የእለት ዜና

በ2008 የቀረበው የቤቶች አስተዳደርና ግብይት ረቂቅ አዋጅ ምላሽ አለማግኘቱ ተገለጸ

በ2008 አጠቃላይ የቤት አስተዳደርና ግብይት አዋጅ በሚል ተዘጋጅቶ ለሚንስትሮች ምክር ቤት የቀረበዉ ረቂቅ አዋጅ እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱን በከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽ ሚኒስቴር ልዩ አማካሪ የሆኑት ኢትዮጵያ በደቻ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ረቂቅ አዋጁ በ2008 ተዘጋጅቶ በ 2010 ለሚንስትሮች ምክር ቤት ተልኮ እስካሁን አለመጽደቁ የቤት ኪራይ የዋጋ ንረት እልባት እንዳያገኝ አድርጎታል። ረቂቁን በሚመለከት የሚንስትሮች ምክር ቤት አይቶት በሰጠዉ አስተያየት መሰረት የተወሰነ ማሻሻያ አድርጎ ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መላኩን አዲስ ማለዳ ካገኘችዉ መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ከተሞች ላይ የሚከራዩ እና የሚሸጡ ቤቶችን የሚመለከት፣ አጠቃላይ የቤቶች አስተዳደርና ግብይት ሁኔታዎችን ትኩረት አድርጎ፣ በቤቶች ዙሪያ ያለዉን የሕብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ ረቂቁን ማዘጋጀቱን ይናገራል። የግብይትና የኪራይ ስርዓቱ ምን መምሰል እንዳለበት ፣የሚነሱ ችግሮች እንዴት እንደሚፈቱ፣ ጎልተዉ የሚታዩ ነባራዊ ችግሮች የትኞቹ እንደሆኑ እና ሕብረተሰቡ ችግሮቹ እንዴት ይፈቱለት የሚል ሃሳብ የያዘ ረቂቅ ነዉ። የተዘጋጀዉ ረቂቅ አዋጅ በሚንስትሮች ምክር ቤት እስካሁን ባለመጽደቁ ችግሩ እንዳይቀረፍ አድርጓል ያሉት አማካሪው፣ ረቂቁ ሲዘጋጅ በተለያዩ መድረኮች ላይ ቀርቦ የሕግ አካላት እና የሕብረተሰብ ክፍሎች ዉይይት እና አስተያየት አድርገውበት ነበር ብለዋል።

መንግሥት ካጸደቀው ያለዉን የቤት ኪራይ ችግር ይቀርፋል የተባለለት ይህ ረቂቅ አዋጅ፣ ያካተታቸዉን ዝርዝር ሁኔታዎች አዲስ ማለዳ ለማወቅ ብትሞክርም አዋጁ ባልጸደቀበት ሁኔታ መግለጽ እንደማይችሉ ልዩ አማካሪዉ አስታዉቀዋል። በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በ2008 የተዘጋጀዉ የቤት አስተዳደርና ግብይት አዋጅ እስካሁን ላለመፅደቁ አንዱ ምክንያት በመካከል የነበረዉ የመንግስት ሽግግር ነዉ ሲሉ ኢትዮጵያ በደቻ ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ከዚህ በላይ የሚያሳስቡት የተለያዩ ጉዳዮች ስላሉ ችግሮቹን ለመፍታት እነዛ ላይ ማተኮሩ ነዉ ተብሏል።

ረቂቁ አከራዩንም የተከራዩንም ሁኔታ ያገናዘበና እና ጥያቄ በማያሥነሳ መልኩ የተዘጋጀ እንደሆነ ልዩ አማካሪዉ አስታዉቀዋል። ረቂቁ ቢዘገይም እየተሰራበትና እየታየ ያለ ጉዳይ መሆኑንም የተናገሩት ልዩ አማካሪው፣ አዋጁ አሁን ላይ የሚነሱ ጉዳዮችንም የሚዳስስ እንደሆነ ተናግረዋል። የቤቶች ኮንስትራክሽን፣ በተከራይና በአከራይ መካክል ያለዉን አለመግባባትና የቤት ኪራይ ንረትን ለመቆጣጠር ሊረዳ የሚችል ረቂቅ ቢያዘጋጅም፣ ችግሩ እንዲፈታ መንግስት ብቻ ሳይሆን ሕብረተሰቡ ኃላፊነት ሊሰማዉና ሊረዳዳ እንደሚገባ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሚዲያዎች ችግሮቹ የሚፈቱበትን መንገድ ሕብረተሰቡን በማወያየት ሊሰሩበት ይገባል ሲሉም አክለዋል። አገራችን የምትከተለዉ ነጻ የገበያ ስርአት ቢሆንም፣ ሕብረተሰቡን ለከፋ አደጋ እና ጉዳት የሚዳርጉ ጉዳዮች ላይ መንግሥት አስፈላጊ ሲሆን ጣልቃ በመግባት ማስተካከል እንደሚችል ጠቅሰዋል። ችግሩ ያለዉ በከተሞች አካባቢ ስለሆነ ይህን ለመቅረፍ በከተሞች አካባቢ በስፋት ቤቶችን መገንባት አንዱ መፍትሄ እንደሆነ አሳውቀዋል። ይህም የተከራይ ቁጥርን ይቀንሳል። የቤት ኪራይ ዋጋ ንረትንም እንደሚያረጋጋዉ ስለታመነ ታቅዶ እየተሰራበት ነው ብለዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስተራክሽን ሚኒስቴር የቤት ችግሩን ለመቅረፍ በአስር አመት ዉሰጥ ወደ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ቤቶችን በሁሉም የአገሪቱ ከተሞች ለመገንባት ማቀዱን አስታዉቀዋል። በጋራ መኖሪያ ቤት ለመስራት ለሚፈልጉ መንግስተ በማደራጀት፣ መሬት በመስጠት እና በሪል እስቴትና በግሉ ዘርፍ ቤት አልሚዎችን በመጠቀም ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚሰራ አስታዉቋል። በቅርቡ ይፋ ይሚደረግ የመንግሰትና የግል ዘርፉ አጋርነት የሚል አዋጅ እየተጠና እንደሆነና ሲጠናቀቅ ያለዉን የቤት ችግር መፍታት ይቻላል ብለዋል ልዩ አማካሪዉ። በአያትና አራብሳ በመሳሰሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የግለሰብ ቤቶችን ተከራይተዉ የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለአዲስ ማለዳ እንዳደረሱት፣ የኪራይ ዋጋ ከቤቱ ስፋት ጋር በማይመጣጠን መልኩ ንሯል፣ ይህም የኑሮ ዉድነቱን እንዳባባሰባቸዉ ገልጸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!