እንመራ እንጂ አንነዳ!

Views: 22

የኢትዮጵያ ሕዝብ በመንጋ እንደሚንቀሳቀስ ሕብረተ-በግ እረኛ እንደሚያስፈልገው የሚስማሙ በርካቶች ናቸው። እንደ አንድ የበግ መንጋ መንቀሳቀስ ያለበት ይህ ሕብረተሰብ ከፊቱ እረኛው እየመራ ይከተላል እንጂ ከኋላ በጅራፍም ሆነ በልምጭ የሚነዳ ከሆነ፣ አመልጣለሁ ብሎ ጠፍቶ የተኩላ እራት መሆን አሊያም ገደል ገብቶ መሞት እጣ ፋንታው ይሆናል። የሕብረተሰቡ አካል እንደ አንድ መንጋ አልሆንም ማለት መብቱ ቢሆንም፣ የራሱን ማኀበረሰብ እረኛ መርጦ መከተል ግን ግድ ይለዋል። የየማኀበረሰቡ እረኛ ደግሞ እርስበርሱ የማይነጋገርና የማይግባባ ከሆነ አንዱ በለፋበት ሌላው ሲዳክርበት እንዲውል ወይም የጋራ አደጋቸውን ለመጠቋቆም አዳጋች እንዲሆን ያደርጋል።

6ተኛው አገራዊ ምርጫ ሊካሄድ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት በቀሩበት በዚህ ወቅት አደገኛ አካሄዶች በግለሰብም ሆነ በመንጋ መሪዎች ሲፈፀሙ እየተስተዋለ ነው። ምርጫው አገር ትልቅ ወጪ አውጥታበት ውጤታማ ልናደርገው ካልቻልን ኪሳራው ለሁላችንም እንደሚሆን አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች። ከተለያዩ ፓርቲዎች የሚቀርቡ ስሞታዎችና ቅሬታዎች አሁንም ተጠናክረው መቀጠላቸው ሂደቱንና ውጤቱን አስጊ ያደርገዋል። የፓርቲ ደጋፊዎችና አባላቶች ከመሪዎቻቸው እውቅና ውጭ ሲንቀሳቀሱና በማኀበራዊ ሚዲያ ያዩትን ሁሉ የግል አስተያየቴ ነው በሚል ብሒል፣ የሌላን አጀንዳ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ተቀብለው ሲያሥተጋቡት ይስተዋላል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ እንደ ዱብእዳ ድንገት ተወርቶ መነጋገሪያ የሆነ አደገኛ ጉዳይ ተከስቶ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተናገሩት የድምጽ ቅጂ ወጣ ተብሎ መረጃውን ብዙዎች ተቀባብለውት ነበር። ስለምርጫው ድብቅ ዓላማቸውን አሳወቁበት የተባለው ይህ መረጃ ሲወጣ ወዲያው ባይገለጽም በኋላ ላይ መቀመጫውን ግብጽ ካደረገ ተቋም መለቀቁ ተነግሯል። “እሞታታለሁ እንጂ ስልጣን አለቅም” አሉ ተብሎ በጥቂት ጊዜ ብዙዎች የተቀባበሉት ይህ መረጃ ምርጫውን ገደል የሚከትና በሕዝቦች መካከል አለመተማመንን የሚፈጥር አደገኛ ጉዳይ ነው። የመረጃውን እውነተኛነት ባለሙያዎች እስኪያጣሩት ድረስና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም አስተያየት እስኪሰጡበት ድረስ ለመታገስ አልተቻለም ነበር።

