የሰሜን ሸዋ ተፈናቃዮች ድጋፍ በአግባቡ እየደረሰን አይደለም አሉ

Views: 29

በሰሜን ሸዋ ዞን ለተፈናቀሉ ከ 235 ሺህ በላይ ዜጎች ድጋፍ ማድረጉን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ቢናገርም ተፈናቃዮች ድጋፉ በአግባቡ እየደረሰን አይደለም ብለዋል፡፡ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከተለያዩ ወረዳዎች ለተፈናቀሉ ከ 235 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ መቻሉን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት ቀዳሚ የማቋቋም ድርሻ የክልሎች ቢሆንም፣ የሰሜን ሸዋው ችግር ከክልሉ አቅም በላይ ስለሆነ የፌዴራል መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ ደበበ አንስተዋል፡፡

በክልሉ የደረሰው ግድያ፣ አደጋ፣ እና መፈናቀል ከክልሉ አቅም በላይ በመሆኑ አነዚህን ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉትን እና ንብረታቸው የወደመባቸውን ለመታደግ በየወሩ ኮሚሽኑ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የሚደረገው ድጋፍ ፍትሃዊነትን ለመከታተል እና ለማስተባበር ከመላ አገሪቱ የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ አባላቱ ወደ ተለያዩ ወረዳዎች ተሰማርተው አሰሳ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ኮሚሽኑ ይህን ቢልም በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በክልሉም ሆነ በፌዴራል መንግስት እየተደረገ ነው የሚባለው ሰብዓዊ እርዳታ በአግባቡ ተደራሽ እየሆነ አይደለም ሲሉ ነግረውናል፡፡

የምንለብሳቸው አልባሳት ቀርቶ የዕለት ጉርሳችንን እንኳን በበቂ ሁኔታ እያገኘን አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ ድጋፉ በቂ አይደለም፣ በአግባቡ እየደረሰን አይደለም እያሉ ቢሆንም፣ ክልሉ ባቀረበልን ጥያቄ መሠረት ድጋፉን እያቀረብን ነው ሲሉ የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ ተናግረዋል፡፡ የተፈናቃዮቹንም ቅሬታ የሀሰት ውንጀላ ነው ብለዋል፡፡ መንግስት በትክክለኛው መንገድ ለተፈናቃዮች እያደረሰ መሆኑን የጠቆሙት ደበበ፣ በዚህ መልኩ የሚነዙ ወሬዎች የአገሪቱን ገጽታ ያበላሻሉ፤ ያስተዛዝበናልም ብለዋል፡፡

አክለውም የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እርዳታውን ለተፈናቃዮቹ በቀጥታ ሰጪ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ክልሉ በጠየቀው መሰረት ኮሚሽኑ ያደረገውን ድጋፍ በትክክል የማከፋፈል እና ተደራሽ የማድረግ ሥራው የክልሉ አመራሮች ነው ብለዋል፡፡
በ2008 ዓ.ም ከ10.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በድርቅ በተጎዱበት ወቅት እና ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን ሲፈናቀሉ ሙሉ በሙሉ እርዳታ ተደራሽ አድርገናል፤ ይህም ድጋፍ ማድረግ ላይ እንደማንታማ ይጠቁማል ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ድጋፉ በየወሩ ይቀጥላል ያሉት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ፣ በመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ላይም ኮሚሽኑ በሚገባ እንደሚሳተፍ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በድርቅ፣ በጎርፍ፣ በመሬት መንሸራተት እና መሰንጠቅ ዜጎቿን ከከፋ ጉዳት ለመታደግ እየሠራች ቢሆንም፣ አሁን አሁን ደግሞ ግጭት ያስከተለው መፈናቀል ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚደረገውን ሥራ የበለጠ እንዲሰፋ አድርጎታል ሲሉ ደበበ ዘውዴ ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች በተከታታይ በተፈጸሙ ጥቃቶች የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ፣ በርካቶች መፈናቀላቸው እና ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት መውደሙ ይታወሳል።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com