በደቡብ ክልል የምርጫ ሂደቱን የሚያስተጓጉል ወንጀል የፈጸሙ 21 ግለሰቦች ተቀጡ

Views: 43

በደቡብ ክልል የምርጫ ሂደቱን የሚያስተጓጉል ወንጀል ፈጽመው የተገኙ 21 ሰዎች በእስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። ምልክትና ፖስተር በመቅደድ እንዲሁም ሌሎች የምርጫ ሂደቱን የሚያስተጓጉሉ ወንጀሎችን በመፈፀም የተጠረጠሩ 110 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም የክልሉ ፖሊስ ገልጿል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የታክቲክ ምርመራ ዳይሬክተር ኮማንደር አዲሴ አወኖ ለኢዜአ እንደገለፁት፣ 6ኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እስከ ወረዳ ባሉ የፖሊስ መዋቅሮች የምርጫ ሂደቱ እንዳይስተጓጎል የወንጀል ድርጊቶችን የሚመለከት ልዩ የምርመራ ቡድን ተዋቅሯል።

“ፖሊስ በደረሰው ጥቆማና ባደረገው ክትትል የፓርቲዎችን የምርጫ ምልክቶች እንዲሁም ፖስተርና ባነሮችን የመቅደድ፣ የምርጫ ቅስቀሳዎችን የማወክ፣ የምርጫ ቁሳቁሶች የመስረቅና ሌሎች የምርጫ ሂደቱን የሚያስተጓጉሉ ወንጀሎች መፈፀማቸውን አረጋግጧል” ብለዋል።

የተፈፀሙ ወንጀሎችን በተመለከተ የክስ መዝገቦች መደራጀታቸውንና በተጠርጣሪዎች ላይ ማስረጃ መሰብሰቡን የጠቀሱት ኮማንደር አዲሴ፣ ባአጠቃላይ 137 ከሚሆኑ ተጠርጣሪዎች ውስጥ 110ሩ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርጎ ለሕግ እንዲቀርቡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። እስካሁን 12 መዝገቦች ለፍርድ ቤት ቀርበው ውሳኔ እንዲያገኙ መደረጉን ጠቁመው በተከሰሱበት ምርጫ የማስተጓጎል ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ 21 ግለሰቦች ከኹለት ወር እስከ አንድ አመት ተኩል በሚደርስ እስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን አስታውቀዋል።
ወላይታ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ጋሞ፣ ሀዲያ፣ ስልጤ፣ ዳውሮና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም ባስኬቶና አማሮ ልዩ ወረዳዎች ደግሞ ወንጀሎቹ የተፈጸመባቸው አካባቢዎች መሆናቸው ተገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com