የእለት ዜና

እየናረ የመጣው የመጻሕፍት ዋጋ

የመጻሕፍት ዋጋ እንደጨመረ ቢታመንም በምን ያህል መጠን እንደሆነ ግን የተጠና ጥናት ባለመኖሩ በመቶኛ መግለጽ ይቸግራል ሲሉ የገለጹልን በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የሕዝብ ግኑኝነትና የማኅበራዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት መሳይ ታደሰ ናቸው።

ከፍተኛ ባለሙያው እንደነገሩን ለመጻሕፍት ዋጋ መወደድ የውጭ ምንዛሬ በወቅቱ አለመገኘት እና የወረቀት ዋጋ መጨመር በዋና ምክንያትነት እንደሚጠቀሱ ነው። የመጻሕፍት ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ጨምራል፤ ይህ ደግሞ አንባቢውን በብዙ መልኩ ይጎዳዋል ያሉት ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዝዳንት አበረ አዳሙ ናቸው። በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያው ከፍተኛ ጫና ያደረሰበት አንባቢ ላይ የመጻሕፍት ዋጋ በከፍተኛ መጠን ሲጨምርበት እንደሚያስደነግጠውና ከመጻሕፍት ይበልጥ እንዲርቅ እንደሚያደርገው ይናገራሉ።

የመጻሕፍት ዋጋ ለመጨመሩ ምክንያት የወረቀት አስመጪዎች በአገራችን አናሳ በመሆናቸው ነው ያሉን ደራሲ አበረ፣ የወረቀት አስመጪዎቹ ከኹለትና ከሦስት የበለጡ እንዳልሆኑም ነግረውናል። ስለዚህ ማተሚያ ቤቶች የወረቀት ዋጋ ሲወደድባቸው ዋጋ የሚጨምሩት በደራሲው፣ በአሳታሚው እና በአንባቢው ላይ ነው።

የደራሲያን ማኅበር ፕሬዝዳንት ‹‹መጻሕፍት የአዕምሮ ምግብ ናቸው፤ አንድ ሰው አንድ መጽሐፍ በ300ብር ወይም በ500 ብር ገዝቶ ከሚያነብ አንድ ኪሎ ስጋ በ800 ብር ገዝቶ ቢበላ ይመርጣል›› ሲሉ አስተያየታቸውን ይናገራሉ።

ደራሲው ብዙ ችግሮችን አልፎ የሚያሳትመው መጽሐፍ ገዢ አጥቶ ሲጉላላና አንባቢ ሲያጣ አቅሙን ይፈታተነዋል። አንዳንድ ደራሲዎች ቤታቸውን ወይም ንብረታቸውን አስይዘው መጻሐፋቸውን እንደሚያሳትሙ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት የመጽሐፋቸውን የመሸጫ ዋጋ ከፍ አድርገው እንዲያሳትሙ ይገደዳሉ። ይህን ከፍ ያለ ዋጋ ደግሞ ክፍሎ ለመወሰድ ብዙም የማንበብ ልምድ የሌለው ማኅበረሰባችን ይቸገራል።
የማንበብ ባህል በጣም ኋላቀር በሆነበት ማኅብረሰብ ውስጥ የመጽሕፍት ዋጋ መወደድ በትንሹም ቢሆን ያለውን የማንባብ ተስፋ ማጥፋት እንደሆነ አበረ አዳሙ ያስረዳሉ።

56 የመንግሥትና የግል ዩንቨርስቲዎች አሉ። በእነዚህ ተቋማት ውስጥ በርከት ያሉ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ይኖራሉ። ከእነዚህም በተጨማሪ በኹሉም አካባቢዎች ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኝ የተማረ ሰራተኛ አለ። ይህ የተማረ ሰው ሃይል ቢያንስ ከ150ሺሕ እስከ 200 ሺሕ የሚደርስ እንደሆነ የደራሲያን ማኅበሩ ፕሬዝዳንት ይናገራሉ። ይህም ማንበብና መጻፍ የሚችለውን ሁሉንም ሳይጨምር ነው። ነገር ግን አሁን ላይ የሚታተመው የመጻሕፍት ብዛት ከ2-3ሺሕ የሚደርስ ነው። በአንባቢያን ዘንድ በጣም የሚወደድ መጽሐፍ ከሆነ እስከ 5ሺሕ ቅጂ ሊታተም ይችላል።ካላይ ከተጠቀሰው የተማረ ቁጥር አንጻር እንኳ ቢለካ የመጻሕፍት ኅትመት ቁጥር እዚህ ግባ የማይባልና ደካማ የማንበብ ባህል የሰፈነ እንደሆነ ያሳያል። ይህ የደራሲውን ፍዳ፣ የደራሲውን ስቃይ ያሳያል።

