ምርጫ ቦርድ እነ እስክንድር ነጋን በዕጩነት ሊመዘግብ ነው

Views: 31

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በወሰነው መሰረት እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ መሪዎች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ በመጭው ምርጫ በዕጩ ተወዳዳሪነት እንዲቀርቡ ለማድረግ ሥራዎችን መጀመሩን አስታውቋል። የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ግንቦት 26/2013 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የምርጫ ጉዳዮች ችሎት ቀርበው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሰብሳቢዋ ቦርዱ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንደሚፈፅምም አረጋግጠዋል ተብሏል፡፡ የዕጩዎቹን ስም ዝርዝር እና በእነ ማን እንደሚተኩ ለቦርዱ ያቀረበው ባልደራስ ለእነ እስክንድር ነጋ የዕጩነት ማረጋገጫ ሰነድ እንዲሰጠው መጠየቁን የፓርቲው የሕግና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ኃላፊ ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ ተናግረዋል። ምርጫ ቦርድ ቀሪ ሥራዎችን አጠናቆ ሰነዱን ግንቦት 30/2013 በፍርድ ቤቱ ፊት እንዲያቀርብም ቀጠሮ ተይዟል።
እንደ ቦርዱ ማብራሪያ ዕጩዎቹን ለማተካካት በተደረገው እንቅስቃሴ ታትሞ የነበረ አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ወረቀት ተወግዷል። በዚህም ቦርዱ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ለተጨማሪ ወጭ ተደርጓል። ምርጫ ቦርድ በእስር ላይ የሚገኙትን የባልደራስ አመራሮችን በእጩነት እንዲመዘግብ በፍርድ ቤት ውሳኔ ቢሰጥም፣ መመዝገብ አልችልም ማለቱ የሚታወስ ነው፡፡


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com