ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ማስቆም ፈታኝ እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ

Views: 43

በኢትዮጵያ ውስጥ እየተበራከተ የመጣውን ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ከምንጩ ለማድረቅ ከባድ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በሰሜኑ አካባቢ የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ የስርጭት መጠኑ እየጨመረ መጥቷል። በቡድን የሚያዙ መሳሪያዎችን ጨምሮ በግለሰቦች የሚያዙ እየተበራከቱ መምጣታቸውን ነው ኮማንደሩ የጠቀሱት። የጦር መሳሪያዎችን በሕጋዊ መንገድ የሚይዙ ፍቃድ ያላቸው እንደሚገኙ ኮማንደር ፋሲካ ጠቁመዋል። የጸጥታ ኃይሉ በማንኛውም ሁኔታ ፍተሻ በሚያደርግበት ጊዜ ፍቃድ እያላቸው ይዘው ያልተገኙትን በመውረስ ፍቃዳቸውን ይዘው ሲመጡ ተመላሽ የሚሆንበት አሰራር መኖሩን ጠቅሰዋል።

አብዛኛው የሚያዙት የጦር መሳሪያ በሕገ-ወጥ መንገድ መሆኑን ያነሱት ኮማንደሩ ከተያዙ በኋላ ወድያውኑ ለሕግ ይቀርባሉ ብለዋል። በመቀጠልም በፍርድ ቤት ሕገወጥነቱ ተረጋግጦ ሲያዘዋውር የነበረው ግለሰብ በሕግ እንዲጠየቅ ይደረጋል። ከፍርድ ሂደቱ በኋላ ንብረቱ ምን መደረግ እንዳለበት አቃቤ ሕግ በሚወስነው ውሳኔ መሰረት ወደ መንግሥት ካዝና እንዲገባ ይደረጋል። መንግሥት ካዝና ከገባ በኋላ ምን እንደሚደረግ የመንግስት ውሳኔ እንደሚሆን ኮማንደር ፋሲካ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ የሚገኘው ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ዝውውር በአገራችን የሚፈጥረው ትልቅ ተጽእኖ ቢኖርም ከምንጩ ለማጥፋት ዓለም አቀፍ ትብብር እንደሚያስፈልግ ነው ኮማንደሩ የገለጹት።

በተለያዩ ጊዜያት የሚያዙ መሳሪያዎች ኤግዚቢት በሚደረጉበት ሰዓት ከሚስተዋሉ ነገሮች አንዱ መሳሪያዎቹ የተለያዩ አገራት ስሪት (ብራንድ) መሆናቸው ነው። ይህ ደግሞ የሚያሳየው ወደ ከተማ ለመግባት በርካታ ድንበሮችን ተሻግረው መምጣታቸውን ነው። እንደዚህ አይነት ዝውውሮችን በዚህ ደረጃ የሚያከናውኑት በሕገ-ወጥ መልኩ የተደራጁ፣ ሕጋዊ አሰራር የማይቀበሉ እና በአቋራጭ ስልጣን መያዝ የሚፈልጉ ቡድኖች በመሆናቸው ለመቆጣጠር እጅግ ከባድ ነው ሲሉ ኮማንደር ፋሲካ ጠቅሰዋል። ይህንን ለመቆጣጠር የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከሌሎች ጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ሥራ እየሠራ ነው። የሥራውንም ውጤት ማየት እየተቻለ ነው ሲሉ ኮማንደር ፋሲካ ተናግረዋል። ለዚህ ውጤት መሳካት የሕብረተሰቡ ጥቆማ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

ባሳለፍነው ጊዜያት ከተያዙት መካከል በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አውቶቢስ ተራ አካባቢ የዘይት መያዣ ጀሪካን ውስጥ የጦር መሳሪያ ደብቀው ለወዛደር አሸክመው ሲሄዱ ተሸካሚው በክብደቱ ተጠራጥሮ ጥቆማ ያደረሰበት ሁኔታ መኖሩን ኮማንደሩ ተናግረዋል።
በ26/ 2013 በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 209 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ ከ156 ሺህ በላይ ዩሮ እና የእንግሊዝ ፓውንድ ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መግለጹ የሚታወስ ነው። በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ቱሉ ዲምቱ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጤፍ ጭኖ ከአዲስ አበባ ወደ ሞያሌ ሲጓዝ በነበረ አሽከርካሪ ላይ በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 209 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ 156 ሺህ 160 ዩሮ እና 24 ሺህ 670 የእንግሊዝ ፓውንድ በላስቲክ ተጠቅልሎ መገኘቱን ኮሚሽኑ ገልጿል።

በተጨማሪም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 አንድ የእንግዳ ማረፊያ ክፍል ተከራይተው ሀሰተኛ የኢትዮጵያ ብር እና የውጪ አገራት የገንዘብ ኖቶችን ሲያትሙ የነበሩ ሁለት የውጪ አገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቅንጅት ግንቦት 24/2013 በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል። ተጠርጣሪዎቹ በተከራዩት ክፍል ውስጥ በተደረገ ብርበራ ከ81 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ብር፣ 330 የአሜሪካ ዶላር እንዲሁም የተለያዩ አገራት ገንዘቦች ተገኝተዋል። ባሳለፍነው ሳምንት ከተያዙ የጦር መሳሪያዎች መካከል 19 ሺህ 739 ተተኳሽ ጥይቶችን በባለ ሦስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪ ጭነው ወደ ባህር ዳር ሊያስገቡ የሞከሩ ሁለት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን በጉምሩክ ኮሚሽን የባህርዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የገለጸው ተጠቃሽ ነው። ግለሰቦቹ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 1-43622 አ.ማ በሆነ በባለ ሦስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪ ጭነው ወደ ባህርዳር ለማስገባት ሲሞክሩ በሻውራ ጉምሩክ ሠራተኞችና በፌደራል ፖሊስ ትብብር በተደረገ የኬላ ፍተሻ ተይዘዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com