የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አዲስ የፋይናንስ ስርዓት ሊተገብር መሆኑን ገለጸ

Views: 92

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ስርዓትን (International Financial Reporting Standard) ለመተግበር እየሠራ ያለውን ሥራ አጠናቆ በቅርቡ ወደ ተግባር እንደሚገባ የተቋሙ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ገልጸዋል። ተቋሙ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ስርዓትን ለመተግበር ‹ፌር ፋክስ እና ፒ ደብሊው ሲ (PWC)› ከተሰኙ ኹለት ኩባንያዎች ጋር ስምምነት በማድረግ ወደ ሥራ መግባቱን ነው ሞገስ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።
ተቋሙ ፒ ደብሊው ሲ ከተሰኘ ኩባንያ ጋር የ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ሥምምነት በማድረግ የIFRS የፋይናንሺያል ሪፖርት ሥራዎች እያከናወነ ይገኛል።

ኩባንያው በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2016 እስከ 2019 ያለውን የፋይናንስ ሪፖርት ማዘጋጀት ችሏል። ከዚህ ውስጥም ከ2016 እስከ 2018 ድረስ ያለው የተቋሙ የመጀመሪያው የፋይናንስ ሪፖርት ለሂሳብና ኦዲት ቦርድ ኮርፖሬሽን አቅርቧል ሲሉ ሞገስ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል። የኦዲት አገልግሎት ቦርድ ኮርፖሬሽን የምርመራ ሥራዉን ካጠናቀቀ በኋላ ተቋሙ ወደ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ሥርዓት ትግበራ እንደሚገባ ሞገስ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። ከፒ ደብሊው ሲ ኩባንያ ጋር በ20 ወራት ውስጥ ሥራዎችን አጠናቆ ለማስረከብ ሥምምነት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ ለተጨማሪ 5 ወራት ውሉ ተራዝሟል። በዚህ የጊዜ መራዘም ውስጥ ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ አለመደረጉን ሞገስ ጨምረው ገልጸዋል።

ተቋሙ ከሚሠራቸው ኹለት ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ይገኙበታል። የሕዳሴ ግድቡ የሙሌት ስራ ለማከናወን የሚያስችሉ ተግባራት በመጠናቀቃቸው በመጪው ክረምት ሁለተኛውን የሙሌት ሥራ ለማከናወን እየተጠበቀ ነው ሲሉ ሞገስ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በኮይሻ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ባሳለፍነው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ፈጣን የሚባል የግንባታ ሥራ መከናወኑን ሞገስ ጠቁመዋል። እንደ ሞገስ ገለጻ ከሆነ የኮይሻ የኃይል ማመንጫ በአሁኑ ሰዓት 40 በመቶ ስራው የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የውጭ ብድሮች በታቀዱት መንገድ አለመለቀቃቸው ለፕሮጀክቱ መጓተት ማነቆ ነው ብለውናል።

ሙሉ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ 2.5 ሚሊዮን ዩሮ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ በዶላር ከሚከፈለው 60 በመቶ ውስጥ አበዳሪ ተቋማት 300 ሚሊየን ዶላር ብቻ መክፈላቸው ታውቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሁኑ ሰዓት እየተሠራ ያለው መንግሥት በሚለቀው በጄት ሲሆን፣ ቃል የተገባው የአበዳሪ ተቋማት ገንዘብ እስከአሁን አለመለቀቁን ሞገስ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል IFRSን ለመተግበር ፌር ፋክስ ከሚባለው ድርጅት ጋር የሚሰራውን የንብረት ቆጠራ መረጃ የመሰብሰብና ወደ ገንዘብ የመተን የዋጋ ክለሳ ሥራ ማጠናቀቁንም አዲስ ማለዳ ሰምታለች። ተቋሙ ፌር ፋክስ ከተሰኘ ኩባንያ ጋር ያሉትን ንብረቶች ለመቁጠርና የዋጋ ክለሳ ሥራዎችን ለማከናወን የ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራርሞ የነበረ ሲሆን፣ ኩባንያው በውሉ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ሥራውን ባለመፈጸሙ ተጨማሪ የጊዜ ማራዘሚያ እንደተሰጠው ለማወቅ ተችሏል።
ፌር ፋክስ በአሁኑ ወቅት ከማጠናቀቂያ ሥራዎች በስተቀር የተሰጠውን ሥራ በውሉ መሰረት ማከናወኑን ሞገስ ጠቁመዋል።

በዋጋ ትመናው ከተካተቱት መካከል የ24 ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች፣ 129 ማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ 36 ሺህ 210 የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች፣ 9 መቶ 48 ተሸከርካሪዎችንና ማሽነሪዎች፣ 48 ሺህ የቤትና የቢሮ ዕቃዎችን እንዲሁም የ3 ሺህ 232 ህንፃዎች የዋጋ ትመና ሥራ ተከናውኗል ተብሏል።

በቆጠራው የተካተቱ ንብረቶች ወደ ገንዘብ ሲተመኑ የተቋሙ ሀብት 382 ቢሊዮን ብር ደርሷል። የቆጠራና የትመና ሥራው የተከናወነው በ2016 እና ከዚህ በፊት አገልግሎት በመስጠት ላይ በነበሩ ንብረቶች ላይ በተካሄደ የአይ ኤፍ አር ኤስና የንብረት ክለሳ ሥራ ሲሆን፣ የዋጋ ትመናው የገናሌ ዳዋ 3፣ የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ እና በግንባታ ላይ ያሉትን ግዙፍ ፕሮጀክቶች አላጠቃለለም።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com