በሌላ በኩል፣ የሚታተመው መጽሐፍ ቅጂ ባነሰ ቁጥር የማሳተሚያ ዋጋው ይጨምራል። ይህ ደግሞ የቅንጦት ነገራቸውን ትተው መጻሕፍትን ለሚመርጡ አንባቢያን ዋጋ ስለሚጨምርባቸው ገዝቶ ለማንበብ ፈተና እንደሚሆንባቸው የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ይገልጻሉ።

ይህንን የመጻሕፍት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ለመቅረፍ፣ መንግሥት አገር ውስጥ ያሉ የወረቀት አምራቾችንና ከውጭ ወረቀት የሚያስመጡት ነጋዴዎችን ቁጥር መጨመር ብሎም የተለያዩ ባለሃብቶች በዚህ ዘርፍ እንዲሰማሩ ማበረታቻ ማድረግ ይኖርበታል።

መንግሥት ብዙ ሚሊዮን ዶላሮችን እያወጣ የማስተማሪያ መጻሕፍትን በህንድና በቻይና ያሳትማል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ጥራት ያለው ትልቅ ማተሚያ ቤት በአገራችን አለመኖሩ ነው ይላሉ የማህበሩ ፕሬዝዳንት።

ማተሚያ ቤትን እና የወረቀት ፋብሪካን ባለሀብቱ መሸሽ እንደሌለበት የጠቆሙት ደራሲ አበረ፣ በአገራችን ከመጻሕፍት ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮች ብዙም ትኩረት አንዳልተሰጣቸው ያመላክታል ብለዋል።
አክለውም ወረቀት ከውጭ ከማስመጣት በተጨማሪ አገር በቀል የሆኑ ዛፎችን በመጠቀምና ተተኪ ደኖችን በማልማት ወረቀት የሚመረትበትን መንገድ መንግሥት ማመቻቸት እንዳለበት አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ሰጥጠዋል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ አዲስ ማለዳ ያነጋገራቸቻው ደራሲ አለማየው ገላጋይ በበኩላቸው፣ ችግሩ ያለው ማተሚያ ቤቶች ጋር ነው ይላሉ። የኅትመት ዋጋ ከሳምንት ሳምንት ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል። የወረቀት አስመጪዎች ጥቂት በመሆናቸው እርስ በእርሳቸው እየተነጋገሩ ዋጋ እንደሚጨምሩ ጠቁመዋል።

ቅድሚያ ሊሰጣቸዉ ከሚችሉ ወደ አገር ዉስጥ የሚገቡ እቃዎች መካከል አንዱ ወረቀት ሊሆን እንደሚገባዉ ተጠቁሟል። አገር ዉስጥ የሚታተመዉን ወረቀት የአመቱን ኮንትራት የሚወስዱት ከዉጪ ወረቀት አስመጪ ድርጅቶች እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል። ስለዚህ የወረቀት ጉዳይ ከአስመጪዎች እጅ ነዉ፤መንግስት የወረቀት አስመጪዎችን በልዩ ሁኔታ ማበረታቻ በመስጠት የአስመጪዎችን ቁጥር መጨመር እንደሚያሥፈልግ ደራሲያኑ ይናገራሉ።

ጉዳዩ መፍትሄ ካላገኝ የዋጋው ነገር በእጥፍ እየጨመረ እንደሚሄድና መጽሐፍን ለሚፈልጉ አሳሳቢ እንደሚሆን ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።የወረቀት ዋጋ መወደድ ለአሳታሚዎችም ፈተና እንደሆነባቸውም ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ ተናግረዋል።

‹‹እጥፍ በሚባል ደረጃ የመጻሕፍት ዋጋ ጨምሯል፤ ምክንያቱ በእርግጥ የተለያየ ሊሆን ይችላል›› ሲሉ የገለጹልን ደግሞ በጃፋር መጻሕፍት ማከፋፋያ መደብር የሽያጭ ሰራተኛ የሆኑት ዳዊት ውድማጣስ ናቸው።

አንድ መጽሐፍ ከኹለትና ከሦስት አመት በፊት የታተመበትና አሁን የሚታተምበት ዋጋ ብንመለከት በጣም ከፍተኛ የዋጋ ልዩነት እንዳለው ዳዊት ተናግረዋል። ለምሳሌ የዴርቶጋዳ መጽሐፍ የመጀመሪያው እትም ከነበረበት 60 ብር ተነሰቶ አሁን ላይ 150 እንደደረሰ አንስተዋል።