በጉዳዩ ላይ የተረጋገጠ ነገር እስኪወጣ የመንግሥት ደጋፊ የሆኑ የማኀበረሰብ አንቂዎች ወዲያው “የተቀጣጠለ የውሸት መረጃ ሳይሆን አይቀርም” ቢሉም የሚተቻቸው እንጂ የሚሰማቸው ለማግኘት ተቸግረው ነበር። በነጋታው ግን ቅንብሩ ከወር ከ10 ቀን በፊት ካደረጉት ንግግር ላይ እየተቀነጨበ የተገጣጠመ የቆርጦ ቀጥሎች ሥራ ነው እያሉ ከትክክለኛው ጋር እያነፃፀሩ አቅርበውታል። አንድ የድምጽ ቅንብር ባለሙያ ወይም ሬዲዮና ቴሌቭዥን ጣቢያ ውስጥ የሠራ ባለሙያ፣ እንዲህ ተደረጎ ያን ያህል ልምድ በሌለው ሰው ተሰርቶ ሊቀርብ እንደሚችል ይገምታል። ተናገሩ ተብሎ ይፋ የተደረገው የአጭር ደቂቃ ድምፅ ያን ያህል ያልተለፋበትና መቀጣጠሉን ለማወቅ ያን ያህል አዳጋች አለመሆኑን ባለሙያዎቹ ቢያውቁትም፣ ፈጥኖ በመሰራጨቱ የፈጠረው ተጽእኖ ከፍተኛ እነደሆነ ይገመታል።

የማንተማመን ዜጎች መሆናችንን በቀላሉ ያየንበት ይህ ክስተት፣ ውሸት መሆኑን መንግሥት እንዲያስተባብል ቢያስገድደውም፣ የለወጠውን አስተሳሰብ ወደነበረበት ለመመለስ አስቸጋሪ ነው። ተመሳሳይ ተግባር እንዲፈፅሙ ለሌሎች በር ከመክፈቱ ባሻገር ውሸት በምን ያህል ፍጥነት ተሰራጭቶ ሊታመን እንደሚችል የታየበት ነው። ይህ አይነት የውሸት ፕሮፖጋንዳ በአገራችን የመጀመሪያ ባይሆንም የተለመደው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ነበር። አሁንም ቢሆን በገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች ተፎካካሪዎች ላይ ያነጣጠረ ውሸት እንደሚለቀቅባቸው የሚናገሩ አሉ። በተለይ በክልል ደረጃ የሚወዳደሩ፣ በገጠር ያሉ ደጋፊዎቻቸው እንዲጠሏቸው የሚያደርግ ተመሳሳይ የሥም ማጥፋት ዘመቻ እንደሚከፈትባቸው ይናገራሉ። ሕብረተሰቡን የሚያወናብድ የውሸት ቅስቀሳ ከትንኮሳ ስለማይለይ፣ ይህ አይነት የተንኮለኞች እንቅስቃሴ በኹሉም የምርጫው ተሳታፊዎች መወገዝ እንዳለበት አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።

ምርጫው በተቃረበበት በዚህ ጥንቃቄ በሚሻ ወቅት የሚነዛ የፕሮፖጋንዳ ወሬ በሕዝብ ዘንድ አስተሳሰብን በአጭር ጊዜ አስቀይሮ አጠቃላይ ውጤት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያመጣ የሌሎች አገራትን የቅርብ ጊዜ ተሞክሮ በማንሳት ማሳየት ይቻላል። እንግሊዝ ከአውሮፓ ሕብረት ትለይ አትለይ የሚለውን በሕዝበ ውሳኔ ለማወቅ ድምጽ ሊሰጥ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ያልተጠበቀ መረጃ እንገንጠል ከሚሉት ወገን ወጥቶ ነበር። አገሪቱ ለሕብረቱ በጤናው መስክ በየአመቱ የምትልከው ብለው የተጋነነና በእውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ የውሸት አሀዝን በማስቀመጥ ገንዘቡን ለራሳችን አስቀርተን እንጠቀምበት የሚል ማስታወቂያ አሳትመው ወሬውን አዳርሰውታል። በገንዘቡ መጠን የተናደዱና የተገረሙ እንግሊዛውያን ለወሰኑት ውሳኔ ይህ መረጃ ትልቅ ተጽእኖ እንዳሳደረባቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ። ዘግይተው እውነታውን ቢያሰራጩትም ማስተባበያው የወሬውን ያህል በፍጥነት ስለማይሰራጭ አልተሳካላቸውም።

