በትግራይ በ76 ሰዎች ላይ ክስ ተመስርቷል 53ቱ ወታደሮች ናቸው ተብሏል

Views: 135

የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ሐሙስ ከሰዓት ጋዜጠኞችን ጠርቶ በሠጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በትግራይ ክልል በመንግስት ወታደሮችና በነዋሪዎች ስለተፈጸሙ ወንጀሎች ማብራሪያ ሰጥቷል። በመንግስት አካላት ክልሉ ውስጥ ተፈጽመዋል ተብለው ስሞታ ሲቀርብባቸው የነበሩ የንጽሃን ግድያዎችና የሴቶች መደፈር እውነትነት እንዳለው መረጋገጡን የፌደራል ዋና ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ(ዶ/ር) አሳውቀዋል።

በክልሉ ተፈጽመዋል የተባሉ ወንጀሎች በ4 አካላት እየተመረመሩ ነው የተባለ ሲሆን፣ ወታደራዊ መርማሪዎች ወታደሮችን የተመለከተውን፣ ፌደራል ፖሊስ ከባድ የጅምላ ግድያዎችን፣ የክልሉ ፖሊስ የሴቶችን መደፈርን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከዓለም አቀፍ ተመሳሳይ ተቋማት ጋር በመሆን መሳ ለመሳ የየራሳቸውን ምርመራ ያካሂዳሉ ተብሏል።

እስካሁን በፌደራል ፖሊስ በተደረገ ምርመራ በማይካድራ ከተፈጸመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ጋር በተገናኘ 200 የሚሆኑ ሰዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃንን መጨፋጨፋቸው ተረጋግጧል። ከገዳዮቹ ውስጥ አብዛኞቹ ሸሽተው ሱዳን መግባታቸው የታወቀ ሲሆን፣ 23 ተጠርጣሪዎች ተይዘው ክስ ተመስርቶባቸዋል። በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እየቀረቡ ባሉት ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ለመመስረት የሚያስችል የ250 ተጎጂዎችና ምስክሮች ቃል መውሰዱን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አሳውቋል። ምርመራውን ለማካሄድ የአሜሪካ ፎረንሲክ ባለሙዎች እገዛ አድርገዋልም ተብሏል።

አክሱም ተፈጸመ ከተባለው ወንጀል ጋር በተገናኘ ከውጊያ ውጭ 40 የሚሆኑ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸው መረጋገጡን የተናገሩት ጌዲዮን፣ 60 የሚሆኑ ደግሞ ከቤታቸው ውጭ በከተማው ውስጥ መገደላቸው ታውቋል ብለዋል። የጅምላ ፍጅትን እንዲያጣራ የተመደበው ፌደራል ፖሊስ ከሰው፣ ከሕክምናና ከተለያዩ ማስረጃዎች ማረጋገጥ እንደቻለው፣ በግለሰቦችና በተቋማት ላይ ወታደራዊ ሕግ በማይፈቅደው መልኩ ግድያና ውድመት የፈጸሙ ላይ አፋጣኝ ውሳኜ እንደሚሰጥ ተነግሯል። በንጹሃን ሞት ላይ የተጠረጠሩ በምን መንገድ እንደሚከሰሱ ይወሰናልም ተብሏል።

የሴቶች መደፈርን በተመለከተ የትግራይ ክልል ፖሊሶች የራሳቸውን ምርመራ ያደርጋሉ በተባለው መሰረት በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች በስፋት ተፈጸሙ ስለተባሉ የሴቶች መደፈር ወንጀል በዝርዝር ያጣራሉ ተብሏል። ወታደራዊ መርማሪዎች ያጣሩትን በተመለከተ፣ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ወታደሮች ጉዳያቸው በወታደራዊ ፍርድቤት እየታየ መሆኑ ተነግሯል። እስካሁን ምርመራ ከተካሄደባቸው መካከል ወታደራዊ የጦር ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው 28 የመከላከያ አባል የሆኑ ወታደሮች ክስ ተመስርቶባቸዋል። ወታደራዊ አስገዳጅነት በሌለበት በፈጸሙት የጦር ወንጀል ተጠያቂ ይሆናሉ ተብሏል።

በሴቶች ላይ ጾታዊ ትንኮሳ አድርሰዋል እና ደፍረዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሌሎች 25 ወታደሮች ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ዋና አቃቢ ሕጉ ይፋ አድርገዋል። እስካሁን ክሳቸው ከታየ የመንግስት ወታደሮች መካከል አራቱ ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን እንደተረጋገጠም አሳውቀዋል።

በትግራይ አሁን በሁለት ቀጠና ብቻ ውጊያ እየተካሄደ እንደሆነ በመግለጫው ያሳወቁት የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሰክሬተሪያት ቢልለኔ ስዩም፣ በተለያየ ቦታዎች ጦርነት እንዳለ አሸባሪዎች የሚያስወሩት ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል። ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ግልጽ የሆኑ እውነታዎችን ትቶ እነሱ በሚነዙት የተሳሳተ ወሬ ስህተት ውስጥ እየገባ እንደሆነ የተለያዩ ነጥቦችን በማንሳት አስረድተዋል።

እርዳታ ድርጅቶች ሕግ በሚፈቅደው መጠን እንዲገቡ መፈቀዱን ያስታወሱት ቢልለኔ፣ አንዳንዶቹ ለአሸባሪዎቹ መሳሪያ ሲያቀብሉ መያዛቸውን አሳውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ መንግስትን ሰይጣን አድርጎ ማቅረቡ አይጠቅምም ያሉ ሲሆን፣ ከእውነታው ውጭ ውሸትን የሚያስተጋቡ ለትግራይ ሕዝብ አይጠቅሙትም ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com