በሳምንት እና በቀናት ልዩነት ውስጥ ከወረቀት ጋር ተያይዞ አሳታሚዎች የኅትመት ዋጋ ይጨምራሉ። የመጻሕፍት አከፋፋዮች ለመጻሕፍት መሸጫ መደብሮች እና አዟሪዎች ከአንድ መጽሐፍ ዋጋ ላይ 5% ብቻ ተጠቃሚ እንደሆኑ ይነገራል። ለምሳሌ የመጸሐፉ ዋጋ 100 ብር ቢሆን ሲሸጡ 5 ብር ብቻ እንደሚያገኙ ነው።

የመጻሕፍት ጀርባ ላይ ያለው ዋጋ ብዙ ጊዜ ተፍቆ ዋጋ ተጨምሮ እንደሚስተካከል ወይም እንደሚጠፉ ይታወቃል። ለዚህም ምክንያቱ የመጻሕፍት አዟሪዎች ከድካማቸው አንጻር የሚያገኙት ትርፍ በቂ አይደለም ብለው ስለሚያስቡ ነው ሲሉ አከፋፋዮች ይናገራሉ። ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ከደራሲያንና አሳታሚዎች ጋር በመነጋገር የተሻለ ትርፍ እና የድካማቸውን ዋጋ እንዲያገኙ አዳዲስ በሚወጡ መጻሕፍት ላይ አዟሪዎች በቅናሽ እንዲደርሳቸው እየተደረገ መሆኑን አከፋዮች ይገልጻሉ።

ይህ ከአሳታሚ፣ ከደራሲዎች፣ ከማተሚያ ቤቶች እና ከአከፋፋዮች ጋር በመነጋገር የሚሠራ ነው። የተሳካ ሥራ ለመሥራት የሕትመት እና የመጻሕፍት ዋጋው ሊመጣጠን እንደሚገባው ይነገራል።
አዲስ ማለዳ የመጻሕፍት ዋጋ ላይ ባደረገችው ዳሰሳ የዋጋ ጭማሪው ከኹለት ዓመት ወዲህ ቀስ በቀስ እየጨመረ እንደመጣ መረጃዎችን ተመልክታለች።

ለዚህም እንደ ምክንያት የሚቀርበው በዋነኛነት የኅትመት ዋጋ መጨመር ነው። የኅትመት ዋጋ መጨመር የመጻሕፍት ዋጋ እንዲጨምር እያደረገ እንደሆነም የመጻሕፍት አከፋፋዮች ይስማማሉ። ማተሚያ ቤቶች በበኩላቸው ለዋጋው ጭማሪ እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት የማተሚያ ቁሳቁሶች መወደድን ነው።

በተጨማሪም በማተሚያ ቤቶች ላይ የታክስ መጠን መጨመር፣ የወረቀት ዋጋ መወደድ ከአሳታሚዎች፣ አከፋፋዮችና መጻሕፍት አዟሪዎች እስከ አንባቢየን ድረስ ተጽእኖ እንዳለው ይነገራል።
አሁን አሁን የማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ብዙም የማንበብ ልምድ የሌለውን ትውልድ ይበልጥ ከመጻሕፈት እንዲርቅ እያደረገው ነው ሲሉ ደራሲዎች ይናገራሉ።

አሁን ላይ የተለያዩ ደራሲዎች የተለያዩ ይዘቶች ያሏቸውን መጻሕፍት ለአንባቢያን እያቀረቡ እንደሆነም ግልጽ ነው። ልቦለድ እና ኢ-ልቦለዶችን ያካተቱ በተለያዩ ደራሲዎች የተጻፉ መጻሕፍት ይገኛሉ። እነዚህ መጻሕፍት ታሪክን፣ ፖለቲካን፣ ኢኮኖሚን፣ ማህበራዊ ህይወትን፣ ባህልንና ወግን እና የመሳሰሉትን በጥልቀት የሚመረምሩ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ያደረገችው ቅኝት ይጠቁማል።

