የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሰብዓዊ መብቶች

Views: 40

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የመጨረሻ ዝግጅት ላይ ትገኛለች። በዚህም የምርጫ መሪ ተዋንያን የሚባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ውድድር ውስጥ የሚያቀርቧቸው ሀሳቦችና የፖሊሲ አጀንዳዎች የመራጩ ዋና መመዘኛ ተደርገው ይወሰዳሉ። ታዲያ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተሳታፊ የሆኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ዘርፍ አሉን ያሏቸውን አማራጭ ሀሳቦች እያቀረቡ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ነው ማለት አይቻልም።

ምርጫ ሲባል በመራጩ ሕዝብ አእምሮ ውስጥ በቀዳሚነት ሊከሰት የሚገባው ነገር ማንኛው ፓርቲ ለአገሪቱ የተሻለ ፖሊሲና አሠራር ይዞ ቀርቧል የሚለውን በምክንያታዊነት መመዘንና መወሰን እንደሆነ ይመከራል። ፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣወን የሰብዓዊ መብቶች አለመከበር እንደ ችግር ወስደው በቁርጠኝነት የሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር ጠንካራ ሀሳብና ፖሊሲ ይዘው እንድቀርቡ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሀሳብ መቅረቡ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የካቲት 16/2013 ለምርጫ 2013 ባለ ስድስት ነጥብ የሰብዓዊ መብቶች አጀንዳ ማስተዋወቁ ይታወሳል። ኮሚሽኑ ባቀረባቸው ባለ ስድስት ነጥብ የሰብዓዊ መብቶች አጀንዳውን በምርጫው የሚሳተፉ አካላት እንዲተገብሩና እንዲፈጽሙ ጥሪ ባቀረበው መሰረት ባለፉት ሦስት ወራት ከተለያዩ ባለድርሻዎች ጋር በመተባበር በርካታ ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱን ባሳለፍነው ግንቦት 22/2013 ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ በተወያየበት ወቅት ገልጿል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ፣ ቦርዱ ባለ ስድስት ነጥብ አጀንዳውን እንደሚደግፍና ቦርዱም አጀንዳውን ለመተግበር የበኩሉን ሚና የሚጫወት መሆኑን ገልጸዋል።“ለምሳሌ፣ ምርጫ ቦርዱ የሚመዘግባቸው ፓርቲዎች በሠላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች መሆናቸው፣ ፓርቲዎች የፈረሙት የመግባቢያ ሰነድ እንዲሁም ፓርቲዎች የሴቶችን እና የሌሎች ልዩ ትኩረት የሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ባገናዘበ መልኩ እንዲሆን በሕግና መመሪያ ማስቀመጡ፣ ኮሚሽኑ ለይቶ ካስቀመጣቸው 6 የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ ነጥቦች የሚስማማ እና ቦርዱም የሚያምንበት ነው” ብለዋል።

ኢሰማኮ፣ በምርጫ 2013 የፖለቲካ ፓርቲዎች ትኩረት አድረገው እንድሰሩባቸው ያሳሰባቸው ሰብዓዊ መብት አጀንዳዎች፣ በምርጫ የሚወዳደሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና እጩዎች በሙሉ ምርጫውን ካሸነፉ ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበር፣ ለማስከበር እና ለማሟላት የሚወስዷቸውን ተጨባጭ እርምጃዎች በምርጫ መወዳደሪያ ጥሪ ሰነዳቸው (ማኒፌስቶ) ውስጥ በግልጽ እንዲያስቀምጡ ጠይቋል። በተለይም ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ የአካል ጉዳተኞችን፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችንና ስደተኞችን ሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ በተመለከተ የሚወስዱትን ተጨባጭ እርምጃዎች ለሕዝብ በይፋ እንዲያሳወቁና ቃል እንዲገቡ ነው የጠየቀው።

ኮሚሽኑ በኹለተኛ ደረጃ ያስቀመጠው፣ በመንግስት ሥልጣን ላይ የሚገኙም ሆነ ሌሎች እጩዎች እና ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ፣ በአጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ ሰብዓዊ መብቶችን አክብረው በሠላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ፣ በአባላቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው የሚፈጸምን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደማይታገሱ በይፋ እንዲያስታውቁ፣ እንዲሁም በአባሎቻቸው የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመመርመር ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ግልጽ የሆነ የውስጥ አሰራር በመዘርጋት ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ ነው።

በሶስተኛነት ከሚሽኑ ያስቀመጠው፣ ምርጫ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያደርግ መሆኑን በመገንዘብ ኹሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሻሻል ግልጽ አመላካቾች ያሏቸውን ስልቶች በመንደፍ እንዲተገብሩ፣ እንዲሁም ኹሉም ባለድርሻ አካላትም የምርጫው ሂደቶች በሙሉ ለሥርዓተ-ጾታ ምላሽ ሰጪ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ነው።

አራተኛ የሰብዓዊ መብት አጀንዳ፣ በምርጫው ያሸነፉም ሆነ የተሸነፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከኹሉም ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ያለውን ውስብስብ የፖለቲካና የሰብዓዊ መብቶች ቀውስ በዘላቂነት ለመፍታት፣ እንዲሁም ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት የሆኑ የሕግ፣ የፖሊሲ እና የአስተዳደር ጉዳዮችን ለመፈተሽ እና በሰብዓዊ መብቶች መርሆች ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አስፈላጊውን የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ለማድረግ በይፋ ቃል የሚጠይቅ ነው።

