ከመተከል የተፈናቀልነውን ለመመለስ የቀረበው ሐሳብ ስጋት ሆኖብናል

Views: 81

ከመተከል ተፈናቅለው በአማራ ክልል አዊ ዞን ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮችን ለመመለስ የቀረበው ሀሳብ፣ አካባቢው ከስጋት ነጻ አለመሆኑን ተከትሎ፣ ስጋት እንደሆነባቸው ተፈናቃዮች ገለጹ። ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን፣ በተለያዩ ጊዜያት በታጣቂ ኃይል በተከሰተ ጥቃት ተፈናቅለው አማራ ክልል አዊ ዞን ቻግኒ አካባቢ በሚገኘው ራንች መጠለያ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮችን፣ ወደ ነበሩበት ክልል ሙሉ በሙሉ ለመመለስ ዝግጅት መደረጉን አዲስ ማለዳ ካገኘችው የእቅድ ሰነድ ለመረዳት ችላለች። አዲስ ማለዳ ያገኘቸው ሰነድ ከአማራ ክልል፣ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልና ከፌደራል መንግሥት ጋር በጋራ በመሆን የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመመለስ የተዘጋጀ ሰነድ ነው። ከመተከል ተፈናቅለው አማራ ክልል የሚገኙ ዜጎችን ለመመለስ የተዘጋጀው የእቅድ ሰነድ እንደሚያሳየው ከሆነ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን በኹለት መንገድ ለመመለስ ታስቧል።

በመጀመሪያቀው እቅድ፣ ከመተከል ዞን ወረዳዎች ተፈናቅለው የነበሩ፣ ነገር ግን ቤታቸው ያልፈረሰባቸው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ማድረግ መሆኑ በሰነዱ ላይ ተገልጿል። ለዚህም ሶስት ወረዳዎች በሰነዱ ላይ የተለዩ ሲሆን፣ ማንዱራ፣ ግልገል በለስና ዳንጉራ ወረዳዎች ተመርጠዋል። በተመረጡት ሶስት ወረዳዎች በመጠለያ ካምፕ ይጠለላሉ ተብለው የተለዩ ተፈናቃዮች ቁጥር 13 ሺሕ 174 ነው። ይሁን እንጅ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ራንች መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች፣ አካባቢው ከስጋት የጸዳ ባለመሆኑ ወደ ቤታቸው ለመመለስ ስጋት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ለዚህም እንደምክንያት የሚያነሱት በመተከል ዞን ቀድሞ ለመፈናቀላቸው ምክንያት የሆነው የታጣቂ ኃይል ጥቃት መሆኑን በማስታወስ፣ ጥቃት አድራሹ ታጣቂ ኃይል ጫካ ውስጥ መኖሩን በማንሳት ነው። ቀድሞውንም ለመፈናቀላቸው ምክንያት የሆነው ታጣቂ ኃይል ሙሉ በሙሉ ከጫካ እስካልወጣ ድረስ ችግራቸው እንደማይቀረፍ ጠቁመዋል።

ኹለተኛው እቅድ፣ ቀድሞ ታጣቂው ኃይል ባደረሰው ጥቃት ቤትና ንብረት የወደመባቸውን ዜጎች በተመረጡ መጠለያዎች እንዲሰፍሩ ማድረግ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያገኘችው ሰነድ ይጠቁማል። በተመረጡ መጠለያዎች እንዲሰፍሩ የታቀደላቸው ቤታቸው የወደመባቸው ተፈናቃይ ዜጎች ቁጥር 16 ሺሕ 485 መሆኑን የሚጠቁመው ሰነዱ፣ ዜጎቹን በድንኳን ለማስጠለል እቅድ እንደተያዘ ያብራራል። ሀሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ያጋሩ ተፈናቃዮች፣ ወደ ቦታቸው መመለሳቸው መልካም ነገር ቢሆንም፣ መንግሥት አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ከስጋት ነጻ ካላደረገው ለኹለተኛ ጥቃት እንዳይጋለጡ ስጋት አላቸው። በተለይ ቤታቸው ጉዳት ያልደረሰበትና ወደ ቤታቸው የሚመለሱ ዜጎች ተጨማሪ ጥቃት ሊደርስብን ይችላል የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ጠቁመዋል።

ተፈናቃዮችን ወደ ቦታቸው ለመመለስ ቅድመ ሥራዎችን ለመሥራትና ለማስተበበር 3 ሚሊዮን ብር እንደሚስፈልግም በሰነዱ ተጠቁሟል። 3 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል የተባለው የተፈናቃዮች መረጃን በየወረዳ ለማጣራት፣ በጊዜያዊ መጠለያ የሚሰባሰቡ ተፈናቃዮችን ለመመለስና ቤታቸው ያልፈረሰባቸው ተፈናቃዮችን ወደ ቤታቸው ለመመለስ ነው። በአማራ ክልል፣ አዊ ዞን ቻግኒ ከተማ ራንች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎችን፣ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎችን ከማዘጋጀት፣ በየአካባቢያቸው ከማደራጀት እና በመንግስት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ከማድረግ በተጨማሪ፣ ተፈናቃዮች በጋራ በማረስ ገቢ እንዲያገኙ እንደሚደረግ ዞኑ ጠቁሟል። በራንች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ 29ሺሕ 959 የተፈናቀሉ ዜጎችን አዲስ በተመረጡ ቦታዎች ለማስገባት ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለመጠለያ የሚሆኑ 500 ድንኳኖች መዘጋጀታቸው ተመላክቷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com