አዲስ ማለዳ በአራት ኪሎ፣ በስታዲየም፣ አምባሳደር እና መገናኛ አካባቢ አግኝታ ያነጋገረቻቸው የመጻሕፍት አዟሪዎችና መንገድ ላይ ዘርግተው የሚሸጡ ነጋዴዎች በዋጋ ጭማሪው ምክንያት ገዢ እንደቀነሰባቸው ይናገራሉ። አብዛኛው ሰው የመጻሕፋቱን ዋጋ አንስቶ ካየ በኋላ መግዛት እየፈለገ አስቀምጦ እንደሚሄድ ለአዲስ ማለዳ ያወጋት በአራት ኪሎ አካባቢ የሚገኝ የመጻሕፍ አዟሪ ነው።
አንዳንድ አንባቢያን መጽሐፍ ከመግዛት ይልቅ ዘመናዊ የማንበቢያ ስልቶችን በመጠቀም በስልኮቻቸው ላይ በመጫን እንደሚያነቡ አዟሪዎቹ ገልጸዋል።

እንዳንዶችም ዘርፍ ለመቀየር እየተገደድን ነው ያሉ ሲሆን፣ ብዙም አንባቢ በሌለበት በዋጋው ላይ ጭማሪ መደረጉ የቀሩትንም ማራቅ ነው ይላሉ። በፊት ላይ የማኅበራዊ ሚዲያው ተጽእኖ ብዙም ስላልነበረ መጽሐፍ የማንበብ ልምድ እንደነበራቸው እና አሁን ላይ በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ላይ በሚቀረቡ ይዘቶች ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ የገለጹት ደግሞ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ወጣቶች ናቸው።

‹‹እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ የሆነውን ትውልድ፣ እንኳን የመጽሐፍ ዋጋ ተወዶ፣ በነጻም ቢሰጠው የጀመረውን መጽሐፍ የማይጨርስ አንባቢ ባለበት የመጻሕፍት ዋጋ መወደድ አስገራሚ ነው። ያሉንን ጥቂት ጠንካራ አንባቢያንን ይዘን ብዙ አንባቢ መፍጠር የሚቻልበት መንገድ መመቻቸት አለበት። አንባቢ ያልሆነ ማሕበረሰብ አያውቅም፤ የማያውቅ ማሕበረሰብ ደግሞ አይጠይቅም፤ እራሱን እንዴት መምራት እንዳለበት እንኳን ግራ ይጋባል›› ሲሉ የተናገሩት ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ እድሜያቸው ከ60 አመት በላይ የሚሆናቸው አባት ናቸው።

አዲስ ማለዳም ለዛሬ አንባቢዎቿ የማንበብ ባህላቸው ይዳብር ዘንድ የሚረዱ ከማኅበራዊ ድረ-ገጽ ላይ የተወሰዱና በመጽሐፍ ዙሪያ በተዋቂ የዓለማችን ሰዎች ከተነገሩ አባባሎች የተወሰኑትን እንሆ ብላለች፤
‹‹መጽሐፍ አስተሳሰባችን የሚያቀላጥፍ መሳሪያ ነው››( አላን ቤኔት)

‹‹መጽሐፍ ከባድ መሆን አለበት። ምክንያቱም ዓለሙ ሁሉ በእርሱ ታጭቋልና›› (ኮሜሊያ ፈንክ)
‹‹ ዛሬ አንባቢ የሆነ ነገ መሪ ይሆናል›› (ማርጋሬት ፉለር)
‹‹ዛሬ ልታነበው የምትችለውን መጽሐፍ ለነገ አታቆየው›› (ስሙ ያልታወቀ ሰው)
‹‹ካነበብኩ ዓለም ለእኔ ክፍት ነው›› (ሜሪ ማክሎድ)
‹‹ዓለም መጽሐፍ ናት ። አለምን ተጉዘው ያላዩ መጽሐፍ ይግለጡ›› (ቅዱስ አውግስጦስ)
‹‹ማንበብ ለአእምሮ ሲሆን፣ አእምሮ አካላችን ምን ማድረግ እንዳለበት ያቀናጃል›› (ስሙ ያልታወቀ ሰው)
‹‹እንደ መጽሐፍ ያለ ታማኝ ጓደኛ የለም››(ኸርነስት ኸርሚንግወይ)
‹‹መጽሐፍ አንድ ቁም ነገር አለው። ይሄውም እግርህን ከቤትህ ሳታነሳ ዓለምን እንድትዞር ያደርግሀል››( ስሙ ያልታወቀ ሰው)
‹‹አንድ ነገር አንርሳ ! አንድ መጽሐፍ፣ አንድ እስክሪብቶ፣ አንድ ህጻን፣ አንድ መምህር ዓለምን መለወጥ ይችላሉ› (ማላላ የሱፍ)


ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com