ለሴፍቲኔት ፕሮግራም የሚውል 30 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በ477 ሚሊዮን ብር ሊገዛ ነው

Views: 32

ለሴፍትኔት ፕሮግራም የሚውል 30 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በ477 ሚሊዮን ብር ለማቅረብ ‹ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል› ጨረታ ማሸነፉን የመንግሥት ንብረት ማስወገድና ግዥ አገልግሎት አስታወቀ። የመንግሥት ንብረት ማስወገድና ግዥ አገልግሎት ለግበርና ሚኒስቴር ግዥውን ለመፈጸም በጨረታ አሸናፊ ለሆነው ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል 30 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ እንዲያቀርብ የአሸናፊነት ማረጋጋጫ(አዋርድ) መስጠቱን የአገልግሎቱ የግዥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወርቁ ገዝሀኝ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። በጨረታው አሸናፊ ለሆነው ፕሮሚሲንግ ኢንተርናል የአሸናፊነት አዋርድ የተሰጠው በጨረታው ከተሳተፉት ድርጅቶች የተሻለ ሰነድ በማቅረቡ ነው ተብሏል።

በግብርና ሚኒስቴር ለሚከናወነው ሴፍቲኔት ፕሮግራም ይውላል የተባለው 30 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ፣ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች በሴፍቲኔት ፕሮግራም እንደሚሰራጭ ተመላክቷል። ግብርና ሚኒስቴር በ30 ቀናት ውስጥ ጨረታውን ካሸነፈው ፕሮሚሲንግ ኢንተርነሽናል ስንዴውን እንደሚረከብ ተጠቁሟል። ለግብርና ሚኒስቴር ለሴፍቲኔት ፕሮግራም አገልግሎት የሚውል 30 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ግዥ ለመፈጸም የወጣው ጨረታ ተጫራቾች በተገኙበት የቴክኒክ እና የፋይናንስ ሰነድ ተከፍቶ የጨረታ ሰነዱን 11 ተወዳዳሪዎች የወሰዱ ሲሆን፣ ኹለት ተጫራቾች የመወዳደሪያ ሰነዳቸውን ሲያስገቡ አንድ ተጫራች ጨረታው ከተዘጋ በኋላ በመድረሳቸው የጨረታ ሰነድ ሳይከፈት ተመላሽ እንደተደረገላቸው ተገልጿል።

ጨረታ ሰነድ ካስገቡት ተወዳዳሪዎች ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል አዳማ መጋዘን ድረስ ለአንድ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ትራንስፖርትና ሌሎች ወጪዎችን ጨምሮ 372 ዶላር፣ ለ15 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር፤ እንዲሁም ኮምቦልቻ መጋዘን ድረስ ለአንድ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ትራንስፖርትና ሌሎች ወጪዎችን ጨምሮ 365 ዶላር፣ ለ15 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ በአጠቃላይ ለ30 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ 11 ሚሊዮን ዶላር አቅርቦ እንደነበር ተመላክቷል። ኹለተኛው ተጫራች ‹ፋልኮን ብሪጅ ሪሶርስ› አዳማ መጋዘን ድረስ ለአንድ ሜትሪክ ቶን ስንዴ የትራንስፖርትና ሌሎች ወጪዎችን ጨምሮ 360 ዶላር፣ ለ15 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ አምስት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም ኮምቦልቻ መጋዘን ድረስ ለአንድ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ትራንስፖርትና ሌሎች ወጪዎችን ጨምሮ 353 ዶላር፣ ለ15 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ አመስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር ነው። በአጠቃላይ ለ30 ሺሕ ሜትሪክ ቶን 10 ሚሊዮን ዶላር ያቀረበ ሲሆን የሁለቱም ተጫራቾች የቴክኒክ እና ሕጋዊ ሰነዶች ግምገማ ከተደረግ በኋላ አሸናፊው ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል ሆኗል።

ኹለቱ ተጫራቾች 30 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለግብርና ሚኒስቴር ለማቅረብ፣ ያቀረቡት የፋይናንስ መጠን ሲነጻጸር የፋርኮን ብሪጅ ሪሶርስ ያቀረበው ዋጋ የተሻለ መሆኑን ሰነዱ ያሳያል። ይሁን እንጅ የቴክኒክ እና የፋይናንስ ጨረታ ሰነድ ሲከፈት ፋልኮን ብሪጅ ሪሶርስ የተባለው ተጫራች ዝቅተኛ ዋጋ እንደሰጠ ቢገለጽም፣ ተጫራቹ የቴክኒክ (የተጠየቀውን የተሟላ) ሰነድ ባለማቅረቡ ምክንያት በጨረታው ውድቅ እንደተደረገ ተገልጿል። በግብርና ሚኒስቴር ስር ለሚከናወነው ሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚውል 75 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ ለማከናወን ፕሮሚሲን ኢንተርናሽናል በ2012 በነበረው የግዥ ሂደት አቅራቢ እንደነበር የሚታወስ ነው። ግዥው የዓለም ባንክ ለግብርና ሚኒስቴር የሴፍትኔት ፕሮግራም ባደረገው 24 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የተፈጸመ ነበር።

በሌላ በኩል የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በ2013 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በውል አስተዳደር በኩል ከ17 አቅራቢ ድርጅቶች ጋር 19 ውሎችን በመፈራረም በጠቅላላው የ548 ሚሊየን ብር ውል ተፈራርሞ 187 ባለበጄት መስሪያ ቤቶችና 22 የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com