የጤፍ ዋጋ በኩንታል እስከ 600 ብር ጭማሪ አሳየ

Views: 125

በአንዳንድ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የጤፍ ዋጋ ከዚህ ቀደም ከነበረበት በኩንታል እስከ 600 ብር ድረስ ጭማሪ ተደርጎ እየተሸጠ እንደሆነ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ። የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለአዲስ ማለዳ እንደገልጹት በአካባቢያቸዉ ነጋዴዎች ጤፍን በድብቅ በኩንታል እስከ 600 ብር ጭማሪ እያደረጉ እየሸጡ መሆኑን ነው። አዲስ ማለዳ የሕብረተሰቡን ቅሬታና ጥያቄ ይዛ በተለያዩ ክፍለ-ከተሞች ያለዉን የጤፍ ዋጋ በስልክና በአካል በመገኘት ለማጣራት ሞክራለች።
በዚህም መሰረት ነጭ ጤፍ(ማኛ) በኪሎ ከ56-60 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ አዲስ ማለዳ ያገኘችዉ መረጃ ያመለክታል።

ከ2 እና 3 ሳምንት በፊት በኪሎ 50 ብር የነበረዉ የማኛ ጤፍ ዋጋ አሁን ላይ ወደ 60 ብር ከፍ ማለቱን ተዘዋውረን ካገኘነዉ መረጃ ለማወቅ ተችሏል። በዚህ አጭር ጊዜ በኩንታል የ600 ብር ጭማሪ በማሳየት ኩንታሉ እስከ 6ሺሕ ብር እየተሸጠ ነው። በተለምዶ ሰርገኛ በመባል የሚታወቀዉ ጤፍ ከኹለትና ሶስት ሳምንታት በፊት በኪሎ 45 እና 46 ብር ይሸጥ እንደነበር ይታወቃል። አሁን ላይ የሰርገኛ ጤፍ ዋጋ ከ48-50ብር በኪሎ እየተሸጠ እንደሚገኝ ከአንዳንድ ወፍጮ ቤቶችና የእህል መደብሮች የተገኘዉ መረጃ ያመላክታል።
ዝቅተኛው የጤፍ አይነት በኩንታል እስከ ከ300-400 ብር ጭማሪ ማሳየቱን ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸዉን የሰጡ ሸማቾች ገልፀዋል።

የዚህ ቅጽበታዊ የጤፍ ዋጋ ጭማሪን ምክንያት ለማወቅ የተለያዩ የእህል መሸጫ እና ወፍጮ ቤቶችን አዲስ ማለዳ ጠይቃለች። ሻጮቹ እንደምክንያት የሚያቀርቡት የክረምት ወራት እየተቃረበ ስለሚገኝ የምርት እጥረት ሊኖር ይችላል በሚል እንደሆነ አስታዉቀዋል። ሌላዉ የገበሬዎች መፈናቀል፣ የእርሻ ማሳዎቻቸዉ መቃጠልና የደህንነት ስጋቶች ጋር ተያይዞ ገበሬዉ በብዛት አለማምረቱን እንደምክንያት ጠቅሰዋል። መጪዉ የክረምት ወቅት የአዝመራ ወቅት በመሆኑ ምርት እንደፈለጉ ማግኘት አስቸጋሪ ከመሆኑ ባሻገር የትራንሰፖርት ችግሮችም አሉ ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮን ለማነጋገር ያደረገችዉ ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካላትም። በተጨማሪም ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ በአዲስ አበባ አስተዳደር የኀብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዉብነህ እምሩ ጉዳዩ የሚመለከተዉ ንግድ ቢሮን ነዉ ሲሉ ተናግረዋል። አክለዉም እሳቸው የሚመሩት ተቋም መንግሥት የገንዘብና የመሬት ድጎማ በሚያደርግላቸዉ የኀብረት ሥራዎች ላይ ብቻ ቁጥጥር እንደሚያደርግ አስታዉቀዋል። አገራችን የምተከተለዉ ነጻ የገበያ ስርአት ከመሆኑ አንጻር ነጋዴዉን መቆጣጠር አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል።

የጤፍ፣ ስንዴና የስንዴ ዱቄት ላይ መንግሥት ድጎማ በማድረግ በሸማቾች ኅብረት ስራ በኩል ማቅረቡን ተናግረዋል። በሸማቾች ኀብረት ስራዎችም የሰርገኛ ጤፍ ዋጋ 41 እና የቀይ ጤፍ ዋጋ 39 ብር በኪሎ እንደሆነ ጠቅሰዉ ሕብረተሰቡ እንደ አማራጭ ከማኀበራቱ ቢሸምት ይሻለዋል ሲሉ ጠቁመዋል። ከዚህ የዋጋ ጭማሪ ጋር በተገናኘም የበርበሬ፣ የዘይትና የቅቤ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ኑራችንን አየተፈታተነን ነዉ ሲሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ አንዳንድ ነዋሪዎች ገልጸዋል። ለአብነትም አንድ ኪሎ ዛላ በርበሬ ከ150- 220 የነበረ ቢሆንም፣ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ከ270-350 ብር ከፍ ማለቱን ከሸማች እና ሻጮች የተገኘዉ መረጃ ያመላክታል። በገና በአል ከ300 እስከ 380 ብር የነበረዉ የአንድ ኪሎ ቅቤ ዋጋ አሁን ላይ ከ510-600 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችላል።


ቅጽ 3 ቁጥር 135 ግንቦት 28 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com