አምስተኛው፣ የፌዴራልና የክልል መንግስት አካላት፣ በተለይም የፀጥታ አካላት፣ ተግባራቸውን በገለልተኝነት እና በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት በመወጣት ኹሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና እጩዎች እንዲሁም ሚዲያ እና ሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶችን ጨምሮ ያለ ምንም ገደብ፣ ክልከላ፣ አድልዎ፣ አግባብ ያልሆነ ጣልቃ ገብነት ወይም የበቀል እርምጃ በሙሉ ነጻነት የመንቀሳቀስ፣ መረጃ የማግኘት፣ የመደራጀትና ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ እንዲችሉ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ተሳትፎ መብቶቻቸው በሙሉ መጠበቃቸውን እንዲያረጋግጡ ነው።
የመጨረሻው፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እጩዎች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ሲቪል ማኅበራት እና የማኅበረሰብ አንቂዎች በኹሉም የምርጫው ሂደት በአጠቃላይ ግጭት ቀስቃሽ፣ ጥላቻ እና ለመብት ጥሰት ምክንያት ከሚሆኑ ንግግሮች እና ተግባራት፣ በተለይም ከማናቸውም አይነት የኃይል እርምጃ ፈጽሞ እንዲቆጠቡ የሚጠይቅ ነበር።

ታዲያ ኢሰማኮ በግልጽ ያስቀመጣቸው የሰብዓዊ መብት አጀንዳዎች በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ኮሚሽኑ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እስካሁን ባደረጓቸው የክርክር መድረኮች በሚጠበቀው ልክ ጎልተው እንዳልታዩ እየተሰማ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች እስካሁን ባደረጓቸው ክርክሮችና ባቀረቧቸው አማራጭ ሀሳቦች የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ቀዳሚ አጀንዳ ከማድረግ ይልቅ እርስ በእርስ የመተቻቸት ላይ ትኩረታቸውን አድርገዋል እየተባሉ ነው።

የሰብዓዊ መብት ጉዳይ የኹሉም ነገር ማዕከል ነው የሚሉት የሕግ ባለሙያው ካፒታል ክብሬ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን የሰብዓዊ መብቶችን እንደ ዋና አጀንዳ አደርግዋቸው አልታዩም ይላሉ። በምርጫ ወቅት የፓርቲዎች ዋና ዓላማ ለሚወክሉት ሕዝብ ከምርጫ በኋላ የሚሰሩትን የሚያሳዩበት ወቅት ሆኖ ሳለ፣ በፓርቲዎች ምርጫ ሂደቱ የሚታየው በዚህ ልክ እንዳልሆነ መታዘብ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

ሰብዓዊ መብቶች እስካሁን በተደረጉ የፓርቲዎች ክርክር በተወሰነ መልኩ የተነሱ ነገሮች ቢኖሩም፣ ሙሉ ናቸው ማለት እንደማይቻል ነው ካፒታል የሚጠቁሙት። ይህ የሆነበት ምክንያትም የክርክር መድረኮች የመንግሥት አወቃቀርና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የመወቃቀሻ መድረክ በመሆናቸው ነው ይላሉ።

በተለይ ኢሰማኮ ቀዳሚ አጀንዳ ሆነው እንዲቀርቡ የጠየቃቸው የሥርዓተ-ጾታ እና የሕግና ፖሊሲ ማሻሻያዎች ላይ እስካሁን በታዩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር አለመታየታቸውና ክፍተቱ ጎልቶ እንደሚታይ ነው ባለሙው የሚገልጹት። በሰብዓዊ መብቶች ውስጥ ኹሉም ነገሮች ይካተታሉ የሚሉት ባለሙያው፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሰብዓዊ መብቶች ላይ ያላቸውን ሀሳብ በግልጽ ካስቀመጡ መሰረታዊ ቁልፉን እንደጨበጡና ለሕዝብ መብት የሚሰሩ መሆናቸውን የሚገልጹበት መንገድ ሊሆን ይችላል የሚል ሀሳብ አላቸው።

የሰብዓዊ መብቶች በዋናነት በሦስት ማዕቀፎች እንደሚካተቱ የሚገልጹት ባለሙያው፣ የሕዝብ ፖለቲካዊ መብቶች፣ ማኅበራዊ መብቶችና የሕዝብ የመልማት መብቶች ናቸው ይላሉ። በእነዚህ መብቶች ውስጥ በርካታ ዝርዝር ሰብዓዊ መብቶች እንደሚካተቱ የጠቆሙት ካፒታል፣ ፓርቲዎች በተለይ በማኅበራዊና የሕዝብ የመልማት መብቶች ውስጥ የሚካተቱ የሰብዓዊ መብቶችን በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ያደረገ ሀሳብ አለማቅረባቸውን እንደ ክፍተት ወስደውታል።

ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሂደት ወደፊት ለሕዝብ ሊሰሩ ያሰቧቸውን ዝርዝር አጀንዳዎች ማቅረብ ካልቻሉ ከምርጫ ብኋላ ሊያቀርቡት የሚችሉት ነገር አለ ተብሎ እንደማይጠበቅ የሚጠቁሙት ባለሙያው፣ ሕዝብ የሚጠይቃቸውን መብቶች ቀድመው ዋና አጀንዳ ማድረግ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። ሰብዓዊ መብቶችን ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ ማቅረብ ያልቻሉ ፓርቲዎች ነገ ለሕዝብ በተግባር የሚሰጡት ነገር እንዲኖራቸው መጠበቅ እንደማይቻል ጠቁመዋል። በመሆኑም ፖለቲካ ፓርቲዎች የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ የኹሉም ነገር መሰረት መሆኑን በመገንዘብ ቀዳሚ ትኩረታቸው መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com