለዋል። አሁን ካለው ትልቅ ችግር አኳያ አሁን ያለው ትንሽ መንግስት ነው ያሉት እኚህ አመራር፣ “ትግራይ በማይሳተፍበት መንግስት ሊገዛ ነው” ማለታቸው ተሰምቷል። የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ተወካይ በበኩላቸው ሕዝባቸው በጅቡቲ፣ በሱማሊያና በሱማሌ ልዩ ኃይሎች ዙሪያውን እየተጠቃ እንደሆነና ሠሞኑን 6 ሠዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካይ፣ የድሮው አባዜ ያለቀቃቸው የመንግሥት አመራሮች አሁንም እያስፈራሩን ነው ብለዋል። “ህወሓት 30 ዓመት ያላደረገብን አሁን በወራት ተፈፅሞብናል” በማለት አነጻጽረውታል። እንደማይካድራ በቢሶበር ጭፍጨፋ ተፈፅሟል ያሉ ሲሆን፣ ግፉ የተፈጸመበትን መንገድም አብራርተዋል። ጁንታው የሕዝቡን አለባበስ እየለበሰ በመንግስት አካላት ላይ እርምጃ ወስዶ ሲሸሽ መከላከያና ልዩ ኃይሉ ሕዝቡ ላይ የአጸፋ እርምጃ እየወሰዱ በሁለቱም በኩል ተጎድተናል ብለዋል።

ከዶባ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የመጡ ተወካይም ሕዝባቸው ሳይፈልግ በከንባታ ዞን ስር በመደረጉ መበደሉን አስረድተዋል። ጥያቄ በማንሳታችን “ነፍሰጡር በአስተዳዳሪ መኪና ተገጭታ ተገድላለች” ያሉት እኚህ ተወካይ፣ የሚያጣላን ሕገመንግስቱ ነው ብለዋል።
ከእነዚህ በተጨማሪ ሌሎች ተወካዮች የምርጫ ካርድን የተመለከቱ ቅሬታዎችን ያቀረቡ ሲሆን፣ አንድ ግለሰብ ከ50 በላይ ካርድ በወሰደበት ሁኔታ ምርጫው እንዴት ፍትሃዊ ይሆናል? ተብሏል። “ምርጫ ቀርቶ ማዛመድ ይሆናል” ያሉ አንድ ተሳታፊ፣ የበታች አመራሩ ችግር እየፈጠረብን ነው ብለዋል። በቤኒሻንጉል የሚንቀሳቀሰው ቦሮ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ፣ የሲዳማ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ፣ የዶንጋ ሕዝብ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ እንዲሁም ሌሎች ቅሬታቸውን ለኮሚሽኑ አቅርበዋል።

ኮሚሽነሩ በመዝጊያ ንግግራቸው የሁሉንም ቅሬታ እንደሚቀበሉ የተናገሩ ሲሆን፣ የተጠቀሱት ብቻ ሳይሆኑ በርካታ የሠብዓዊ መብት ቀውስ በሁሉም ክልል ማለት በሚቻል መልኩ መኖሩን ተናግረዋል። አንዳንድ ኃላፊዎች ግኝቶቻችንን አንቀበልም ይላሉ ያሉት ዳንኤል፣ ባለን ውስን አቅም ጥረት እያደረግን ስለሆነ ወደፊት እንደሚስተካከል እምነት አለን ብለዋል። የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የማጣራት ሥራ በኮሚሽኑ መሠራት ቢኖርበትም፣ ካለው በርካታ ቅሬታ አኳያ ብቻውን መሥራት ስለማይችል ፓርቲዎችም መረጃዎችን በማሰባሰብና በመጠቆም ሊረዱ እንደሚገባ ተነግሯል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ እርስ በርሳቸው የሚያደርጉት ወቀሳ ምርጫው ላይ ስለሚኖረው ተጽዕኖ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑትን ካሳሁን ብርሃኑን (ፕሮፌሰር) አነጋግረን ነበር። እነደአሳቸው አሰተያየት ፓርቲዎች እርስበርስ መወቅቀሳቸው ምርጫው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አይኖረውም። በውሸት ላይ የተመረኮዘ የሥም ማጥፋት ዘመቻ እስካልሆነ ድረስ ስሞታቸውን ለሚመለከታቸው አካላትም ሆነ ለሕዝብ በቀጥታ ማቅረባቸው ችግር የለውም። ይህን ሲያደርጉ ሕዝቡ ትክክለኛውን ለማወቅና የሚፈልገውን ለመምረጥ ያግዘዋል።

የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን በተመለከተ ምርጫው ነጻና ፍትሐዊ እንዳይሆን ከሚያደርጉ ማናቸውም ድርጊቶች ሁሉም መቆጠብ እንዳለባቸው አሳስበዋል። በፓርቲዎች የሚነገረው ቅሬታ በምርጫው ሂደትም ሆነ ውጤት ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ስለመኖሩ በጊዜ ሂደት የሚታይ ስለሆነ በትዕግስት መጠበቁ ይሻላል ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com