ኢትዮ ቴሌኮምን ተጠቅመው በሕገ-ወጥ መንገድ የደንበኞችን ብር የሚወስዱ ድርጅቶች መኖራቸው ተገለጸ

Views: 666

የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ድርጊቱ ከተፈጸመ ኢትዮ ቴሌኮም ተጠያቂ ነው ብሏል

ኢትዮ ቴሌኮም በሚመራው ሥርዓት ውስጥ የሚያልፉ አጭር የመልዕክት ሳጥን ቁጥር በመጠቀም በሕገ-ወጥ መንገድ የኢትዬ ቴሌኮም ደንብኞችን ሂሳብ እየቀነሱ የሚወስዱ እንዳሉ አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራት አረጋግጣለች። በኢትዮ ቴሌኮም ሥርዓት(ሲስተም) የሚተዳደሩ(የሚመሩ)፣ የተለያዩ አገልግሎቶችን በአጭር የስልክ መስመር ለመስጠት ፈቃድ የወሰዱ ድርጅቶች ወይም አጭር የመልዕክት ሳጥን ቁጥሮች፣ ያለ ደንበኞች ፈቃድ ብር በመውሰድ ደንበኞችን እያማረሩ መሆኑን የታዘበችው አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ጉዳዩን ስትከታተል ቆይታ፣ ምንም አይነት የደንበኞችን ፈቃድ ሳያገኙና ምንም አይነት አገልግሎት ሳይሰጡ የደንበኞችን ሂሳብ እንደሚቀንሱ አረጋግጣለች።

አዲስ ማለዳ ባደረገቸው ማጣራት በሕገ-ወጥ መንገድ የደንበኞችን ሂሳብ የሚቀንሱ አጭር የመልዕክት ሳጥን ቁጥሮች፣ በኹለት መንገድ የደንበኞች ሂሳብ ያለ አግባብ እንደሚቀንሱ በኢትዮ ቴሌኮም ውስጥ ጉዳዩን በቀጥታ ከሚከታተሉ ምንጮች አረጋግጣለች።
የመጀመሪያው ሕገ-ወጥ የሂሳብ መቀነሻ ስልት፣ አጭር የመልዕክት ሳጥን የሚጠቀሙ ድርጅቶች በኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ስልክ ላይ ምንም አይነት መልዕክትና ፈቃድ ሳይጠይቁ ሂሳብ የሚወስዱ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ከኢትዮ ቴሌኮም ባደረገችው ማጣራት ተገንዝባለች።

በዚህ ሕገ-ወጥ የደንበኞች ሂሳብ መቀነሻ ሰልት ውስጥ ሲሳተፉ የነበሩ፣ ማለትም ምንም አይነት የፈቃደኝነት ጥያቄ ለደንበኞች ሳይልኩና መልዕክት ሳያደርሱ ሂሳብ ተቀናሽ የሚያደርጉ አራት አጭር የመልዕክት ሳጥን ቁጥሮች መኖራቸውን አዲስ ማለዳ ባደረገችው የማጣራት ሂደት አረጋግጣለች።

ኹለተኛው መንገድ ደግሞ፣ ደንበኞች የአገልግሎት ተጠቃሚነት ፈቃደኝነት መልዕክት ተልኮላቸው ፈቃደኝነታቸውን ካረጋገጡ በኋላ፣ ላልተጠቀሙት አገልግሎት የሚቀነስ ሂሳብ ነው። በዚህ ሥልት ውስጥ የደንበኞች ሂሳብ ያለ አግባብ የሚቀነሰው አንዳንድ ጊዜ ሊሆን ይችላል።

አዲስ ማለዳ በራሷ መንገድ ጉዳዩን ከኢትዬ ቴሌኮም ሰዎች በኩል ለማጣራት ባደረገችው ሙከራ፣ በእንደነዚህ አይነት ሕገ-ወጥ ተግባራት ብዙዎች ሂሳባቸው እንደሚቀነስባቸው ሰምታለች። እንደዚህ አይነት ቅሬታዎች በብዛት ከደንበኞች የሚመጡ ከሆነና ደርጅቶቹ ከድርጊታቸው ካልተቆጠቡ ሙሉ በሙሉ ሊዘጉ እንደሚችሉም ተመላክቷል።

አጭር የመልዕክት ሳጥን ተጠቅመው የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ድርጅቶ ፈቃድ የሚያገኙት ከኢትዮጵያ ኮሚኒኬሽን ባለስልጣን ሲሆን፣ የአሠራር ሥርዓታቸውን የሚቆጣጠረውና ሥራ ላይ የሚያውለው ኢትዮ ቴሌኮም ነው። በዚሁ መሰረት አዲስ ማለዳ የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ(ኢ/ር) በጉዳዩ ላይ አነጋግራ፣ ደርጊቱ ከተፈጸመ ኢትዮ ቴሌኮም እራሱ በሕግ እንደሚጠየቅ ገልጸዋል። ባልቻ ምክንያቱን ሲያስረዱ ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን አሠራር የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለበትና ድርጅቶቹ ከሚያገኙት ገቢ የሚጋራ በመሆኑ ነው ብለዋል።

“በሕገ-ወጥ መንገድ የደንበኞች ገንዘብ ደርጅቶቹ ከወሰዱ፣ ኢትዮ ቴሌኮምም በሕገ-ወጥ መንገድ የደንበኞችን ገንዘብ ወስዷል ማለት ነው።” ብለዋል ባልቻ። በዚህ መሰረት በሕገ-ወጥ መንገድ የደንበኞች ገንዘብ መወሰዱ ከተረጋጋጠ ደርጅቶቹም ኢትዮ ቴሌኮምም ተጠያቂ ናቸው ብለዋል።

ባልቻ የአጭር የመልዕክት ሳጥን ቁጥር አገልግሎት አሰራርን ሲያብራሩ፣ በማንኛውም የግለሰብ ስልክ ላይ ማስታወቂያ ለማስተላለፍና መልዕክት ለመላክ የደንበኛውን ፈቃድ መጠየቅ ግደታ ነው ብለዋል። ይህ የሚሆነው ደግሞ አጭር የመልዕክት ሳጥን የሚጠቀሙ ደርጅቶች መጀመሪያ የሚሰጡትን አገልግሎትና የሚያስከፍሉትን ሂሳብ አሳውቀው ደንበኛው ፈቃደኛ መሆናቸው ሲያረጋግጡ ነው። “ይህ ካልሆነ ሕገ-ወጥ አሰራር አለ ማለት ነው። በዚህም መንግስት ተጠቃሚ እየሆነ ነው። ይህ በጣም አደገኛ እና ተገቢ ያልሆነ ነገር ነው።” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

ባለስልጣኑ እንደዚህ አይነት ሕገ-ወጥ የሂሳብ ቅነሳ ያጋጠማቸው ደንበኞችን ማስረጃ ካገኘ፣ ጉዳዩን አጣርቶ እርምጃ እንደሚወስድ ዋና ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። አዲስ ማለዳ ጉዳዩን ካጣራች ብኋላ ኢቴዮ ቴሌኮም ምላሽ እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርባ፣ ጥያቄዋን በጽሑፍ እንድታቀርብ ከሚመለከተው ክፍል ተጠይቃ ጥያቄዋን በጽሑፍ ብታቀርብም ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ምላሽ ማግኘት አልቻለችም።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com