በሌላ በኩል በአሜሪካ ፕሬዝንዳታዊ ምርጫ ወቅትም ዶናልድ ትራንፕ ተፎካካሪያቸውን ሂላሪ ክሊንተንን ያሸነፉት በተመሳሳይ የውሸት ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ ይነገራል። ድምፅ ለመስጠት ጥቂት ቀን ሲቀር የአገሪቱ ጠላት ተደርጋ ከምትወሰደው ራሽያ ጋር ሂላሪ ግንኙነት አላት በሚል የተነዛው ወሬ ብዙዎች ወደ ሪፐብሊካኑ እጩ እንዲሄዱ ማድረጉ ይነገራል። በኋላ ከረፈደ ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው ቢባልም ፕሬዝዳንቱ ከ4 አመት በኋላ እንዳይመረጡ ከማድረግ ውጭ ፋይዳ እንዳላመጣ ይታመናል።

ኢትዮጵያ ካለባት ውስብስብ የውስጥ ችግር አንፃር የውጮቹ ተደምረውበት አለመረጋጋቱን ወደ ባሰ ውጥንቅጥ እንዳይጨምሩት ሁላችንም ልናስብበት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ሁሉም በየጎራው ተሰልፎ ሌላውን ገደል ለመክተት በሚጥርበት በዚህ ወቅት በፍትሐዊ መንገድ ካልሆነ በማጭበርበር ተሸንፎ ዝም ብሎ ሌላ 5 ዓመት የሚጠብቅ ይኖራል ብሎ ለመገመት ይከብዳል። ሁላችንም ሀቅን ይዘን እንጓዝ የምንለው በምርጫው ሰማይ ቤት ይገባል ብለን ሳይሆን፣ ምድራችንን ሲኦል እንዳናደርጋት ነው። “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” እንደሚባለው የወሬን ጉልበት የተረዳ በበጎ እንጂ ለክፉ መጠቀም እንደሌለበት ይረዳል። እውነት ተደብቃ እንደማትኖር እስኪሰለቸን ሲነገር ብንሰማም፣ ከፖለቲከኞች መዋሸት እንደሚጠበቅም ሲነገር እንሰማለን። አሳምኖ ለመመረጥ ብሎ የሚዋሽን ሰው ሀብታችንን አስተዳድርልን፣ በፍትሐዊነት አኑረን ተብሎ ኃላፊነት ለመስጠት እንዴት ይታመናል?

የውሸት ፕሮፖጋንዳ ገና ከመነሻቸው በማሰራጨት የሚታወቁት ህወሓቶች አሁንም ቢሆን በምንም ነገር እንደማይታመኑ ግልጽ ነው። በሁሉም ነገር አለመታመናቸው የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ሌላው እንዳይተማመን ጥለውብን የሄዱት መጥፎ ባህል በቀላሉ የሚለቅ አይመስልም። ባለሥልጣን ሲናገር ከማመን ይልቅ ወደመጠራጠር እንድንሄድ የሚያደርጉን የፖለቲከኞቹ የራሳቸው ተግባር መሆኑ ግልጽ ነው። ያም ቢሆን ግን ለየት ያለ መረጃ ያለማስረጃ በወጣ ቁጥር ዝም ብለን አምነን ከምናሰራጭ ጊዜ ወስደን እስኪጣራ ብናመነታ እንጠቀማለን እንጂ አንጎዳም። ህወሓቶችና ደጋፊዎቻቸው እመኑን እያሉ በማስረጃ አስደግፈው ቢያቀርቡ እንኳን ለማመን ለምን አንደሚቸገር አውቀን ከእነሱ ካልተማርን መጨረሻችን ምን እንደሚሆን ግልጽ ነው። ሁሉም ፓርቲዎች በዚህ አሳሳቢ ወቅት የሚናገሩትን ደጋግመው እያሰቡ፣ ደጋፊዎቻቸውንም እየመከሩ ካልተጓዝን መዘዙ ለሁላችን ይተርፋል። ካሁኑ ሳይታረም ቀርቶ በኋላ ላይ ሁሉም እረኛ ነኝ የሚል የሚከተለው ሊያገኝ ቀርቶ ጅራፍ ይዞ ቢያሳድድም ከመጥፋት በስተቀር መንጋውን መሰብሰብ እንደማይችል አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com